>

ይድረስ ለእነ ሰልፍ አውጋዦች!  ባንዲራ ረጋሚዎች!?! (እስክንድር መርሐጽድቅ)

ይድረስ ለእነ ሰልፍ አውጋዦች!  ባንዲራ ረጋሚዎች!?!
በእስክንድር መርሐጽድቅ
በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በለቀምት፣ በጅማ፣ በጎንደር፣ በወራቤ፣ በሆሳዕና፣ በወልዲያ፣ በወልቂጤ፣ በ… ሰዉ የመጣውን ለውጥ ለመደገፍ የወጣው የጭፈራ አራራ ይዞት መሰላችሁ? ወይ ደግሞ እናንተ እንደምትሉት ህገ-መንግሥታዊ አሠራርን ለመናድ? ወይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻን ለማወጅ? ትምክህተኝነትን እና ጠባብነትን ለማስፋፋት? ህዝብን በጅምላ፣ “ጅቦች!” ለማለት? “ጅቦች!” ብሎስ የትግራይን ህዝብ ከሙሰኛ እና ገሪፊና አስገራፊ ሹመኛ ህወሀቶች ጋር በጅምላ ሊኮንን?
እያለ ያለው “ግርፉ፣ መከፋፈሉ፣ አድሏዊነቱ፣ ዝርፊያው፣ ፍረጃው፣ ‘ለእኔ ብቻ’ው፣… ይቁም!” ነው። ደግሞስ ጅብ የአንድ ብሔር ሹመኛ ሙሰኛ ብቻ ነው አለ’ዴ? ጅብ ከአማራም፣ ከሶማሌም፣ ከጉራጌም፣ ከኦሮሞም፣ ከወላይታም፣ ከሐረሪም፣ ከጉቤኒሻንጉልም፣ ወዘተ አለ። ደግሞስ… “ህገ-መንግሥቱ ተጣሰ” እያሉ ህዝብን ለማሳደም ጭምር መገናኛ ብዙሀንን እና ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ በበላውም፣ ባልበላውም ምሁር እና ባለሥልጣን አንደበት ማስፈራራትን ምን አመጣው? ህዝብ የመንግሥቱ ኃ/ማሪያምን ፎቶ ይዞ ሲወጣ ሰውየው አምባገነን እንዳልሆኑ ለመመስከር አይደለም፤ “ከእናንተ አይብስም!” ለማለት እንጂ! ልሙጡ ሰንደቅ ዓላማን፣ “እኛ ከጨርቁ ጉዳይ የለንም፤ ከርሱ ጀርባ ያለውን ግፍ ስለሚያስታውሰን’ጂ!” ብለው አቶ መለስ እንዳሉት ህዝብ ባለ ኮከቡን “አልይ!” ያለው ከ27 ዓመታት በፊት ከተሰሩት ግፎች በልጦ ስለተገኘ ነው። ሰንደቅ ዓላማ በተግባር ካልተተረጎመ እንደተባለው ክብሩ ከተራ ጨርቅነት አያልፍም። እሱን እያውለበለቡ ብልትን መስለብ ህገ-መንግሥታዊነት ነው? ሲኮላሽ የምናውቀው ኮርማ ነበር። “ህገ-መንግሥታዊ” ተብሎ ግን ሰዎች ተኮላሽተዋል። እግርን እንደ ፅድ እየከረከሙ፣ “ለምን ይህ ተፈፀመ?” ባይን “ህገ-መንግሥትን ጣስክ” አራዶቹ እንደሚሉት ሼም ነው! ዛሬ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና የአማራ መገናኛ ብዙኃን እያሳዩን ያለው ዘግናኝ በምርመራ እና በ”ህገ-መንግሥትን ጣሳችሁ!”  በሚል ሰበብ የደረሰው ግፍ በዶ/ር ዐብይ የስልጣን ዘመን የተፈፀመ ነው’ዴ? በጅጅጋም፣ በሌሎችም እስር እና ማሰቃያ ቦታዎች “ተፈፅሟል” እየተባለ ያለው በምርመራ ሰበብ መፈጠርን የሚያስጠላ ከድብደባም በላይ ቅጥቀጣ እና ጫፍ የወጣ አካል ማጉደልም ሆነ ግድያ የተከናወነው ባለፉት ሦስት ወራት ይመስል የጠ/ሚ/ሩን መንግሥት ማዋከብ እና የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል ምንኛ ይሆን?
ደግሞም እንደ አዲስ የተጀመረው አማራን ከኦሮሞም ሆነ ሌላውን ከሌላው ለመለያየት የመስራትም ሆነ ከመቼውም በላይ ህዝብን የማበጣበጥ ሙከራ በዜጎች ህይወት ላይ ቁማር መጫወት ነውና አሰማሪዎቹ በቀደመውና ጊዜ እየጠበቀ ባለው ወንጀላችው ላይ ሌላ ወንጀል ባይጨምሩ። ይህ የቅጣት ማክበጃ’ጂ ማቅለያ ወይም ማስተሰሪያ አይደለምና!
ይህ መንጠራወዝ የተሠራውን ወንጀል በሰንደቅ ዓላማ፣ በህዝብ እና መንግሥቱ ኃ/ማሪያምን በመሳሰሉ ሰዎች ፎቶ ሰልፍ ላይ መውጣት ተቃውሞ ስም አጀንዳን ማስቀየስ የተበላ ዕቁብን ያህል ነው። እነሱ “ህገ-መንግሥቱን የጣሰ ወንጀል ነው!” ሲሉ’ኮ ፍርድ ቤት፣ “ለጥፋቱ ያነሳሳቸው ነገር ምንድን ነው?” ማለቱ አይቀርም። መግባት ካለ ተያይዞ ይገባል’ጂ ህገ-መንግሥት ልጓሙ እየተያዘ እንደተፈለገ እንደሚታዘዝ የጋማ ከብት አይነት አይደለም።
ይልቅስ፣ “አላርፍ ያለች ጣት. .. ጠንቁላ ትወጣለች” እንደተባለው በእጅ የማይመዘዝ መዘዝ ውስጥ መግባት እንዳይሆን!
Filed in: Amharic