>

የመስዋእት በጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ!!! (ሰይፍአርድ አምደጽዮን)

የመስዋእት በጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ!!!
ሰይፍአርድ አምደጽዮን
ታላልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያልቸው ሴራዎች የሚውጠነጠኑትም ሆነ የጥፋት እርምጃዎች የሚተገበሩት የስርአቱ የቤት ልጅ የሆኑት ሶስቱ ተቋማት:-
– ፌደራል ፖሊስ የስም ወንጀል መከላከል በተግባር ግን የወንጀል ማምረቻ ሀይል
– የቢሔራዊ መረጃና ደህንነት ፈንጅ አምካኝ እና አጥማጅ የልዩ ጥበቃ ዋና መምሪያ 
– የአጋዚ ኮማንዶ ቀይ ቤሪ መለዮ ለባሽ ተደራቢ ሀይል !!!
ሰኔ 16 2010 ዓ/ም ቅዳሜ በመዲናችን አ/አ ከተፈፀመው የቦንብ ፍንዳታ ጋር በተገናኘ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነርን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት የፖሊስ ኮሚሽኑ የስራ ሀላፊዎች የፌስቡክ ጏደኛችን ዘውዴ ታደሰ ባወጣው መረጃ መሰረት:-
1. ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ:
2. ኮማንደር ገብረኪዳን፣
3. ኮማንደር ገብረሥላሴ፣
4. ኮማንደር ግርማዬ በርሄ፣
5. ኮማንደር አንተነህ፣
6. ምክትል ኮማንደር አባቡ ዳምጤ፣
7. ኮማንደር ገመቹ ታፈረ፣
8. ምክትል ኮማንደር አብዲሳ ባይሳ፣
9. ምክትል ኢንስፔክተር ነገሪ ፈይሳ:
10. ዋና ሳጅን ከድር ዓሊ የተባሉ ተጠርጣሪዎች
ከአዲስአበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ያትታል::
እኔ ደግሞ ከነዚህ ውስጥ የምጠረጥረውን እጠረጥራለሁ:: ነገር ግን ለ27 አመት በምናውቀው ልምድ እንኳን ለርዕሰ መንግስት (head of government) ይቅርና ለተራ ባለስልጣን በሚደረግ የጥበቃ አገልግሎት እና የጥበቃ ሽፋን የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት አስተዋፅኦ ምንጊዜም የተደራቢነት አገልግሎት ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው የጥበቃ አገልግሎት ሽፋን ሲያደርጉ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም!!!
የመጀመሪያ ሙሉ የጥበቃ ሀላፊነት የሚወስደው:
1. ለስም እና ለበጀት ድልድልና አገልግሎት በፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን ስር የተደራጀው በሀቅ እና በተግባር ግን የፈለገውን: ህጋዊ ወይም ኢህጋዊ: መልዓካዊ ወይም ሰይጣናዊ: ቅዱስ ተግባር ወይም የእርኩሰት ተግባር: የማቀድ: የማድረግ ወይም ያለማድረግ: የመፈፀም ወይም ያለመፈፀም: የመተው ወይም ያለመተው አይነኬ የአድራጊ ፈጣሪነት ስልጣን ያለው በተግባር ግን በእነግርማይ ማንጁስ ወይም በተክላይ ፀሀይ የሚመራው የስም ወንጀል መከላከል የሚባለው በተግባር ግን /የወንጀል ማምረቻ ሀይል/ ተቋም እና በስሩ በተኮለኮሉ ወፈሰማይ የጊዜው ሰዎች አማካኝነት ነው!!!
2. በሁለተኛ ደረጃ ሲቪል ለባሽ በሆኑ የቢሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አካል የሆነው ፈንጅ አምካኝ እና አጥማጅ የልዩ ጥበቃ ዋና መምሪያ ሰራተኞች: የሀገር ውስጥ ደህንነት ዋና መምሪያ ጊሪሳ ስውር ታጣቂ ሀይል: በጥምር በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት ሲሰራ የኖረና የነበረ ነው!!!
3. ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱን ሀይሎች ጨምሮ በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት የአጋዚ ኮማንዶ የአዲስ አበባ ተጠባባቂ ሁሌ ዝግጁ (standby) ሀይል ቀይ ቤሪ መለዮ ለባሽ ተደራቢ ሀይል እንደአስፈላጊነቱ የቅርብ ሽፋን እና እገዛ ያደርግለታል!!!
