>
5:13 pm - Wednesday April 19, 9848

ይድረስ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ! (ስዩም ተሾመ)

ይድረስ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ!

ስዩም ተሾመ

ይህንን አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላይ ስለተቃጣ የግድያ ሙከራ የሚል ርዕስ የሰጠሁበት ምክንያት የወንጀል ፈፃሚዎቹ /የተጠርጣሪዎቹ/ ፍላጎት እሳቸውን መግደል እንደነበረ እና ወደሳቸው ሊወረወር የታሰበውን ቦንብ በወቅቱ በቦታው የነበሩ ሰዎች ለማስጣል ባደረጉት ሙከራ እዚያው አካባቢ በነበሩ ከመቶ በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱንና ለሁለት ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ በመታወቁ ነው፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ሌሎች የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ቢፈልጉ ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የሚያደርጉበት ቦታ ድረስ መጠጋት ሳያስፈልጋቸው ካደረሱት ጉዳት በላይ ውጤት በሚያገኙበት ቦታ ላይ በመሆን በበርካታ እጥፍ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ለጉዳዩ ተገቢውን ርዕስ መስጠት የአጥፊዎቹን የጥፋት ደረጃ በተገቢው ለመረዳት የሚያስችል በመሆኑ ይህንን ርዕስ ሰጥቼዋለሁ፡፡

ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቦንብ የፈነዳበትን ቅፅበት የሚያሳይ ምስል

በማብራሪያው ላይ የምርመራን ስራ ምንነት፤ መርማሪ ፖሊስ ሊኖረው ስለሚገባ እውቀትና ክህሎት፤ የሚያስፈልጉ የማስረጃ አይነቶች እና የሐገራችን ፖሊስ ምርመራ ያለበትን ደረጃ በጣም በአጭሩ ለመግለፅ ተሞክሮ ከዚያም ስለዋናው የሰሞኑ የግድያ ሙከራ በቀጥታ በመግባት የውጪ ሐገር የምርመራ አካል ተሳትፎን አስፈላጊነት ለማብራራት ተሞክሯል፡፡ መልካም ንባብ

1. ወንጀል ምርመራ ምንድን ነው?

ወንጀል ስንል አንድ በህግ እንዲደረግ የታዘዘ ወይም እንዳይደረግ የተከለከለ ነገር ተፈፅሞ መገኘት ሲሆን የወንጀል ምርመራ ስራም የሚነሳው ከዚሁ የህግ ጥሰት ነው፡፡ በአጭሩ የወንጀል ምርመራ ስራ አንድን የተፈፀመ የወንጀል ድርጊት መርምሮ በማስረጃ እውነቱን የማረጋገጥ ዘዴ ነው፡፡ ይህ እውነትን የማረጋገጥ ስራ በውስጡ የተፈፀመው ወንጀል ምንነት፤ የት፤ መቼ፤ በማን፤ እንዴት እና ለምን እንደተፈፀመ እንዲሁም ወንጀል ፈፃሚው ይህንን ድርጊት ለመፈፀም የተጠቀመበትን መሳሪያ፤ ስልት፤ እና ምን እንዳነሳሳው ጭምር የሚመልስ ነው፡፡

2. ለምርመራ የሚያስፈልጉ ግብአቶች

ሀ. ለሞያው ታማኝ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል፡- ምርመራ በሰው የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ይህንን ተግባር ለመፈፀም በህግ ስልጣን የተሰጠው ለሙያው ታማኝ የሆነ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ተግባሩን ለመፈፀም የሚያስችል መሳሪያ እና ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋል፡፡ ይህም የሰለጠነ የሰው ኃይል /ፖሊስ/ ሞያውን በመጠቀም ባለው መሳሪያ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ባገኘው መረጃ በመታገዝ የታክቲክና የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ እውነቱን አረጋግጦ ለሚመለከተው የፍትህ አካል /አቃቤ ህግ/ የሚያቀርብ ነው፡፡

