>
5:13 pm - Tuesday April 20, 6432

ሱዳን ድንበር ውዝግብ ጉዳይ መጨረሻው ምን ይሆን ? (ቹቹ አለባቸው)

ሱዳን ድንበር ውዝግብ ጉዳይ መጨረሻው ምን ይሆን ?

ቹቹ አለባቸው

በማውቀው ልክ ያለኝን መረጃ ለማካፈል መቆየቱን መርጨ ነበር፡፡ አሁን ግን ዛሬ በመተማና ቋራ ከባቢ የምሰማው ነገር ጥሩ ባለመሆኑ፤ ስለጉዳዩ ቲንሽ መተንፈስ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ ስለሆነም ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ ጥናቱን አብረውኝ ከሰሩት ጓደኞቸ ጋር ተነጋግረን የምናካፍላችሁ ሁኖ፤ለጊዜው እና ለማቆያ ትሆናችሁ ዘንድ ጥቂት ልበላችሁ፡፡

1. ስረ- ነገሩ፡
የሱዳንና ኢትዮጵያ ደንበር በውል የተለየ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይም ለሰ/ጎንደር ዞን እንደፈተና ሁኖ መከሰት የጀመረው ታሪኩ እረዥም ቢሆንም፤ በውል መታወቅ የጀመረው ግን ከደርግ ውድቀት በኃላ ነው፡፡ ሱዳኖች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት የተሰመረውን በተለምዶ ጊወን ላይን የሚባለውን መሰመር እንደ ወሰን ይቆጥሩታል፤ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ይህን ባለመቀበል የሀገራችን ደንበሩ ጓንግ ወንዝ ነው እንላለን፡፡ በዚህ በኩል ስምመነት የለም፡፡ በዚህ በኩል ስምመነት ለመድረስም ቡዡ ጥረት ተደርጓል፤ ግን አልሰመረም፡፡ በዚሁ የሁለቱ አገሮች የደንበር ውይይት እኔው እራሴ በአንድ ወቅት የተሳተፍኩበት ሲሆን፤ ከእኔ በኃላ ስለተከናወነው ስራም በሂደቱ የተሳተፉ አንዳንድ ደፋርአመራሮች ሁኔታውን አጫውተውኛል፡፡ ስለሆነም ሙሉም ባይሆን ቡዙም የመረጃ ችግር አይኖርም ማለት ነው፡፡

2. የደንበር ማካለሉ ስራ እውን የአገራችንን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እተካሄደ ነው?

አሁን መንግስት ከሱዳን ጋር ደንበሩን ለመወሰን እየሄደበት ያለው መንገድ በወሳኝነት የአገራችንን ጥቅም የሚያስከብር መሆኑንን ይናገራል:: እውነት ነው በዚህ በኩል እንዴው በደፈናው ጥሩ ነገሮች እንዳሉ እኔም አውቃለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን በዚህ በኩልም ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ እያጣነው ያለና ያጣነው ጥቅምም እንዳለ መታወቅ አለበት፡፡
ሁለቱን አገሮች ደንበር ለመወሰን ለመወሰን፤ከረዥም አመታት ጀምሮ ከሁለቱም አገሮች የተውጣጡ ኮሚቴዎች ተቁቁመው ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡ በአንድ ወቅት በተለይም በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች፤እኔም የዚህ ኮሚቴ አባል ሁኘ ተሳትፌ ነበር፡፡ እስከማስተውሰው ድረስ በዚህ ወቅት አማራን በመወከል ተሰማ ገ/ሂ፤አዲሱ ለገሰ፤በረከት ስምኦን፤ዋነኞቹ ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፤ ከወረዳ አመራሮች ደግሞ ቹቹ አለባቸውና ሙሉአለም ገሌ( መተማ አስተዳደሪ የነበረ) ተሳታፊዎች ነበርን፡፡ ትገራይን በመወከል ደግሞ ኪሮስ ቢተው ዋነኛ ተሳታፊ ነበር፡፡