4. አዲስ አበባ ፖሊስ የሚታዘዘው ለይስሙላ ከትጥቅ ነፃ ሆኖ በዩኒፎርም በአራተኛ ረድፍ ላይ ቢበዛ ዱላ ይዞ ሀይል ለማሳየት(show of force) የፀጥታ ሀይል ቁጥር ብዛት ለማሳየት እና ከመጀመሪያ የጥበቃ ሪንግ ወይም ቀለበት ሲለካ የመጨረሻ ዙር ከማህብረሰብ ተሳትፎ ያልዘለለ የመጨረሻው ረድፍ ምንጊዜም ከወያኒያዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ መስመር አንፃር የማይታመን የተገለለ ሀይል ሆኖ ሲያበቃ የፍተሻ ስራ እና የእጀባ አገልግሎት ብቻ ዱላ ይዞ የደንብ ልብስ ወይም የፖሊስ ዩኒፎርም ለብሶ ስራውን የሚያከናውን መሳሪያ ከያዘም በበቂ እርቀት በመኪና ፓትሮል ውስጥ እና አካባቢ ብቻ እንዲቀመጥ ሲደረግ የኖረ ሀይል ነው:: መሳሪያ ከያዘም ከመስቀል አደባባይ ቁልፍ የጥበቃ ስራ እርቆ ለእለትተለት የወንጀል መከላከል ስራ ማከናወኛ የፖሊስ ፓትሮል መኪና ወይም በፓትሮል የፖሊስ ሾፌር የሚያዝ ሽጉጥ ወይም በመኪናው ላይ በሚመደቡ ተወርዋዎች የሚያዝ AKM 47 የነብስ ወከፍ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከመሰል 30 ጥይት ጋር ብቻ የሚይዙ ሲሆን በተለይ በማታው ክፍለ ጊዜ የተለመደ የወንጀል መከላከል ስራ የሚሰሩበት ነው:: በእጀባ ሰአት ግን በተለይ የሀገር መሪ VVIP( Very Very Important Person) ከሆነ ለመስቀል አደባባይ የእጀባና የጥበቃ ቁልፍ ተግባርና ስራ የሚመደቡት በእርቀት መተላለፊያ መስመሮችን በመዝጋት የእገዛ ስራ:-
* ኦሎፒያ: ሙሉሸዋ: ደንበል አካባቢ: * መሿለኪያ አራተኛ ክፍለጦር ሪቼ አካባቢ: * ቡናና ሻይ ሜክሲኮ አካባቢ: * ሰንጋተራ ኮሜርስ በእድሉ ህንፃ አካባቢ: * ኢትዮጵያ ሆቴል ቢሔራዊ ቲያትር: * አምባሳደር ቲያትር አካባቢ: * ካሳንቺስ ሱፐር ማርኬት አካባቢ: * አስመራ መንገድ ሳልኮስት መግቢያ: * ባንቢስ ድልድይ ዮርዳኖስ ሆቴል አካባቢ የሚያጠቃልል ሆኖ በዚህ ራዲየስ ክልል የመግቢያ በሮችን በመዝጋት ቁጥጥር እና ክትትል ወይም የይስሙላ ጥበቃ ያደርጋሉ: ይህ ሁሉ ከጫካ አለመምጣት: የከተማ ልጅ መሆን: ህዛባዊ ሀገራዊ ቢሔራዊ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ያለው መሆን ጋር በተያያዘ እና ስርዓቱ ወይም መንግስት የማይወደው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የ27 አመት የሊቀሰይጣን ወያኔ ክፋት ጋር የተቆራኘ ጎጂ ልማዳዊ ኢፕሮፌሽናል ድርጊት ነው!!!
