>
5:13 pm - Sunday April 19, 3429

አሸባሪው ህወሃት (መስፍን ማሞ ተሰማ)

አሸባሪው ህወሃት!

መስፍን ማሞ ተሰማ 

“ዘረኛ ከሆንክ የዓለማችን ርካሽ ሰው አንተ ነህ” ሠኔ 16 ቀን (ዕለተ ትንሣኤ) 2010 ዓ/ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድንና የባልደረቦቹን የለውጥ እርምጃ ለማመስገንና ለመደገፍ በሚሊዮን የሚቆጠረው ህዝብ በመስቀል አደባባይ ይዞ ከወጣቸው መልዕክቶች መካከል አንዱ።

“…መግደል መሸነፍ ነው። መግደል መዋረድ ነው። በደስታ አንድ ሆኖ ሀገሬን የሚልን ህዝብ በራሱ ዜጋ ሠዎች አቅዶ አስቦ እንዲጨነግፍ መሥራት ትንሽነት ነው። ኢትዮጵያውያን ግን ትንሽ አይደለንም። ትልቅ ህዝቦች ነን። ከትንንሾች ጋር ወርደን ትንሽ አንሆንም። ይህንን ቀን ደስታችንን ለማጨለም፤ ፍቅራችንን ለማጨለም፤ አንድነታችንን ለማደፍረስ ያሰባችሁ ሃይሎች አልተሳካላችሁም።…ትላንት አልተሳካላችሁም። ዛሬ አልተሳካላችሁም። ነገም አይሳካላችሁም…”  ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ ሠኔ 16/2010 ዓ/ም በእርሱና በባልደረቦቹ የተጀመረውን ለውጥ በማመስገንና በመደገፍ በመስቀል አደባባይ ለተገኘው በሚሊዮን ለሚቆጠር ህዝብ ንግግር ካደረገ በሁዋላ በአሸባሪዎች ከተሰነዘረበት የቦንብ ጥቃት ተርፎ በዛው ዕለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ካስተላለፈው መልዕክት የተወሰደ።

************************************************************************

እናንተ ህወሃቶች በሞት ጣዕር ላይ የምትገኙ አሸባሪዎች ናችሁ። እናንተ የመደመርና የአብሮነት ሳይሆን የመቀናነስና የመገነጣጠል ሣጥናዔላዊ ልብና ደም የተገጠመላችሁ ዘረኞች ናችሁ። ቅድመ ግንቦት 83ን እንኳን ብንተው ከድህረ ግንቦት 83 እስከ ሠኔ 16/2010 ዓ/ም ከተከዜ በታች እስከ ሞያሌ ከጋምቤላ ጥግ እስከ ሀረር ቀንድ ስንትና ስንት ኢትዮጵያውያንን ፈጃችሁ?

ስንትና ስንት እናቶችን ማቅ አስለበሳችሁ? ስንትና ስንት አባወራዎችን እንደወጡ አስቀራችሁ? ስንትና ስንት ህፃናትን ወላጅ አልባ አደረጋችሁ? ስንትና ስንት ወጣቶችን ገረፋችሁ? ጨለማ ቤት አኖራችሁ? አኮላሻችሁ? ደብዛቸውን አጠፋችሁ? የእናንተ የአሸባሪው ህወሃት ወንጀል እስከ ወዲያኛው ትውልድ ድረስ ገና ይፃፋል።

ሀገርንና ህዝብን በመንግሥትነት ተደራጅቶ የሚሰርቅና የሚገድል በዓለም መንግሥታት ዘፍጥረት ታሪክ ከናንተ ከህወሃት ሌላ አልነበረም፤ የለም፤ አይኖርምም። ህወሃት ማለት የበቀል የርኩሰት የክፋት የጥፋት የሴራ የምቀኝነት የሌብነትና የዘረኝነት – መገለጫና ትርጉም ማለት ነው።