————-//////————-
በነዚህ የደንበር ውይይቶች ከባለስልጣናት በተጨማሪ፤ በሁለቱም ወገኖች በኩል አካባቢዎቹን ጠንቅቀው የሚያውቁ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌወችም አብረው ይሰሩ ነበር፡፡ ከነዚህ መካል ከአርማጭሆ( አብደራፊ) አቶ ጥጋቤ እንዲህነው፤አቶ መንግስቴ፣አባ አለሙ፤እንዲሁም ከከቋራ ወረዳ አባ መንቴ፤ከመተማ አቶ ዘጌ እሸቴና አባ አረጋዊ፤የተባሉ ሽማግሌዎች በአንድ ወቅት በማካለል ሂደቱ በነበሩ ውይይቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከሱዳን በኩል ደግሞ በተመሳሳይ የአገር ሽማግሌዎችና የከባቢው አስተዳደሮች( የዶካ ከባቢ አስተዳደዳሪ አቶ ጋሲ እና ሌሎች የጦር መኮንኖች)ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
———————/////————-
ደንበሩን የማካለል ሁኔታ በሂደት ታላቆቹ አመራሮች ከደንበር ኮሚቴነቱ ውይይት እየራቁ ጉዳዩ በዋነኛነት ለክልሉቹና ለከባቢው አመራሮቸ እየተተወ የሄደበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህም መሰረት፤በአማራ በኩል አቶ ደሴ አሰሜ፤ደሳለኝ አንዳርጌ፤ደመላሽ እና ታረቀኝ እማኙ የተባሉ የዞንና ወረዳ የመንግስት አመራሮች የተሳተፉባቸውንና ከቋራ እስከ አብደራፊ ያለውን ከባቢ ለመከለል የተካሄደውን እንቅስቃሴ ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ሽማግሌዎችን በማስተባበር የአገራችንነ ጥቅም ለማስጠበቅ ቡዙ እንደደከሙ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ከተካሄዱት ውይይቶች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ጓንግ መለስ በታሪክ የኢትዮጽያ እንደሆነ እና ከሱዳን የመጡትም የአር ሽማግሌዎች “ወላሂ አንዋሽም የዚህን ከባቢ መሬት ኢትዮጽያዊያን ያርሱት እንደነበር እናውቃለን”ብለው ሱዳኖች እራሳቸው በወቅቱ ምስክርነታቸውን እንደሰጡ በወቅቱ የነበሩ እማኞች አረጋግጠውልኛል ፡፡
———–//////——–
3. የውዝግቡ ጭብጥ ምንድን ነው?
እዚህ ላይ ያለው ጉዳይ ግልጽ መሆን አለበት፡፡እኛ ኢትዮጽያዊያን ከሱዳን ጋር በተላይም በአርማጭሆ ግንባር ያለው ወሰናችን ጓንግ ወንዝ ነው ብለን እናምናለን፤በሱዳኖች በኩል ደግሞ ጓንግ ወንዝን ተሸግረን ቦታ አለን ይላሉ፡፡ ለዚህ የሚያቀርቡት ማስረጃ ደግሞ ከላይ እንዳነሳሁት በቅኝ ግዛት ወቅት እንግሊዝ ያሰመረውን የጊዎን ላይን የሚባለውን ሃሳባዊ መሰመር ነው፡፡ ስለሆነም ክለላው በዚህ መርህ እንዲፈጸም ይፈልጉ ነበር፡፡ በኛ በኩል ደግሞ ይሄን እንደማንቀበል ሲነገራቸው በጉዳዩ ላይ ቡዙም እንዳልተጋፉ በወቅቱ በድርርሩ የነበሩ ሰዎች አጫውተውኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ በወቅቱ በሁለቱም መንግስታት የተደረሰው ስነምምነት ታሪክ በመቁጠር ሳይሆን በተጨባጭ አሁን መሬቱን ማን እየተጠቀመበት ነው በሚለው ጉዳዩ እንዲታይ ስምምነት ተይዞ ደንበሩን ለመወሰን ሙከራ ተደረገ፡፡ በኔ እምነት ይህ የተሻለው አማራጭ ነበር፡፡እሂን ውሳኔ መቀበላችንም የከፋ ጉዳት ያስከተለብን ጉዳይ አድርጌ አላየውም ፡፡