ከዚህ ውጭ ከልዩ ሀይል ወይም ወንጀል መከላከል በጣምራ ወይም በተናጠል በሚሰጠው የስራ ግዳጅ ማለትም ድንገተኛ እና ያልታቀዱ ወይም የታቀዱ እና የተለመዱ በሰውና በተሽከርካሪ ላይ የሚደረጉ የፍተሻ ስራዎችን ብቻ በጣምራ እንዲሰራ ያደርጋሉ::
የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትም ደስ ብሏቸው የሚሰሩት ከትክክለኛ የፖሊስ ሙያ ጋር የተገናኘው  ዋና ሚና በእለትተለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚፈፀሙ ደረቅ ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝም በ1949 ዓ/ም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና ስነስርዓት ህግ መሰረት አሁን ደግሞ በ1996 ዓ/ም የወንጀል ህግና የስነስርዓት ህጉ ያው የ1949 ዓ/ም ስነስርዓት ህግ ነው ለብቻ አልወጣለትም እና በዛ መሰረት ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃዎችን ከወንጀል ስፍራ(crime scene) በሚሰበሰቡ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ የተፈፀመን የወንጀል ተግባር ወይም ድርጊት ምርመራ አጣርቶ መዝገብ አደራጅቶ ለአቃቢ ህግ መላክ ነው::
በነገራችን ላይ በፖለቲካ ጉዳይ የሚያዙ ሰዎች እዛው ፌደራል ወንጀል ምርመራ ዋና መምሪያ እነታደሰ መሰረት እና ግበረበላዎቹ የሚወጡት ተግባር ነበር:: የአዲስ አበባ ፖሊስ አይታመንም ነበር ሚስጥር ያወጣብናል ለሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር አለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃ ያወጣብናል ያስተላልፋል ብለው ስለሚያስቡ እና ሰራዊቱም በእንዲህ ያለ ጉዳይ ውስጥ የመግባት ፍላጎት ፈፅሞ አልነበረውም!!!
እርግጥ ነው ከ1997 ዓ/ም ምርጫ በሗላ በተወሰነ ደረጃ በጣምራ ተጠያቂ ለማድረግ ያለትጥቅ ነገር ግን ያለፍላጎቱ እየጎመዘዘው እንዲሳተፍና ማኖ ለማስነካት በከፍተኛ ተፅኖ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል:: ሆኖም ያንን ሁሉ እኩይ ተግባራቸውን ተቋቁሞ ነገሮች ወደነበሩበት ከተመለሱ እና ከተረጋጋ በሗላ statuesque ante maintain) ከተደረገ በሗላ የአዲስ አበባ ፖሊስ የስርዓቱን የአፈና እና የጭካኔ ተግባር በዝምታና በፀጥታ አላለፈውም:: እንዲያውም አዋጅ ቁ. 313/1996 ዓ/ም የወጣውን በገዛ ፈቃድ ከሰራዊቱ ስራን ስለመልቀቅ የሚደነግገውን አዋጅ በመጠቀም ተቋሙን አብዛኛው ሆብሎ ለቆ ወጥቷል::
በአንድ ቀን ከ60-80 እጅግ የሰለጠነ ከፍተኛ ልምድ ያለው እና መሰረታዊ በቂ ሊባል የሚችል እውቀት ያለው ሀይል ይብራብኝ እያለ ለሙያውና ለሀገሩ እንባ እየተናነቀው ስውር ውታደራዊ ሰላምታ እየሰጠ ለቆ ወጥቶ ሲሄድ ጉድ የተባለ ታሪክ ሲሆን በምትኩ ለስርዓቱ ውርደትና አንገት አስደፊ ተግባር ነበር!!!
ይህ አስደናቂ እና አስገራሚ ክስተት ተቋሙን ለቆ ለሄደው ሰራዊት መሳሪያ በስርዓቱ ላይ ከማዞር ያልተናነሰ የወገኑን ህመም የህዝቡን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ድፍጠጣ ቁጭት የተወጣበት ታላቅ አኩሪ ተግባር ነበር!!!
ይህ ተግባር የተፈፀመው ሊቀሰይጣን ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ግንቦት 20, 1983 ዓ/ም በሗላ ከ1984 – 1998 ዓ/ም በተለያየ ጊዜ ከ1ኛ ኮርስ – 9ኛ ኮርስ ከአዲስ አበባ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተመልምለው: በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ሰልጥነው: በፖሊስ ስራ ላይ የነበሩ ሲሆን: የስርዓቱ ታማኞች እና ምንደኛ ሀይሎች በአ/አ ህዝብ ላይ በቅንጅት የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመበቀል በህዝብ ላይ የፈፀሙትን አይን ያወጣ ጭፍጨፋና ግፍ እጅግ ያሳዘናቸው እና ያበሳጨቸው በመሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በወቅቱ ከነበረው 6500 (ስድስት ሺህ አምስት መቶ) የማይበልጥ የሰው ሀይል ከ1998-1999 ዓ/ም ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሰራዊት የሚወደውን ሙያ በመተው ለሀገሩና ለህዝቡ በሚሰራበት አፍላ የወጣትነት እድሜ ለህዝብና ለሀገር ሲል ስራውን ለቅቆ ወጥቷል!!!
