>

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሦስት ወራት ምዘና! (በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሦስት ወራት ምዘና!

በፈቃዱ ዘ ሃይሉ

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ ሦስት ወራቸውን ነገ (ማለትም ሰኔ 24, 2010) ይደፍናሉ። እኔም መጋቢት መጨረሻ ላይ ባሰፈርኩት መሥፈርት መሠረት የመጀሪያ ሦስት የሥራ ወራት ስኬታቸውን እንደሚከተለው መዝኜያቸዋለሁ።

☞ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማቋረጥ (5 ነጥብ ከ5 አግኝተዋል)

☞ ሁሉንም (በክልሎች እና የፌዴራል መንግሥታቱ ሥር የተያዙ) የፖለቲካ እና የኅሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት (8 ነጥብ ከ10 አግኝተዋል)

☞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ተብለው የተፈረጁትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ ፍረጃ ማንሳት (20 ነጥብ ከ20 አግኝተዋል። /የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህንን የሚጠይቅ ረቀቂ አዘጋጅቶ ስለላከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእርሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።/)

☞ ከላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶች ለፖለቲካዊ የእርቅ ድርድር መጥራት (5 ነጥብ ከ20 አግኝተዋል። /5 ነጥብ የሰጠኋቸው በተፈረጁበት ፓርላማ ለድርጅቶቹ ቀና አመለካከት በማሳየታቸው እንጂ መደበኛ ጥሪ አላደረጉም።/)

☞ በፖለቲካ ክስ እና ፍረጃ የተሰደዱትን ዜጎች ያለመታሰር ዋስትና ሰጥተው እንዲገቡ መፍቀድ (7 ነጥብ ከ10 አግኝተዋል። /ይህም በሕግ ለተወሰነው ሳይሆን ጥቂቶች ወደ አገር ቤት እየገቡ ስለሆነና ቢገቡ ስለማይታሰሩ፣ በጅምላ ለመፍቀድም የምኅረት አዋጁ ተሰናድቷል በሚል ነው።)

☞ ከሶማሊ ክልል (እና ሌሎችም አካባቢዎች) የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ (-5 ነጥብ ከ15 አግኝተዋል። /አምስት ነጥብ የተቀነሰባቸው ችግሩ በመባባሱ ነው።/)

☞ ሲቪል ማኅበራት ላይ የተጣለውን የ10/90 የገቢ መርሕ ማሻሻል፣ የብዙኃን መገናኛዎች ባለቤትነት መብት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎችም መፍቀድ (3 ነጥብ ከ10 አግኝተዋል። ሦስት “የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሚድያ ሕግጋት ይሻሻላሉ” ለሚለው ዜና፣ ቃል ለተገባው ሪፎርም እና ለተቋቋመው ጉባዔ ነው።/)

☞ አፋን ኦሮሞን የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ማድረግ (0 ነጥብ ከ10 አግኝተዋል።)

ውጤቱ

ቀድሜ ባስቀመጥኩት መሥፈርት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ 43 ነጥብ ከ100 አግኝተዋል። በዚህም ‘C-’ አግኝተዋል።

የምዘናው ምዘና

የምዘና መሥፈርቶችን ሳወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀላሉ ያሳኩታል የሚል ግምት ስለነበረኝ ያዳላሁላቸው መስሎኝ ነበር። እንደምታዩት ተሳስቻለሁ። ነገር ግን ፌስቡክ ላይ በወቅቱ የተሰጡኝ ምላሾች ባብዛኛው “ሦስት ወር ግዜ አጠረ” እና “የሚመዘኑባቸው ነጥቦች ተመጣጣኝ አይደሉም” የሚሉ ነበር። በተግባር ሲፈተሽ የገጠመኝ ችግር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔ ካስቀመጥኳቸው ውጪ ሌሎች ስኬቶችን ያስመዘገቡ በመሆኑ እነርሱን መመዘን አለመቻሌ አግባብ ሆኖ አላገኘሁትም። ለምሳሌ አገር የማረጋጋት ሥራቸው፣ የኢትዮጵያ እና ኤርትራን ጠብ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት መቁረጣቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ ጠፍቶ የነበረውን ተስፋ በከፍተኛ ሁኔታ ማጫራቸው፣ በሌሎች አገራት የታሰሩ ዜጎቻችንን ከእስር ማስፈታታቸው በቀላሉ የማይገመቱ አስተዋፅዖዎች ናቸው። ሌላው ደግሞ ቀድሜ ባስቀመጥኳቸው የምዘና መሥፈርቶች ውስጥ ከአጣዳፊ ሥራዎች መካከል “አፋን ኦሮሞ የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ” የሚለው ከጥያቄው አንፃር ሳይሆን፣ ከጊዜው አንፃር አግባብ እንዳልሆነ አምኜያለሁ። እነዚህን የምዘናዬ ድክመቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ 20 ነጥብ ‘ቦነስ’ በመስጠት 43 ነጥብ ከመቶ ያገኙትን፣ 63 ነጥብ ከመቶ እንዲያገኙ በማድረግ የ3 ወራት አመራራቸውን ውጤት በማሻሻል ‘B-’ ሰጥቻቸዋለሁ። 😊

የቀጣይ ምዘና ‘ቼክ ሊስት’

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አካሔድ እስካሁን በትክክለኛው ጎዳና ላይ ነው ብዬ አምናለሁ። የፍጥነታቸው ጉዳይም ቢሆን ለኛ ለጥያቄ አቅራቢዎቹ የረዥም ግዜ ጥያቄዎች ቢሆኑም፣ ለርሳቸው ለመልስ ሰጪው ካላንደር ገና ሦስተኛ ወራቸው ነው። ስለሆነም የኛንም የእርሳቸውንም የጊዜ ሰሌዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በቀጣይነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለ2012ቱ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያዘጋጇት ነው የምፈልገው። ለዚህም የሚከተሉት ነገሮች በቶሎ መልስ እንዲያገኙ እጠብቃለሁ።

 የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት እና ሚዲያ ዐዋጆችን ማሻሻል፣
 የፍትሕ አካላትን (ማለትም ፍርድ ቤቶችን፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት እና መከላከያ)፣ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ብዙኃን መገናኛዎችን እንዲሁም ምርጫ ቦርድን ለሕዝብ እና ሕገ መንግሥቱ ወገንተኛ እንዲሆኑ በማድረግ መልሶ ማዋቀር።

(እነዚህን ካደረጉ ምን እፈልጋለሁ?)

Filed in: Amharic