>

ያልሰማነው ነብይ!!! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

ያልሰማነው ነብይ!!!
***
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
በ1960ዎቹ አጋማሽ በ“ጥናት ክበብ” ስም በየመንደሩ ለውይይት መሰባሰብ ፋሽን በነበረበት በዚያን ዘመን፣ ታላላቅ አገራዊና ወቅታዊ አጀንዳዎችን በግራ-ዘመም አስተምህሮ በማጥናት የፖለቲካ “ፊደላትን”  ሀሁ… ብሎ መቁጠር የጀመረው ያሬድ ጥበቡ፣ ከአቻዎቹ ጋር “አብዮት” የተሰኘ ፀረ ዘውድ ምስጢራዊ ቡድን ከመመሥረት ያገደው አልነበረም፡፡
ግና፣ ለውጥ በብሶት ክምችት እንጂ በቀጠሮ አይመጣምና እነያሬድ በ‹ዳስ-ካፒታል› ሲራቀቁ፣ በስታሊን ከራቫት ሲወዘገቡ፣ በማኦ ሰላምታ ሲነታረኩ፣ በሆችሚኒ ስም ሲፈላሰፉ፣ በስያሜያቸው ሲጠበቡ … የየካቲቱ አብዮት “ደረስንባቸው ሳይታጠቁ” ሆነና፣ ንጉሣዊው ሥርዓት ወድቆ ተማሪዎቹ ባነበቧቸው መጻሕፍት የማይተነተን አዲስ መደብ የፈጠረው ወታደራዊው አስተዳደር ሥልጣኑን በመዳፉ አዋለው፡፡
ይኽንን ተከትሎ ነው ያሬድ ጥበቡ ብረት-ነካሹን ኢሕአፓ ካዋለዱ የያ ትውልድ ልጆች አንዱ ይሆን ዘንድ ታሪክ ያጨችው፡፡ ውሎ-አድሮም ቤተ-መንግሥት ከገባው ጋ ብቻ ሳይሆን በተራማጆች መካከልም የልዩነቱ ክረት ጠርዝ በመርገጡ፣ የፍርድ-ደጆች ተዘግተው ፍትሕ በቀለም-ሽብር ሥር ለመውደቅ ተገደደች፡፡ በውጤቱም የፖለቲካ ሥልጣንን የጨበጠው ኀይል ሲያሸንፍ፤ ተቀናቃኙ ተቸንፎ ፊቱን ሙሉ ለሙሉ በገጠሩ ሽምቅ ውጊያ ላይ አዞረ፡፡ ያሬድም ተወልዶ ያደገበትን ውቤ-በረሃ ተሰናብቶ አሲምባ-በረሃን ቤቱ አደረገ፡፡
ከአሲምባ እስከ ጠለምት በዘለቀው ጉዞው በኢሕአፓ መስመር ፍፁማዊነት ቅንጣት ጥርጣሬ ባይኖረውም፣ በአመራር አባላቱ “.. ግዴለሽት፣ ጭካኔ፣ ዘገምተኝነት… ተከፍተናል” ያሉ መሰሎቹን በማሰባሰብ ኢሕዴንን መሥርቶ ለድፍን አምስት ዓመት ታግሎ ስለማታገሉም የሰሜን ተራሮች በሕያው ምሥክርነት ይቆጠሩለታል፡፡
(በነገራችን ላይ፣ ያሬድ ጥበቡን ጉምቱ ፖለቲከኛና ጥልቅ አሰላሳይ ብቻ ብሎ ማለፍ ቤተ-መቅደስን በጫማ የመርገጥ ያህል ድፍረት ይመስለኛል፡፡ ስለምን ቢሉ? የሥነ-ጽሑፍ አውሊያ ከሰፈረባቸው ተለማኝ ‹አማልዕክት› ተረታ የሚመደብ ባለቱባ ብዕረኛ ነውና)
የሆነ ሆኖ፣ ደራሲው በዚህ “ወጥቼ አልወጣሁም” ሲል በሰየመው መድብል ያቋደሰን አበርክቶ፡- የብሔር ፖለቲካን መርገምትና በረከት፣ የአገዛዙን ድክመትና ጥንካሬ፣ ሴራና ሽወዳ፣ የማኅበረሰብንና የሠራዊቱን ሥነ-ልቦና፣ የታሪክ ሙግትን … የመሳሰሉ ግዙፍ ጉዳዮችን በመተንተን ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዛሬ ኢትዮጵያችንን እየናጡና እያፈረሱ ስላሉ ሥርዓት-ወለድ ክስተቶች ከዓመታት በፊት ሰሚ-አልባ እንደነበሩት የኦሪት ነብያት ድምፁን ከፍ አድርጎ የጮኸባቸው መሆኑን ከመጽሐፉ ስንረዳ የነብይነት ፀጋ ተቀብቶ ይሆን እንዴ? ስንል ለመጠርጠር እንገደዳለን፡፡
ትርክቴን በማሳያ ለማጠናከር፤ በኢሕአዴግ ወገብ ላይ እንደዘንዶ የተጠመጠመው የሕወሓት የበላይነት በጊዜ ካልተገታ የነለማ መገርሳን ዓይነት ኦሕዴድ በመፍጠር ራሱኑ መቃብር ሊከተው እንደሚችል በ1989 ዓ.ም. ካስነበበን ትንቢተ-ያሬድ የሚከተለውን እጠቅሳለሁ፡-
