>
5:13 pm - Tuesday April 20, 1706

ግባቸው የፓርላማ ወምበር የሆነ ለጥገናዊ ለውጥ የሚሰሩ ተቃዋሚዎች አሉ!!! (እስክንድር ነጋ)

ግባቸው የፓርላማ ወምበር የሆነ ለጥገናዊ ለውጥ የሚሰሩ ተቃዋሚዎች አሉ!!!
እስክንድር ነጋ
ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው እስክንድር ነጋ ላልፉት ሶስት ሳምንታት በኢሳት ቴሌቪዥን ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ማድረጉ ይታወሳል፤ በውይይቱ የመጨረሻው ክፍል ላይ ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ተጠይቆ የሰጠውን ምላሽ እነሆ:-
 
 ጋዜጠኛ ሲሳይ:- ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር እንዴት ነው የምትገመግመው?
እስክንድር ነጋ፦ገና ነን።  በሂደት ላይ ነን። በየት አቅጣጫ እንደምንሄድ ግልፅ አይደለም። በአንድ በኩል ህዝብ አለ፣ ይሄ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ለውጥ ማለት; ጥገናዊ ለውጥ አይደለም። በኢህአዴግ ውስጥ የስልጣን ሽግሽግ እንዲደረግ አይደለም የሚፈልገው – ወይም ደግሞ፣ የነፃነት ደሴቶችን ለመፍጠር አይደለም። ይሄ ህዝብ የታገለው ነፃ ምርጫ ቦርድ ለማቋቋም አይደለም። ይሄ ህዝብ የታገለው;  የፕሬስ ህጉ ተነስቶ፣ ጋዜጠኞች በመጠነኛ  ደረጃ የሚንቀሳቀሱበት ስፔስ ለመፍጠር አይደለም። ለአጠቃላይ ነፃነት ነው የታገለው። በአንድ በኩል ይሄ ፍላጎት አለ። በሌላ በኩል በፓርቲው ውስጥ ይህንን የለውጥ ፍላጎት ተመልክቶ የተከሰተ የሃሳብ ልዩነት አለ። ይሄ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት አሳይቷል… ለዚያ ምላሽ መስጠት አለብን የሚል ሃይል አለ። ይሄ የለማ ቲም የሚባለው ነው።በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሁንም በጉልበት መቀጠል እንችላለን ፣ እንደበፊቱ ማስቀጠል የሚችል ሃይል ስላለን እስከመጨረሻው ታግለን በዚያ መንገድ ማስቀጠል አለብን የሚል አለ። ይሄ ነባሩ ሃይል ነው። ስለዚህ ሶስት ካምፕ አለ ማለት ነው። 1/ አጠቃላይ ነፃነት የሚፈልግ  2/ ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረ ሁለት ካምፕ አለ።  በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ በሚፈልገውና በነባሩ ሃይል አመራር መካከል ያለው ፍጥጫና የሃይል ሚዛን ገና አለየም። እርግጥ አሁን የበላይነቱ ያለው; በሪፎርሚስቶቹ እጅ ነው። ይህንን እንዴት አልክ ያልከኝ እንደሆነ፣ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን እንዳይመጡ የተቻላቸውን ያህል ሲያደርጉ አይተናል። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ምርር ያለ ካምፔን ነው ያደረጉት። በፓርቲው ውስጥም፣ ምርር ያለ ትግል አድርገዋል። በተለይ መጨረሻ ላይ ዶ/ር አብይን ለመምረጥ በተደረገው ጉባዔ ላይ ከፍተኛ ትግል አድርገው ተሸነፍዋል። ስለዚህ፣ እነዚህ ሁለት ሃይሎች በዚህ መንገድ ለግዜው ቢለያዩም; መሉ ለሙሉ ግን ለውጥ የማይፈልጉት ሃይሎች ተሸንፈዋል ማለት አይደለም። አሁንም ገና አለየም። አንድ የመጨረሻ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።