—————-////—————-
እዚህም ላይ አንድ እውነታ እናንሳ ፤ አገራችን የርስ በርስ ጦርነት በነበረችበት ወቅት የሱዳን አዋሳኝ የሆኑት የሰ/ጎንደር ወረዳዎችን ማለትም፡ ቋራ፤ መተማና ታች አርማጭሆ ወረዳዎችን የኢትዮጽያ መንግስት ለረዥም ጊዜ በተገቢው ያስተዳደራቸው የነበሩ ከባቢዎች አልነበሩም፡፡ጉልበት ያለው ሁሉ፤ኢህአፓ፤ኢዲዩ፤ህውሀትና ኢህዴን ከባቢዎቹን በመሸሸጊያነትና በትግል ሜዳነት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በሌሉ ጊዜም የየከባቢዎቹ ህዝብ ራሱን በራሱ ያስተዳደር ነበር፡፡ ከ1976 ዓ.ም በኃላ ህውሀትና ኢህዴን በአርማጭሆ ከባቢ እግር መትከል ጀመሩ፤ ይሁን እንጅ በወቅቱ ኢህዴንና ህውሀት ስለ አገር የደንበር ወሰን እንዲያስቡ የሚፈቅድላቸው ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታ ለሱዳኖች ጥሩ ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸው፡፡ መንግስት የማይቆጣጠረው ከባቢ ስለነበር የፈለጉትን ማድረግ ቻሉ፡፡ በ3ቱም ወረዳዎች ደንበር እየተሸገሩ ሰፋፊ እርሻዎችን መስርተው ለበርካታ አመታት የእርሻ ምርት ያለተቀናቃኝ አፈሱበት፡፡ በርግጥ መነሻቸው ከላይ የገለጽኩትን የጊየን መስመር ታሪክ እያነሱ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
—————//////—————-
4. መሬታችን ከሱዳን የማስመለስ ዘመቻ አጀማመር፤
ሱዳን በኢትዮጵያ ነበረውን ጠርስ በርስ ጦርነት እንደጥሩ አጋጣሚ ጠቅማ መሬታችን በመግፋት ስትጠቀምነበት ኖራለች፡፡ ከጊዜ በኃላ ሁኔታዎች መቀያየር ጀመሩ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ በአንጻራዊነት ሰላም የሰፈነባት፤ ከደረግ በተሻለ አንጻራዊ ሰላም ያገኘ ዳርደንበሯን ሙሉ በሙሉ የሚያውቅና የሚያስተዳድር መንግስት አግኝታለች፡፡ ቀደም ሲል መንግስት የማያውቃቸው ወይም በተገቢው የማይቆጣጠራቸው የነበሩት የቋራ፤ሽንፋ፤ መተማና አርማጭሆ በረሀዎች አሁን በመንግስት አይን ስር ገብተዋል፤ ማንም እንደፈለገ የሚፈኘጭባቸው ዘመን እያከተመ መጣ፡፡ በሂደትም ኢህአዴግና የየአካባቢው ህዝብ ሱዳኖች ያላግባብ ወሰን ዘለውና ተሸግረው መሬታችንን ይዘዋል ይውጡ የሚል አቋም ደረሱ፡፡ሱዳን አሁንም ጉዳዩን አጢና ከመሬታችን ከመውጣት ይልቅ ማንገራገር መረጠች፡፡ በመጨረሻም በ1988ዓ.ም ከከቋራ እስከ አብደራፊ በተዘረጋው ሰፊ ቦታ ላይ ከባድ የደንበር ጦርነት ተካሄደ(በርግጥ የዚህ ጦርነት እውነተኛ መነሻ ሌላ ፖለቲካዊ ሰበብም ነበረበት )፡፡ እኔም በወቅቱ የታች አርማጭሆ አስተዳደሪ ነበርኩና ነገሯን ጥሩ አድርጌ አውቃታለሁ፡፡