እናንተ ህወሃት በተባለው የሽብር ‘ኢንኩቤተር’ የተቀፈቀፋችሁ ‘የጫጨ’ ህሊና ያላችሁ በሙሶሎኒ ፋሽስታዊ መንፈስ የምትኖሩ የክፍለ ዘመኑ ዘረኞችና ክፉ ሰዎች ናችሁ። በህወሃታዊው አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተለከፉት ህወሃት ያልሆኑ ህወሃታውያን ደግሞ  የዘራፊዎችና የሌቦች የገዳዮችና የሽብርተኞች ቅጥረኞችና አገልጋዮች ናቸው። በደቡብ፤ በጋምቤላ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ፤ በኦሮምያ፤ በሶማሊ፤ በሐረሪ፤ በአፋር፤ በአማራ ህዝብ መኻል የተተከሉ የኢትዮጵያ አረሞች። አረሞቹን ስንመነግልና ከስራቸው ስንነቅል እናንተ – ህወሃት እንደ ስብስብ ትመክናላችሁ። የእናንተ የህወሃት መምከን ደግሞ ለኢትዮጵያ ሠላምንና ፍቅርን፤ አብሮነትንና መደመርን ያሰፍናል፤ ኢትዮጵያዊነትን ያነግሣል!!

እናንተ ለኢትዮጵያ ውጋት እንጂ ትንፋሽ አይደላችሁም። እናንተ ኢትዮጵያዊነት ሲዘመር ኢትዮጵያዊነት ከፍ ሲል ዛራችሁ ይነሳል። ታብዳላችሁ።  ደም ይናፍቃችዃል። ኢትዮጵያ ለእናንተ – ለህወሃት – ላሜ ቦራ እንጂ እናት ሀገር አይደለችም። ስታልቧትና ስታደርቋት እርካታንና ሣጥናዔላው ሀሴትን ታገኛላችሁና። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሲደሰቱና ሲደመሩ ደምስሮቻችሁ ይቆማሉ፤ ዓይኖቻችሁ ይቀላሉ፤ እጆቻችሁ ይገድላሉ።

ደደቢት ላይ በልባችሁ የተተከለው የርኩሰት ደዌ በዘመን ሂደት እየመዘመዘ እነሆ ከመቃብራችሁ አፋፍ ደርሳችሗል፤ በጣዕረ ሞት ተይዛችሗል። እርግጥ ነው መቃብራችሁ ከተቆፈረ ሰንብቷል። የተጠናቀቀው ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ/ም የጆሮዎቻችሁን ታንቡሮች በታትኖ በትናንሽ ጭንቅላቶቻችሁ ውስጥ እንደ ነጎድጓድ ባስተጋባው የኢትዮጵያዊነት ደወል ነበር፤ እኛ ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን – በሚለው በአእላፍ ኢትዮጵያውያን መሥዋዕትነትና በአብይ ፆም ፀሎት ባገኘነው ሙሴያችን አብይ መሪያችን አንደበት በምክር ቤት አዳራሽ ሲያስተጋባ!!

ከዚህ ወቅት ጀምሮ ለየላችሁ። ትንሽነታችሁ ይበልጥ አነሰ። ድውይ አስተሳሰባችሁ ይበልጥ ድውይ ሆነ። ጡረተኛና አኩራፊ ደደቢቶች ከነምልምል ሎሌዎቻችሁ ተጠራርታችሁ መቀሌ ላይ ለሙሾና ለሴራ ተቀመጣችሁ።

ገዳዮች ሌቦችና ሀገር ሻጮች ሁላ አብይ መሲሃችንን አብይ መሪያችንን አብይ ሙሴያችንን ለመግደል ስትዶልቱ ከረማችሁ። የከንቱዎች ስብስብ ከንቱ ሴራ! አብይን ገድላችሁ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንን ልትሾሙብን ነበር የዶለታችሁት? ያሰባችሁት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ግን ማዕበሉ መቀሌ በምን ቅፅበት እንደደረሰ ሳታውቁት ይጠራርጋችሁ ነበር!!!