ፖሊስ ሰራዊቱ ውስጥ በተለያየ ጊዜ ከፍተኛ የሐገሪቱ ሃብት እየፈሰሰባቸው በፖሊስ ሳይንስ የሰለጠኑ በርካታ ልምድ የነበራቸው መኮንኖች የነበሩ ቢሆንም ሆነ ተብሎ በሚደረግባቸው በደልና ግፊት ተቋሙን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ በየጊዜው የሚመረቁ ወጣት መኮንኖችም ሁለት አመት እንኳን ሳያገለግሉ በተለያየ አስተዳደራዊ በደልና ሞያቸውን በማንቋሸሽ በሚደርስባቸው የሞራል ስብራት ስራቸውን ለቀው እየወጡ በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች በመቀጠርና ሌሎች የግል መተዳደሪያ ስራዎች በመፍጠር በማይመጥናቸው ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ አሁንም በተቋሙ ውስጥ የቀሩት በጣት የሚቆጠሩ ባለሙያዎች የስራ ምደባው በብሄርተኝነትና የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከመድረኩ የተገለሉ እና የጡረታ ጊዜያቸውን የሚጠብቁ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ያለው የሐገራችን አጠቃላይ የፖሊስም ሆነ የወንጀል ምርመራ ስራው የሚመራውም ሆነ የሚሰራው የመጀመሪያ ደረጃ የፖሊስ ስልጠና እንኳን ባልወሰዱ አቶዎችና ታጋዮች ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመንግስት በኩል ፖሊሱን በክህሎትና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዝ ለማድረግ ፍላጎት የሌለ በመሆኑ ለዚህ የሚሆን በጀት መመደብና ስልጠና ለመስጠት የሚደረግ እንቅስቃሴ እምብዛም አይታይም፡፡ የዚህም ዋነኛ ምክንያት መንግስት የሚፈልገው በርከት ያለ ቁጥር ያለው የወንጀል መከላከል ኃይል ጎዳና ላይ በማሰማራት የህዝቦችን ጥያቄ የሚያፍን ሃይል መፍጠር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ መልክ ሰልጥነውና ተቃኝተው የወጡት የሰራዊቱ አባሎችም በየጉዳዩ ላይ የሚወስዱት እርምጃ ከህብረተሰቡ አይን የተሰወረ አይደለም፡፡

በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎች በሚኖሩበት ጊዜም መርማሪዎቹ ካለባቸው የስነ-ምግባርና የእውቀት ችግር በተጨማሪ በእነዚህ አለቆቻቸው የወንጀል ድርጊት የፈፀሙትን ሰዎች ወልዳችሁ አምጡ ተብለው ታንቀው ስለሚያዙ በማንኛውም ሁኔታ ተጠርጥሮ በእጃቸው የገባ ሰው ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመፈፀም የአለቆቻቸውን አፍ ለማስያዝ ሲሉ የፍትህ ስርዓቱን አሁን የገባበት አዘቅት ውስጥ ሊከቱት ችለዋል፡፡ ዛሬ በየምርመራ ክፍሉና በየማረሚያ ቤቶቹ የምናያቸው እሮሮዎችም ከዚህ የመነጩ ናቸው፡፡

ለ. የታክቲክ እና የቴክኒክ ማስረጃ፡- የታክቲክ ማስረጃ በተበዳይ፤ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆኑ ምስክሮች እንዲሁም ተከሳሹ በፍቃደኝነት በሰጠው የእምነት ቃል . . . ላይ ተመርኩዞ የወንጀሉን ድርጊት ማስረዳት ሲሆን የቴክኒክ ምርመራ ግን ሳይንሳዊ በሆነ መልክ የሚሰበሰብ ተጠርጣሪውን ከተፈፀመው የወንጀል ድርጊት ጋር የሚያገናኝ ተጨባጭ ወይም ቁሳዊ ማስረጃ ነው፡፡ ይህም ማለት ተጠርጣሪው በወንጀሉ ስፍራ የተወው ማናቸውም ነገር ለምሳሌ ከአካሉ የወጣ ደም ወይም ሌላ ፈሣሽ፤ የእግር ወይም የጫማ ዱካ፤ አሻራ፤ ለብሶት የነበረ ልብስ ቅዳጅ፤ ወንጀሉን ለመፈፀም የተጠቀመበት ቁሳቁስ ወይም መሳሪያ ወይም የዚህን ቅሪት . . . ወዘተ በመጠቀም ተጠርጣሪውንና ወንጀሉን ማገናኘት ነው፡፡