ከዚህ ከባድ ጦርነት በኃላ ሱዳን ተጠራርጎ ይዞት ከነበረው ግዛታችን ወጣ፡፡ የኛ ጦርና የከባቢው ህዝብም ለዘመናት ሱዳኖች ተቆጣጥረው ሲጠቀሙበት የነበረውን የራሳችንን መሬት በሙሉ ከጓንግ ወንዝ በመለስ እንደገና በጃችን አስገብተን መጠቀም ቻልን፡፡ በወቅቱ ካስመለስናቸው መሬቶች መካከል የተወሰኑትን ለመግለጽ ያክል( በአርማጭሆ ግንባር ብቻ)፤ አቡጢር እስከ ሱፍ ውኃ፤ገላሉባን፤ ኮረደም፤ኮርሁመር፤ ስናር ፤ደለሎ ወዘተ… ይጠቀሳሉ፡፡ በመተማና ቋራ ስለነበረው ሁኔታ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
————///////———
5. ፍቅር እንደገና ፤
ይሁን እንጅ አሁንም እንደገና ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ ከጊዜ በኃላ ደግሞ ሱዳንና ኢትዮጽያ መልካም ግንኙነት ፈጥረው ግንኑነታቸውን ማደስ ጀመሩ፤ አዲስ ፍቅር ውስጥም ወደቁ ፡፡ ይህ ሁኔታ የሱዳን ባለሀብቶች በጦርነት ለቀዋቸው የሄዱትን መሬቶች እንደገና እየተመለሱ ማረስ እንዲጀምሩ በር ከፈተላቸው፡፡ ይህ ድርጊት በስፋት የታየው ድሮ የአርማጭሆ ወረዳ ይዞታ በነበረውና በኃላ በ1987 ዓ.ም ወደ መተማ ወረዳ ወደ ተከለለው ደለሎ በተባለው ሰፊ ለም የእርሻ ከባቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ደለሎ በታሪክ የታች አርማጭሆ ወረዳ አካል የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ አርማጭሆ በጣም ስለሰፋብን ለመተማ ወረዳ ቆርጠን ከሰጠናቸው 2 ሰፋፊ በረሀማ ቀበሌዎች መካከል አዋሳ በተሰኘው ቀበሌ ስር የሚገኝ ሰፊና ለም መሬት ነው፡፡ አዋሳ የተሰኘው ቀበሌ ያለ ማጋነን አንድ ትልቅ ወረዳ የሚያክል የቦታ ስፋት ያለው በረሀማ ቀበሌ ነው፤ ሌላው ወደ መተማ የሸኘው ቀበሌደግሞ አቸራ ይባላል ፡፡
————-///////———
ይህ አዲስ መልካም ግንኙነት እንደተጀመረ ፤ ደለሎ ላይ ከማል የተባለ ሱዳናዊ ባለሀብትነና ሌሎች 5 የሚሆኑ ባለሀብቶች የደለሎን መሬት እንደገና ወረው ማረስ ጀመሩ፡፡ በወቅቱም በሁኔታው የክልሉ መንግስትና የከባቢው አስተዳደር በመቆጣታቸው በሁለቱ መንግስታት መካከል በተደረገ ውይይት መሰረት የሱዳን ባለሀብቶች የዘሩትን ሰብል ሰብስበው ከባቢውን እንዲለቁ፤ ለሰሩት ስህተትም ከሚገኘው የሰሊጥ ምርት 25%፤ ከማሽላ ደግሞ 35% ለኢትዮጽያ መንግስት እንዲያስገቡ ተወስኖ መጨረሻም ተግባራዊ ተደረገ፡፡ ይህ በወቅቱ በቅጣት መልኩ ከሱዳኖች የተሰበሰበው ሰብል ገቢ የተደረገው በወቅቱ አንባሰል ለተባለ የብአዴን የንግድ ድርጀጅት ነው፡፡ የሱዳን ባለሀብቶችም ቀሪውን ሰብላቸውን ሰብስበው ከባቢውን ለቀው በሰላም ደንበራችንን ለቀው እንዲሻገሩ ተደረገ ፡፡
————–/////////———–
6. ተስፋን ጭሮ የነበረው የዘለቀ እርሻ ልማት ነገር