ሠኔ 16 ቀን 2010 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ አብያችንን ለመግደል የወረወራችሁት/ያስወረወራችሁት ቦንብ ስለምን እንደከሸፈ ታውቃላችሁ?  ዕለቱ ከመሲሁ አብያችን ጎን ቆመን ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ቃል የገባንበትና የምህረትም ኪዳን ያደረግንበት ቀን በመሆኑ – ዕለተ ኪዳነ ምህረት! የኢትዮጵያ አምላክ በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ የሠፈነበት ዕለት በመሆኑ። የርኩሳንን እና የክፉ ሰዎችን ጦር ማምከኛው ቀን በመሆኑ! ሕዝቤን ልቀቁት ያለው ሙሴያችን አብይ የዕለቱን ምስባክ ሲጀምርልን ‘ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይባርክ’ በማለቱ። ይኸው ነው ምሥጡሩ፤ የፈጣሪ ተዓምሩ፤ የአብይ መዳን ትርጉሙ፤ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ይፋ የመሆኑ!!

እንግዲህ የደደቢት ህወሃትና አሸርጋጆቹ ህወሃታውያን ሁሉ እነሆ ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን እንነግራችሗለን። ከዚህ ወዲህ የመቃብር ስፍራ የማግኘታችሁን ነገር ተጨነቁበት እንጂ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የመግዣና የመግደያ ጊዜያችሁ ማክተሙን እወቁ!!! የገዳዩና የዘራፊው የዘረኛውና የከፋፋዩ የሌባውና የሀገር ሻጩ የህወሃት የበላይነትና የአምባገነንነት ዘመን ከእንግዲህ አይመለስም!! በእናንተው ጣልያናዊ ቋንቋ…አዲዮስ!!!

እኛ ግን፤

ሠኔ 16 በሞታችንና በደማችን ሙሴያችንን አብይን ታድገናል።

ሠኔ 16 በሞታችንና በደማችን የኢትዮጵያን ትንሳኤ በአደባባይ አብስረናል።

ሠኔ 16 በሞታችንና በደማችን የእናንተን የህወሃትንና ህወሃታውያንን ትንሽነትን እኩይነትንና ሽንፈትን አሳይተናል። መጪው ዘመን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን የፍቅር የሠላም የመደመር የይቅርታና የትንሣኤ ዘመን መሆኑን እነሆ ከአብይ መሪያችን ጋር ሆነን አውጀናል።

አብያችን ሆይ! የኢትዮጵያ አምላክ እንኳንም ለሀገርህ ለኢትዮጵያ  ለህዝብህ ለኢትዮጵያውያን ለልጆችህ ለባለቤትህና ለወዳጅ ቤተሰቦችህ ሲል ከቀን ጅቦች መንጋጋ አተረፈህ!

እናንት በአብያችን ዙሪያ ወገባችሁን አጥብቃችሁ ነገን በመደመር አብያዊ ራዕይ ደፋ ቀና የምትሉ የለውጡ አጋሮችና አራማጆች ከእንግዲህ በንቃትና በብቃት ራሳችሁንም ሆነ አብያችንን ከሚታወቁም ሆነ ከተደበቁ የቀን ጅቦች ጠብቁልን! ከእናንተ አንዱስ ስንኳ ቢጎድል ኢትዮጵያን ትጎዳላችሁና። እናንት በተለይ ከአብያችን ጎን የቆማችሁ የኢትዮጵያ የቁርጥ ወቅት የለውጥ አራማጆች በአብይ መትረፍ እንኳን ደስ አላችሁ! ከእንግዲህ አትዘናጉ፤ ተጠንቀቁ፤ የቀን ጅቦቹንም መንጥሩ!!!

እናንት በደማችሁና በህይወታችሁ ለኛና ለኢትዮጵያ ትንሳዔ መሥዋዕትነት የከፈላችሁ የሠኔ 16 የመስቀል አደባባይ ሠማዕታት ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ እንደሚያበሩት ከዋክብት ትሆናላችሁ! በትውልድ ሁሉ ስትዘከሩም ትኖራላችሁ!

የተሰዉትን ፈጣሪ ነፍሳቸውን ከገነት ያኑርልን!

መፅናናት ለተጎዱትና ለመላው ቤተሰብ ሁሉ ይሁን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይባርክ!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር

ሠኔ 2010 ዓ/ም (ጁን 2018)

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

  

Filed in: Amharic