>

አባይ ጨለማዬን ሰሟኋቸው (ደረጀ ደስታ)

አባይ ጨለማዬን ሰሟኋቸው

ደረጀ ደስታ

አባይ ፀሐዬ እሚባሉ የህወሓት ትልቁ ሰው የተናገሩትን ሰማሁት። የለውጥ ብልጭታውን በአጭሩ “ጤናማ ያልሆነ ሤራ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ተበሎ የተጠነሰሰ ሴራ ነው።” በሚል አጣጥለውታል። የኦሮሞና የአማራው ህብረት የትግራይን ህዝብን ነጥሎ ለመግፋት የተባበረ ኃይል አድርገውም እንደሚያዩትም በገደምዳሜ ገልጸውታል። “ካሁን በፊት ሲጣሉ ነው እምናውቀው አሁን ምን አገናኝቷቸው ነው?” ብለው ጠይቀዋል። እንደሳቸው እምነት አማራውንና ኦሮሞውን እንወክላለን እሚሉ ኃይሎች ፍጹም ወዳጅነት የሌላቸው ነገ በሥልጣን ክፍፍል ሊጣሉ እሚችሉ ኃይሎች እንደሆኑም በድፍረት ገልጸውታል። ኤርትራን ጨምሮ እነዚህ ኃይሎች ለገዛ ህዝባቸው እማይጨነቁ ብቻ ሳይሆን ሲያጠፉት የኖሩ መሆናቸውንም በመግለጽ ወቅሰዋል። ከዚያ ውስጥ ድርጅቶች ለሥልጣን ሲሉ መጣላታቸውና መጠላለፋቸው እውነትነት ያለው መሆኑን መቸም እኛ ከእሳቸው በላይ አናውቅም። ሻዕቢያ ግንቦት ሰባት ኦነግ እያሉ ከነዚህ ኃይላት ጋር ህብረት መፍጠር የማያዛልቅ ወዳጅነት መሆኑን አብራርተዋል። ከነሻዕቢያ ጋር የቃል ህብረት ብቻ ሳይሆን በደም የተከፈለ ህብረት በመፍጠር እሳቸውና ድርጅታቸው የበለጠ ልምድ አላቸውና ተብሎ ተብሎ የተሰለቸ ነገር ነው። የእነሱ ሲሆን ልክ የሌላው ሲሆን ስህተት የመሆኑ ድርቅናቸው መቸም በዘመን እማይለወጥ ዓይን አውጣነት መሆኑን መናገርና መስማታችንም ሰልችቶናል። ከሁሉ ከሁሉ በላይ የሰለቸን ግን የትግራይ ልጅ ያልሆነ ሁሉ የትግራይ ልጅ ጠላት ነው እሚለውና ለዘመናት እንደ ጅረት እሚፈሰው እምነትና ጥርጣሬ ነው። ሌላው ቀርቶ በዚህ ፍቅር አንድነት ከኢትዮጵያዊነትም በላይ አፍሪካዊነት እየተባለ በሚሰበክበት ዘመን ሁሉን ነገር ፀረ ትግራዊነት አድርጎ መመልከት ያልተገላገልነው ጨልምተኝነት ይመስለኛል።

አማራውን ኦሮሞውን ሶማሌውን እየነጠሉ አፋቸውን ሞልተው እሚዘልፉና እሚጠሉ እንዳሉ ሁሉ የትግራይን ህዝብም እንዲሁ እሚጠሉ ሲያበሻቅጡ እሚውሉ የኛም ሠፈር ዋልጌዎች ሞልተዋል። ዓለም ከትግራይ ብቻ እንደተፈጠረች አድርገው እሚያስቡት እንደሞሉ ሁሉ ኦሮሞ ወይም አማራ የሰው ልጅ መገኛ አድርገው እሚያስቡም አሉ። ራስ መውደድንም ሆነ መጥላትን በሞኖፖል የያዘ ጎሰኝነት ያልበቀለበት ማንም ብሔርም ሆነ ጎሳ የለም። ይህ ሀቅ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እምትናገሩት ለአገር እምትመኙት ሁሉ ፀረ ትግራይ ነውና አርፋቸው ተዘግታችሁ ተቀመጡ ማለት ግን እስከመቼ ያዋጣል? ገና ለገና የንዑሳን (ማይኖሪቲ) ስጋት መቸም መኖሩ እማይቀር ነው ብለን እስከመቼ እንጨነቃለን። አንዱን በቁጥር አብዝቶ አንዱን አሳንሶ የፈጠረው አምላክ ሆኖ ሳለ፣ እኛ ላላበዛነውና ላላሳነስነው የህዝብ ቁጥር፣ የሁልጊዜ ተጠያቂና ተጠቂ እምንሆንበት ምክንያቱስ ምንድነው? እንዴ ኦሮሞና አማራ እኮ እንኳን አንድ ላይ ሆነው ለየብቻም ቢሆኑ በቁጥር ብዙ ናቸው፡ በስምምነትም በህገመንግሥትም በኃይልም ወይም በማናቸውም መንገድ እኩል ቁጥር ልናደርጋቸው አንችልም።

