>

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ- ኣስፈጻሚ ኮሚቴ የኣቋም መግለጫ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ- ኣስፈጻሚ ኮሚቴ የኣቋም መግለጫ
Resolutions of the Oromoo Liberation Front
National council
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ ኣስፈጻሚ ኮምቴ የድህረ 4ኛ ጠቅላላ ጉባዔ 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ከሰኔ 9 – 19 ቀን 2018ዓም ኣካሂዶ በስኬትና በድል ኣጠናቋል። የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው በዚህ ስብሰባ የሊቀ-መንበሩን ጽ/ቤትና የየዘርፎቹን ሪፖርት ኣድምጦ ከመገምገሙም በተጨማሪ በስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ዋዜማ በኦሮሞ ምሁራንና በኦነግ ኣመራር መካከል በተካሄደው የፖሊሲ ጉዳዮች የምክክር ኮንፈረንስ (Policy Consultation Conference) ላይም ተወያይቶ ኣስፈላጊውን ውሳኔ ኣሳልፏል። በመቀጠልም በኦሮሞ ህዝብና በኦሮሞ የነጻነት ትግል፣ የኢትዮጵያ ኢምፓዬር  ስርዓት ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በቀጠናችንና የኣለምኣቀፍ ሁኔታዎች ላይ ሰፊና በሳል ትንታኔና ውይይት ኣካሂዶ ከዚህ በታች ያለውን የኣቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባውን ኣጠናቋል።

የኦሮሞን ህዝብና የኦሮሞ የነጻነት ትግልን በተመለከተ

የኦሮሞ ህዝብ በጠመንጃ ኣፈሙዝ የተነፈገውን ነጻነቱን መልሶ በመጎናጸፍ በሃገሩ፡ ኦሮሚያ፡ ላይ እንደህዝብ ያለውን መብት ሙሉ በሙሉ ኣስከብሮ ለመኖር ለዓመታት የነጻነት ትግል ሲያካሄድ ነበር፥ ዛሬም በማካሄድ ላይ ይገኛል። ለነጻነት እያካሄደ በላው በዚህ ፍትሓዊ ትግልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ኣመርቂ ድሎችን እያስመዘገበ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ፣ በሃገር ቤትና በውጪ ሃገራት የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላትና ደጋፊዎች ኣልፎም ባጠቃላይ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ የህይወት መስዋዕትነት፣ የኣካል መጉደል፣ የረጅም ዓመታ እስርና የመሳሰሉትን መስዋዕትነቶች እየከፈሉበት በከፍተኛ ቆራጥነትና ጽናት ያለማቋረጥ ያካሄዱት መራር ትግል ጠላትን ኣናግቶ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ከኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች እንዲለቀቁ የኢሕኣዴግ መንግስትን ኣስገድዷል።
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ኢምፓዬር ስርዓት በህዝባችን ላይ የተዘረጋው ጭቆና፣ የመከላከያ ሃይል፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ ዝርፊያ መዋቅር ዛሬም እንደቀጠለ ነው። ይህንን በመገንዘብ የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግልን ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ወደፊት በማራመድ የህዝባችንን የነጻነት ዕለት ለማቅረብ ሲባል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትንና የቄሮን እንቅስቃሴ ከማጠናከር በተጨማሪ በሁሉም ረገድ የሚካሄደው ትግል በእጥፍ ድርብ እንዲፋፋም ለማድረግ በከፍተኛ ቆራጥነት እንዲሰራ የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል።

