>
5:13 pm - Friday April 19, 2520

‘የሞት መድኃኒት’ የሚምሰው ህወሃት (መስከረም አበራ)

ህወሃት የተባለው ብልጣብልጥ ፓርቲ ኢህአዴግ በሚባለው መጋረጃ ተከልሎ የልቡን ሲሰራ እንደኖረ አያነጋግርም፡፡ኢህአዴግ በሚባለው ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ አጋር ሆኑ አባል ፓርቲዎችም ህወሃት የሚተርከው የአስራ ሰባት አመት ጠመንጃ ነክሶ ዱር የማደር ታሪክ የላቸውምና የተጋዳላዮቹን ወንበር ከመሸከም የዘለለ ተግባር አልነበራቸውም፡፡ ፓርቲው አድራጊ ፈጣሪ ሌሎቹ አቤት ባይ ተላላኪ ሆነው የኖሩበት ዘመን ህወሃት በጎ ሊሰራ የተዘጋጀ ፓርቲ ቢሆን ኖሮ ብዙ እድሎች ነበሩት፡፡ሆኖም ህወሃት ለበጎ አልተተከለምና በጎ ሊያፈራ አልቻለም፡፡ አሁን ሞቱን እያፋጠነለት ያለውም የራሱ የእበልጣለሁ ባይነት አካሄድ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡በሰለጠነ የእኩልነት  ዘመን ‘እኔ እና ቤቴ ብቻ እንግዛችሁ’ ማለት ሩቅ የሚያስኬድ ሃሳብ አይደለም፡፡ እንደውም እንዲህ ያለ ውዳቂ ሃሳብ ይዞ እስካሁን እንዴት ቆየ የሚለው ነው ማስገረም ያለበት፡፡

መናገርን እንጅ መነጋገርን የማያውቀው ህወሃት አንቅሮ ያስተፋው የማሰር፣ የመደብደብ፣ የመርገጥ ዘይቤውን ከጀግንነት የሚቆጥር ነውር ጌጡ ፓርቲ ነው፡፡ህዝብ እንደ አይኑ ብሌን የሚያያቸውን የነፃነት ታጋዮቹን በሰንሰለት አስሮ ሲስቅ ሲሳለቅ  ጉልበታምነቱን ማሳየቱ ነው እንጅ ወድቀህ ተነሳ የሚለው የሚያሳጣ ውርደቱ እንደሆነ አያገናዝብም፡፡ የሚያስተዳድሩትን ህዝብ በር ዘግተው የተሳደቡ ጋጠ ወጦችን እሹሩሩ እያለ ከህዝብ ጋር ተራ ብሽሽቅ ውስጥ ኖሯል፡፡ ‘የሚናገረኝን ልክ አስገባለሁ’ እያለ ሲያወራ ለራስ ልክ መግባት ሊመጣ እንደሚችል ትዝ አይለውም፡፡

ለፍተው ሃብት ያፈሩ ሰዎችን ደን ጨፍጫፊዎች ሲል ስም ለጥፎ ወይ ልዩ ፖሊስ ልኮ እያዳፋ ማፈናቀሉ ስልጣን ላይ የሚያሰነብት ጉብዝናውን ማመሳከሪያው እንጅ አይንህ ላፈር የሚያስብለው እንደሆነ ያስብ ዘንድ ማስተዋል የለውም፡፡ ፋብሪካን ሁሉ “ክተት!” ብሎ በሰፈሩ መትከሉ በናቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የሚያመጣው መጥፎ ነገር ያለ አይመስለውም፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ የሚወደውን ስልጣኑን ሊያሳጣው ከመሰለው እንኳን ከክፋቱ አንድስ እንኳን ከሚያጎድል ይልቅ ከነክፋቱ የሚያኖረው የሞት መድሃኒት ለመማስ ጠመንጃውን ተደግፎ ይፋትራል፡፡ ይሄ ገና ከፅንሰት ውልደቱ የተካነበት ነው፡፡

