>

አ”ሰ”ብ ሲያደርጉት! (ደረጀ ደስታ)

አ”ሰ”ብ ሲያደርጉት! 

ደረጀ ደስታ

ህዝብ ደስ ሲለው ደስ ይላል። ለባሰበትም ያስለቅሳል። እንባውን ጨምቆ የዛሬውን የአስመራ ነገር ያየ ሰው ሁሉ ሀሳብ ይነዳውና አሰብ ያደርጋል። እናም ይላል….አሁን ኢዚያ መኪናው ውስጥ ለብቻቸው ሆነው የኤርትራው መሪ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ወደ ጠቅላይ ምኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዞር ብለው፣ በጨዋታቸው መካከል፣ “ስማ ልጅ አብይ! በነገራችን ላይ የአሰብ ወደብን እንደፈለጋችሁ አድርጉት…!”ብለዋቸው ቢሆንስ? እና አጅሬው አብይ ደግሞ በነገው የአደባባይ ንግግራቸው፣ እኛ አሰብን ሳይሆን እምንፈልገው የወንድማችንን የኤርትራን ህዝብ ፍቅርና አንድነት ነው። እኛ ፍቅር ብንሆን አሰብና ቀይ ባህር ቀርቶ መላው ዓለም የሁላችንም ይሆናል! ብለው ቢናገሩስ። እንዲህ ያለው ንግግር ሕገመንግሥታዊ አይደለም ተብሎ ያስጠይቃቸው ይሆን? ወይስ እኛ አሰብን ተከራክረን እና ህዝቡም ተወያይቶበት እንጂ ዝምብለን አንቀበልም ይባል ይሆን? እንደዚያ ግልብጥ ብሎ በመዉጣት ፍቅሩን የገለጸው የኤርትራ ህዝብም ቢሆን እኛ ሳንመክርበትና ፍቅሩ ህገመንግሥታዊ መሆን አለመሆኑን ሳንወስንበት ገና ለገና ህዝብ ተዋዷል ብለን እምንገባበት ፍቅር አይሆንም እየተባለ መራቀቅና ፍቅር መሰንጠቅ ይኖር ይሆን?
እግዜር አሁንም “አሰብ የማን ናት?” ከሚለው ክርክር “ሕገ መንግሥቱ የማነው?” ወደሚለው ክርክር እንድንሻገር የሁለቱን መሪዎች ፍቅር ያሰንብትልን። መቸም ከአብይ በፊት ይቺ ሕገ መንግስት የማን እንደነበረች ኢሳያስ ያውቋታል። እሳቸውንስ ቢሆን እግዜር እና ጊዜ ብዙ ነገር ሳይገልጡላቸው ይቀራል? እንግዲህ ጸብና ፍቅሩን አይተውታል። አሰብ ቀርቶብን እንደ ህዝባቸው ልባቸውን ቢሰጡን ሁሉ ነገር ያበቃል! ኢትዮጵያም የሳቸው እንደነበረችው ኤርትራም የኛ ትሆናለች። ኦሮማይ ማለትስ ያን ጊዜ ነው!

Filed in: Amharic