የኢትዮጵያ መንግስትን በተመለከተ

የኢህኣዴግ መንግስት ለራሱ ጥቅም ካቋቋመው የጦርና የደህንነት ሃይል መዋቅር በተጨማሪ በተለያዩ ክልል
መስተዳድሮች ውስጥ ያሰለፋቸውን ኣጫፋሪዎቹን በመጠቀም በስልጣን ዘመኑ ሙሉ በሁሉም የኢትዮጵያ
ኢምፓዬር ህዝቦች ላይ ባጠቃላይ፡ በተለይም ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ወደር የለሽ ጉዳት ሲፈጽም ቆየ። ይህ ከባድ ሰቆቃ፡ ውድ መስዋዕትነት በጠየቀ መራር ትግል ተመክቶ የኢህኣዴግን ሃይል እያዳከመና እያንበረከከ መጣ። ከዚህ ሁኔታ ውጥረት ውስጥ የገባው ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ፓርቲ፡ ኢህኣዴግ፡ ሰሞኑን ተሃድሶ በሚል ስም ለውጥ የሚያስገኝ ኣስመስሎ እራሱን በማቅረብ ህዝቡ እውን የማይሆን ተስፋ እንዲሰንቅ ለማድረግ ኣሳሳችና ኣወናባጅ ዲስኩሮችን በስፋፍ በመንዛት ላይ ይገኛል። ይህ ፓርቲ በተግባር እየፈጸመ ያለው ግን ላለፉት 27 ዓመታት እጃቸው በደም የተጨማለቀ መሪዎቹንና ሹማምንቱን ከፊሉን እየሸለመና እያወደሰ ከግዴታቸው እያሳረፈ ከፊሉን ደግሞ ተጨማሪ ስልጣን መሾምና መንበረ-ስልጣን ላይ እንዲቀያየሩ ማድረግ ነው። እንዲህ ያለው ኣካሄድ ወደ ለውጥ የሚወስድ እርምጃ ሳይሆን ኢህኣዴግ የስልጣን ዘመኑን በማራዘም ላለፉት 27 ዓመታት በህዝቦች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት ኣሁንም ለማስቀጠል ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ መሆኑን ብቻ የሚያሳይ መሆኑ በሁሉም መታወቅ ኣለበት።
ላለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ኢምፓዬር ህዝቦች እያሰቃየ ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግር ምንጩ የኢህኣዴግ ፓርቲ የተመሰረተበት የጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ- ነጻነት ዓላማና ፖሊሲ ነው። ስለሆነም ኢህኣዴግ ለሱ ብቻ እንዲሆን ብሎ የመሰረተው የጦር፣ የደህንነት፣ የኢኮኖሚና የኣስተዳደር መዋቅር በህዝቦች ትግል ተቀይሮ ህዝቦች በነጻነት የሚበጃቸውን መንግስት መርጠው ለመተዳደር የሚያስችላቸው ሁኔታ እስከሚፈጠር ድረስ በዚህ መንግስት ስርዓትና መዋቅር ውስጥ ህዝቦችን የሚጠቅም ለውጥ ሊገኝ ኣይችልም። በመሆኑም ህዝባችን መሰረታዊ ለውጥለማገኘት ሲል እስከዛሬ ድረስ ውድ መስዋዕትነት ከፍሎበትኣሁን ካለበት ደረጃ ያደረሰውን ትግሉን ኣጠናክሮ በመቀጠልከግቡ ለማድረስ በርትቶ መንቀሳቀስ ኣለበት።