እነዚህ ሁለት የማስረጃ አይነቶች እንደሁኔታው በመተጋገዝ ወይም በተናጠል የወንጀሉን ድርጊት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሲሆን በተለይ የቴክኒክ ማስረጃ ሰው ባለመሆኑ ሊዋሽ፤ ሊሳሳት ወይም ሊደለል ስለማይችል ተአማኒነቱ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ወንጀሉ በተፈፀመበት ስፍራ የሚደርስ ፖሊስ /ባለሞያ/ ሌሎች ሰዎች እና እንሰሳት ወደ ወንጀሉ ስፍራ እንዳይገቡ በመጠበቅ በቂ የማስረጃ ፍለጋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በቦታው የደረሰው ባለሞያ ይህን ካላደረገ ማስረጃዎቹ በሌላ ሰው ወይም እንሰሳት ሊነካኩ፤ ሊቀያየሩ እና ሊበላሹ ስለሚችሉ የማስረጃነት ዋጋቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡

ከ1991 የኒውዮርኮቹ መንትያ ህንፃዎች የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ በለንደን ፖሊስ ቀዳሚነት የተጀመረውና ፕሮአክቲቭ ፖሊሲንግ በመባል በሚታወቀው አሰራር በርካታ ከተሞች ቀድሞ በሚተከል ካሜራና የሳተላይት ምስል በመታገዝ እየተከናወነ ያለን ድርጊት ገና ከጅምሩ ማክሸፍ ከሚችሉበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸውም ባሻገር ከወንጀል ድርጊት በኋላም ቢሆን ተቀርፀው የተቀመጡ ምስሎችን ወደኋላ ተመልሶ በመመልከት የወንጀል ድርጊቶችን በማየት ፈፃሚዎች እና ግንኙነታቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በአገራችን የቴክኒክ ምርመራው ያለበትን ደረጃ ስንመለከት በጣም የሚያሳዝንና ሞያውን ለሚያውቁ ሰዎች በጣም የሚያሳፍር ደረጃ ላይ መድረሱን እናያለን፡፡ ይህ ክፍል ከሰው ኃይሉ ውሱን ስልጠና ባሻገር አባሎቹ ማስረጃ ለመሰብሰብ ከመስታወት እና ከተሸከርካሪ አካል ላይ አሻራ ማጉላት የሚችሉ ሁለት አይነት /ግራጫና ጥቁር ፓውደሮችን/ ይዘው የሚወጡት ሲሆን ሊሎች ማስረጃዎችን ቢያገኙ እንኳን ሊሰበስቡ የሚችሉበት ምንም አይነት አጋዥ መሳሪያ የላቸውም፡፡ በነዚህ ፓውደሮች የሚያጎሏቸው አሻራዎችም ከወንጀለኛ አሻራ ክምችት ጋር ስለማይመሳከሩ ተጠርጣሪው በተበዳይ ተጠቁሞ ወይም ተይዞ ካልቀረበ በስተቀር ክፍሉ ማመሳከር እና ተጠርጣሪ መፍጠር አይችልም፡፡

በተጨማሪም ክፍሉ በባዮኬሚካል ምርመራ የሚደረግባቸውን እንደ ደም፤ ምራቅ፤ እስፐርም . . . .ያሉትን ማስረጃዎች ካለመሰብሰቡም ባሻገር ሌሎች የተሰበሰቡ ማስረጃዎችም ቁጥር ይዘው ሳይበላሹ የሚቀመጡበት ቦታ የሌላቸው በመሆኑ ከወንጀል ስፍራ የሚሰበሰቡ ማስረጃዎች ወደ ቢሮው ተወስደው በየጓሮው እና በየስርቻው የሚጣሉ ናቸው፡፡

ፖሊሱ በየትኛውም የታክቲክም ሆነ የቴክኒክ ምርመራ ስራ ብቃት እንደሌለው ማሳያ የሚሆነው በተለያየ ጊዜ ወንጀል ተፈፅሞባቸው ለማመልከት ወደ ፖሊስ የሚቀርቡ ሰዎች ማስረጃ አቅርቡ፤ ምስክር አላችሁ ወይ፤ ምስክር ይዛችሁ ኑ . . . እየተባሉ መጠየቃቸው እና ይህንን ማድረግ ካልቻሉ የአብዛኞቹ ሰዎች ክስ ሳይደመጥ መቅረቱ ነው፡፡ ይህ ማስረጃን የመሰብሰብ እና የመተንተን የምርመራ ስራ የፖሊሱ ሆኖ ሳለ ፖሊስ ተበዳዮቹን እናንተ ስሩልኝ እኔ አልችልም ማለቱ በትንንሽ ጉዳዮች ላይ እንኳን ፖሊሱ ያለበትን የአቅም ውሱንነት ያሳያል፡፡

