>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7814

"ዶ/ር አብይ የእሳቸውን ራዕይና አስተሳሰብ የሚያራምድ መዋቅር ከወዲሁ ማደራጀት አለባቸው!!" (መሳይ መኮንን) 

“ዶ/ር አብይ የእሳቸውን ራዕይና አስተሳሰብ የሚያራምድ መዋቅር ከወዲሁ ማደራጀት አለባቸው!!” 
  በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን  
ነገሮች ፍጥነታቸው ይገርማል። እየተደራረቡ እየመጡ ለመጨበጥ እስኪቸግር ሆነውብናል። ኤፍ ቢ አይ ለምርመራ አዲስ አበባ መግባቱ ጮቤ የሚያስረግጥ ዜና ነው። ይህ ዓይነቱ በመንግስት መዋቅር የተፈጸመን የግድያ ሙከራ፡ በኢትዮጵያ መርማሪዎች አቅም የሚቻል አይደለም:: ጥቃቱን የፈፀመው አካል ምርመራውን ማድረጉም ተቀባይነት አይኖረውም:: ደህንነቱና ፌደራል ፖሊሱ ከህወሀት ተጽዕኖ ፈጽሞ ባልተላቀቀበት በዚህን ወቅት እውነተኛ ምርመራ ይደረጋል ብሎ መጠበቅም ጅልነት ነው። የኤፍ ቢ አይ መግባት ለህወሀት ደህነቶች መርዶ ቢሆንም ለውጤቱ ተአማኒነት ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውና እረፍት ይሰጣል።
በቅዳሜው የግድያ ሙከራ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተሰምቷል። እነዘርዓይ ወልደሰንበት የሚመሩት ፍርድ ቤት እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን። ችሎት ተሰይመው በሀሰት ሲፈርዱ የሰነበቱ ዳኞች ሞራላዊ ብቃት እንደማይኖራቸው መታወቅ አለበት። ህወሀት የፍትህ ስርዓቱን መጫወቺያ አድርጎት ቆይቷል። ከእንግዲህ ይህ አሳፋሪ ዘመን ማብቃት አለበት። ፍትህ ስርዓቱ በህወሀት ልክ የተሰፋ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል። የቅዳሜዎቹ ተጠርጣሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በእውነተኛ ዳኞች ይዳኛሉ ብለን እናምናለን።
የሽፍራው ሽጉጤ መልቀቅ የሚጠበቅ ቢሆንም መጨረሻው ከቃሊቲ መሆኑ እስኪረጋገጥ ትክክለኛ እርምጃ ነው ለማለት ጊዜው ገና ነው። ሺፈራው የመለስን ራዕይ በፊርማው በማስፈጸም ጉራፈርዳ ላይ በጭካኔ ባፈናቀላቸው የአማራ ተወላጆች ብቻ ከርቸሌ መግባት የሚገባው ሰው ነው። ሽፈራው በገዛ ውሳኔው ከስልጣን መልቀቁ በራሱ መፈተሽ ያለበት ቢሆንም ዋናው መልቀቁ ነው።
የምክትሉ ሲራጅ ፈርጌሳ ባለበት ይቀጥላል መባሉ ደግሞ አስገራሚ ነገር ነው። ከሽፈራው ሽጉጤ ያልተናነሰ ወንጀል የፈጸመው ሲራጅ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ ይገባው ነበር። በስልጤና ጉራጌ መሀል ለሰራው የጥፋት ተግባር በሚኒስትር ደረጃ ስልጣን የተሰጠው እንደሽልማት ተቆጥሮ እንጂ በብቃቱ እንዳልሆነ ራሱም ያውቀዋል። የሰሞኑ የወልቂጤ ግጭትም የሲራጅ እጅ የተነከረበት እንደሆነ ይታመናል። ሽፈራው ለቆ ሲራጅ የሚቀጥልበት ውሳኔ ጎዶሎ ነው። የወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የደኢህዴን አዲሱ ሊቀመንበር ሆኖ መምጣት አያስደንቅም። ሴትዬዋ እንዳረጓት ናት። አትጎዳም። አትጠቅምም።