እዚህ ላይ ቁልፍ ነጥብ አለ…ይሄ ሪፎርሚስት እነ ዶ/ር አብይ (ቲም ለማ) ነባሩን ሃይል ማሸነፍ ቢችሉ፣ ምን ዓይነት ለውጥ ነው ያሰቡት? የሚለው ገና ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። ሁለት ዓይነት መንገድ ግን አለ። በአንድ በኩል ኢህአዴግ ውስጥ የስልጣን ሽግሽግ ተደርጎ በጥገናዊ ለውጥ መልኩ ለፕሬሱ ትንሽ ክፍተት ሰጥቶ; በምርጫ ቦርድም በኩል ትንሽ ክፍተት ሰጥቶ; የሚቀጥለውን ምርጫ ክፍት አድርጎ የመቀጠል ፍላጎት ሊኖር ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የህዝቡን እውነተኛ የለውጥ ጥያቄ የመመለስም ሊሆን ይችላል። የትኛውን መንገድ እንደሚከተሉ ግልፅ አይደለም። ግን ወደትልቁ ጥያቄ ከመሄዳችን በፊት በፓርቲው ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ መለየት አለበት። ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ” የቱ ይሻላል?” ያልከኝ እንደሆነ፣  ሪፎርሚስት ሃይሉ ቢያሸንፍ ይሻላል። ወዴት እንደሚሄድ ባናውቅም እሱ ይሻላል። ቢያንስ የለውጥ ሃይል ህዝቡ ውስጥ እንዳለ ተረድቷል። በእኔ ግምገማ ማሸነፍ የሚችል ሃይል ነው። ነባሩ አመራር የተቻለውን  አድርጎ ተሸንፏል። ተዳክሟል ማለት ነው። ይህንን ዕውነታ ይዞ አዲሱ የኢህአዴግ አመራር;  እነ ቲም ለማ ወደፊት መግፋት ይችላሉ።ፀረ- ዲሞክራሲው ሃይል ነባር አመራሩ መሪ የለውም። ስለዚህ፣ ሊመታ የሚችል፣ (ፊዚካሊ ማለቴ አይደለም) ነው። በደህንንነት  ውስጥ ካለው መዋቅር ላይማግለል የሚቻል ነው።እንደሃይል ሆኖ መታገል የሚችል አይደለም። በአስተሳሰብ ተበትኗል። ይህንን ሂደት ቢጨርሱት ደስ ይለናል። ይሄ ካለቀ በኅላ፣ እውነተኛ ለውጥ የምንፈልገው ከነአብይ መልስ እንፈልጋለን። ጥገናዊ ለውጥ ነው የምትፈልጉት ወይስ እውነተኛ ለውጥ ለሚለው ምላሽ እንፈልጋለን።
ጋዜጠኛ ሲሳይ:- በዚያ ሃይል አንዱ የነበረበትን ለማስቀጠል የሚፈልግ እንደሆነ በግልፅ ቋንቋ…አምባገነንነቱ፣ ዘረኝነቱ፣ የህወኅት የበላይነቱን በማስቀጠል በዚያው መንገድ ለመቀጠል የሚፈልግ አለ። ሌላው፣ ትክክል አይደለም ዘመኑን የሚመጥን ለውጥ ያስፈልጋል ብሎ የተነሳ ቡድን አለ። ያ ለውጥ የሚፈልገው ቡድን ደግሞ የበላይ ሆኖ የመውጣት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ አውስተሃል። ይሄ ቡድን የሆነ ቦታ ከደረሰ በኅላ ግን መጨረሻ ግቡ ምን እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን ብለሃል። ያ ቡድን ምንም ሆነ ምን፣ ቆሞ ከቀረው ሃይል የሚሻል ከሆነ ባለው ትግል ውስጥ አሸንፎ እንዲወጣ ለውጥ ፈላጊው፣ በተለይ ህዝቡ በምን መልኩ ሊደግፍ ይችላል? ወይስ መደገፍ የለበትም?