እነዚህ የሱዳን ባለሀብቶች ደለሎን ለቀው እንዲወጡ ከተደገረ በኃላ፤ ዘለቀ የእርሻ ልማት የተባለ የብአዴን የልማት ድርጅት ሱዳኖች የለቀቁትን ሰፊ የደለሎ መሬት ተረክቦ በ1987 ዓ.ም ወደ ከባቢው እንዲገባና ስራ እንዲጀምር ተደረገ፡፡ በዚህም ዘለቀ እርሻልማት ይሄን አካባቢ ከ1987-1994 በይዞታው ስር አድርጎ በኢንበስትመንት እየተጠቀመበት ቆየ፡፡ በዚህ ወቅት ሁኔታውን ያውቁ የነበሩ የከባቢው አመራሮች በጣም ተደስተው ነበር፡፡ እነዚህን አመራሮች ደስታ የፈጠረባቸው ጉዳይም ያንን ሰፊ ከባቢ ዘለቀ እርሻልማት መያዙ የሱዳኞችን የይገባኛል ጥያቄ የሚያረግብ መሆኑ አንዱ ምክንያት ሲሆን፤ሌለው ደግሞ ከጎንደር ተቆርሶ ወደ ትግራይ በተከለለው የሁመራ ከባቢ በህውሀት የተቋቋመውን የሂዎት እርሻ መካናይዜሽን እያዩ፤የከባቢው አመራሮች በቅናት እርር ድብን ይሉ ስለነበር፣ የዘለቀ እርሻ ልማት መቋቋም ይህንን ብስጭታቸውን የሚቀንስላቸው መስሎ ስለተሰማቸው በወቅቱ ትልቅ ደስታ ተሰምቷቸው እንደነበር ዛሬም ይናገራሉ፤ ከነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ እኔው ነኝ፡፡
————–////—————
7. የሱዳን ዜጎች በመንግስታቸው ላይ ማሳደር የጀመሩት ጫና መበራከትና የደለሎ ጉዳይ፤

ይሁን እንጅ ጊዜ ጊዜን እየወለደ ሲሄድ ሌላ ፈተና ተከሰተ፡፡ ከችግር ወጥቶ መለስተኛ መግባበት ማሳየት ጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት ግንኙነት፣ ወደ አዲስ የተጠናከር ፍቅር እያደገ መጣ ፡፡ ይህን መልካም ግንኙነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሱዳን ባለሀብቶች የተነጠቁትን መሬት እንደገና ለማስመለስ በመንግስታቸው ላይ ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ልክ የኛ አገር ህዝብ ኢህአዴግን መሬታችንን ለሱዳን ሰጠ እየተባለ እንደሚወቀስው ሁሉ፤ በሱዳን በኩልም በመንግስቱ ከዜጎች በተለይም ከባለሀብቱ፤ ከህዝቡ፤ ከጦሩ የሚሰነዘርበትን ጫና ከባድ ነበር፡፡ ስለሆነም ይህን ጫና ለማቅለል በሱዳን መንግስት በኩል ቀደም ሲል በሱዳናዊያን ሲለሙ ከነበሩት መሬቶች መካከል በሂደት ወደ ኢትዮጽያ የተመለሱ የኢትዮጵያ መሬቶች/ይዞታወች አንዳንዶቹን እንዲመለሱለት ተከታታይ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ማድረግ ጀመረ፡፡በዚህ በኩል በደለሎ ከባቢ የነበረው የሱዳን ፍላጎትና ግፊት በጣም ጠንካራ ነበር፡፡
የኢትዮጽያ መንግስትም ከሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ይፈልግ ስለነበርና ( በተለይም ሱዳን ለኢትዮጽያ ተቃዋሚዎች መሸሸጊያ እንዳትሆን ይፈለግ ስለነበር) ቀስ በቀስ የሱዳኞችን ጥያቄ በመጠኑም ቢሆን ማስተናገድ ጀመረ፡፡ በዚህም መሰረት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ለማሻሻል በሚል ተከታታይና ቋሚ ውይይቶች እንዲካሄዱ ተደረገ፡፡ በተለይም በደንበሮች ከባቢ የሚገኙ አመራሮች ግንነኙነቱን ለማሻሻል ታስቦ ተቀራርቦ የመስራት ባህሉን በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል እንዲሰሩ መመሪያ ወርዶላቸው ተገበሩት፡፡ ይህ ሁኔታ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሰምቻለሁ፡፡