ከዚህ ውስጥ ዛሬ የት እንዳሉ በትክክል ባላውቅም ከኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ በተለያየ ጊዜ ከፍተኛ የፖሊስ ሳይንስ እና አካዳሚክ ትምህርት የተማሩ ሲኒየር መኮንኖችና በተለይም የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ 33ኛ መደበኛ ኮርስ ተመራቂ ታምረኛ አይበገሬ ስርአቱ ጥርስ የነከሰባቸው ወጣት እሳት የበሉ መኮንኖች በስራ እና የሙያ ግዴታቸውን በመወጣት ዕረገድ እንዲሁም በህዝብ ወገንተኝነት: በሀገር ፍቅር: በሙያ ክብር ተምሳሌት: በሰራዊቱ ሞዴልና ተወዳጅ የነበሩ: ከህዝቡ አብራክ የወጡ ወጣት የአዲስ አበባ ፖሊስ መኮንኖች በከፍተኛ ብስጭት እና ቁጭት ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ በራሳቸው ፍላጎት ማንም ሳያስገድዳቸው የአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን የአመራር ስራቸውን ለቀው የወጡ ይገኙበታል!!!
ወደአነሳነው ዋና ጉዳይ ስንመለስ ምንም እንኳን የስርአቱ ውሃ ጥማት አምልኮት የነበረባቸው ጥቂት ታጋይ የሚባሉ ሀይሎች አዲስ አበባ ፖሊስ ውስጥ የነበሩ ቢሆንም ሚናቸው በብዙሃኑ የሰራዊቱ አባላት: በህዝባዊ ሀገራዊ: ቢሔራዊ: ኢትዮጵያዊ: አመለካከት ባላቸው ሙያቸውን: ደንብና መመሪያ: ህግና ስነስርዓቱን አክብረው በሚሰሩ ሀይሎች የተዋጡና እዚህ ግባ የሚባሉ አልነበረም:: ተፅኗቸውም ከባድ እና አሳሳቢ አልነበረም!!!
ሆኖም ከ2000 ዓ/ም በሗላ የስርዓቱ ደጋፊ ሀይል በተወሰነ ደረጃ ከፍ እንዳለ መገመት ይቻላል:: ለምን ቢባል እስከ 1998 ዓ/ም ድረስ የነበረው የመደበኛ ፖሊስ ምልመላ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ከአዲስ አበባ ብቻ መሆኑ ቀርቶ አ/አ የፌደራል መንግስት መቀመጫ ስለሆነች ከሁሉም ክልል ይመልመል በሚል አናሎጂ ምልመላና ስልጠናው መፈፀሙ ነው!!!
ከ1997 ዓ/ም ምርጫ በሗላ የሰራዊቱን ማዕበላዊ መልቀቅ ተከትሎ ሚያዚያ 1998 ዓ/ም ከተካሄደው በአንድ ጊዜ 3250 ሰው ከፌደራል ክልሎች በሚል ሽፋን ትግራይ: ቤኒሻንጉል: ጋምቤላ: ደቡብ ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ እንደነገሩ ለይምሰል አማራና ኦሮሞ ቀላቅለው በዘመቻና በማባበል በማታለል መልምሎ ሁርሶ መከላከያ ጦር ማሰልጠኛ በትውስት ወስዶ ለ3 ወር ብቻ ሰልጥኖ ተመርቆ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ሲመደብ ከዚህ ውስጥ ለአ/አ ከአዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ እንደፌደራል ፖሊስ ከሁሉም ክልሎች እንዲመለመል ተደርጎ ሰልጥኖ ተመርቆ ሲመደብ አ/አ 250 ሰው 25% ብቻ ማለትም ከአሉት 10 ክፍለ ከተሞች እያንዳንዳቸው 25 ሰው ብቻ እንዲመለምሉና እንዲያቀርቡ በኮታ ተሰጠ::
ለምን ሲባል አዲስ አበባ ሳሩም ቅጠሉም ቅንጅት ነው ስርዓቱን አይደግፍም የአመለካከት ችግር አለበት ለዛ ነው 100% በምርጫው የተሸነፍነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ:: ህዝባዊነት ኢትዮጵያዊነት አመለካከት ከያዝክ ለእነሱ ህመምና ስቃይ ነው!!!