ህወሃት እንደ ተወለደ እንዳይሞት መድሃኒት አድርጎ የወሰደው ኢትዮጵያዊ ሃይሎችን ከትግራይ ምድር ማጥፋት ነው፡፡ ኢህአፓን፣ኢዲዩን መሰል በፓርቲ ደረጃ የተደራጁትን ቀርቶ በግለሰብ ደረጃ ኢትዮጵያዊነታቸውን አስቀድመው በሚፈልገው የትግራዊነት ጠባብ ቀረጢት ያልገቡለትን ትግሬዎች ሲያሳድድ እንደኖረ ብዙ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ቀጣዩ የሞት መድሃኒት በማሌሊት ምስረታ ስም ርጋፊ የዲሞክራሲ አመለካከት ያላቸውን በህወሃት ውስጥ ያሉ ታጋዮችን መግደል ወይ ማሰደድ ነበር፡፡ ኢህዴን የተባለውን ገባር ድርጅት አንጉቶ መጋገሩ ደግሞ ጉና ተራራ ላይ ጭቃ ሆኖ ከመቅረት አትርፎታል፤ ኮሳሳ የመንደር ፓርቲነቱን አስረስቶ ‘እልፍ  እንሆናለን’ ሲል አዘምሮታል፡፡ ቀጥሎ እልፍ አእላፍ መሆን ሲያምረው ኦህዴድ እና ደኢህዴን የተባሉትን የኢህዴን ቢጤ ፓርቲዎች ጠፍጥፎ የአዲስ አበባው ወንበሩ እንዲደላደል አደረገ፡፡ ከዛም በኦነግ እጅ እግር ገብቶ የሽግግር ወቅቷን ቅዝምዝም ካለፈ በሁዋላ ውለታ ቢስነቱን በሚመጥን ሁኔታ የክፉቀን ጓዶቹን በሌጣ ፓስፓርት ወደ አትላንቲክ ማዶ አሻገረ፡፡

ቀጣዩ ገዳይ በሽታ የህወሃት የቤት ጣጣ (ህንሽፍሽፍ) ነበር፡፡ ይሄው ውስጥ ለውስጥ ሲብሰለሰል የኖረው የቤታቤት እርግጫ፣የዘመድ ጠብ መንስኤው ለጌታ ሻዕብያ የመታዘዝ እና ያለመታዘዝ፣ የትግራዊነት እና የኤርትራዊነት ዘር ከልጓም የመጎተት ነገር እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ነገሩ ለኢትዮጵያ ከማሰብ የተነሳ ቢሆን ኖሮ ይህ ስንጥቃት መነሳት የነበረበት አንድ አይሉ ሁለት ወደብ ተመርቆ የተሸኘ ጊዜ ነበር፡፡ ይሄው የጦፈ የዘመድ ጠብ ቦናፓርቲዝም፣መበስበስ እና መጠንባት በሚባል ማስታገሻ መድሃኒት ገለል ከተደረገ በሁዋላ ሰላም ሆነ፡፡

እንዲህ እንዲህ እያለ ያወፈራት ነፍሱ ክፉ ተግዳሮት የገጠማት በ1997ቱ ምርጫ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ሁሌ ሲደነግጥ እንደሚያደርገው ገደለ፣አሰረ፣አሰደደና ከድንጋጤው መለስ ሲል እንደልማዱ የሞት መድሃኒት መማስ ጀመረ፡፡ልማት የሚባል ነፍስ አድን መድሃኒት አገኘ፡፡ልማታዊ መንግስት የሚባል ሙዚቃ ሰርቶ አውራ ፓርቲ በሚባል ዜማ አጅቦ እድሜውን ቀጠለ፡፡ አውራ ነኝ ሲል ሌላው ይዋጥለት አይዋጥለት የህወሃት ጉዳይ አይደለም፡፡ የእርሱ ጉዳይ የሚባል ነገር ማግኘቱ ብቻ ነው፤ይህ የማይዋጥለት “ይዝለል” ወይ “በሊማሊሞ ያቋርጥ”!

እውነት የሌለው አካል መበርገግ ልማዱ ነውና በአንደበቱ አውራ ነኝ የሚለው ፓርቲ  በመግሪብ ሃገሮች በተደረገው የአረብ ፀደይ አብዮት መደናገጥ ጀመረ፡፡ ሙአምር ጋዳፊ መሞታቸው ሲሰማ እሱን እሱን መስለውት መብረክረክ ጀመረ፡፡ ይህን አብዮት በክፉም በደግም ያነሳ ሁሉ ወደ ማይሞላው እስርቤት ተጋዘ፡፡ እስክንድር ነጋ፣አንዱአለም አራጌ፣ርዕዮት አለሙ ሁሉ በዚሁ ድንጋጤ የታሰሩ ሰዎች ነበሩ፡፡

