>

"ምስጋና ከሚቀበል ሰው ይልቅ ምስጋና የሚሰጥ ታላቅ ነው!!!" (ዶክተር አብይ አህመድ)

“ምስጋና ከሚቀበል ሰው ይልቅ ምስጋና የሚሰጥ ታላቅ ነው!!!”
ዶክተር አብይ አህመድ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ላለው ድጋፍ የምስጋና መልእክት አስተላልፈዋል።
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች ሆይ
ምስጋና ከሚቀበል ሰው ይልቅ ምስጋና የሚሰጥ ታላቅ ነው፡፡ ያለ ጥርጥር ይህንን እንረዳለን፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ጭላንጭል፤ አሁን የሀገራችን ህዝብ እየሰጠን ካለው ወሰን አልባ ድጋፍ እና ፍቅር ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ ብንገነዘብም መንግስት ይሄንን ድጋፍ ፣ ፍቅር ፣ ክብር እና አለኝታነት ለተሰሩ ስራዎች እንደተሰጠ ምስጋና ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እንሰራቸው ዘንድ ለሚገቡን በርካታ ስራዎች ተግባራዊነት የተላለፈ የአደራ መልእክት እንዲሁም የአጋርነት ማሳያ አድርጎ በመቁጠር ከምን ጊዜውም በላይ በፍጹም ቁርጠኝነት እና ትጋት ለማገልገል በጽናት ይሰራል፡፡
እስካሁን የታየው የለውጥ ወጋገንም ሆነ ወደፊት የምናስመዘግበው ድርብ- ድርብርብ አንፀባራቂ ድል ባለቤት ህዝብ እና ህዝብ ብቻ ነው፡፡ አሁን ከጀመርነው የፍቅር ፣ የይቅርታ፣የመደመር፣ የአንድነት እና እንደ ሀገር የመለወጥ ጉዞ ሊያናቅፈን የሚችል መሠናክል – ሊያናጥበን የሚችል ስጋትአይኖርም በሚል መንፈስ ተነስተን በጽናት እየተደመርን የምንገኘውም ህዝብ ታግሎ ያላሸነፈበት ምንም የትግል አውድ የፍልሚያ ግንባር እንደሌለ እና እንደማይኖርም ጭምር በውል ስለምንገነዘብ ነው፡፡
ከምስራቅ እስከ ምእራብ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያላችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከሰራነው ስራ እጅግ ለሚልቀው እና ትርጉም- አንድምታውም ፍጹም ለሚረቀው ወሰን አልባ ድጋፋችሁ እና ፍቅራችሁ በያላችሁበት ሆናችሁ እነሆ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡ የቸራችሁን ምስጋና የኛ ብቻ ሳይሆን የናንተም ድምር ውጤት ነውና እናንተ አመስጋኞቹ ዋናዎቹ ተመስጋኞች መሆናችሁን ለአፍታም ቢሆን አንዘነጋም፤መዘንጋትም አይቻለንም፡፡ እናም ተመስጋኞቹ አመስጋኞች የለገሳችሁንን አብሮነት በፍቅር – አደራ ያላችሁንን የነገ ትግል በክብር ተቀብለን ታላቂቱን ሀገር ወደ ቀድሞ እና ከዚያም ወደላቀ ታላቅነት ከፍታዋ ለመመለስ ቃል ስንገባላችሁ በታላቅ አክብሮት እና በፍጹም የእንሻገራለን ቁርጥ ስሜት ነው፡፡
ውዶቹ የጉራጌ ምድር ፈርጦች – የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ጌጦች – ዘርማዎች፤ ቃላችንን ሰምታችሁ እና ለሰላማችን ዘብ ለመቆም ከኛ ውጪ ማንም ስላለመኖሩ በውይይት የደረስንበትን ድምዳሜ በመቀበል በይቅርታ ቀስተደመና ደምቃችሁ የጸብን ደመና ስለገፈፋችሁ የአክብሮት ምስጋናዬ ካላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡ በሰራችሁት አኩሪ ገድል እኔም ሆንኩ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በእናንተ እንደኮራን የምገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ ነው፡፡ በዚህ ፍጹም የመደመር ተግባራችሁም በገጠር ከተማችሁ- በሰፈር ቀኤያችሁ ሁሉ ሰላም እና ፍቅርን ያለመናወጥ እንደምትተክሉ ፊታችሁንም ወደሃገር ግንባታና ልማት በማዞር ተጨባጭ ውጤት እንደምታመጡ እምነቴ የጸና ነው፤ ላደረጋችሁት ኢትዮጵያዊ የይቅርታ፣ የፍቅር እና የሰላም ተምሳሌታዊ ተግባርም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
