>
5:14 pm - Friday April 20, 5477

የባህር ዳሩ ኢሜግሬሽን ስውሩ 'ኦሽዊትዝ' የህወሀት ማሰቃያ !!! (ቹቹ አለባቸው)

የባህር ዳሩ ኢሜግሬሽን ስውሩ ‘ኦሽዊትዝ’ የህወሀት ማሰቃያ !!!
ቹቹ አለባቸው
አሁን የማነሳው ነገር በቀጥታ ከጎንደር ጋር የሚያያዝ ሁኖ ሳይሆን አባባሉ ለሁሉም የአማራ ከባቢዎች  ስለሚሰራ ነው፡፡ ሰሞነን አማራ ቴሌቪዥን በነማስረሻ ሰጤና በሌሎቹ ወንድሞቻችን ላይ ዘራቸውን መሰረት ተደርጎ የተፈጸመውን  ግፍ በቀጥታ ህዝብ እንዲመለከተው ማድረጉን ተከትሎ አዳዲስ ተዳፍነው ቆዩ ነገሮች እወጡ ነው፤ገናም የሚወጡ ይመስለኛል፡፡በዚህም አማራ ቴሌቪዥን እውነተኛ አማራ ህዝብ ሀብት ለመሆን እየዳዳው ይመስለኛል፡፡ ምን አልባት  ቹቹ አላባቸውና ሻንበል ከበደ እንዲሁም ሙሉጌታ የተባለ የህግ ባለሙያ በትላንትናው እለት በአማራ ቴሌቢዥኝ ቀርበው ያካሄዱትን ውይይት እንዳለ ሳይቆራርጥ ካቀረበው በተቋሙ ላይ ማሳደር የጀመርኩትን እምነት ከፍ ያደርግልኝ ይሆናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የፌስ ቡክ ጓደኞቸ ይህን አውቃችሁ ውይይታችን በአማራ ቲቪ ከሰሞኑ ይቀርብ ይሆናልና ተከታተሉት፡፡
————-////—-
ወደ ነገሬ ልመለስ፡፡ እኔም የነማስረሻ ሰጤን ግፍ እንዳዳመጥኩ እንደ አንድ አማራ የምለው ቢጨንቀኝ ፤የባህር ዳር ኢሚግሬሽን ይዘጋለ፤ወይ ይፍረስ የሚል ሃሳብ አቀረብኩ፡፡ ይህን ሃሳቤን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ደረሱኝ፡፡ አንዳንዶቹ አባባሌን በደንብ ካለመረዳት ነው፡፡ ይሀ ቢሮ ይዘጋ ማለት ተቋሙ አገልግሎት መስጠቱን ያቁም ማለት አይደለም፡፡ ማዕከላዊ ሲዘጋ ሌላ ማሰሪያ ቤት አልተዘጋጀም እንዴ? ባ/ዳርም ይዘጋ ሲባል ማፈኛ የማይሆን ሌላ ቦታ ላይ ተቋሙ ይቋቋምና አገልግሎቱን ይቀጥል ማለት እንጅ ፤ ከነጭራሱ አገልግሎቱ ይቋረጥ፤ ህዝቡ ወደ አዲስ አበባ እየሔደ አገልግሎቱን ያግኝ ማለት  አይደለም፡፡በዚህ ተረዱት፡፡
ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ አንድ ወዳጀ ይህ  ቢሮ  ይፍረስ ማለቴን ተከትሎ በመገረም ወይ ጉድ አንተም እስከዛሬ አታውቀውም?  ሲል በግርምት ጠየቀኝ ፡፡ እውነት ነው እኔም እንደ አንድ የባ/ዳር ነዋሪ ይህን ቢሮ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት  ተመላልሸበታለሁ፡፡ ነገር ግን የሰዎችን ሂዎት አክሞ ነብስ ከሚዘራው ፈለገ-ሂዎት ሆስፒታል አጠገብ እንዲህ የአማራ ልጆች የሚሰቃዩበት ቦታ ይኖራል ብሎ የሚገምት ምን አይነት ሰው ነው? ከትልቅ አስፓልት ፊት