ወደጥበቃ እና እጀባ ስራው ዋና አጀንዳችን ስንመለስ ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በአላት:- ጥምቀት እና ደመራ አረፋና መውሊድ በአላት ጥበቃ ካልሆነ በስተቀር የስርአቱ ባለስልጣናት የሚገኙበት ማንኛውም ቀላልና ከባድ ዝግጅት የውጭ መሪዎች ወደሀገር ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ: ለገሰ ዜናዊ ለጉብኝት እና ለስራ ሲወጣና ሲገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መሳሪያ ይዞ ከ800-1000 ሜትር እርቀት ውስጥ እንዲገባ ወይም እንዲንቀሳቀስ አይፈለግም:: ከገባም ዱላ ይዞ ከሆነ በፌድራል ፖሊስ የአይነቁራኛ ጥበቃና ቁጥጥር እየተደረገበት የእጅ ፍተሻ ስራ እና እገዛ በጣምራ እንዲያደርግላቸው ብቻ ይደረጋል!!!
በተረፈ ለሾው ኦፍ ፎርስ ይጠቀሙበታል!!!
ሲጠቃለል የቅዳሜው አሳፋሪ እጅግ እጅግ አሳዛኝ የቦንብ ፍንዳታ እና አደጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ለወደፊት ትምህርት የሚወሰድበት በዛው ልክ ሀገርን ህዝብን የዶክተር አብይን የለውጥ ማራኪ አስተዳደር ከቀጣይ አደጋ ለመታደግ እጅግ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ ተግባር መሆኑን እየጠቆምኩ የማጣራቱ ስራ ግን አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዳይሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስጋት አለኝ!!!
ለምን ቢባል የ27 አመቱ የሊቀሰይጣን ወያኔ የጭካኔ አስተዳደር ባህሪን ጥንቅቅ አርጎ እንደሚያውቅ ሰው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ወይም የወንጀል ማምረቻ ሀይል በተለይ አመራሩ በአለፉት ዘመናት አዛዥ ናዛዥ እራሱ መንግስት አድራጊ ፈጣሪ እና በአብዛኛው የትምህርት የእውቀት ፎቢያ ያለባቸው በጫካ ወለድ በሽታ ቫይረስ ተይዘው የሚሰቃዩ እጅግ አደገኛ ጥቅመኞች በሀብትም እረገድ ወደ ቡርዣነት ማማ የወጡ የከበርቴ በዝባዥ ሀይሎች ጥርቅም ስለሆነ እና ስልጣን ብቻ ሳይሆን በዘረፋና በምዝበራ የገነቡትን ሀብት እንደሚያጡት ስለሚያስቡ እና ስለሚገምቱ ነው!!!
የሚፈፀመው ሴራ ወለድ ጥቃትም ስውር በማስመሰል ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከባድ ሀገር እና ህዝብ አጥፊ በሰው ህይወትና አካል: በንብረትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይም አውዳሚ ውጤት የሚያስከትል ተግባር ነው!!!
በአዲስ አበባ ፖሊስ ውስጥም በነበረው የአዛዥ ናዛዥነት ሚናው የራሱ ታማኝ ሴል ያለው ሆኖ በማንኛውም ሰአት ለቲናንሽ አፍራሽ ተልዕኮ ሊጠቀምበት ቢችልም እንኳን በእራሱ ለራሱ ለዘመናት በገነባው ከባድ ሀይል የሚመካ እና የሚመፃደቅ ሴራወለድ የጭካኔ የጥፋት ክህሎቱን  አግዝፎ የሚያይ:-
 “እኛ የምንሰራውማ ሞሳድ እንኳ አይሰራውም”
እያለ መመፃደቅ የሚያበዛ እጅግ ግብዝ የአንድ ነገድ ሀይል ነው!!!
ይህ የወንጀል ማምረቻ ሀይል እጅግ ማሽንክ እና ጨካኝ በሆኑ ሀይሎች ከታች እስከ ላይ የተደራጀ በመሆኑ ጊዜ ሳይባክን ማስረጃዎችም ሳይበላሹ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ፀረለውጥ ሀይሎች ሳይሰወሩ ወይም ሳያመልጡ እና ሌላ ተጨማሪ የከፋ እኩይ ድርጊት ሳይፈፅሙ ምርመራው በአስቸኳይ እዛ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል እላለሁ!!!
ቸር ይግጠመን እግዚአብሔር እውነቱን ያውጣው!!!
Filed in: Amharic