አስሮም ማረፍ የለም! አሁንም የሞት መድሃኒት ያስፈልጋል- የአባይ ግድብ የሚባል ፍቱን መድሃኒት ተገኘ፡፡ ይህ መድሃኒት የተፈራውን የአረብ አመፅ  ከማስቀረት ባለፈ ብዙ ጥቅም ነበረው፡፡ መለስ ዜናዊ በመከበሩ ላይ መመለክ ጨመረለት፣መለስ ሲጨንቀው ያመጣውን “አባይ አባይ” የሚል ዜማ አጅቦ ያላጨበጨበ ሁሉ የሃገር ጠላት ተደረገ፣ግድቡን የጀመሩት እነሱው ሳይጨርሱት ከስልጣን መውረድ የማይታሰብ ተደርጎ ተደሰኮረ፡፡ስለ አረብ የፀደይ አብዮት ከማውራት ይልቅ የቦንድ ግዥ ሽያጩ ነገር ተጧጧፈ፡፡ አነቃቂው እስክንድር ነጋም የእስር ቤት በር ተከረቼመበት፤የአረብ አብዮት ስጋት ከእስክንድር ጋር እንደታሰረ እርግጠኛ የሆኑ ገዥዎች ሃገር ሰላም ብለው ቀጥቅጦ በመግዛታቸው ቀጠሉ፡፡

እንዲህ ለፓርቲያቸው እና ለወንበራቸው የሞት መድሃኒት ሲምሱ የኖሩት አቶ መለስ ዜናዊ ለራሳቸው የታዘዘውን ሞት ማምለጥ አልቻሉምና ላይመጡ ቢሄዱም ስማቸው የሞት መድሃኒት ሆኖ ማገልገሉ አልቀረም -“የመለስ ራዕይ” የሚለው የሞት መድኃኒት እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ መለስ ከሞቱ በሁዋላ ጓዶቻቸው አንድ ወር ሙሉ ሬሳቸውን አጋድመው ለቅሷቸውን ለማሳመር የተለፋው የለቅሶውን ፊልም የመለስ ራዕይ በሚል ዜማ አጅበው፣የፈረደበትን አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን አስቀድመው የህወሃትን እድሜ ለማርዘም ነው፡፡ግራ እንደገባቸው ጀምረው ግራ እንደገባቸው  የጨረሱትን አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በወንበራቸው ላይ በነበሩበትም ሆነ በቃኝ ብለው ወንበራቸውን ካስረከቡ በኋላ በህወሃት ነፍስ ላይ ያንዣበበው የሞት ጆፌ ግን እንደ ወትሮው በቀላሉ ማስ ማስ ተደርጎ መድሃኒቱ የሚገኝ  አይመስልም፡፡

አቶ ኃ/ማርያም በአቶ መለስ ወንጀለኛ ወንበር እንደተቀመጡ ይህ ነው የሚባል ችግር ሳይገጥማቸው ወደ ሶስት አመት ያህል አሳልፈዋ፡፡ከሁለት አመት ወዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ የገባበት ኮስተር ያለ ትግል በአዛዥ ታዛዥ ድራማ የደቆውን ኢህአዴግን ጓዳ ለማናጋት ጭምር አቅም የተረፈው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ህወሃት ስልጣን ላይ ለመወዘት ከጠመንጃው እኩል የሚመካው በኢህአዴግ ውስጥ በነበረው የህወሃትን የበላይነት በመቀበል ላይ በቆመ እኩልነት አልቦ ውስጠ-ፓርቲ “አንድነቱ” ነበር፡፡ ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡

እኩልነት አልቦ አንድነትን እንደትክክለኛ መርህ ተቀብሎ ሃያ ሰባት አመት የቆየው ካድሬም ሆነ በሰለጠነ ዘመን የሰው አናት ላይ ፊጥ ብየ እኖራለሁ ባዩ ህወሃት አርቆ ማሰብ የተሳናቸው እንደሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ህወሃት የበላይነቱን የሚያፀናው ለአባል እና አጋር ካድሬዎቹ የትጥቅ ትግል ገድሉን  እስኪያቅራቸው እየተረከ ነው፡፡ የዛሬ ስንት አመት የተደረገ ወንድምን የመግደል ታሪክ ዘር ማንዘርን በኢትዮጵያ አናት ላይ ሁሉ አስፍሮ ሁልጊዜ ለመግዛት  የይለፍ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሄ ነገር በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው ገናድሮ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሃገሪቱ ሰፊ ህዝብ ህወሃትን አያሳየኝ የሚለው፡፡ ዛሬን ለየት የሚያደርገው በመቀየራቸው ተስፋ የቆረጥንባቸው፣ህወሃትም በሎሌነታቸው ተማምኖባቸው የኖረው የእህት ፓርቲ ካድሬዎች ከባርነት ማምለጫው መንገድ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል መቀላቀል መሆኑ ዘግይቶም ቢሆን ተገልፆላቸው“ህወሃት ሁሌ የሚመለክ አምላክ አይደለም!” ማለት መጀመራቸው ነው፡፡