ለፊት ፤ከፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ ፊት ለፊት፤ ከክልሉ አስተዳደር ጽ/ቤት ፊት ለፊት፤ አንድ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋም፤እንዲህ ማሰቃያ ይሆናል ብሎ የሚተነብይ ነብይ ማነው? ለነገሩ እንኳን እኔ ብአዴን እንደ ድርጅትም (ግለሰቦች ይኖሩ ይሆናል)፤በዚህ ተቋም ውስጥ እንደዚህ ያለ ግፍ እየተፈጸመ ስለመሆኑ  የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ብአዴን ብቻ አይደለም የክልሉ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ፤ እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎችም፤ የዚህን ቢሮ ውስጣዊ ሁኔታውን በደንብ  ስለማወቃቸው እጅግን ሲበዛ እጠራተራለሁ፡፡ ለምን እንደዚህ እንደምል ቀጥየ አጫውታችኃለሁ፡፡ በዚህ ቢሮ ውስጥ እንደዚህ አይነት ግፍ እንደሚፈጸም  የማወቅ እድሉ የሚኖራቸው በአብዛኛው የደህንነት ሰው ብቻ መሆኑን መገመት ተገቢ ነው፤ ከደህንነትም ደህንነት ተመርጦ ሊሆን ይችላል፡፡
———————/////////
ቢሮው ይፍረስ የሚል አስተያየት መስንዘሬን  ተከትሎ በቀጥታ የደረሱኝ አስተያየቶች እንዳሉ ሁኖ ገራሚው መረጃ የመጣልኝ ግን በውስጥ መስመር ነው፡፡ ቀዳሚው አየር መንገድ ውስጥ  ከምትሰራው እህቴ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ የዝች ልጅ አባት ሰጠኝ ምህረት ይባላል (አሁን ጡረታውን አስከብሮ  አዲስ ዘመን ከተማ ይኖራል፤በትላነቱ እለት ደግሞ ታሪኩን በመጽሀፍ ጽፎ አስመርቋል)፡፡ ይህ አጎቴ በለሳ ውስጥ  ከነበረከትና አዲሱ ለገሰ ጋር ኢህአፓ ሁኖ ታግሏል፡፡ አባቱ ኢህአፓ ሁኖ ከደርግ ወታደር ጋር ሲፈላም በጀግንነት ተዋግቶ አንድ ሰው ሊፈጽመው ይቻለዋል ተብሎ የማይገመት ታሪክ ሰርቶ አልፋል፡፡ ይህ ሰው የኔ አያት ምህረት ታየ ይባላል፤ በለሳ ውስጥ ይህን ሰው የማያውቅ ቡዙም  አየይኖርም ፡፡ የበረከት አባት (አባ ገ/ሂዎት) የበለሳን ት/ቤቶች በ1960 ዎቹ እየዞረ ሲሰራ ማረፊያው  የምህረት ታየ ቤት ነበር፡፡ ተስፋ ምህረት የተባለው የሰጠኝ ምህረት ወንድም ደግሞ ከኢህዴን ጋር ሲታገል ደርግ ገደለው፡፡ ብቻ ቤተሰቡ እንዲህ አልቆ ሰጠኝ ምህረት ተረፈ፡፡
———/////————–