3. የሰኔ 16 የፍንዳታ ወንጀል ትንታኔ

ሀ. የሰኔ 16 የድጋፍ ሰልፍ ፕሮግራም ቀደም ተብሎ በመገናኛ ብዙሃን የተገለፀ በመሆኑ ፖሊስ ለጥበቃ የሚሆን በቂ ዝግጅት ማድረግ ይችል የነበረ ሲሆን በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የሌሎቹን እንግዶች ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የሰራዊት ቁጥር ከመድረኩ አቅራቢያ መመደብና ተሰብሳቢውን በበቂ ርቀት ማገድ ሲገባው ይህንን አላደረገም፡፡

ለ. ፍንዳታውን የፈፀሙት ሰዎች የነበሩበትን ርቀት ስናይ ጉዳቱን ለማድረስ በሚያስችል በቂ ርቀት ላይ እንዲገኙ ቀደም ተብሎ ታስቦ የነበረ መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተለመደው ንግግሩን ጨርሰው ቢወጡ ኖሮ በቀጥታ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ለነበሩበት ቦታ የበለጠ ቅርብ በሆነ ርቀት ያልፉ ስለነበረ በቀላሉ ያሰቡትን ማሳካት ይችሉ ስለነበር ነው፡፡

ሐ. ሰልፉ አራት ሰዓት ላይ እንደሚጀመር ቀደም ብሎ በመገናኛ ብዙሃን ተደጋግሞ በመነገሩ ወንጀሉን ለመፈፀም የተዘጋጁት ሰዎች ይህንን ሰዓት ከግምት በማስገባት ዝግጅት በማድረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብለው በመገኘት ንግግሩን አድርገው መጨረሳቸው የወንጀለኞቹን እቅድ ያዛባባቸው ይመስላል፡፡

መ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሩር በሚያደርጉበት ጊዜ አንበሳ ህንፃ ላይ ይለቀቅ የነበረው ሙዚቃና የነበረው ግርግር የተመልካቾችን እይታ ወደዚያ ለመሳብ የተደረገና በዚህም ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበለጠ እንዲጠጉና ቦንቡንም ሲያወጡ በሰዎች እይታ ውስጥ እንዳይገቡ ለማገዝ የተደረገ ይመስላል፡፡ የዚህም አንዱ ጠቀሜታ ወንጀለኞቹ በቀላሉ ያሰቡትን ለማሳካት እንዲችሉ ሲሆን ሁለተኛም ቦንቡን የወረወሩት ሰዎች ሳይያዙ እንዲቀሩ ለማድረግ ይመስላል፡፡

ሠ. ፖሊስ አንበሳ ህንፃ ላይ ይደረግ የነበረውን ግርግርና የድምፅ ረብሻ ለማስቆም አለመሞከሩም ቀደም ብሎ የታቀደ ነገር ነበር የሚለውን ጥርጣሬ ያጠናክረዋል፡፡

ረ. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሩን አድርገው ከጨረሱ በኋላ ህዝቡን ተሰናብተው ሊሄዱ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ዝግጅቱ ያለቀ ስለመሰላቸው ያዘጋጁትን ቦምብ ካወጡ በኋላ የአዘጋጅ ኮሚቴው የቀረ ፕሮግራም አለ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲመልሳቸው ወንጀል ፈፃሚዎቹ ግን ቦንቡን ወደነበረበት መመለስ ስለማይችሉ እዚያው ሊያፈነዱት ተገደዋል፡፡

ሰ. ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መግለጫ ሲሰጡ የድጋፍ ሰልፉ በርካታ ህዝብ የተሰበሰበበት በመሆኑ ጥበቃው ከባድና አስቸጋሪ እንደነበር ገልፀው ከዚህ አንፃር ሲታይ በሰላም እንደተጠናቀቀ ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ቦንቡን ያፈነዱት ሰዎች ቀደም ሲል ወደቦታው አልፈው በመግባት ዝግጅት ያደረጉ በመሆኑ ጉዳት ሊያደርሱ ችለዋል ብለዋል፡፡

