>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6941

ማእከላዊ አልተዘጋም!!! (ብርሀኑ ተክለ ያሬድ)

ማእከላዊ አልተዘጋም!!!
ብርሀኑ ተክለ ያሬድ
ከወዳጄ ፍቅረ ማርያም አስማማው ጋር ፖሊስ በእስር ወቅት የነጠቀንን ንብረቶች ለማስመለስ ማእከላዊ ተቀየረ ወደተባለበት ዮርዳኖስ ሆቴል ጎራ ብለን ነበር ወደዛ ከማምራታችን በፊት ልደታ ፍርድ ቤት ህንፃ ላይ ወደሚገኘው አቃብያነ ህግ ፅ/ቤት ደብዳቤ ለማፃፍ በሔድንበት ወቅት የይፈፀምላቸው ደብዳቤ ለማፃፍ ልደታ ፍርድ ቤት ውስጥ ወደሚገኘው አቃብያነ ህግ ቢሮ ባመራንበት ወቅት ለውጥ ለውጥ የሚሸት አየር ነበር የጠበቀን ቢሮው ውስጥ የነበሩ ሰራተኞች በአግባቡ አስተናግደውናል አቃብያነ ህጎቹም አዳዲሶች ናቸው ነባሮቹም ቢሆኑ ምንም እንኳን ፀፀታቸው ጅብ ከሔደ…. ቢሆንም “በማረሚያ ቤት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚደርስባችሁኮ እናውቃለን ክሳችሁም የውሸት እንደነበር እናውቃለን ምን እናድርግ ብላችሁ ነው እኛ የተሰጠንን መዝገብ ነው የምንሰራው” ብለውናል።
ከልደታ የተሰጠንን ደብዳቤ ይዘን ወደ አዲሱ ማእከላዊ “ዮርዳኖስ ሆቴል” ባመራንበት ወቅት የተመለከትነው ግን የዚህን ተቃራኒ ነው ምድር ቤቱ ላይ በሚገኝ የመርማሪዎች ቢሮ ውስጥ የቀድሞው ማእከላዊ የስቃይ ተውኔት መሪዎችና የሰው ልጅ አራጆች የወንድ ልጅ ብልት የሚያኮላሹ የእጅና የእግር ጣቶችን የሚነቅሉ መርማሪዎች በኩራት በየወንበሩ ላይ ይሽከረከራሉ ይህን ሁኔታ የተመለከተ ማንኛውም ሰው የቀድሞውን ማእከላዊ ያስታውሳል።
ወደፎቅ በምንወጣበትም ወቅት በሊፍቱ ላይ አብሮን ይጓዝ የነበረው ሰው በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት ሸዋሮቢት ማጎሪያ ቤት በምርመራ ሰበብ ፍቅረ ማርያምን ያሰቃየው የነበረ ቸሬ የተባለ አረመኔ ነው የድብደባው ህመም ከአካልህ ሳይጠፋ ደብዳቢህ እያጉረጠረጠብህ በአንድ ሊፍት በጋራ መጓዝን የመሰለ ህመም ይኖር ይሆን? ፍቅረ ማርያም በሀዘን ስሜት ራሱን እየነቀነቀ “አልደነቆርኩም አንተ ጆሮዬን ለማደንቆር ነበር በተደጋጋሚ ጆሮ ጆሮዬን ትመታኝ የነበረው ” አለው። መርማሪው አይኑን ከማጉረጥረጥ ውጪ ምንም አልመለሰም።
አስገራሚው ነገር ደብዳቤውን ለማስፈረም የገባንበት ቢሮ ውስጥ ያገኘናቸው ሰዎች ማንነት ነው። አረመኔው ተክላይ የቂሊንጦው ቃጠሎ አሰቃቂ ምርመራ ሀላፊ የነበረው ኢንስፔክተር አለማየሁ በጭካኔ ድብደባና ማሰቃየት ወደር የማይገኝለት ፅጋቡ ተቀምጠው ያውካካሉ እነዚህን ሰይጣናት በለውጥ ጉዞ ላይም ሀላፊዎች ሆነው ማየት ካላሳመመ ምን ሊያሳምም ይችል ይሆን?? እነዚህን ካላሰቃዩ ያልመረመሩ የማይመስላቸው ሰዎችን ይዞ ተለውጠናል ማለት ይቻላል? ማእከላዊስ ህንፃ ከመቀየር ውጪ ምኑ ነው የተለወጠው?
እመኑኝ ማእከላዊ አልተዘጋም!…. እነዚህን አረመኔዎች ከምርመራው ቢሮ አካባቢ እስካላራቅናቸው ድረስና የተጠረጠሩ ሰዎችን ጉዳይ በሳይንሳዊ መንገድ የሚያጣሩ መርማሪዎች እስከሌሉን ድረስ ማእከላዊ አልተዘጋም ዜጎች ላይ የሚደርሰውም ጥቃት ይቀጥላል ይህ ለሁላችንም አይበጀንምና ህንፃ መቀያየሩን ትታችሁ ማእከላዊን ዝጉት።
Filed in: Amharic