——–////////———
ላይ ላዩን ላየው ሰው ከሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ታስቦ በመንግስታችን የተወሰዱት ስራዎች በወሳኝነት ጥሩ ናቸው ብሎ ያስብ ይሆናል፡፡ እውነት ነው እስከማውቀው ድረስ በሁለቱ መንግስታት ግንኙነት ጥሩና ኢትዮጵያን የጠቀሙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንዳሉ መመስከር እችላለሁ፡፡ ሁኖም በዚህ በኩልም የተፈጸመው ስህተትም እናዳለ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ስህተትም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለማሻሻል ተብሎ በተደረገ ድርድር በመተማ አካባቢ ያላግባብና ህጋዊ አሰራርን ባልተከተለ መንገድ በባለስልጣናት ቁም ፍርድ ብቻ ወደ ሱዳን ተቆርጦ የተሰጠ መሬት ስለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ነታወቅ አለበት፤ተዳፍኖ መቅረት ለበትም፡፡
————////////————–
8. ባልበላው ጭሬ እደፋው፡

ነገሩ እንዲህ ነው፤ ከላይ እንዳነሳሁት ዘለቀ እርሻ ልማት ከ7 አመት በላይ ሲያለማው የቆየው መሬት ቀደም ሲል በሱዳኖች እጅ ገብቶ የነበረና በአንድ ወቅት በጦርነት አስመልሰነው በጃችን ገብቶ የነበረ መሬት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ዘለቀ እርሻ ልማት ባልተጠበቀ ሁኔታ ከ7 አመት በላይ ሲጠቀምበት የቆውን ሰፊና ለም መሬት በ1994 ለቆ እንዲወጣ በብአዴን ታዘዘ፤ ድርጅቱም ስራውን አቋርጦና ከባቢውን ለቆ ወጣ፡፡ ዘለቀ እርሻ ልማት ደለሎን ለቆ እንደወጣ ቡዙም ሳይቆ ይህ ሰፊና ለም መሬት እንደገና ተመልሶ ለሱዳኖች ተሰጠ፡፡ ይህ መሬት ለሱዳኖች እንዲሰጥ ቦታው ድረስ ተገኝቶ ትእዛዝ የሰጠው አቶ አባይ ጸሀየ ነው፡፡ ከአባይ ፀሀየ ጋር ደግሞ በወቅተ አንድ የክልልና አንድ የዞን የብአዴን አመራሮች አብረው እንደነበሩና የውሳኔው አካልም እንደነበሩ ማወቅ ተችሏል፡፡
———————//////————-
በወቅቱ ድርጊቱ ሲፈጸም ከቦታው አብሮ የነበረው ሰው እንዳረጋገጠልኝ፤ አባይና እነዚህ ሁለቱ የብአዴን ጉዶች መሬቱን ለሱዳን ያስረከቡት በቀጥታ ከሱዳን ገዳሪፍ ተነስተው በሄሊኮፕተር ደለሎ ድረስ በመሄድ ነው፡፡ ልብ በሉ ይህ መሬት ለሱዳን ተላልፎ የተሰጠው ከሱዳን የሚመጣ የጸጥታ ስጋትን ለማስቀረት እንጅ መሬቱን የኢትዮጽያ አድርጎ ለማስቀጠል የሚያስችል ሁኔታ ያልነበረ ሁኖ አልነበረም፡፡ ይህ ጉዳይ ” ባልበላው ጭሬ እደፋው” የሚለውን አባባል እንድናስተውስ ያደርገናል፡፡ ባለፈው አርቲክሌ እንደነገርኳችሁ፤ የሕውሀት አመራሮች ቀደም ሲል ይህን ከባቢ ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ሳይሳካላቸው ስለቀረ፣ወይም በተለያየ መልኩ ሞክረውት ያልተሳካላቸውን ግዛታቸውን እስከ መተማ ከባቢ የማስፋቱ እቅድ እንደማይሳካ እየተገነዘቡ ሲመጡ፤ያንን ከባቢ ለሱዳን በመሰጠት የሱዳንን ወዳጅነት አጠናክሮ መቀጠሉ የተሸለ ሁኖ እንዳገኑትና እንደወሰኑ ማየት ያስፈልጋል፡፡
