>

እልቂት እና ጉብኝት (ደረጀ ደስታ)

እልቂት እና ጉብኝት

ደረጀ ደስታ

ጠቅላይ ምኒስትሩ አፋር ገብተው በመዲናዋ ሰመራ ከተማ ከህዝቡ ጋር እየተነጋገሩ ነው። በክልሉ ይቋቋማል ለተባለው የኢንደስትሪ ዞን የመሠረተ ድንጋይ ያኖሩ መሆናቸውም ተዘግቧል። ጉብኝቱ ቀደም ሲል በተያዘ ፕሮግራም መሠረት እሚከናወን መሆኑ ቢገመትም እንደ ቤንሻንጉል ክልል አሶሳ ባሉ አካባቢዎች ሁከት እየተፈጠረ ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል። ሰውየውን እንደዚህ ከመሰሉ የሥራ መርሃ ግብሮች በማስተጓጎል ግጭት በተፈጠረበት አካባቢ በሙሉ እንደ እሳት አደጋ እየተወረወሩ- በሰው እልቂትና ግጭቶች ዜና እየተወጠሩ እንዲቀሩ የተፈለገ ይመስላል። ከዚህ ጋር ግንኙነት ያለው መሆን አለመሆኑ ባይታወቅም ትናንት ሌሊት በመርካቶ አንዋር መስጅድ እንዲደርስ የታሰበው አደጋ የከፋ ቢሆን ኖሮ ሊከሰት እሚችለውን ነገር ማሰብ አያዳግትም። ጠ/ሚሩ ሁኔታዎችን መቆጣጠር ቢያቅታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ወደሚያስገድዳቸው ጫና ለማድረስ ቁርጠኝነት ያለ ይመስላል። ሊመጣ ያለውን እልቂት አስቀርተው ወደ ሰላም እሚያመራ ለውጥ አነሳስተዋል የተባሉት ሰው ሥልጣን ላይ መቆየታቸው የበለጠ እልቂት ያመጣል ወደሚለው ንግግር እንዲቀየር እየተሠራ ይመስላል። “ሰዎቹ” (መቸም ይህ ነገር ባለቤት ይኖረዋልና..) ”ካለኛ አይሆንም እኛ ከሌለን መጠፋፋት ይኖራል” በሚል አስጠንቅቀውናል። ከነሱ በመገላገሉ ተስፋ የተደሰተ አገር ወደነሱ ይመለሳል ተብሎ መቸም አይታሰብም። እነሱም በነጻ እንደማይገላገሉን እያሳዩን ሳይሆን አልቀረም። ስለዚህ የትኛውም መንገድ ዋጋ ማስከፈሉ እንደማይቀር ግልጽ እየሆነ የመጣ ሆኗል። ጥያቄው ዋጋውን ማስቀረቱ ላይ ሳይሆን ዋጋውን መቀነስ እሚቻልበት ፈጣን አማራጭ የትኛው እንደሆነ መምከሩ ሳይሆን አይቀርም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ የለውጡ ደጋፊ ህዝብ “እርቅና ይቅርታ” ጥሩ ነው ከሚለው የካህን ስብከት በተጨማሪ ይቅርታና እርቁ በተግባር ሊመጣ እሚችልበትና ይህን እልቂት ሊያስቀር ካልሆነም ሊቀንስ እሚቻልበትን መንገድ ሊያመላክቱ የሚገባቸው ይመስለኛል። እሳት በበዛበት አገር ነዳጅና ጋዝ ማውጣት ጥሩ ቢሆንም እድገት እንደተመልካቹ ልብና ቅንነት ነውና አንዱ ለልማት አንዱ ለክብሪት እሚመኘው ጋዝ እንዳይሆን ያሰጋል። እናንተ ምን ትላላችሁ?

Filed in: Amharic