ይህ ጣኦት የማፍረስ ድፍረት የተማመነው የኢትዮጵያን ህዝብ ክንድ ነው፡፡ህወሃት የፈለገውን ያህል የሞት መድሃኒት ፍለጋ ጋራ ጋራውን ቢዞር እንደ ድሮው መድሃኒቱን ማግኘት ቀላል የማይሆንለት ለዚህ ነው፡፡ ህወሃት ከፍ ባለ ወንበር ተቀምጦ ሲያፈርስ ሲሰራ የኖረበት “ቤተ-መቅደስ” ተከፍቶ “መጋረጃው ተቀዷል፡፡” ምስጢሩ የእበልጣለሁ ባይነት የቤታቤት ህግ አደባባይ ወጥቷል፣ቀን ከፍቷል፣አሽከር አንጓጧል፣በተኮሱት ጥይት ልክ ስልጣን ላይ የመወዘፍ አምሮት መሳቂያ ሆኗል፡፡ ይህን ሁሉ አርጀቶ አስተሳሰብ እንደተሸከሙ ከሞት ለመዳን የሚማስ መድሃኒት ፈውስ አያመጣም፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ አምርሯል፡፡

የህዝብን ትግል መከታ አድርገው የህወሃትን ቤት የባርነት ሰንሰለት ለመበጠስ የሞከሩት ኦህዴድ እና ብአዴን ለወትሮው ህወሃት እነሱን እያጋጨ ለእኩይ መንገዱ ብርሃን የሚፈጥርባው ሁለት ባልጩቶቹ ነበሩ፡፡እየተፋጩ ለጌታ ብርሃን ሲፈጥሩ የነበሩት ሁለቱ “ባልጩቶች” ይህን ያህል አመት ሳያስቡት የኖሩት በአንድ የመቆም ጥበብ ድንገት ተገልፆላቸው ተፋጭተው ለጌታ ብርሃን በመፍጠሩ ቦታ በጌታቸው አናት ላይ ቢወድቁ ፈንክተው መጣል እንደሚችሉ ስለተረዱ የህዝቡን ትግል ተመክተው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ይህ እንደ እኔ የኢህአዴግን ካድሬ ለማመመን ለሚቸገር እውነትነቱ ቢያጠራጥርም አንዳንድ አሳማኝ  ምልክቶች ታይተዋልና እየተጠነቀቁም ቢሆን ማመኑ አይከፋም፡፡

ህወሃት ግን የመጣበትን ያመነ አይመስልም፡፡ከሰሞኑ ያወጣው እጅ እግር አልቦ መግለጫ የሚያሳየው ህወሃት የበላይነቱን እንጅ ሌላ የማይሻ፣እኩልነት ሞት የሚመስለው፣ሞቱን ደግሞ ዝም ብሎ የማይሞት ይልቅስ በማንኛውም ቀዳዳየሞት መድኃኒት ከመማስ የማይመለስ ፓርቲ እንደሆነ ነው፡፡ መግለጫው እውነት የሌለበት ስለሆነ ጣዕም አልቦ፣ጭብጥ የሌለው፣አሰልች፣ እንደ ተለመደው ይሉኝታ ቢስ፣ተስፋ መቁረጥ የሚስተዋልበት፣ተንኮልም የማያጣው ነው፡፡

በ “ሀ” እና “ለ” የተከፈለው አሰልች መግለጫ መላልሰው ቢያነቡት እንኳን ጠብ የሚል ቁምነገር ለማግኘት ያዳግታል፡፡  በ ፊደል  “ሀ” ስር የተቀመጡ ሃሳቦች ህወሃት አባል ሆኖ በወሰናቸው ጉዳዮች ላይ እንዳላየ እንዳልሰማ የውጭ ሰው የሚቃጣቸው ሃሳቦችን ያጨቀ ግራ አጋቢ ነው፡፡   በተራ ቁጥር አራት ላይ  የተቀመጠው የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ለባሃብቶች የመሸጥ ጉዳይን አመልክቶ የሰፈረው ሃሳብ በድርጅቶቹ መሸጥ ላይ ህወሃት ያለውን ስምምነት ገልፆ  አጥብቆ የሚያነሳው የሽያጩን አፈፃፀም በተመለከተ ነው፡፡ የሽያጩ አፈፃፀም ህወሃትን አጥብቆ የወዘወዘው ለምንድን ነው? ‘አፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ፣ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመራችንንም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን አለበት’ የሚለው ውትወታ ምስጢሩ መመርመር አለበት፡፡