ለዚህ መፍትሔው ሁሉም ሰው እኩል እሚሆነበት የዜግነት ሥርዓት እንጂ የብሔር ወይም የቡድን ፖለቲካ ይቁም ብንል አልሰማ ብላችሁ፣ እሱ እሚሆነው በመቃብራችን ላይ ነው ያላችሁት እናንተ ናችሁ። እና ታዲያ ዛሬ በቡድን ፖለቲካ የበዛው ቡድን በዝቶ ቢያጥለቀልቃችሁ በገዛ ጨዋታችሁ እኛን ምን አድርጉን ትሉናላችሁ? ደግሞስ የኦሮሞና አማራ ህብረት የፖለቲካና የሤራ ብቻ ለምን ይመስላችኋል? አማራ እና ኦሮሞ ነን ከሚሉት የተወለድን፣ ደም ያቆራኘን የአባትህና የእናትህ ወገኖች ሲጣሉ ጥግህን ያዝ እሚያሰኘን ሚሊዮኖች እንደሆንስ ለምን አታስቡም? ከናንተስ ቢሆን ስንቱ ትግሬ፣ ትግሬ ካልሆነው ተዋልዷል። ለፖለቲካውም ቢሆን እንኳ ስንት አማራና ኦሮሞ አስራችሁ ስትገርፉ እንደኖራችሁ እስኪ ዞር ብላችሁ አስተውሉ። መቸም ያሰራችሁትን ብትክዱ ከእስር ቤት እንደወንዝ ፈታችሁ የለቃቅችሁትን የሰው ጎርፍ አትክዱንም።
ለብቻችሁ በር ዘግታችሁ ስትሰበሰቡ እምትውሉት ይህን ሐቅ ወዴት ለመቀየር ነው? ሕወሓት በተተቸ ቁጥር የትግራይ ህዝብ የተሰደበ እያደረጋችሁ መናገራችሁ አያዋጣም። የትግራይ ህዝብ ወንድማችን ነው ሞተራችን ነው እሚለው ጥብቅናችንም ቢሆን የአንድ ወገን ብቻ እየሆነ አጸፋው በወዲያም በኩል ካልተሰማ እሚያሳዝን ልብ እሚሰብር መሆኑ አይቀርም። “እኛ እኛ” ማለታችሁ “እናንተ እናንተ እነሱ እነሱ” ማለትን ይወልዳልና በተለይ በዚህ ጊዜ ስለራሳችሁ ብቻ ሌት ተቀን ማውራቱን ቀንሳችሁ ብትደመሩ ጥሩ ነው። ያው መቸም ያለጠላት አትኖሩምና ለጠላቶቻችሁ እምትመቹ ልትሆኑ ትችላላችሁ። አመል ሆኖባችሁ ነው እንጂ እነ ዶ/ር አብይ እኛን የወከሉ ጠላቶቻችሁ አልነበሩም። ለነገሩ እኛም ይወክሉናል አላልንም። እንደግፋቸዋለን ማለትና ይወክሉናል የተለዩ ናቸው። ድጋፋችን እሚወክለን ሥርዓት እንዲመጣ ይረዱናል በሚል ብቻ ነው። ውክልናቸውማ ከኛ ይልቅ ለናንተ ይቀርባል።

ለማንኛውም የደጋፊዎቻቸውን ደካማ ጎን እሚያዉቁት የህወሓቶቹ የእነባይ ጸሐዬ ሤራ ይገባናል። ህወሓት ሲነካ የትግራይ ህዝብ ይቆጣል ስለዚህ እሚነካን የለም እያላችሁ፣ በዚህም ድጋፍ እያገኛችሁ፣ ህዝብና ድርጅት አንድ ነው ወደሚለው ህብረት ከደረሳችሁ፣ እኛም ደካሞች ነንና ከወጥማድችሁ እንወድቃለን። “በቃ አሁንስ ሰለቸን ታዲያ የትግራይስ ህዝብ ራሱስ ቢሆን ወዲያ ቢቀር ምን እንዳይመጣ ነው፣ የምን እሹሩሩ ነው….” ከሚያሰኘን አዘቅት ከወደቅን ተያይዘን እናልቃለን። እንዲህ ሲባል ግን ደግሞ ልብ በሉ፣ በቃ እኛም እምንፈልገው ይህን ተያይዞ ማለቅ ነው እሚለው ሴራ ግን፣ ይፋ ብቻ ሳይሆን ዓላማና ማስፈራሪያ እየሆነ ከመጣ ትልቅ አገር ትልቅ ነውና ሲቀንሱት ቢውሉ አያልቅም። ኢትዮጵያን ያለ – እንኳን ሚሊዮን ሆኖ አንድም ቢሆን ይዟት ይኖራል እንጂ ለኔ ካልሆንሽ ብሎ አይጨርሳትም። እናጫርስ እንጨርሳት እሚሉትንም አይታገሰም። ዋናውን ይዞ በተጠባባቂ አገር እሚጫወት ያሻውን ይጫወት እንጂ አንዲት አገር ብቻ ያለችው በዚያች አንድ አገሩ አይጫወትም። አገራችን አንድ ናት!

Filed in: Amharic