>

"ለውጡን እንቀበል!" - "ልንፋለመው ይገባል!" በሁለት ጽንፍ የቆመው የመቀሌው ዱለታ!!! (በፍቃዱ ሞረዳ)

“ለውጡን እንቀበል!” – “ልንፋለመው ይገባል!” በሁለት ጽንፍ የቆመው የመቀሌው ዱለታ!!!
በፍቃዱ ሞረዳ
የቀድሞዉ የደህንነት ዋና ባለሥልጣን አቶ ጌታቸዉ አሰፋ (ወዲሻለቃ) ‹‹ ታሰሩ፣ለፖሊስ ቃል ሰጥተዉ ተመለሱ›› የሚል መረጃ በሶሻል ሚዲያ ላይ ሲመላለስ ነበር ዛሬ፡፡ሰዉዬዉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በቅዳሜዉ ሰልፍ ላይ ከታዩ በኋላ ይህ ነገር መሰማቱ ያለምክንያት አይመስልም፡፡ ሰዉዬዉ በእጃቸዉ ያለዉን የመንግሥት ንብረት እንዲያሰረክቡ መታዘዛቸዉ ከታማኝ የቅርብ ምንጮች እየተነገረ ነዉ፡፡ ለጊዜዉ ፈቃደኛ የሆኑ አይመስልም፡፡ ግፋ ቢል ከሦስት ያላነሱ የመንግሥት መኪኖች አላቸዉ አሉ፡፡ መሣሪያንና ሌሎች ለደህንነት ሥራ ይገለገሉበት የነበረዉን መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና ምንነት አናዉቅም፡፡ ‹‹በድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አባልነቴ ጥቅሜ ሊጠበቅ ይገባል ባይ ናቸዉ›› አሉ፡፡ ከሃያ ዓመት በላይ አንድን የመንግሥት ተቋም እንደግል ርስቱ ይዞ ለኖረ ሰዉ ሦስት መኪና ምን አላት ? ጠባቂዎቻቸዉ ተነስተዉ ብቻቸዉን ሲቀሩም የሚሰማዉን ስሜት ማሰብ ነዉ፡፡ ከምቾትና ከክብር ማማ መዉረድን ስንቱ እንዲህ በፀጋ ይቀበላል?
   በተለምዶ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ማንኛዉንም በእጁ ያለዉን የመንግሥት ንብረት እንዲያሰረክብ ሲታዝ ሊከተል የሚችለዉ ነገር ማሰብ ይቻላል፡፡ በአነስተኛ ግምት ለሌላ ሹመት መታጨት ነዉ፡፡ አምባሳደር ዓይነት፡፡ በሰፊ ግምት ደግሞ ቂልንጦ መሄድና በሰፈሩት ቁና መሰፈር፡፡
  ለማንኛዉም ሰዉዬዉ በእምብታቸዉ ከፀኑ የሚከተለዉ ነገር የኃይል እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ እጅ ስጥ፤ አልሰጥም፡፡›› ከዚያም…ይለይለታል፡፡
  የመቀሌዉ ዱለታም ‹‹ለዉጡን እንቀበል፣አብይን እንደግፍ››በሚለዉ ወጣት መሰል ቡድንና  ‹‹ሰዉዬዉ (አብይ) በድርጅቱ ደንብና ሕግ ሳይሆን በሞቭ ፍላጎት እየተመራ ነዉና ልንፋለመዉ ይገባል›› የሚለዉ  የእኔ ብጤ ገትጋታ በታደመበት መሀከል ዙሩ የከረረ ይመስላል፡፡ ‹‹ጊዜ ለመግዛትና እንደገና ለመጠናከር እንዲረዳን እነአብይን እንደግፍ›› ብሎ የሚለዉ ቡድን አምበል ጌታቸዉ ረዳ ሲሆን፣ በወዲያ ወገን ያሉት ደግሞ በአቶ ስብሃትና በስዩም የሚጦዙ ናቸዉ እያሉን ነዉ፡፡
 ለስድብና ለዛቻ ይመቻቸዉ ዘንድ ‹‹ይጠራልን›› ያሉት የኢሕአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባም በሊቀመንበሩ እምቢ ባይነት የተጨናገፈ ይመስላል፡፡ ጠሚዉ ‹‹ አይሆንም!›› ማለት መጀመራቸዉን አመልካች ሳይሆን አልቀረም፡፡
ትልቁ ዉሳኔ ግን የትግራይ ሕዝብ ነዉ፡፡ በአረጀዉ ሕወሓት ጭቆና ሥር መቆየት ፣አለያም ከአዲሱና ከጊዜዉ ሀቅ ጋር ቆሞ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር ለዉጡን መርዳት፡፡ ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነዉ፡፡››
እኛ ግን ለዉጥ ደጋፊ ተጋሩዎች ‹‹አጁኻ!›› እንላለን፡፡
Filed in: Amharic