ለወትሮው እንዲህ አይነት ስብሰባ ሲኖር ፖሊስ ቀደም ብሎ ቦታው ላይ ፍተሻ እንደሚያደርግና ከፍተሻውም በኋላ ሌላ ሰው ወደ ቦታው አልፎ እንዳይገባ ጥበቃ እንደሚያደርግ እየታወቀ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ቀድመው የገቡ ናቸው የሚለው አባባል ለማንም የሚያሳምን አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽነሩ በሰልፉ ላይ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ጥበቃ የሚደረገው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሌሎች በመድረክ ለነበሩ እንግዶች ሆኖ ሳለ እነሱ ላይ ይህንን ያህል ጥቃት በተሰነዘረበት ሁኔታ የተሳካ ጥበቃ አድርጌያለሁ ማለታቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ከዚህ በላይ ምን ሊከሰት ነበር የሚል ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ሸ. የነበረውን የጥበቃ ክፍተትና ወንጀሉን ለመፈፀም ወደቦታው የመጡት ሰዎች የፖሊስ ሰሌዳ ያለው ተሸከርካሪ መጠቀማቸውን ስንመለከት ከፖሊስ ተቋም ውስጥ ቀደም ብሎ ወንጀሉ እንደሚፈፀም የሚያውቅ አካል መኖሩንና ትብብር ያደረገ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ቀ. ሌላ የፖሊስ ተሸከርካሪም በግምት አራት ሰዎችን በኮፈኑ ላይ አስተኝቶ ለሰልፍ በተሰበሰበው ህዝብ መሐል በፍጥነት እያሽከረከረና ሰው እየገጨ ሲሄድ በመጨረሻም ማለፊያ ቦታ በማጣቱ አንድ ሰው እግር ላይ እንደቆመ በህብረተሰቡ ትብብር እንዲቆም የተደረገ መሆኑን ናሆ ቴሌቪዥን የቀረፀው ምስል አሳያል፡፡ ይህ ተሸከርካሪ በርካታ ቦንቦችን ጭኖ ሲጓዝ እንደነበረ በቦታው ነበርን የሚሉ ሰዎች ሲያወሩ የተደመጠ ሲሆን ይኸው ተሸከርካሪ ከተቃጠለ በኋላ በውስጡ ብሪፍ ኬዝ የመሰለ ቦንብ ተቀምጦበት ነበር የተባለ ሻንጣ ተመልክተናል፡፡

በ. ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ላይ ወንጀለኞቹ ቀደም ብለው ወደቦታው የገቡ ናቸው ብለው በርግጠኝነት የተናገሩበትን ሁኔታ ስንመለከት ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ብለው ይግቡ ወይም በሰልፉ ወቅት ይግቡ በምን ተረጋግጦ ነው በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ሊሉ የቻሉት ወይንስ ቀደም ብለው ያውቁ ነበር የሚል ጥያቄ በህብረተሰቡ ዘንድ አስነስቷል፡፡

ተ. ወንጀሉ ከተፈፀመ በኃላ በህብረተሰቡ ትብብር ተጠርጣሪዎቹ ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ ፖሊስ የወንጀሉን ስፍራ ለመከለልና ለመጠበቅ ያለመሞከሩ ሲታይ በተከሳሾቹ ላይ ማስረጃ እንዲጠፋ በማድረግ በወደፊቱም የምርመራ ውጤት ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ለማድረግ የታሰበ ነገር እንዳለ ያሳያል፡፡

እንደሚታወቀው የፈንጂ ነገሮች ምርመራ ከምስክሮችና ከተጠርጣሪዎች ቃል በተጨማሪ በዋናነት የወንጀል ስፍራውን በማጠርና የፈነዳው ነገር ምን እንደሆነ፤ ፍንዳታው ምን ያህል ራዲየስ እንደሸፈነ . . . በማወቅ የፈነዳውን ነገር መጠን፤ አይነትና የየት ሐገር ስሪት እንደሆነ እንዲሁም ከቀረቡ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ይህንን የፈነዳ ነገር ለማግኘት አክሰስ ያለው አካል ማን እንደሆነ በማወቅ ዋናውን ተጠርጣሪ ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ መረጃ ማግኘት የሚቻለው በወንጀል ስፍራ ምርመራ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ምርመራ ህዝቡም ሆነ የፖሊሱ አካል ለተጎዱት ሰዎች እርዳታ ካደረጉ በኋላ የወንጀሉን ስፍራ ማጠርና መጠበቅ እንዲሁም በቂ ጊዜ ወስዶ ማስረጃ መሰብሰብ ሲገባ ይህ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡

ቸ. የዚህን ጥቃት አድራሾች ማንነት ስንመለከት ሁለቱ ጎዳና ተዳዳሪ የመሰሉ ሴቶች በመሆናቸውና ከዚህ ቀደምም በባህር ዳርና በጎንደር መሰል ወጣቶች ቦንብ ይዘው መገኘታቸውን ስናስታውስ እንዲሁም የፖሊስ ተሸከርካሪውን ተሳትፎ ስንመለከት ከእነዚህ ወጣቶች ጀርባ ሌላ አካል እንዳለ አመላካች ነው፡፡

ነ. አንዳንድ ሰዎች ከድጋፍ ሰልፉ አስቀድሞ ወደሰልፉ እንዳይሄዱ ነገር ግን ቢሄዱ በቦምብ ተቆራርጠው እንደሚመለሱ ለመንግስት ቅርበት ባላቸው ወዳጆቻቸው የተነገራቸው ቢሆንም ይህንን ባለማመናቸው ሄደው የሆነውን ነገር በመመልከታቸው በጣም እንደተገረሙ ገልፀው አስቀድሞ የታሰበ ነገር ነው እያሉ በከተማው በሰፊው የሚወራ በመሆኑ ይህን በቀጥታ በቦምብ ትቆራረጣላችሁ የሚል አገላለፅ ከተራ ጥርጣሬ ያለፈ በመሆኑ ምርመራውን የያዘው አካል በዚህም ዙሪያ ጠንካራ ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡

4. ምርመራው በሌላ አካል እንዲሰራ የመደረጉ አግባብነት

ከላይ በአጭሩ ለማሳየት እንደተሞከረው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ቦንብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ተመሳሳይ ወንጀል ፈፃሚዎች መገኘታቸውን ስንመለከት ከፖሊስ ተቋሙም ከፍ ባለ ደረጃ ያለ አካል በወንጀሉ ሳይሳተፍበት እንዳልቀረ የሚያስጠረጥር ነው፡፡ የፖሊስ ተቋሙም ውስጥ ቢሆን የወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦች ያሉ በመሆኑ ምርመራውን ለመስራት የሚያስችል እምነት የሚጣልበት ተቋም አይደለም፡፡ በአጠቃላይ በሐገራችን ፖሊስ ውስጥ የምርመራ ስራ አለ ለማለት የሚያስችል ምንም አይነት የሙያ ክህሎትና ታማኝነት እንዲሁም ቴክኖሎጂ የሌለ በመሆኑ የሃገሪቱ ፖሊስ በዚህ ምርመራ ላይ ቢሰማራ እንኳን ወደፊት የሚያመጣው የምርመራ ውጤት የሚታመን አይሆንም፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የሐገራችን ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራውን ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ የሌለው በመሆኑ ይህንን ስራ ሌላ ብቃት ያለው ገለልተኛ አካል ሰርቶት እውነቱን በማያጠራጥር ሁኔታ ለህዝቡ ቢያቀርብ በውጤቱ መተማመን ላይ ለመድረስ ከማስቻሉም ባሻገር አጥፊዎቹም ላይ በተረጋገጠ ማስረጃ ህጋዊ ፍርድ ለመስጠት ያስችላል፡፡

ወደ ፖሊስ ተቋሙ ኃላፊዎች ስንመጣ በዚህ የወንጀል ድርጊት ላይ የነበራቸው ተሳትፎ በኢቲቪ እንደተገለፀው ክፍተት በመፍጠር ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በተሳታፊነት፤ በተባባሪነት፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት እና ሆነ ብሎ ማስረጃ እንዲጠፋ በማድረግ በተደራራቢ ወንጀል መጠየቅ ያለባቸው መሆኑን የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡

ይቀጥላል…

***

የፅሁፉ አቅራቢ ከ20 ዓመት በላይ በተለያዩ የምርመራ ዘርፎች ላይ በሰራተኝነትና በኃላፊነት ደረጃ ሲሰራ የነበረና የተቋሙን ሁኔታ በዝርዝር የሚያውቅ በመሆኑ በዚህ ፅሁፍ ላይም ሆነ በሌላ የተቋሙ አሰራሮች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች እንደአስፈላጊነቱ ተከታታይ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ይወዳል፡፡ Seyoum Teshome

Filed in: Amharic