በርግጥ ይህ የመረጃ ምንጨ እንዳረጋገጠልኝ ይህ መሬት ለሱዳኖች ተሰጥቶ የነበረው ለጊዜው ነበር፤ በሂደት ግን በጊዚያዊነት የተሠጠው መሬት በዛው ለምዶ ቀረ፡፡ በወቅቱ ይህንነ ድርጊት ለመቃወም የሞከሩትን የወረዳ አማራች አባይ ጸሀየ ለብቻ ሳብ አድርጎ እንዲህ አላቸው ” ስሙ ምን ያጩካችሃል፤ ይህ ከባቢ እኮ እንኳን ከሱዳን ጋር፤ ከትግራይ ጋርም ገና ውዝግቡ ያለየለት ከባቢ ነው፤ አርፋችሁ ቁጭበሉ” ፡፡ ይህን አባይ ጸሀየ ማስጠንቀቂያ ተቀብላ አርፋ ቁጭ ያላለ፤ች አመራር፤ነገር ተፈልጎላት 8 አይነት ክስ ተዘጋጅቶላት፤የ7 አመት እስራቷን ጠጥጣ ወጣች እላችኃለሁ፡፡
—————////////——
9. በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት፤
እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ይሄውም ይህ ውዝግብ ሲነሳ መሬቱ በትግራይ ከባቢ ቢሆን ኖሮ ህውሀት እንዲህ በቀላሉ መሬቱን ለሱዳኖች አሳልፎ ይሰጥ ይሆን ?፡፡ሁላችንም እንደምናምነው ይህ ጉዳይ የማይታሰብ ነው፡፡አይደለም ውዝግብ ስለተነሳ ብቻ በአለም አቀፍ ፍ/ቤት ውሳኔ ያረፈበትን የባድመ መሬት እንኳን ህውሀት ለኤርትራ አላስረክብም በማለቱ እሄው ከ16 አመት በላይ ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡ እንኳን የራስን መሬት የሌሎችን መሬት እንኳን ለመመለስ ወይም መሬትን ቆርሶ መስጠት እንዲህ ያስጨንቃል፡፡ ታድያ ህውሀቶች የባድመን መሬት በህጋዊ መንገድ ላስፈረደችው ኤርትራ ለማስረከብ የቸገራቸውን ያህል የአማራን መሬት ለሱዳኖች ተቆርሶ እንዲሰጥ እንዴት አልጨነቃቸውም? በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት የሚባለው አባባል እሄ ነው፡፡
————////////———–
10. እኛው ነን፤
ለነገሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በሕውሀት ብቻ መፍረድም ከባድ ነው፡፡ አማራ ሳይሆኑ በአማራ ወንበር ላይ የተፈናጠጡት ሁለቱ የብአዴን አመራሮች ከአባይ ፀሄ ጋር ሁነው እኮ አብረው ደለሎን ሰጥተውብናል ፡፡ አንድ ነገር ግን ልብ በሉ፤ከአባይ ጋር ደለሎ ድረስ አብረው ተጉዘው ያስረከቡት አመራሮች እነማን እንደሆኑ በወቅቱ አብሮ የተሳተፈው ሰው ልቡ ሲሞላ እስኪነግረን እንጠብቃለን፤ አሁን ጊዜው ስለደረሰ ሰውየው የሚደፍር ይመስለኛል፡፡ በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ሁኑ፤ ይሄውም አሁን በስራ ላይ ያለው የክልሉ የብአዴን አመራር በዚህ ጉዳይ 100% የለበትም፡፡
አንድ የቸገረ ነገር ግን አለ፡፡ ይሄውም የብአዴን ከፍተኛ አመራር ባልደገፈው ውሳኔ እነዚያ ሁለት የብአዴን አመራሮች ከአባይ ፀሀየ ጋር ሁነው የጎንደርን መሬት ባልተወለደ አንጀታቸው እንዲያ ዘንጥለው ለሱዳን የመስጠት አቅም ሊኖራቸው ይችላል? ይህ በሂደት ሊጣራ ይገባዋል፤ እኔ ግን አይመስለኝም፤ ለጊዜው ግን መረጃ የለኝም፡፡
————–//////——–
11. ዘለቀ እርሻ ልማት ደለሎን ምን ለቆ ወጣ?
