>

የመካከለኛው ምስራቅን እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን የእጁ መዳፍ ያህል ጠንቅቆ የሚያውቀው ሻለቃ!!! (በካሳ አንበሳ)

የመካከለኛው ምስራቅን እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን የእጁ መዳፍ ያህል ጠንቅቆ የሚያውቀው ሻለቃ!!!
በሀገር ፍቅር የነደደው ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ
(በካሳ አንበሳ)
**የብላታ ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ ልጅ ነው፤ ብላታ በንጉሱ ዘመን የማስታውቂያ ሚንስቴር ሚንስትር የነበሩ እና “አዲስ ዘመን” የሚባለውን ጋዜጣ ያቋቋሙ የሀገር ባለውላታ ናቸው፤
**ብላታ ወ/ጊዮርጊስ ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ያላቸው ቤተሰባዊ ቅርርብ ልጁን መሬት ላራሹን ከማቀንቀን አላስቆመውም፤ ምናልባትም እጅግ የሚወዳቸው እና የሚያክብራቸው አባቱ (“አባባ” ብሎ ነው የሚጠራቸው) ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ የተከፉበት በዚህ ሊሆን ይችላል፤
**በጉብዝናው ወቅት ሀገሩን በውትደርና አገልግሏል፤ የሀረር የጦር አካዳሚ ምሩቅ ነው፤ በሀገር አሜሪካም የውትድርና ትምህርት ቀስሟል፤ ከመጀምሪያዎቹ አየር ወለዶች ውስጥም አለበት፤
**የመጀመሪያ ዲግሪውን ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ በህግ የትምህርት አጊንቷል፤ አሰፋ ጫቦ እና ጎሹ ወልዴ የክፍል ጉደኞቹ ነበሩ፤
**ማስትሬት ከገናናው ኮሎምቢያ የኒቨርስቲ በአለም አቀፍ ህግ ወስዷል፤ ፕሪስተን ዩኒቨርስቲ ሪሰርች ፌሎ ነበር፤ ኦስተን ዩኒቨርስቲ ሶስተኛ ዲግሪውን እየሰራ ባለበት ወቅት አብዮቱ ፈነዳ፤ ሲመኝው እና ሲጠብቀው የነበረውን ለውጥ ለማገዝ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ አቀና፤
**በደርግ ዘመን የዕድገት በህብረት ም/አዝማች፣ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ም/ሚንስትር፣ የኤርትራ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ እንዲሁም የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግሏል፤ የደርግ መንግስት ወደ ፍጹም አንባገነናዊነት ሲቀየር ስራዓቱን ከድቶ አሜሪካ ገባ፤ የደርግ ስርዓት ጥሎ የኮበለለው የመጀመሪያው ከፍተኛ ባለስልጣን ደዊት ወ/ጊዮርጊስ ነው፤
**አሜሪካ ገብቶ እጅ እና እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም፤ ጫፍ ደርሶ የነበረውን የግንቦቱን 1981 መፈንቅለ መንግስትን ጨምሮ ሶስት መፈንቅለ መንግስቶችን ጠንስሷል፣ አስተባብሯል፤ ኤርትራ ድረስ ሂዶ ሻብያ ተኩስ እንዲያቆም ተደራድሯል፤
**የዳዊት ግብ ለሁሉም ዜጎች ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን ማየት ነው፤ ስለሆነም ደርግ ውድቆ ወያኔ ወደ ስልጣን ሲመጣ ወደ ኢትዮጵያ አልገባም፤  ትግሉን ቀጠለ እንጂ፤ ሲጽፍ፣ ሲናገር፣ ሲያስተምር ከ30 ዓመት በላይ ሆነው፤
**ጋሽ ዳዊት የመካከለኛው ምስራቅን እና የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ የእጁ መዳፍ ያህል ያውቀዋል፤ የአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ኤክስፐርት ነው፤ የተባበሩት መንግስታት የልኡካን ቡድን መርቶ የራዋንዳን የዘር ፍጅትን መርምሯል፣ ራዋንዳ ተመልሳ በሁለት እግሯ እንድትቆም አስተዋጾ አድርጓል፤  ብሩንዲም የተሳተፈ ይመስለኛል፤ በአሁኑ ወቅት Africa Institute for Strategic and Security Studies (AISSS) የሚሰኝ ድርጅት አቋቁሞ በመላው አፍሪካ ጥናት እና ምርምር ያደጋል፤
**በእንግሊዘኛ እና በአማረኛ በርካታ መጽሐፍትን አሳትሟል፤ ከሁሉም መጸሐፍ ሽያጭ ሰባራ ሳንቲም ወደ ኪሱ አልከተተም፤ ገቢው ለተለያዩ በጎ አድርጎት ስራ እንዲውል አድርጓል፤
**ከሱ ትውልድ ሰዎች በተለየ ተራማጅ ነው፤ ወጣቱን ላይ ከፍተኛ እምነት አለው፣ ወጣት ያቀርባል፣ እኔ አውቃለውና እኔን ብቻ ስሙ አይነት ነገር ዳዊት ጋር የለም፤ የወጣቱን ስሜት እዚሁ ፌስቡክ ላይ አድፍጦ ይከታተላል፤ ብትደውልለት እንደ ጓደኛ ያናግርሀል፤
**ይህ በሁለት እጅ የማይነሳ ምሁር ተቀድቶ ከማያልቀው እውቀት ወጣቱን እንዲያቋድስ የሁል ጊዜ ምኞቴ ነው፤ እግሩ ስር ተቀምጠው መማር ከሚመኙት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ፤ ጋሽ ዳዊት አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመህ የምትችለውን ሁሉ እንደምታርግ ተስፍ አለኝ፤
በነገራችን ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት ድሬክተር ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮርጊስ የሻለቃ ዳዊት ታናሽ እህት ናቸው፤
Filed in: Amharic