>

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ "የቁጥር ማሟያ ከመሆን መቅረቱን መርጫለሁ" - ለሸገር ታይምስ

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ “የቁጥር ማሟያ ከመሆን መቅረቱን መርጫለሁ”ለሸገር ታይምስ

ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በትላንትናው ፕሮግራም ላይ  ከቤተመንግስት ተባረረ እና መሰል ወሬዎችን በማህበራዊ ድረገፆች ስንሰማ እውነታው የት ጋር ነው? ስንል ለድምፃዊው ስልክ መታን፡፡

ድምፃዊ አጫሉ በማህበራዊ ድረገፅ “ከስብሰባው ተባረረ፣ ሀገር ውስጥ የለም” እና መሰል ወሬዎችን መስማቱን ገልፆ እውነታው ግን ያ አይደለም ይላል፡፡ እንዲየውም ፕሮግራሙን ለመታደም ቤተመንግስት በር ላይ ከደረሰ በኋላ ባየው ነገር አዝኖ መመለሱን ነው ለሸገር ታይምስ የገለጸው፡፡

“እንደ ማንኛውም አርቲስት የጥሪው ወረቀት ደርሶኝ ቦታው ላይ ከተገኘሁ በኋላ ተገቢ ያልሆነ ነገር በማየቴ ኃሳቤን ለውጬ ተመልሻለሁ፡፡” የሚለው ድምፃዊው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርቲስቶች እንዲጠሩ ደብዳቤ የፃፉት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር መሆኑን ጠቁሞ “ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ግን አጠራሩ ፍፁም ትክክል ያልሆነ እና ተገቢም አልነበረም” ይላል::

ጥሪው ሲደረግ ከአምስት ያልበለጡ የኦሮሞ አርቲስቶች ብቻ እንዲጠሩ መደረጉ እንዳሳዘነው የሚገልፀው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ “ የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም እኔም በግል የማከብራቸው እና አሁን ለመጣው ለውጥ ሲገረፉ እና ሲታሰሩ የነበሩ የኦሮሞ አርቲስቶች ይገኛሉ ብዬ ጠብቄ ነበር ነገር ግን ቦታው ላይ ስገኝ አንዳቸውንም ላይ አልቻልኩም በሌላው ቋንቋ ግን ቦታው ላይ ያልተገኙት የትያትር ቤት ጥበቃ እና የፅዳት ሰራተኛ ብቻ ናቸው በዚህም ምክንያት እነኚያ ትልልቅ አርቲስቶች ገሸሸ በመደረጋቸው አዝኜ ከቤተመንግስት ለመመለስ ወስኛለሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደመሩ ሲሉ 500 ለ5 አይደለም፡፡” ብሏል፡፡

“ከሰዓሊ አንስቶ አስከ ሙዚቃ አቀናባሪ እና ተወዛዋዥ ድረስ ተጠርቶ ባለበት ሁኔታ ይህን በመመልከቴ በመደመር ውስጥ መቀነስ እንዳለ ስለገባኝ ሃሳቤን ለውጬ ተመልሻለሁ ይሄ ማባዛት እንጂ መደመር አይደለም” የሚለው ሃጫሉ “አሁን ላለንበት ለውጥ እና ልተፈራርስ  የነበረችውን ኢትዮጵያን ለማትረፍ የተገረፉላት፣የተሰቃዩላት፣የደሙላት ታላላቅ የኦሮሞ አርቲስቶች ተዘንግተዋል” ብሏል፡፡ ድምፃዊው ሲቀጥልም “አፍን ሞልቶ ተደምረናል የሚባለው ሁሉንም ያካተተ ጥሪ ቢደረግ ነበር ” ይላል፡፡

ይህ ሁሉ ጥፋት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን የባህልና ቱሪዝም ጥፋት ነው የሚለው ድምፃዊው “ዶ/ር አብይ እከሌ ጎበዝ ነው፤እከሌ ሰነፍ ነው ብሎ ሳይሆን የኢትዮጵያ አርቲስቶችን እፈልጋለሁ ነው ያለው የኢትዮጵያ አርቲስት ሲባል ደግሞ  አማራው፣ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ወላይታው እና ሌሎቹም እነጂ አንዱን አርቆ አንዱን አቅርቦ የሚደረግ መደመርን በፍፁም የምቀበለው አይደለም ጥሪውን ያደረገው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በኦሮምያ ያሉ አርቲስቶችን የማያውቅ ከሆነ በኦሮምያ ባህልና ቱሪዝም በኩል ማስጠራት ይችል ነበር፡፡” ያለው ታዋቂው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ “ በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የተሰራው ነገር አሁን ካለው ለውጥ እና ወደፊት  ልናደርገው የምንፈልገው ለውጥ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ብሎም ሌላ ጥያቄ ሊያመጣ የሚችል ድርጊት በመሆኑ እዛ ውስጥ ተሳትፌ ቁጥር ማሟያ ከምሆን  መቅረቱን መርጫለሁ ይህ የሚያሳየው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ውስጥ አሁንም ያልታደሱ ሰዎች መኖራቸውን ነው፡፡”  ሲል ነው ለሸገር ታይምስ የተናገረው፡፡

Filed in: Amharic