>

ዛሬ የሁለቱ ህዝቦች አዲስ የታሪክ  ምእራፍ የጅማሮ ሁለተኛ ገጽ ገልጠናል!!! (ነኣምን ዘለቀ)

ዛሬ የሁለቱ ህዝቦች አዲስ የታሪክ  ምእራፍ የጅማሮ ሁለተኛ ገጽ ገልጠናል!!!
ነኣምን ዘለቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰለ ኤርትራ  ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ያላቸው ራእይ  በአደባባይ የተናገሩት ከ3 ወር በፊት የጠ/ሚኒስትርነቱን ስልጣን በተረከቡ ጊዜ ባደረጉት ንግግር መሆኑን አስታውሳለሁ። ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የኤርትራን ልኡክ ሲቀበሉ፣ ዛሬ ደግሞ ወደ አስመራ በመጓዝ  የጀመሩት ተግባራዊ መንገድ  ላለፉት አመታት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን  ብዙ የለፉበት ጉዳይ ነው። በህወሓቶች፣ እንዲሁም በማወቅና ባለማወቅ ይህን መልካም ራእይ ለማጠልሸት በተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ቡድኖች በሚደርስባቸው ውርጅብኝ ሳይበገሩ እነዚህ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን  በየአደባባዩ የተናገሩበት፣ የጻፉበት መልካም ራእይ ተግባራዊ ያደረገ እርምጃ  በመሆኑ ከፍተኛ እርካታ የሚሰጥ ነው።

የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦችን ግንኙነት አዲስ ጎዳና ተጀምሮአል፣ ዛሬ የሁለቱ ህዝቦች አዲስ የታሪክ  ምእራፍ የጅማሮ ሁለተኛ ገጽ ገልጠናል። ዛሬ ልዩና ታላቅ፣  የወደፊት ትውልዶች  በታሪክ ማህደሮች ሆነ በልብ ወለድ ድርሰቶች ጭምር  የሚያነቡት፣የሚያከብሩትም  ሊሆን የሚችል እለት  ነው። በሁለት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባና በአስመራ ያየናቸው ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖችን ለማየት መብቃት በራሱ ታላቅ  ጸጋ ነው። ትልቅ ብስራት፣ ትልቅ ደስታ። እነዚህ ልዩና ታሪካዊ እለቶች እውን እንዲሆኑ ለደከማችሁ፣ ተስፋን ሰንቃችሁ የዛሬዋን ታሪካዊ ቀን ለናፈቃችሁ የኢትዮጵያና  የኤርትራ ህዝቦች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ዛሬ ላይ ለተደረሰበት ልዩ ቀን  የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ብዙ መስዋእትነት እነደከፈሉ ግልጽ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የሕወሀት አገዛዝ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ገንብቶ የነበረው  የጥላቻ ግንብ ለመናድ ብዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ብዙ አይነት ስራዎችን ሰርተዋል፣ ብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ውስጥ ታልፎዓል።

ልዩ ልዩ  ህዝባዊ መድረኮች፣ የተለያዩ ምሁራዊ ጥናቶች፣  ልዩ ልዩ ጽሁፎች በምሁራንና በአክቲቪስቶች ተጽፈው በድህረ ገጾች ለንባብ በቅተዋል። የኢሳት ጋዜጠኞች የኤርትራና የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያቀራርቡ ፕሮግራሞችን ሰርተዋል፣ ልዩ ልዩ ድረ ገጾችም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያጠነጠኑ መጻጽፍትን አስነብበዋል አክቲቪስቶች፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮችና አባላት ስለሁለቱ ህዝቦች የወደፊት የጋራ እድል፣ የጋራ እጣ ፈንታ መልካም ራእዮችን በየመድረኩ ተናግረዋል። በመከባበር ላይ የተመሰረተ የወንድማማች ህዝቦች ግንኙነት የእነዚህን  የተለየ  የዘመናት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊና፣ ስትራቴጂካዊ ትስስር  ያላቸው ህዝቦች ሰላም  ከማረጋገጥ አልፎ ከፊታቸው የተደቀኑት፣ ውስስብ እየሆኑ የሚገኙ አለም አቀፋዊና ከአፍሪካ ቀንድ  ጋር የተገናኙ የጂኦኤኮኖሚክ፣ በጂኦፓለቲካና ጂኦስትራቴጂክ ነባራዊ ሁኔታዎች (realities) ጋር  ስጋቶችን  በጋራ ለመቋቋም፣ ከእነዚህ ሚመነጩ የጋራ እድሎችን ደግሞ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጥቅም፣ የጋራ ብልጽግና፣  የጋራ ደህንነት፣ ጠ/ም አብይ ዛሬ በአስመራ  በቤተ መንግስት እንደተናገሩት “የላቀ ትስስር” ወይንም የኤርትራ ፕሬዝደንት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት “ዝ ስካይ ኢዝ ዘ ሊሚት” (the sky is the limit) እንዳሉት ሁሉ በጋራ   የሚቋደሱበትን/የሚጋሩበት ሁኔታ የሚያበስር አዲስ የታሪክ ምእራፍ ነው። ሌላም ሌላም ብዙ ማለት ቢቻልም ሄዶ ሄዶ ዛሬ ላይ ለተደረሰው ውጤት እንዲመጣ በጎ ያለሙና የሰነቁ ህልሞችና ሃሳቦች አቸናፊ ለመሆን በቅተዋል።

ባለፉት አመታት ያራመድናቸው ሃሳቦች፡ ራእይና ህልማችን እውን የመሆን ጅማሮውን ለማየት በቅተናል። ብዙ ስራ፣ ብዙ ትግልም ይቀራል። መተማመን፣ መከባብር፣ መተሳስብ፣ በሁለቱም ወገን  የአጭር  ጊዜ ብልጣ ብልጥነት ትላንት እንዳለዋጡ ተረድቶ  ሩቅ አዳሪና ስትራቴጅካዊ አስተሳሰብ ከቅንነት ጋር መጋመድ ከተቻለ፣ በጣም ሩቅ ልንጓዝ እንችላለን። እንደ ሁለት ልዩ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ህዝቦች፣  በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሁለንተናዊ ሽርክና። ለዘመናት የሚዘልቅ።

Filed in: Amharic