>
5:13 pm - Thursday April 20, 2372

ያቺ መዝገብ - ከአብይ ጠረጴዛ…! (ደረጄ ደስታ) 

ያቺ መዝገብ – ከአብይ ጠረጴዛ…!
ደረጄ ደስታ 
ሰልፍ ያልወጣች ይቺ መዝገብ የራሷን ጊዜ ጠብቃ ትወጣለች። ካሁኑ ሰልፍ በኋላ ወደዚህች መዝገብ እምናቀና ይመስለኛል። መፈክራችንም “መዝገቢቷን የደፈረ ጀግና!” እሚል ይሆናል። አልገለጥ አለችኮ!
አሁንማ አስር ዓመት ሊሞላው ነው። ኦክቶበር 17 2008 (ጥቅምት 7/2001) በአቶ መለስ ጊዜ ተጀምሮ በአቶ ኃ/ማ ጊዜ ቀጥሎ የነበረው የባለሥልጣናት ሀብትና ንብረት ምዝገባ ይፋ የመለቀቁ ነገር ዝም እንደተባለ ነው። ምዝገባውና መዝገቡ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚገኙ ተሿሚዎችን፣ ሚኒስትሮችንና ግለሰቦችን በሙሉ የሚመለከት ነበር።
የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ መለስ በፓርላማ ላይ ካወጁበት ጊዜ አንስቶ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት (2003-2004) የመንግሥት ተሿሚዎችን፣ የተመራጮችና  የሚመለከታቸውን ሠራተኞች ሀብትና ንብረት መዝግቦ መያዙንና ሪፖርቱንም አሳውቋል። መንግሥትም “የመጀመሪያው ዙር” ብሎ የጠራው መዝገቡን በጥቂት ወራት ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በወቅቱ አስታውቋል። ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ለመንግሥት ከሰጠ ካስረከበ በኋላ ምናልባትም ሁለተኛውን ዙር ምዝገባም እንዳደረገም እንገምታለን። ምክንያቱም ተከታትሎ መመዝገቡ ለጸረ ሙስና ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠው ሥራ ነው።
ይሁን እንጂ አቶ መለስን የተኩትና ይፋ ያደርጉታል ያልናቸው አቶ ኃይለማርያም ይፋ ሳያደርጉት አልፈው አሁን ዶ/ር አብይ አህመድ ደግሞ ተተክተዋል። በኢህአዴግ ግምገማዎች በተለይም በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ “አንተ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር አለህ፣ የለም ውሸት ነው እኔ ያለኝ ይቺን ታህል ሚሊዮን ብር ብቻ ናት” እየተባባሉ ባለሥልጣናት ሂሳቸውን እስከገንዘባቸው ሲወጡ መወራቱንም ሰምተናል። ልናጣራው ግን አልተቻለንም። የተመዘገበውን መዝገብ እንድናይ ተፈቅዶልን ማጣራት ያልቻልን፣ አሉባልታውን ምን እንደርገዋለን? ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የተሰጠው ይህ ሪፖርት (መዝገብ) ግን ለህዝብ እንዳይቀርብ ምን ይሆን ያገደው? ብዛቱ አስደንግጦን እንዳንወድቅ ይሆን ወይስ ሰዎቹ ቤሳ ቤስቲን የሌላቸው ምስኪኖች ሆነው አፍረን እንዳንሸማቀቅ? ወይስ ጊዜው የእርቅና የይቅርታ ስለሆነ እሱን መዝገብ መገላለጥ አያስፈልግም?
ለነገሩ ስለሌብነት ተማሮ የነገረን መንግሥት ነው። ሌቦችንም ለፍርድ ስለማቅረብ ያሳወቀን እሱ ነው። ኮሚሽን አቋቁሞ ሥራዬ ብሎ አጣርቶ ብቻ ሳይሆን በየግምገማው ሂስና ገንዘብ እያወራረደ በተሐድሶ አሸብርቆ ደምቆ እሚወጣው እሱ ነው። አሁን አሁን ደግሞ ይሁን ግድ የለም – ያለው ከነገንዘቡ – የሌለው ከነማህተቡ “ተደምሬያለሁ” በሚባባልበት ዘመን እሚያውኩን፣ “እነዚያው ሌቦች ናቸው” ሲባል ግራ ይገባል። እንዲያውም አንዳንዶቹ፣ ህዝባችን አሳልፎ አይሰጠንም ብለው በተለይ ከመቀሌው የመሸጉት፣ ለውጡን ለመቀልበስ እንደራጃለን እያሉ ነው መባሉንም እየሰማን ነው። ታዲያ እኛ ለፍርድ እነሱ ለእርድ እየተመኙን እንዴት ይሆናል? መቸም ጠቅላይ ሚኒስትራችን፣ እንኳን መዝገቢቷ ከጠረጴዛቸው ተቀምጣ ማን ምን እንደዘረፈ፣ በቃላቸው እሚያዉቁ ይመስለናል። እንኳን ያገሩን ውስጥ እያንዳንዷ ባለሥልጣን በውጭ አገር ባንኮች ሳይቀር ያስቀመጥችውን ገንዘብ እናውቃለን እያሉ ሲያወሩ ሰምቻለሁ እሚል ተንታኝም እያደመጥን ነው። የኤፍ.ቢ.አይ ሰዎችም ሌላ ሌላ ቦታ ተመልከቱ ሲሏቸው ገንዘብ ገንዘቢቷን መከተል እንደሚወዱ እናውቃለን። ይህ ማለት ደግሞ አብይም ያውቃሉ ማለት ነው።  ድሮስ አለነገር መች አስፈራርተው ነዷቸው – ወይ አንቺ መዝገብ- ቀን ይውጣልሽ!
Filed in: Amharic