>

ገዳይ፣ ገራፊዎቻችንም እኛም እኩል ነጻነት ምን ያህል ርቦን እንደነበር ያመላከተች ቀን!!!  (ይልማ ኪዳኔ)

ገዳይ፣ ገራፊዎቻችንም እኛም እኩል ነጻነት ምን ያህል ርቦን እንደነበር ያመላከተች ቀን!!! 
ይልማ ኪዳኔ
ትናንት የመንግስት ተቃዋሚን በአደባባይ እያሳደዱ በዱላ እንደ እባብ አናት አናት ሲሉ የነበሩት የፌደራል ፖሊሶች ጭካኔ እንደ እንሳሳ እንዳያቸው ያደርገኝ ነበር። ከጭካኒያቸው ብዛት የተነሳ ገና ስማቸው ሲጠራ የሰማ ሰውም ይሁን የቤት እንሰሳ እንደ እብድ ይሮጥ ነበር። ይህ ያነሰን ይመስል መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን የሚጠቀምባቸው አጋዚ እያለ የሚጠራቸው ልዩ የሰራዊቱ ኃይል ጭካኔ ደግሞ ለጉድ የሚባል ነበር። አጋዚዎች ጦር ሜዳ ያሉ ይመስል ስንቱን ዜጋ ግንባርና ደረቱ ላይ አልሞ በመተኮስ ብዙ ወጣትና ሕጻናት ሳይቀሩ በመግደል ወላጆቻችንን ሲያስለቅስ የነበረውን ይህን ኃይል የማየው እንደ ጠላት ጦር ነበር። በእነሱ ቤት ዜጋቸው ላይ ሳይሆን የውጭ አሸባሪ ላይ የሚተኩሱ ሳይመስለቸው የቀረ አይመስለኝም። እጅግ በጣም ይገርመኝ የነበረው ነገር ደግሞ ይህን እንዲፈጽሙ መንግስት ሲልካቸው ከሚሄዱበት አካባቢ ነዋሪ ጋር በቋንቋ መግባባት  እንኳን የሚቃታቸውን እየመረጠ ስለነበር ውጭ አገር የዘመቱ ዓይነት ሳይሰማቸው የቀረም አልመሰለኝም። መቼስ ይሄ ድህነት የሚሉት ነገር ያጨካክን ይሆን? መጥናት ያለበት ነገር ይመስለኛል።
ዕድሜ ለጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በአደባባይ መንግስትም አሸባሪ እንደሆነ ተነገራቸው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ግን ፌደራሎቹም፣ አጋዚዎቹም ከህዝቡ ጋር ተደመሩና የሚይዟቸው ዱላዎችና ጠመንጃዎች የት ገቡ እስኪባል ድረስ በእጃቸው ምንም ነገር ሳይዙ ደስታቸውን ከህዝቡ ጋር ሲካፈሉ ማየት እጅግ በጣም ደስ የሚል ነበር። ነገሮች ሁሉ ተገለባበጡና ትናንት ሲያሳድዱት የነበርው ወጣት አብሯቸው ፎቶ ሲነሳና ያ በጣም ሲፈሩት የነበረውን የሴጣን ምልክት የሌለውን ባንዲራ እያከናነበ እስኪበቃቸው ድረስ ፎቶ በፎቶ አደረጋቸው። መቼስ ትናንት የዳቦ ነገር ሆኖባቸው እንጂ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መሆናችንን ዘንግተውት አይደለም። ሰልፉ ላይ ግን የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር እነሱ እኛም እኩል ነጻነቱ ምን ያህል ርቦን እንደነበር ነው። የዚያን ቀን አገሬ ላይ ያይሁትን ዓይነት መደመር በህይወቴ አይቼ አላውቅም። የመደመርን ጥቅም ብናውቅም በተግባር አስፈላጊነቱ የገባን ግን የዚያን ቀን ይመስለኛል። ስንሞት ኢትዮጵያ መሆናችን ካልቀረ በህይወት እያለን ኢትዮጵያዊ ሆነን እንዴት አንደመር። ጉራ አይሁንብኝ እና እንደ እኔ ያለ የሸገር ልጅ መደመር እንጂ መቀነስ የሚባል ነገር መኖሩን ሰምቶም አያውቅ። እንኳን ተደማመርን።
© ይልማ ኪዳኔ
Filed in: Amharic