እስክንድር፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። ድጋፍ የሚለው አጨቃጫቂ ሊሆን ይችላል። በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ሃይል ለዲሞክራሲው እንቅስቃሴ ታክቲካል አጋር ሊሆን ይችላል። ታክቲካል አጋርነት ምንድን ነው?…ነባሩ ፀረ- ዲሞክራሲና በሙስና የተጨማለቀውን ሃይል ከመድረክ ላይ ለመጨረስ ነው።ከፖለቲካው መድረክ ላይ ለማስወገድ ነው። ከፓርቲው መዋቅር ውስጥ ለማስወገድ ነው። በዚህ መንገድ ሁለት የዲሞክራሲያዊው ሃይልና የለውጡ ሃይል ታክቲካል አጋርነት ሊፈጥሩ የሚችሉበት ሁኔታ ይታየኛል። ይሄ ችግር የለውም። ስትራቴጂካል ግን ሊሆን አይችልም። ግባቸውን በትክክል ስለማናውቀው። ነባሩ አመራር ከተመታ በኅላ፣ በነገራችን ላይ ነባሩ አመራር ተመትቷል; አንድ እግሩ ወጥቷል፣ ሌላኛው እግሩ ሙሉ ለሙሉ ከወጣ በኅላ፣ምን እንደሚፈልጉ ስለማናውቅ ስትራቴጂክ አሊያን ከእነሱ ጋር መፍጠር አንችልም። በጥንቃቄ ነው  ልንመለከታቸው የሚገባው። የወጡትም ከኢህአዴግ ውስጥ ነው። ህዝቡንም አልተደራጀም…አሁን ላይ ተደራጅቶ ለመጠየቅ አቅም የለውም ብለው ስለሚያስቡ ስልጣናቸውን ይዘው ለመቀጠል የሚፈልጉበት ሁኔታ አለ። ነጥቡ ግን፣ ሥር-ነቀል ለውጥ የሚፈልገው ያልተደራጀም ቢሆን፣ በሂደት ተደራጅቶ መመለስ ይችላል።  አሁን ነባሩን አመራር የጠራረገ ማዕበል እንደተፈጠረ ሁሉ፣ እነሱን ተክቶ አዲስ ገዥ መደብ፣ አዲስ አምባገነናዊ ስርዓትን መፍጠር የሚፈልገውንም ጠራርጎ የሚሄድ ማዕበል መፍጠር ይቻላል።
ጋዜጠኛ ሲሳይ:- የለውጡ ሃይል የመጨረሻ ግቡ ምን ይሆናል ላልከው … አንተ እንደገለፅከው በጥገናዊ ለውጥ ይሻገሩታል ወይስ ሥር-ነቀልመሰረታዊ ለውጥ ይሄዳሉ የሚለው አልተመለሰም። ግን፣ ወደ መሰረታዊ ለውጥ በሚደረገው ጉዞ ላይ  ተቃዋሚ የሚባለው ሃይል ራሱን ለዚያ አዘጋጅቷል ወይ ነው? ምክንያቱም ፣ አንዳንዶች ከወዲሁ በማናቸውም ሁኔታ ከነዶ/ር አብይ ወይም ከነለማ ቀድመው ራሳቸውን ለጥገናዊ ለውጥ ያዘጋጁ ሃይሎች አሉ። ይሄ ኢትዮጵያ ወደ መሰረታዊ ለውጥ እንድትሄድ በዚህ በኩል ያለውን እንቅፋት አመራሩ ላይ ያሉትን ሰዎች ከመጠየቅ ተቃዋሚዎች፣ አክቲቪስቱ፣ ሌላውም ክፍል እነሱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የለበትም ወይ? ምክንያቱም ፣ እነሱ ብቻ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የለውጡን ጉዞ፣ የተስፋውን ጭምር ማምከን አይሆንም ወይ? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች አንድም ሁለትም ወንበር ካገኙ ..ፓርላማ ውስጥ ወንበር ካገኘሁ ይበቃኛል በሚል አጠቃላይ ሂደቱን ለማምከን የሚደረግ ነገር  ይመስለኛል…