የደቡብ ክልል የሀገራችን የሕብረብሄራዊነት – ማሳያ አንድ ሰበዝ የደግነት እና የፍቅር ምሳሌ የሆናችሁት ሲዳማዎች በቱባ ባህላዊ መገለጫዎቻችሁ ውስጥ ጉዳዬ ተብሎ በማይፃፍ ጥቃቅን ምክንያቶች መነሻነት በአካባቢያችሁ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት እና ሁከት አስወግዳችሁ እንደ አኩሪ ባህላችሁ እና እሴታችሁ መክራችሁ እና ዘክራችሁ ጥላቻን ድል ስለነሳችሁ ያለኝን አክብሮት እና አድናቆት ስገልጽላችሁ በቀጣይም ይሄንኑ አጽንታችሁ በመያዝ እንደምትጓዙ በጽኑ በማመንም ጭምር ነው፡፡ ዛሬ ላይ ከአካባቢያችሁ ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ የወላይታ ወንድም- እህቶቻችሁን፤ ወላጅ ልጆቻችሁን እንደገና ወደነበሩበት ለመመለስ ቤት በመስራት ላይ እንደሆናችሁ መረዳት የርምጃችሁን ቁርጠኝነት አመላካች ነው፡፡ አውቃለሁ፡፡ ይህ የተቀደሰ መልካም ተግባራችሁ በልጅ ልጆቻችሁ ውስጥ ይተከል እና አብዝቶም ይበቅል ዘንድ ስለሚገባው እና በዘመናት መካከልም በናንተ ምድር ለነገሰው ፍቅር ይበልጥ ጥንካሬ፣ ውበት እና ድምቀት እንደሚደርብለት እምነቴ የጸና ነው፡፡ ለወላይታ ወገኖቻችሁ መልሳችሁ የምትገነቡላቸው ቤት ሀገራችሁን በፍቅር የመገንባት ተምሳሌታዊ ውክልና አለውና በዚህ የኢትዮጵያዊነት ቅን ተግባራችሁ ወገኖቻችሁ ሁሉ እንደሚደሰቱ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሲዳማዎች እና የሲዳማዎችን በጎ ተግባር በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የደገፋችሁ ወገኖቼ በሙሉ ልባዊ ምስጋናዬ እና አድናቆቴ ከተለየ አክብሮት እና ፍቅር ጋር በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ እያልኩ በቀሪው ጊዜ ፊታችሁንም ወደሃገር ግንባታና ልማት በማዞር ተጨባጭ ውጤት እንደምታመጡ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
በሀገራችን ከተሞች እና በአካባቢያችሁ አደባባዮች ወጥታችሁ ከሚገባን በላይ ያከበራችሁን፣ የደገፋችሁን እና በቀጣይ ጉዟችንም የአብሮነታችሁን ማረጋገጫ ኪዳን የሰጣችሁን የሀገራችን ህዝቦች ለክብር ምስጋናችሁ የሚመጥን ምንም ስጦታ ባይኖርም ልባዊ ምስጋናችን ግን በፍቅር ይድረሳችሁ፡፡ ምስጋና ድጋፋችሁ የቀጣይ ትግላችን ሀይል ነውና ያስታጠቃችሁንን የመደመር እና የፍቅር ትጥቅ ታጥቀን ለዚህች ታላቅ ሀገር እድገት እና ብልጽግና አበክረን ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ዝግጁ መሆናችንን ስገልጽላችሁ በፍጹም ክብር ነው፡፡
በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኛችሁ የአዲስ አበባ እና የሌሎች አካባቢም ህዝቦች፤ በያላችሁበት ሆናችሁ በሀሳብ፣ በጸሎት እና በመደመር ከጎናችን የሆናችሁ ወገኖች፤ በተለይም በወቅቱ በተፈጠረው የእኩያን ድርጊት የተጎዳችሁ እና በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የአካል እና የስነልቦና ስብራት የደረሰባችሁ ወገኖች እናንተ በዚህች ሀገር የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ የራሳችሁን ግሩም ጡብ ያኖራችሁ ጀግኖች ናችሁና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሀገራዊ አንድነታችን እና ለለውጥ ግስጋሴያችን ድጋፍ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን የጥረት ልፋታችንም አካል ለመሆን ስትሉ ህይወታችሁን ያጣችሁ ወገኖቻችን እናንተ ለኛ የምንጊዜም ጀግኖቻችን ናችሁ፡፡ የናፈቃችኋትን እና እውን እንድትሆንም የተጋችሁላትን ሀገር በአንድነት በመገንባት አልፋችሁም እንኳን ህያው እንድትሆኑ አበክረን በመስራት በህልፈታችሁ ላይ ያበበች ሀገር እውን በማድረግ የምናረጋግጥ ቢሆንም ክብር እና ምስጋናችን በአጸደ ነፍስ እንዲደርሳችሁ በማሰብ እናመሰግናለን ስል ግን በተለየ የሠማዕት ክብር እና ፍቅር ነው፡፡
መላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉ ስላደረጋችሁልን እና ወደፊትም ስለምታደርጉልን ድጋፍ፣ ፍቅር እና አብሮነት ከልብ እናመሰግናለን፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
አመሰግናለሁ!
Filed in: Amharic