>

‹‹ …ያኔ በምወደው የጋዜጠኝነት ሙያ እየሰራሁ እቀጥላለሁ›› ጀግናው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ከቃሊቲ እስር ቤት

በጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ

‹‹ …ያኔ በምወደው የጋዜጠኝነት ሙያ እየሰራሁ እቀጥላለሁ››
ጀግናው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ከቃሊቲ እስር ቤት)
=========
ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ከታች በፎቶግራፍ የምንታይ [ፎቶግራፉን ያነሳው አብነት ረጋሳን ጨምሮ] fጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በዓለም የጋዜጠኞች እና የዜና አታሚዎች ማኅበር የዓመቱ የወርቅ ብዕር የ “pen Golden of freedom 2014” ተሻላሚ በመሆኑ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› ለማለት ኬክ አስጋግረን ወደቃሊቲ አምርተን ነበር፡፡
ቁጥራችን መብዛቱ በቃሊቲ ያሉ ፖሊሶችን ግር ማሰኘቱ አልቀረም ነበር፡፡ ተፈትሸን ስንገባ አንድ የፖሊስ ኃላፊ አስቁመውን ‹‹የመጣችሁበትን ነገር አውቀነዋል፣ ቀለበት ይዛችኋል›› አሉን – ቆጣ በማለት፡፡ እኛ አስክንድር ነጋን እና አንዷለም አራጌን ልንጠይቅ እንደመጣን አስረዳናቸው፡፡ በዕለቱ አንዲት በቃሊቲ የታሰረች ሙስሊም እና በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታስሮ የሚገኝ ሙስሊም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት የሚያደርጉበት ፕሮግራም በመኖሩ መረጃው ለፖሊሶች በመድረሱ ነበር ፖሊሱ እኛን እንዲጠየቁ ያስገደዳቸው፡፡ [የሙሽሮቹን ጉዳይ ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን በፌስ ቡክ ገጹ ከሁለት ቀን በፊት ጽፎታል]
ገሚሶቻችን እስክንድርን አስጠራን፡፡ የተወሰኑ ደግሞ አንዷለምን በማስጠራት እየተቀያየርን ሁለቱንም ለማነጋገር እንደተለመደው አቅደን ነበር፡፡ ሆኖም ፖሊሶቹ እስክንድርን ያስጠራን ጠያቂዎች ወደ አንድ ጥግ እንድንሆን ነገሩን፡፡ የአንዷለም ደግሞ በአንድ ሌላ ጥግ ላይ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እስክንድር ተጠርቶ መጣ፡፡ በወቅቱ እስክንደርን ሳየው የ18 ዓመት ወጣት መስሎ ታየኝ፡፡ ጂንስ ሱሪ ከእጅጌ ጉርድ ሸሚዝ ጋር አድርጓል፡፡ ፊቱ ላይ ተፈጥሯዊ ወዙ ያንጸባርቃል፡፡ እውነተኛ ውስጣዊ ፈገግታውን ለሁላችንም ቸረን፡፡ በሽቦ ውስጥ አሳልፍን ጣቶቹን በየተራ ጨበጥናቸውና በዕለቱ ስለተደረገው የአጠያየቅ ሁኔታ ነገርነው፡፡ ‹‹ለምን እንዲህ ይደረጋል? በማለት አጠገቡ የነበረውን ፖሊስ ቆጣ ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹ሰው ስለበዛ!›› የሚል አጭር ምላሽ ፖሊሱ ሰጠ፡፡ እስክንድር ደጋግሞ ጥያቄውን አቅርቦ ነበር፡፡ ‹‹በቃ የመጠየቂያዋ ጊዜ አጭር በመሆኗ ተወው›› አልኩት፡፡ ‹‹አይ! መሆን የለበትም፣ ኃላፊዎቹን ስመለስ አነጋግራለሁ›› ካለ በኋላ ከጠያቂዎቹ ጋር መጫወት ጀመረ፡፡
እስክንድር አብሮን በነበረበት አጭር ጊዜ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ከሰላማዊ ምክሮች ጋር ለግሶናል፡፡
በመጨረሻም ይህቺን መልዕክት አስተላልፏል፡-
‹ሀገር ስትወረር ወይም ጠላት በሀገር ላይ ጦርነት ሲያውጅ ሁሉም ኢትዮጵዊ በአንድነት ‹‹ሆ!›› በማለት የተቃጣውን ወረራም ሆነ ጦርነት ለመመከት እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ሁላችንም ዴሞክራሲ ያሻናል፡፡ ሁላችንም ሀገር ሲወረርብን እና ጦርነት ሲታወጅብን በአንድነት እንደምንቆመው ሁሉ ይህንን ያጣነውን ዴሞክራሲ ለመጎናጸፍ፣ ሁላችንም በሰላማዊ መንገድ አጅ ለእጅ ተያይዘን እና አንድ ሆነን መታገል ይኖርብናል፡፡ ከትግሉም በኋላ ለውጥ ይመጣል፡፡ ያኔ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ስለሚፈጠር ሁሉም በየመንገዱ ይጓዛል፡፡ ለምሳሌ እኔ፣ ምንም የምፈልገው ሥልጣን የለም፡፡ ፍላጎቴም አይደለም! የሕይወት መስመሬ ጋዜጠኝነት ነው፡፡ ያኔ በምወደው የጋዜጠኝነት ሙያ እየሰራሁ እቀጥላለሁ፡፡ የህይወት መስመሩ ፖለቲከኝነት የሆነም ሰው በዚያው ይቀጥላል፡፡ ምሁሩም አካዳሚካዊ ነጻነት ስለሚያገኝ ወደሚወደው የትምህርት፣ የምርምርና ጥናት ዘርፍ ላይ በነጻነት ይሰማራል – ሌላውም በመንገዱ፡፡ ይህ እንዲፈጠር ግን ዛሬ ላይ በጋራ መታገል የግድ ይለናል!››
….‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› በማለት ይዘን የሄድነውን ኬክ ሰጠነው፡፡ ሽልማቱ የእኔ ብቻ አይደለም›› በማለት ደስ ብሎት ተቀበሎን በዚያ በሚማርከው ፈገግታው ‹‹ቻው›› ብሎ እጁን በማውለብለብ ተለየን፡፡ አንዷምን መጠየቅ ያልቻልነው ጠያቂዎች ከርቀር ስሙን ጠርተን በእጅ ሰላምታ፣ አክብሮታችንንና ፍቅራችንን ለገስነው፡፡ አንዷለምም በእጆቹ ከንፈሩን እና ልቡን እየነካ ልባዊ ሰላምታውን ሰጠን፡፡ …እኛም ቃሊቲን ተሰናብተን ወጣን፡፡
ለሐሳብ ልዕልና እንኑር!

Elias Gebru Godana's photo.
Elias Gebru Godana's photo.
Filed in: Amharic