በተለይ የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመራችንን በማይጎዳ መንገድ ማለት ኢፈርትን የመሰሉ የልማት ድርጅቶች በሽያጭ ግዥው ውስጥ ፊታውራሪ እንዲሆኑ ዳርዳር የማለት ጉዳይ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን አይቻለም፡፡ በተለይ ህወሃት ከዚህ ቀደም በፕራይቬታይዜሽን ስም የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት እንዴት የነስየ አብረሃ ቤተ-ዘመድ ጥሪት እንዳስደረገ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ከሁለት አመት በፊት የጠይቱ ሆቴልን መቃጠል አስምመልክቶ ባሰፈረው ፅሁፍ በጥሩ ሁኔታ ገልፆት ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ዳዊት በወቅቱ ጉዳዩን አስመልክቶ በመረጃ የተደገፈ መከራከሪያ በመፃፉ ‘የስየን ክብር ነካህ’ ተብሎ ዘብጥያ እንደወረደ ከሁለት ሶስት ቀን በፊትም ፅፎ አስነብቦናል፡፡

እንዲህ በልጅ አመካኝቶ አንጉቶ መብላት የለመደው ህወሃት ዛሬ አፈፃፀም ላይ አተኩሮ የቁራ ጩኽት ሲያበዛ በመንግስት ስም ሻጭ፣በኢፈርት ስም ገዥ ሆኖ በለመደው መንገድ ለመቅረብ ፈልጎ እንደሆነ መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ አብረው ሰልቀው በፈጩት ነገር ላይ ወደ መቀሌ ተጉዞ እንደ አዲስ ማሳሰቢያ ማብዛት ከዚህ ሌላ አላማ ሊኖረው አይችልም፡፡ ምናልባት የጩኽቱ ብርታት ዛሬ ከማስተናበሩ ወንበር ገለል በማለታቸው የጠ/ሚ/ር አብይ መንግስት ደግሞ እንደልባቸው ሻጭም፣ገዥም፣ደላላም የሚሆኑበትን በር ስለዘጋባቸው ሊሆን ይችላል፡፡

በተራ ቁጥር አምስት እና ስድስት ላይ የተቀመጡት ሃሳቦች ከተራቁጥር አራትም ሆነ እርስ በእራሳቸው ያላቸው ልዩነት ግልፅ ባይሆንም በተለያዩ ቁጥሮች መቀመጣቸው ብዙ ስህተት የተሰራ ለማስመሰል፣ጩኽት የማበርከት አካሄድ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ የሆነ ሆኖ ከተራ ቁጥር 5-6 የተቀመጡት ሃሳቦች ሲጠቃለሉ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከፊል ሽያጭ ጉዳይም ሆነ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበርን በተመለከተ የፍርድቤቱን ውሳኔ የመቀበሉ እና የማስፈፀሙ ነገር አስመልክቶ ከመፈፀሙ በፊት የኢህአዴግ ምክርቤት፣አጋር ድርጅቶች እና የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመክርበት ይገባል የሚል ነው፡፡ ይህ አባባል  ህወሃትን ግምት ውስጥ የሚጥሉ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ነጥቦችን ይዟል፡፡

እንደሚታወቀው ሞት ብቻ ከስልጣን ያወረዳቸው፣ህወሃቶች እንደ አምላክ ሊቆጥሯቸው ምንም የማይቀራቸው አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣን ላይ በቆዩበት ዘመን ሁሉ በርካታ ትልልቅ ሃገራዊ ጉዳዮችን ሲወስኑ የአጋር ድርጅቶችንም ሆነ የኢህአዴግ ምክርቤትን አማክረው የኢትዮጵያን ህዝብ አወያይተው ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ሁለት ወደብ የነበራትን ሃገር ወደብ አልቦ የሚያደርግ ውሳኔ ሲሰጡ የኢትዮጵያን ህዝብ አማክረው፣ህዝቡ ተስማምቶበት አልነበረም፡፡ከኤርትራ ጋር የነበራቸው ሽርክና ወደ መሸካከር ሲቀየር የኢትዮ-ኤርትራን ግጭት በተመለከተ ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ሲሰልቁ የነበሩት ህወሃቶች ብቻ እንደነበሩ አቶ ገብሩ አስራት በመፅሃፋቸው ገልፀዋል፡፡ ያኔ ህወሃቶች ዛሬ ያወጡትን አይነት መግለጫ አውጥተው የኢትዮጵያ ህዝብ ይምከርበት አላሉም፡፡ ህወሃቶች በአቶ መለስ መሪነት በራቸውን ዘግተው ሲመካከሩ እንደነበረ የታወቀው እንኳን ከስንት አመት በኋላ ተሰንጣቂ ህወሃቶች አኩርፈው ከወጡ በኋላ በፃፉት መፅሃፍ ነው፡፡ በኋላም የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ይግባኝ እቀበላለሁ ሲሉ ‘የሚመለከተውን ክፍል አማክር እንጅ’ አልተባሉም፡፡