ሰጠኝ ምህረት ደግሞ በብአዴን ጊዜ በበለሳ ወረዳ ውስጥ የወረዳ አመራር ሁኖ ተሸመ፡፡ ወቅቱ 2001 ዓ.ም ነው፡፡ እኔያኔ  ጅማ ዩኒቭርስቲ እማር ነበር፡፡ አንድ ቀን ሰጠኝ ምህረት የብአዴንን ተልኦኮ ለማሳካት፤ በለሳ ወረዳ  አጭቃን ማሪያም  የምትባልን ቀበሌ ህዝብ ሰብስቦ እያወያየ ነው፡፡ ስብሰባው ላይ እንዳለ የታጠቁ ፖሊሶች ከመድረክ አንስተው ሰጠኝን በመኪና ጭነው ጉዞ ወዳልታወቀ ቦታ፡፡ ይህን ሰው ትረፍ ሲለው የጓህላ ከተማ ህዝብ ነገሩን ይሰማማና ያችን መኪና አንለቅም፤ ወንድማችንን አንሰድም ይላል፡፡ ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር ሲል በሽማግሌዎች ነገሩ ይበርደና ነገሩ ተጣርቶ ይመለሳል ተብሎ ሰጠኝ ምህረት ወደ ህግ ይቅረብ ተብሎ በለሳን ተሰናብቶ ከአሳሪዎቹ ጋር ይሄዳል፡፡
ሰጠኝ ከበለሳ ከወጣ በኃላ ቀናት እያለፉ ነው፤ ነገር ግን ሰጠኝ እንኳን  ቶሎ ወደ ቤቱ ሊመለስ ያለበት አድራሻውም አልታወቅ አለ፡፡ እኔም ጅማ ሁኘ አስተዳደርና ፀጥታ ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችን ቢያንስ አድራሻውን እንዲነግሩን ብማጸንም  እነሱም አናውቀውም አሉኝ፡፡ የት እንሂድ ፡፡ በዚህ መልኩ 32 ቀን ሙሉ የሰጠኝን አድራሻ ሳናውቅ ከረምን፡፡ በ32 ኛው ቀን ማታ የሆኑ ሰዎች ለሰጠኝ ምህረት ቤተሰብ ስልክ ይደውሊና ነገ 2፤30 የ 50, 000 ብር ዋስ ይዛችሁ በመቅረብ አባታችሁን ማስፈታት ትችላለችሁ ይባላሉ፡፡ ወድያውኑ ደስታና ድንጋጤ  በፈጠረው ስሜት ከቤተሰቦቹ  ለደዋዩ ሰውየ ቀረበው ጥያቄ የት እንምጣ? የሚል ነበር፡፡ ደዋዩ ሰውየ ባ/ዳር ኢሚግሬሽን ቢሮ ብሎ እርፍ፡፡
—————///———
ይህን ነገር ያወቅኩት ( አጎቴ ለ32 ቀን ታፍኖ ቆየበትን ልዩ ቦታ ማለቴ ነው) ገና ትላንት ማታ ነው፡፡ እስከዛሬ የነበረኝ ግንዛቤ አጎቴ ያን ያክል ጊዜ ታፍኖና ታስሮ የነበረው መኮድ  ውስጥ እንደነበር ነው የምገምተው ፡፡ አሁን ይች እህቴ (የሰጠኝ ልጅ) ነገሩን ሁሉ ስታስተውሰኝ፤ እነ ሰጠኝ፤ ፍ/ቤት የሚቀርቡት ማታ ማታ እንደነበር ፤ይሄንም የሆነ ሰው ነግሯት ማታ ማታ ከናቷ ጋር ከሆነ ቦታ ተደብቃ ፍ/ቤት ሲገቡ እና ሲወጡ ስትከታተል እንደነበር አጫወተችኝ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ፍ/ቤቶቻችንም ከመደበኛው የስራ ስአት ውጭ በደህንነቱ እየተገደዱ በምሽት ሁሉ ይሰሩ ነበር ማለት ነው፡፡በመጨረሻም ይች እህቴ እንደነገረችኝ ከሆነ እስከዛሬም ድረስ ከጭንቅላቷ ያልወጣላት ነገር ቢኖር፤ አባቷን ለመስፈታት በሄደችበት ወቅት አንድ ትግርኛ ተናጋሪ የተናገራት ነገር ነው፡፡ እኔ እኮ የመደመር ነገር ሲነሳ ጥያቄ ማነሳው ፤ ከነዚህ ሰዎች ጋር እንዴት በአንድ ተደምሮ በአንድ አገር ከነዚህ ሰዎች ጋር በጋራ መኖር እንደሚቻል ስለሚጨንቀኝ ነው፡፡
———–///////——–
