>
5:13 pm - Thursday April 20, 5511

የባድመ ጉዳይ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

የባድመ ጉዳይ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

የባድመ ጉዳይ ምንጩ የኤርትራ መገንጠል ነው፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ጎደሎ ሆነች፤ ኢትዮጵያም ጎዶሎ ሆነች፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጎዶሎነት አንዱ ሌላውን የመፈለግ የተፈጥሮ ግዴታን አመጣ፤ ለሁለት የተከፈለ አንድ ባሕርይ ዘለዓለም ሲፈላለግ ይኖራል፤ ችግሩ ከሰዎቹ ነው፤ የባድመ ጉዳይ የሁለት ጎዶሎ አገሮች አንዱ ሕመም ነው፤መቼ ተጀመረ?

አንዳንድ ሰዎች ስለአልጄርስ ስምምነት ሲገልጹ የመንደር ስምምነት ያስመስሉታል፤ አንደኛ ስምምነቱ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ስር በተባበሩት መንግሥታት የመቋቋሚያ ሰነድ አንቀጽ 102 መሠረት ነው፤ ዋናው አደራጅ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ሆኖ የተከናወነው በተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ነበር፡፡

ሁለተኛ ለስብሰባው በእማኝነት የተገኙትና የፈረሙት የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊዎች፣ የአልጂርያ ፕሬዚደንት፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው፤ እንግዲህ እንደዚህ ያሉ ከባድ ከባድ እማኖች ተሰልፈውበት በዓለምአቀፍ መድረክ ላይ የተፈጸመን ስምምነት አሌ ማለት እንዴት ይቻላል? ከተቻለም ሙሶሊንን ወይም ሂትለርን መሆን ነው፡፡ 

ወያኔ/ኢሕአዴግ ኤርትራን ለማስገንጠል በሚዘጋጅበት ጊዜ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተቃውሞ ሰልፍ ወጥተው ነበር፤ በ,ያኔ ኢሰብአዊ የጭካኔ ጭፍጨፋ ሰልፉ ተቋረጠ፤ እንግዲህ በኤርትራና በባድመ ጉዳይ ውሳኔዎች በሚሰጡበት ዘመን ትንፋሹን ውጦ እስከዛሬ የቆየ ሕዝብ ዛሬ ከየት ፈልቶ ነው ተቃውሞ የሚያሰማው? ለነገሩ ከአለመኖር ወደመኖር መምጣት ሁሌም የሚያስደስት ነው፤ ትናንት የፈራ ዛሬ ቢደፍርም አያስከፋም፤ ታዝቦ ማለፍ ነው፡፡

Filed in: Amharic