በሌላ በኩል አቶ መለስ በ1997 ህዝብን ስምንት አመት ሙሉ ወደ አደባባይ ወጥቶ እንዳይተነፍስ ያደረገ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻቸውን ያወጁ ሰው ነበሩ፡፡ ይህን ሲያደርጉ የኢህአዴግ ምክርቤት ይጠራ አልተባለም፡፡ የአባይ ግድብን ከሰማይ ዱብ ሲያደርጉ፣ ቁርሱን ሳይበላ ግድቡን መስሪያ ብር አዋጣ የተባለውን ህዝብ አማክረው አልነበረም፡፡ብቻቸውን ህዝብ አክለው ይሄን ሁሉ ነገር በክንዳቸው ብርታት ብቻ ሲያደርጉ የኖሩት አቶ መለስ አምባገነንነታቸው፣እብሪተኛ ፈላጭ ቆራጭነታቸው ከጀግንነት ተቆጥሮላቸው ኖረዋል፤ሲሞቱም የጉብዝናቸው ሙሾ ሆኖ ሰምተነዋል፡፡ የመለስን አምባገነንነት እንደ መመኪያ ሲቆጥር የኖረው ህወሃት ታዲያ ዛሬ የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚ ተሰብስበው ህወሃቶች ራሳቸው በነበሩበት የተላለፉ ውሳኔዎችን ጥፋት ያላቸው አድርጎ ማቅረብ አስተዛዛቢ እና የማያድን የሞት መድኃኒት የመማስ ግን ደግሞ ሞትን የሚያፋጥን ሙከራ ነው፡፡

“አጋር ድርጅቶች ይመርምሩት፣ይወያዩበት” የሚለው አባባል ህወሃት ያንጓጠጡትን የኦህዴድን እና የብአዴንን እርምጃ ለመግታት ነገሬ ብሏቸው የማያውቃቸውን አጋር ድርጅቶችን መጠቀም እንደፈለገ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ የእነዚህ አጋር ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋርም ሆነ በሃገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው መስተጋብር ሁሌ የሚገርመኝ እና መልስ ያላገኘሁለት ግራ አጋቢ ነገር ነው፡፡አንድ አጋጣሚ ለማስታዎስ ያህል የእነዚህ አጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ኢህአዴግ ስንተኛ ጉባኤውን ባህርዳር ላይ ሲያካሂድ ከሱዳኑ SLM እና ከቻይናው CCP ፓርቲዎች እኩል ወረፋ ተይዞላቸው ንግግር ሲያደርጉ ስመለከት በጣም እንደገረመኝም እንዳዘንኩም አስታውሳለሁ፡፡

ከዚህ ቀደም ያደረገውን ሳይሆን ዛሬ የፈለገውን ብቻ የሚያሰላው ህወሃት ታዲያ በውህደት ስም አለያም ግንባሩ እንዳለ ‘የአባል ድርጅቶች ቁጥር መጨመር አለበት፣ አጋር ድርጅቶች አባል የሚያደርጋቸውን አቅም ገንብተዋል’ የሚል የፕሮፖጋንዳ ከበሮ ደልቆ አጋር ብሎ ሲያርቃቸው የነበሩትን ፓርቲዎች አባል አድርጎ ወደግንባሩ አስገብቶ አሽከር ቢሄድ አሽከር ይተካል በሚል በቀደመ የአለቅነት ወንበሩ ለመቀመጥ እያሴረ እንደሆነ ያስጠረጥራል፡፡