ገራሚው ነገር ግን የኢሚግሬሽን ጽ/ ቤቱ ከአስተዳደርና ጸጥታ እና ፖሊስ ኮሚሽን መ/ቤቶች ፊት ለፊት ሁኖ እያለ፤  እንዴት ነው ነገሩ ከነዚህ ተቋማት ኃላፊዎች  እውቅና ውጭ ይሄ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም የኖረው የሚለው ነው፡፡ መቸም የነዚህ ተቋማት ኃላፊዎች ይህንን ቦታ የግፍ መፈጸሚያ ቢሮ መሆኑን አናውቅም ነበር ብለው ቢናገሩ የሚያምናቸው አንድም ሰው ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ እኔ ግን በወቅቱ ቢያንስ በፖሊስ እርግጠኛ ባልሆንም፤ አስተዳደርና ጸጥታ ላይ ኃላፊ በነበሩት ሰዎች ግን እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ኃላፊዎቹ ስለ አጎቴ መታሰር አውቀዋል፤በጤንነት መኖሩንም አረጋግጠዋል፤ ከየትኛው ቦታ ታፍኖ እንዳለ ግን በርግጠኝነት ያውቁ ነበር ለማለት አልችልም፡፡ ከነሱ አፍንጫ ስር ታፍኖ እንደነበር ያውቁ ነበር ብየ አልተረጠርኩም፡፡ ይህን የምልበት ምክነያት አንደኛው ነገር እንደራሴ አድርጌ  የማምነው ጓደኛ፤የፈለገ ቢሆን ነገሯን አንተ ብቻ በሚስጥር ያዛት ይሀል እንጅ፤ እንደዛ  ጓደኛው ያን ያክል እየተጨነቀ ነገር ይደብቀዋል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ፤እነዚህ አመራሮች ሁሌ  የሰውየውን አድራሻ ለማወቅ የኔን ያክል ሲዳክሩ እንደሚውሉ በየቀኑ ይነግሩኝ ነበር፡፡ እኔ እንግዲህ ጓደኛ አማኝ ስለሆንኩ ዛሬም እነዛን ጓደኞቸን አያውቁም ነበር በሚለው እምነቴ ነው ያለሁት፡፡ የኔን ጓደኝነት ክደው በወቅቱ ዋሽተውኝ ከሆነ ምንም ማድረግ አልችልም፤ እኔ ግን ዛሬም አምናቸዋለሁ፡፡
——–///////////———
ለሁሉም ከዚህ የምንማረው ትምህርት አለ፡፡ ይሄውም፤
1. ህውሀትና ደህንነቱ፤ይችን አገር ምን ያክል በብቸኝነት ሲገዘግዛት እንደኖረ፤
2. ብአዴንና የጸጥታ ተቋማቱ፤አስፈላጊውን መረጃ ከማግኘት ጀምሮ የአማራን ህዝብ ከጥቃት በመከላከል በኩል ምን ያክል አቅመቢስ ሁነው እንደኖሩ፤
3. አሁንም በየከተሞቻችን ( በተለይም ጎንደር ፤ባ/ዳርና ደሴ)፤ ተመሳሳይ የማሰቃያ ተቋማት እንዳሉና ፤ በስፋት አሰሳ በማድረግ ማጋለጥ እንዳለብን፤ወዘተ…….ናቸው፡፡
አሁን ለጊዜው ይብቃኝ፡፡ ነገር ግን ሌሎች በዚሁ ተቋም ዙሪያ ( የባ/ዳር ኢሚግሬሽን)፤ የደረሱኝ ሌሎች አስገራሚ  መረጃዎች ስላሉ እነሱን በሌላ ክፍል አካፍላችኃለሁ፡፡ እስከዛው ግን ሁሉም ወጣት ከተሞቹን ይሰስ፤ መረጃ ይሰብስብ፤ቢያንስ ለታሪክ ህዝቡ እነዚህን የማሰቃያ ተቋማት፤ይወቃቸው፤ተቋሞቹም እርማቸውን ያውጡ፤ ይናዘዙ፡፡
Filed in: Amharic