እስክንድር፦ መቸኮሉ አስፈላጊ አይደለም። በተለይ ተቃዋሚዎች አብረው መጓዝ የሚችሉበት ስትራቴጂ ቢኖራቸው ይመረጣል። ሆኖም ግን፣ እነዚህ ተንጠባጥበው ወደ ውስጥ የሚገቡ ድርጅቶች መኖራቸውና አለመኖራቸው በመጨረሻ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። እያሳነስኳቸው አይደለም። ሁሉም ተቃዋሚዎች ተናብበው ቢሄዱ፣ የትግላችንን ዘመን ያሳጥርልናል። ባይችሉ ግን፣ በህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። መጨረሻ ላይ የህዝቡ ፍላጎት ነው በኢትዮጵያ ተፈፃሚነት የሚያገኘው። ህዝቡ የስርዓት ለውጥ ይፈልጋል። ስለዚህ አሁን ቸኩለው የሚገቡት ድርጅቶች ራሳቸውን ትዝብት ላይ ከመጣል ባሻገር ህዝቡ ላይ የሚያመጡበት ተፅእኖ የለም። ራሳቸውን ከህዝብ ከመነጠል ባሻገር። ይህ በረጅሙ ሂደት ነው። በአጭሩ ሂደት ግን፣ ለጨቋኙ ስርዓት ተጨማሪ  ጉልበት ሊሆኑለት ይችላል።
ጋዜጠኛ ሲሳይ:- በጥገናና በመሰረታዊ ለውጥ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?…
እስክንድር፦ ጥገናዊ ለውጥ ማለት፣ በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ሆኖ ደሴቶችን መፍጠር ነው። ድርድር ውስጥ መግባት ማለት ነው። አምባገነናዊ ስርዓት እንዳለ ይቀጥል ግን ነፃ የሆነ ወይም ከበፊቱ የተሻለ የምርጫ ቦርድ ፈጥረን …ትንሽ ፓርላማ ውስጥ የሚያስገባን፣ ስፔስ እንፍጠር ፣ የሚዲያውን ስፔስ ትንሽ የሚያሰፋ ነገር በማስደረግ; የፕሬስ ፀረ- ሽብር ህጉን በማንሳት፣ የሲቪክ ማህበረሰቡን ህግ በማንሳት…ትንሽ ሰፋ፣ ሰፋ ማድረግ…ይሄ ነው ጥገናዊ ለውጥ። ስፔሲፊክ ነገሮች ላይ አተኩሮ በዚያ ነገር ውስጥ መቀጠል ማለት ነው።
መሰረታዊ ለውጥ ደግሞ፣  በሁሉ አቀፍ ጉባዔ በኩል ሁሉም ድርጅቶች የሚሳተፉበት የብሄራዊ አንድነት የሽግግር መንግስት መስርቶ፣  ህዝቡን አጠቃላይ ነፃነት አጎናፅፎ ለነፃ ምርጫ የሚያበቃ ነፃ ተቋማት መገንባት ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ምርጫ ቦርድ መፍጠር ያለበት፣ ምርጫ ቦርድን ነፃ አድርጎ መገንባት የሚችለው ስልጣን ላይ ያለው ሃይል ነው። ይሄ ማንዴት ለአንድ ድርጅት ሊሰጥ አይቻልም። ሁሉም ድርጅቶች መንግስት ሆነው ነው ነፃ ተቋማት መፍጠር ያለባቸው። ፖሊሱን ነፃ ተቋማት፣ ሰራዊቱን ከፖለቲካ ተቋማት ማፅዳት አለባቸው። ሂደቱን በሃላፊነት መምራት ያለባቸው ሁሉም ድርጅቶች ናቸው።ይሄ ሃላፊነት ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት በተናጠል መሰጠት የለበትም።  የብሄራዊ አንድነት አስፈላጊነት  ደግሞ በተቋም  መደገፍ አለበት። እነዚህን ነፃ ድርጅቶች መፍጠር የሚችሉት ሁሉም ድርጅቶች መንግስት ሆነው ሲፈጥሯቸው ነው። ለአንድ ድርጅት የሚሰጥ ሃላፊነት አይደለም ። በዚህ መንገድ ነው ወደ ስር ነቀልና መሰረታዊ ለውጥ መግባት የሚቻለው።
Filed in: Amharic