ይህ ነገር ለለውጥ ፈላጊዎቹ የኦህዴድ እና ብአዴን አባላት ፈተና መጋረጡ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አጋር ፓርቲዎች የኢህአዴግን ፕሮግራም እያስፈፀሙ ግን ደግሞ አባል ፓርቲዎች ያሏቸው በጠ/ሚ/ርነት ወንበር መቀመጥን ጨምሮ ብዙ መብቶችን ተነፍገው መኖራቸው እንዴትም አድርገው ቢያስቡት ልክ አይደለም፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት መሲህ ነኝ ባዩ ኢህአዴግ እንዲህ ያለ አግላይነትን ሲያጧጡፍ አጋር ፓርቲዎችን ተጠቅሞ የፈለገውን መስራቱንም ያላቆመ ግፈኛ ፓርቲ ነው፡፡ ‘መቶ ፐርሰንት አሸነፍኩ ማለትህ  ልክ አይደለም፤እውነት ሊሆን የሚችልም አይደለም’ ሲባል ‘እኔ ሰማኒያውን ብቻ ነው ያሸነፍኩት ቀሪው ሃያው የአጋር ድርጅቶች ነው’ እያለ ሲፈልግ ሲያርቃቸው ሲያሻው ደግሞ በፓርላማ እጃቸውን እያስወጣ የፈለገውን ለመስራት በስማቸው ሲነግድ ኖሯል፡፡ ይሄ ትልቅ ግፍ ነው!

የእነዚህ አጋር ተብየ ፓርቲዎች ካድሬዎች ራሳቸው እንዲህ ያለውን ሁለተኝነት ተቀብለው ይህን ያህል አመት እንዲቀመጡ ያደረጋቸው አፍዝ አደንግዝ ምጢርም አስገራሚ ነው፡፡ እንደ ኢሶዴፓ ያሉት ፓርቲዎች እንደውም ዘዋሪው ህወሃት ከወከለው ህዝብ ብዛት  የበለጠ የህዝብ የወከልን ነን የሚሉ መሆኑ ነገሩን የባሰ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ የሆነ ሆኖ የፈለገውን ነገር በፈለገው ሰኣት መዞ ‘እኔ ልባስ’ የሚለው ህወሃት ራሱ የደወረውን የእነዚህን አጋር ፓርቲዎች በደል እንደ አዲስ አነሳስቶ በዚህ አጣብቂኝ ሰዓት ለራሱ ጥቅም ሊጠቀምበት እንዳሰበ ነው ከመግለጫው መረዳት የሚቻለው፡፡ ይህን መቀበሉም አለመቀበሉም ለጠ/ሚ/አብይ ፈተና ነው፡፡

ፓርቲዎቹን በአባልነት መቀበሉ ተገቢ እንደውም የዘገየ ነገር ቢሆንም አሁን መሆኑ ደግሞ ችግር አለው፡፡ የአጋሮቹ አባል መሆን (ቀድሞ ህወሃት ፓርቲዎቹን ከጎኑ ለማሰለፍ የሰራው ስራ ስለማይጠፋ) ብአዴን፣ህወሃት እና ከፊል ደኢህዴን የህወሃትን በላይነት በብዙሃን ድምፅ የሚገዳደሩበትን አካሄድ የሚፈታተን ሊሆን ይችላል፡፡ ጠ/ሚ/ር አብይ የሚመሩት ቡድን ይህን ፍራቻ በግልፅ አባልነታቸውን አልቀበልም ካለ ደግሞ የብሄረሰቦችን እኩልነት ባለመቀበል በሃፍረተ-ቢሱ ህወሃት ሊከሰስ ይችላል፡፡

መውጫው መንገድ ቀኑ ከመድረሱ በፊት ከአጋር ፓርዎቹ አመራሮች እና ካድሬዎች ጋር መነጋገር ያዋጣል፡፡ ፓርቲዎቹን ለማግባባት በሚደረገው ጥረት ላይ ህወሃት ራሱ ሲያገላቸው የኖረውን ፓርቲዎች ዛሬ ለምን ፈለጋቸው የሚለው ነጥብ ላይ አጥብቆ መስራት ፓርቲዎቹ ታሪካዊ ስህተት ከመስራት የሚታደጋቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ ይረዳል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ፓርቲዎቹ አባል የመሆን መብት እንዳላቸው ነገር ግን ጊዜው አሁን እንዳልሆነ ጭምር አብሮ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም ግንባሩ አጋር ፓርቲዎችን አባል የማድረጉን ስራ በሩጫ ማድረግ ስለሌለበት ወደ ተግባር ከመኬዱ በፊት ይህንኑ የሚያዝ የፓርቲ ህገ-ደምብ መርቀቅ እንዳለበት መከራከር አጋር ፓርቲዎቹን ለማናገሩም ሆነ ለማሳመኑ በቂ ጊዜ ለመግዛት ያመቻል፡፡ አጋር ፓርቲዎቹም አውቀው ካልተኙ በቀር የነገሩ ልብ አይጠፋቸውምና ከሚጠፉ ጋር ከማበር ይልቅ ከሚለሙት ጋር መወገኑን በመምረጥ ከስህተት መቆጠብ አለባቸው፡፡