“. ሕወሓት በረዥም ዓመታት ባዳበረው ድርጅታዊ ልምድ ምክንያትና ባለውም ድርጅታዊ ጥንካሬ የተነሳ ኢሕአዴግ ውስጥ የፖሊሲ ሐሳብ፣ የታክቲክና ስትራቴጂ ወዘተ. ሰነዶች አቅራቢ ነው፡፡ ሌሎቹ የሚከራከሩበትን አጀንዳ የሚያስይዝና መረጃ የሚያቀርብ የሕወሓት ፖሊት ቢሮ በመሆኑ የሌሎቹ ድርጅቶች ተወካዮች ከቀረበላቸው ረቂቅ ሰነድ ውጪ የመወሰን አቅማቸው የተሰለበ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ያልተመጣጠነ ሒደት በቀጠለ ቁጥር በውስጡ ሌሎች ብሔርተኞች ጥያቄ ማንሳት የሚጀምሩበት ሒደት ጀርሙን በውስጡ እንዳቀፈ ነው የሚጓዘው፡፡ በተለይ በአቶ መለስ የሚታየው የተንኳሽነትና የበላይነት እንዲሁም የማፌዝና የማሳነስ ወዘተ. ግለሰባዊ ባሕርይዎች ውለው አድረው እንቢተኛ የሆኑ ግለሰቦችን መፍጠሩ የማይቀር ይመስለኛል፡፡ ይህም የግለሰቦች ኩርፊያ በድርጅታዊና ብሔረሰባዊ ጥያቄ ወዘተ. መልክ የመከሰት አቅጣጫ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ ቅዥት ሆኖ ሊቀር ይችላል፤ ወይም ሊከሰት ይችላል፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለን፡፡”
በተጨማሪነት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በታኅሣሥ 2010 ዓ.ም. ያካሄዱትን 18 ቀናት የፈጀ ግምገማ መጠናቀቅ ተከትሎ ሊቀ-መናብርቱ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል አንዳንድ የትግራይ ተወላጆች ሥርዓቱን ተገን አድርገው በሕገ-ወጥነት መበልፀጋቸውን በጣም ዘግይቶ ያመነውን ሐቅ፣ ያሬድ ጥበቡ ያኔ ገና ሕወሓቶች እንዲህ እንደዛሬው የነጋበት ጅብ ከመሆናቸው በፊት “… በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ በየኮሚሽኑ፣ በየባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የትግሬ እጥረት እስከሚፈጠር ድረስ ቢሮክራሲውን ሲሞሉ ሌላውስ ሁለተኛ ወይም ዐሥራ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ይጠመዋል ብለው እንዴት ሊያስቡ ቻሉ?…” በሚል ኀይለ-ቃል የድርጅቱን ዐይን ያወጣ ስግብግብነት ወደፊት መጥፊያው ሊሆን እንደሚችል ከዓመታት በፊተት በጻፈው ጽሑፍ ማስረዳቱንም ከዚህው ድርሳን እንረዳለን፡፡
ያሬድ ጥበቡ “እነሆ በረከት” ባለን ጥራዝ የተካተቱት መጣጥፎች ከትምህርት ቤትና ከንባብ በተገበየ ዕውቀት ብቻ የተዋቀሩ አይደሉም፡፡ አብዛኛው ዘመኑን በሰዋበት የፖለቲካ ባሕር ወለል ድረስ ሰምጦ፣ አንድም ሕልሙን ለማሳካት፣ ሁለትም በሕይወት ለመትረፍ ካደረገው ግብግብ ጭምር ባገኘው ግንዛቤ የተቀመረ በመሆኑ ለመጽሐፉ ቅቡልነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ እናም የ66ቱን አብዮት መንፈስ፣ የኢሕአፓ-ኢሕአዴንን እንዲሁም የኢሕአዴግን አመጣጥና የአስተዳደር ዘይቤ ሥረ-ምክንያት ለመመርመር፤ ጎን ለጎንም ወቅታዊውን የሕወሓት የጥንጣን ጉዞ እና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ለመረዳት ከሚጠቅሙን ወሳኝ ድርሳናት መካከል አንዱ ስለሆነ ሁላችንም ልናነበው ይገባል ስል እመክራለሁ፡፡
Filed in: Amharic