በቀደመው ጽሁፌ እንዳልኩት የሶማሌው ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ወይ ወደ አማኑዔል ሆስፒታል አልያም ወደ ቃሊቲ በአስቸኳይ እንዲገባ ማድረጉ ለነገ የሚተው እርምጃ አይደለም። የአፋር ክልል ፕሬዝዳንትም አስቸኳይ እርምጃ የሚፈልግ ሰው ነው። አፋሮች ህወሀት ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ሌላ ሰው እንዳያዩ ተደርገው ከ4ኛ ክፍል መዝለቅ ባልቻለ አቅመ ቢስ ሰው እንዲመሩ የተፈረደባቸው ዘመን ሊያከትም ይገባል። ሰውዬው የአፋር የተፈጥሮ ሀብት በስግብግብ የህወሀት ሰዎች እንዲጋጥ በማድረግ፡ ለአፋሮች የባርነትን ዘመን ያስተዋወቀ፡ ያስቀጠለ ነው። ወደ ከርቸሌ ወርዶ ተገቢውን ፍርድ ሊያገኝ ይገባዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ድርጅት የህወሀቱን ኮሎኔል ማባረሩም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የህወሀት ሰዎች በርስትነት የያዙት የኢጋድ ቦታ ነበር። ኢጋድ የፖለቲካው ንፋስ ወዴት እየነፈሰ መሆኑን ተረድቶ የደረሰበት ውሳኔ ይመስለኛል። መልዕክቱ ግን ትልቅ ነው። ክፈለአሁጉራዊ ተቋማት የህወሀትን አቅም ተረድተው አሰላለፋቸውን ማስተካከላቸው የሚጠበቅ ነው። ዓለም ዓቀፍ ሌሎች ተቋማትም ያለዕውቀታቸውና አቅማቸው በህወሀት ጫና ቦታ የሰጧቸው ሰዎች ካሉም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ይጠበቃሉ። የሚያዋርዱት ሀገርንም ጭምር በመሆኑ ነው።
የግድያው ሙከራ ቢያስደነግጠንም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚታየው የአንድነትና የፍቅር ስሜት ተስፋን ያለመልማል። ከአዲስ አበባ እስከሎሰንጀለስ፡ በውስጥም በውጭም የሚታየው ነገር ልብ ያሞቃል። እሰየው ነው። ይህ ህዝብ በቃው። ጭቆና ትከሻውን አጎበጠው። ስቃይና መከራው ይቋጭ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። እስቲ ትንሽ እፎይ ይበል። ደስታ። ፍቅር። አንድነት። ኢትዮጵያ!!!
ከዶ/ር አብይ ቀጣይ ስትራቴጂ አንጻር የሚሰማኝን ልበል። የቅዳሜውን ዓይነት መሰል ጥቃት ዳግም እንዳይፈጸምና ስጋቱንም የሚቀነሰው በዶ/ር አብይ ውስጥ ያለው ራዕይ ጥልቅ፡ ሀገራዊ ፍቅር፡ የወገን ተቆርቋሪነትና በርካታ የዶ/ሩ መልካም ጎኖች ተቋማዊና መንግስታዊ መልክና ቅርፅ ሲኖሯቸው ነው:: እውነት ለመናገር የእሳቸው አስተሳሰብ ከእሳቸው ሌላ ማን ጋር አለ? የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋ አለ? ካቢኔ ውስጥ አለ? የየክልል መስተዳድሮች ጋ አለ? እሱን መፈተሹ ወሳኝ ነው::
እኔ አብዛኞቹ በመንግስታቸው ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናት የድሮው ስርዓት ናፋቂ ይመስሉኛል:: የድሮው ሲባል የህወሀት አገዛዝ ለማለት ነው። በዶ/ር አብይ ውስጥ የተቀመጠውና መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እየሰጡ ያሉትን ኢትዮጵያዊ ራዕይ ተቀብሎ በዛ ላይ የተሰመረ ስራ ለመፈፀም የተዘጋጁ አይመስለኝም:: ይህ አዲሱ የዶ/ርአብይ አካሄድ ጥቅማቸውን የሚያሰቀርባቸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም ምክንያት አዲሱን ሀገራዊ ራዕይ ከውስጥና ከምር ተቀብለው ያስፈጽማሉ ብዬ አልጠብቅም:: ይልቅስ ህወሀት እነዚህን የሷን ስርዓት ናፋቂ ባለስልጣናትን ተጠቅማ መረበሿን: የቅዳሜው አይነት መሰል ጥቃት ከመጎንጎን ወደ ኋላ እንደማትል መጠርጠሩ አይከፋም።
ዶ/ር አብይ የእሳቸውን ራዕይና አስተሳሰብ የሚሸከም ካቢኔና መዋቅር ከወዲሁ ማደራጀት መጀመር አለባቸው። በእነዚህ በአሮጌው አስተሳሰብ በተለከፉና ወደኃላ በቀሩ ሰዎች ወደፊት መራመድ አይቻልም።
Filed in: Amharic