ዘለቀ እርሻ ልማት ድርጅት ስራውን አቁሞ እንዲወጣ ሲወሰን፣ ዘለቀ ለምን ስራውን አቆመ ሲባል ይሰጥ የነበረው ምላሽ ውጤታማ ባለመሆኑ ነው የሚል ነበር፡፡እና መፍትሄው ዘለቀን ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል ነው ወይስ ዘለቀን መሬቱን ቀምቶ ለሱዳን መስጠት? ያም ሆነ ይህ የዘለቀ እርሻ ልማት ማቋረጥ በወቅቱ ደስ ብሏቸው ለነበሩ የብአዴን አባለት፣ አስከፍቷቸው አልፏል፡፡ ቡዙዎቹ ዛሬም ድረስ ጉዳዩ ሆን ተብሎ እንደተሰራ ያምናሉ ፡፡ ነገሩም ግልጽ ነው በአንድ በኩል ዘለቀ እርሻ ልማት የህውሀቱን እርሻ መካናይዜሽን (ሂዎት እርሻ ) እንዳይቀናቀን ታስቦ የተፈጸመ ድርጊት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ደለሎን ለሱዳን በመስጠት ከሱዳን የሚነሳን ጸረ-መንግስት እንቅስቃሴ ለመግታት ይጠቅማል ከሚል ስሌት የተሰራ ስራ ነው፡፡ በዚህ በኩል ዝርዝር መረጃ የሚፈልግ ሰው በቅርቡ ወደ አማሪካ ከተሰደደው በሪሁን ጥሩ መረጃ ማግኘት ይችላል፡፡ በሪሁን ጥሩ ዘለቀ እርሻ ልማት ሲፈርስ የእርሻ ልማቱ ስራ አስኪያጅ የነበረ ሰው ነው፡፡
—————//////———–
12. ማጠቃለያ-
በዚህ ጉዳይ በቀጣይ በቋራ እና በቀሪዎቹ ወሰን ከባቢዎች ስለነበረው ሁኔታ በዝርዝር ይዠ ለመመለስ እሞክራሉ፡፡ እስከዚያው ግን ነገሩ እንደባድመ እንዳይሆን ከወዲሁ ህዝባችን ግልጽ መረጃ እንዲሰጠው መንግስትን መጠየቅ አለበት፡፡ መንግስታችን የተስማመው ነገር ካለ ይፋ ያድርግ፤ባልተስማማው ነገር ከሆነ ሱዳኖች እየወረሩን ያሉት ለርስታችን ስንል እንዋደቅ፡፡ ነገር ግን መንግስት ህዝቡን ፈርቶ ነገር በመደቁቅ፤ህዝባችን ባላወቀው ነገር በጦርነት እንዲማገድ ከተደረገ ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት፡፡ ከባድመ ልንማር ይገባል፡፡ ህውሀት ባድመ የኤርትራ መሆኗን ሆዱ እያወቀ፤የኢትዮጵያን ወጣቶች አስጨረሰ፤ ዛሬ ደግሞ ባድመን ተረከቡን እያልን ነው፡፡ ስለዚህ አሁን በሱዳን ከባቢ ያለው ነገርም ዳግማዊ ባድመ እንዳይሆን ብአዴንና የፌደራሉ መንግስት፤ የተለየ ነገር ካለ ግልጽ መረጃ ለህዝቡ መስጠት አለባቸው፡፡ የመንግስትን ውሳኔ የማያከብር ህዝብ አይኖርም፤የኤርትራንና አሰብን ጉዳይ እንኳን ተላምደነው አድረናል፡፡

ያም ሆነ ይህ የዚህ ደንበር ነገር ከሌሎች ጋር መነካካቱ አይቀሬ ነው

Filed in: Amharic