በፊደል “ለ” ከተቀመጡት ትርጉም አልቦ ሃሳቦች ውስጥ በተራ ቁጥር ሁለት የተቀመጠው ህወሃት ለወደፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለማድረግ የሰነቀውን ስንቅ የሚያስረዱ ሃሳቦች መሽገዋል፡፡ ይህ ሃሳብ ህወሃት ምን ያህል ከህዝብ ጋር መግባባት የማይችል ፓርቲ እንደሆነ የሚያሳይ ነገር አለ፡፡ በዚህ ተራቁጥር የተቀመጠው ሃሳብ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እየወደደው ያለውን የጠ/ሚ/ር አብይ ጅምር እርምጃ ራሱን የልማት እና የዲሞክራሲ አለቃ አድርጎ ሾሞ የጨረሰው ህወሃት የጥገኞች ስራ አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ያለው ትግል በጥገኞች(የለውጥ ሃይሎች) እና በዲሞክራት/ልማታዊያን (ህወሃቶች እና የህወሃት የቤተ-ዘመድ ልማት ተጠቃሚዎች) መሃከል የሚደረግ ትግል አድርጎ ወስዶ ‘የልማታችን ተጠቃሚዎች ሁሉ ትግላችንን ተቀላቀሉ’ አይነት ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ ህወሃት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥሩ ነገር ሰንቆ የማያውቅ ፓርቲ ቢሆንም ይህኛው ስንቅ ግን አደገኛ ይመስላል እና በአንክሮ መታየት ያለበት ነገር ነው፡፡

ነገሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ህወሃት አሁንም መሳሪያው ታቅፎ ያለ እንጅ እኛ እንደምናስበው ልጡ የተማሰ ሬሳ አለመሆኑ ነው፡፡ ህወሃት የልማቱ ተጠቃሚ፣የልማታዊ ዲሞክራሲ ሰልፈኛ አድርጎ ጥሪ የሚያቀርብላቸው አብዛኞቹ ሰዎች በውትድርናው እና በደህንነቱ የተሰገሰጉ፣ ብረት ከትከሻቸው ያላወረዱ፣ዘረኝነት ብቻ የሚነዳቸው ሰዎች ናቸው፡፡ከመንግስት መዋቅሩ በዘለለም የታጠቁ ግን ደግሞ ከህወሃት መዋቅር ውስጥ በገሃድ የሌሉ  ነገር ግን ህወሃት የተገፈተረ ሲመስላቸው አነር የሚሆኑ ኤርሚያስ ለገሰ በሁለተኛው መፅሃፉ “ዲሞቢላይዝድ ካድሬዎች” የሚላቸው ሰዎችም የዚሁ ጥሪ ታዳሚዎች እንደሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ በዚህ ላይ በአንድ ሳምንት ቱጃር የሆኑ የልማት ተጠቃሚ ተብየዎችም በገንዘባቸው እንደሚደግፉ መታመን አለበት፡፡ እነዚህ አካላት በናፍቆት የምንጠብቀውን የኢትዮጵያ ደህና ቀን የማጨለም አቅም እንደማያጡ ማሰብ እንጅ ህወሃት አልቆላታል ብሎ መዝናናቱ መጥፎ አደጋ ይኖረዋል፡፡

በተራ ቁጥር አራት የተቀመጠው ነባር አባሎቻችንን ሽልሙልን የሚለው አይነ-ደረቅ አካሄድ ደግሞ እነሱ ለፃፉት አንባቢን የሚያሳፍር ነው፡፡ የትኛው የህወሃት አንጋፋ አባል ለየትኛው በጎ ተግባሩ እውቅና ሊሰጠው እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም፡፡ በየደረሱበት ኢትዮጵያን እና ህዝቧን መሳደብ፣ክብር ማጉደል፣ የሃገር ጥቅም አሳልፎ መስጠት፣የአንድ ሃገር ህዝቦችን ጠላት እና ወዳጅ አድርጎ አቧድኖ ማናከስ ፍርድቤት ይገትር ይሆና እንጅ የሚያሸልም ነገር አይደለም፡፡

መስከረም አበራ | June 26, 2018
Filed in: Amharic