>

ባንዲራው!!! (አፈንዲ ሙተኪ)

ባንዲራው!!!
አፈንዲ ሙተኪ
“ይህንን ባንዲራ የምጠላው የአጼዎቹ ስርዓት መለያ ስለሆነ ነው” የሚል አስተያየት የሚያቀርቡ ወንድሞች ተከስተዋል።
አሁን ገባኝ! ለዚህ ነበር በልሙጡ ባንዲራ ላይ ክርክር የተከፈተው? አጀንዳው ይህ ከሆነ መልሱ ቀላል ነው።
 የአጼዎቹ ባንዲራ ይህ አይደለም። የአጼዎቹ ባንዲራ ከመሃሉ ባለ ዘውድ አንበሳ ነበረው። አንበሳውን አንስቶ ባንዲራውን ወደ መሠረታዊ ቀለሞች የለወጠው የደርግ መንግስት ነው። ይህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖትና ብሄረሰብ ሳይለዩ የደገፉለት እርምጃ ነው።
በነገራችን ላይ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ስር ነቀል ለውጥ ያደረገው መንግስት “ደርግ” ነው። ከሚጠቀሱለት ዋነኛ ተግባራት መካከል
# ንጉሣዊውን ስርዓት ማስቀረቱ
# የመሬት አዋጅ ማወጁ
# ሁሉም ብሄረሰቦችና የሃይማኖት ቡድኖች እኩል እንደሆኑ መታወጁ (በትምህርት፣ በፍርድ፣ በስራ ቅጥርና በማህበራዊ አገልግሎቶች ብሄረሰብና ሃይማኖት እንደ መመዘኛ ሆኖ መቅረቡን ማስቀረቱ)
# የሃይማኖትና የመንግስት መለያየት (የእስልምና ሃይማኖትን በተመለከተ የተካሄዱ ስር ነቀል ለውጦችን ጨምሮ)
# የብሄረሰቦችና የአካባቢዎችን መጠሪያ ስሞች በተመለከተ ማስተካከያዎች መካሄዳቸው (ለምሳሌ በሃይለ ስላሴ ዘመን የተለመዱት “ገሙጎፋ”፣ “አሩሲ”፣ “ለቀምት” የመሳሰሉ ስሞች በትክክለኛ ስማቸው ጋሞጎፋ፣ አርሲ፣ ነቀምቴ ተብለው የተስተካከሉት በደርግ ዘመን ነው። “አዳል”፣ “ደራሼ”፣ “ወላሞ”፣ “ጃንጀሮ” የመሳሰሉ የብሄረሰብ መጠሪያዎችም “አፋር”፣ “ጌድኦ”፣ “ወላይታ”፣ “የም” ተብለው የተስተካከሉት በደርግ መንግስት ነው)።
# “ባለ ዘውዱ አንበሳ የገዥውን ስርዓት እንጂ ህዝቡን አይወክልም” በማለት አንበሳውን ከባንዲራው ላይ ያነሳው ደርግ ነው።
# ከአማርኛ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎችም የሬድዮ ስርጭት መጀመሩ ( በኃይለሥላሴ መንግስት መጨረሻ ገደማ ከሀረር ሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፍ የኦሮምኛና የሶማሊኛ ስርጭት ተጀምሮ ነበር። ነገር ግን ስርጭቱ ከሶማሊያ የሚተላለፈውን ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ የተከፈተ በመሆኑ ዋናው ታርጌቱ ከአዋሽ በታች ያለው ህዝብ ነበር። ደርግ ግን ከዋናው የኢትዮጵያ ድምጽ ብሄራዊ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ድምፅ ዓለም አቀፍ አገልግሎት እና ከአስመራው ሬድዮ ጣቢያ የሚተላለፉ ፕሮገራሞችን ከፍቷል። በዚሁ መሠረት ኦሮምኛና ትግርኛ ከአዲስ አበባ፣ ሶማሊኛና አፋርኛ ከዓለም አቀፍ ድምፅ፣ ትግርኛና ትግረ ከአስመራ ሬድዮ ይተላለፉ ነበር። የሀረር ሬድዮም ፕሮፓጋንዳውን ትቶ መደበኛ የሬድዮ ፕሮግራሞችን ጀምራል። በመቱ ከተማ የተከፈተው አዲስ ጣቢያ ደግሞ በኦሮምኛ፣ በአኙዋክ እና በኑዌር ቋንቋዎች ፕሮግራሞችን ያሰራጭ ነበር)።
# “የተማረ ያስተምር፣ ያልተማረ ይማር” በማለት በመሃይምነት ላይ የከፈተው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆት አስገኝቶለታል።
—-
እርግጥ ደርግ ገዳይ መንግስት ነበር። በስልጣኑ ለመጣበት ምህረት የለውም። ሆኖም የሰራቸው በጎ ነገሮች መረሳት የለባቸውም። ታሪክ ሙሉእ የሚሆነው ሁለቱም ጎን ለጎን ሆኖ ሲነገር ነው።
በተረፈ የባንዲራው ጉዳይ ይህንን ያህል አንገብጋቢ ነው እንዴ? አንገብጋቢ ነው ካላችሁ ጊዜ ወስደን ሪፈረንደም እናካሂድበታለን።
አሁን ግን ቅድሚታ የሚሰጣቸው ሌሎች እጅግ በጣም አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮች አሉን። እኛ በዚህ ስንወዛገብና ክፍፍል ስንፈጥር ማጅራት መቺዎቹ የለውጥ ሂደቱን እንዳይቀለብሱት ተጠንቀቁ።
ተጠንቀቁ! ተጠንቀቁ!
Filed in: Amharic