ከኢትዮጵያ እስር ቤቶች የተለቀቁ የኦሮሞ ዜጎችን በተመለከተ

ህዝባችን ባጠቃላይ በተለይም ደግሞ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላት፣ ሌሎች የተጨቋኝ ህዝቦች ድርጅቶች በቀጣይነት በከፈሉት መስዋዕትነት በኦነግ ስምና ባጠቃላይ በኦሮሞ የነጻነት ትግል ስም ለዓመታት በኢህኣዴግ ወህኒ ቤቶች ውስጥ ሲሰቃዩ የነበሩ በብዚ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሄርተኞችና የሌሎችም ተጨቋኝ ህዝቦች ተወላጆች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ እስር ቤቶች መለቀቃቸውና ኣሁንም በየእስር ቤቶቹ ውስጥ የቀሩ መኖራቸው ይታወቃል።
ለህዝባችሁ ነጻነት ሲባል ያለኣንዳች ወንጀል በደባ ታስራችሁ ለስብዓዊ ፍጡር የማይገባ ሰቆቃ ሲፈጸምባችሁ የነበራችሁ፡ ከፊሎቻችሁ ለኣካል መጉደልና ለከፍተኛ የኣእምሮ መታወክ የተዳረጋችሁ ጀግኖች የኦሮሞ ብሄርተኞች ከእስር ቤቶች በህይወት በመውጣታችሁ እንኳን ደስ ኣላችሁ! እንኳን ደስ ኣለን! እያልን የከፈላችሁት መስዋዕትነት ከባድና ኣሰቃቂ ቢሆንም እናንተ ለጉዳት የተዳረጋችሁበት የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ኣብቦና ጎልብቶ ደጋፊዎችን በሚሊዮኖች ኣፍርቶ ህዝባችሁ በነጻነት ዋዜማ ላይ ደርሶ ማየታችሁ ኣስደሳችና የምትጽናኑበት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ይሁን እንጂ በደባ ኣስሮኣችሁ ይህንን ሁሉ ሰቆቃ ያደረሱባችሁ ሰዎችና ኣካላት ህግ ፊት ቀርበው የሚገባቸውን
ውሳኔ እስከሚያገኙና ለደረሰባችሁ ጉዳት ተገቢው ካሳ እስካልተሰጣችሁ ድረስ ፍትህ ኣግኝታችኋል ማለት ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን የኦነግ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ኣጥብቆ ያስገነዝባል። በማከልም ዛሬም በኢህኣዴግ ወህኒ ቤቶች ውስጥ ቀርተው ሰቆቃው እየተፈጸመባቸው ያሉትና የት እንደገቡ ያልታወቁት ሁሉ ያለኣንዳች ቅድመ-ሁኔታ በኣስቸኳይ እንዲለቀቁና ሁኔታቸው ለህዝቡ ይፋ እንዲሆን የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው ኣጥብቆ ይጠይቃል። ህዝባችንም በበኩሉ ነጻነቱን ሊያጎናጽፉት ሲሉ ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው የነበረውን እነዚህን ጀግኖች ልጆቹን በሚገባቸው ፍቅርና ክብር ተንከባክቦ በመያዝ ሞራላቸውን እንዲያጠናክርና በኣስፈላጊው ሁሉ እንዲደርስላቸው የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው ኣጥብቆ መልእክቱን ያስተላላፋል።

ኢህኣዴግ በህዝባች መካከል እያስፋፋ ያለውን ጦርነት በተመለከተ

የኦሮሞን መሬት በሁሉም ኣቅጣጫ ቆራርሶ ለባዕዳን በማከፋፈል ኦሮሚያን የሚቻላቸውን ያህል ማጥበብና
የኦሮሞን ህዝብ ዲሞግራፊ መቀየር ኢህኣዴግ እንደፖሊሲ ኣስቀምጦት በእቅድ ሲተገብረው ዛሬን የደረሰ ጉዳይ ነው። ኢህኣዴግ ይህንን ከሚያደርግበት ዓላማ መካከል ኣንዱና ዋነኛው የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ማዳከም ነው። በዚህ የኢህኣዴግ ፖሊሲ በኦሮሞ ህዝብ ላይ በርካታ የዘር- ማጥፋት ዘመቻ ተካሄዷል። በቁጥር ከኣንድ ሚሊዮን (1,000,000) የሚልቁ የኦሮሞ ዜጎች በኦሮሞነታቸው ብቻ ከቄዬና ከኑሮኣቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እንዲበተኑ ተደርገዋል። የኢትዮጵያ መንግስት(ኢህኣዴግ) በተለያዩ ክልል መንግስታት ኣስተዳደር ውስጥ ያሉ ኣጋሮቹንና በብሄር ስም የተደራጁ ኣንዳንድ ድርጅቶችን በመታገዝ በሰሜን፣ በምስራቅ፣ በደቡብ-ምስራቅ፣ በደቡብና በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል ሆን ብሎ ኦሮሞና ኣጎራባቾቹ ህዝቦችን ለማናቆር እስከ ዛሬ ድረስ እያካሄደ ያለው ጦርነት ከዚሁ የኢህኣዴግ ቋሚ ፖሊሲ የሚመነጭ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች ቦታዎችም በተለያዩ ህዝቦች መካከል በዚሁ የኢህኣዴግ ፓርቲ ሴራ ውጊያ እየተስፋፋ ይገኛል። ኢህኣዴግ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም በህዝቦች መካከል ፈጥሮ እያስፋፋ ያለው ይህ ጦርነት ዛሬ በህዝቦች ላይ እያደረሰ ካለው ከባድ ጉዳት በተጨማሪ በነዚህ ህዝቦች መጻዒ ግንኙነት ላይም በቀላሉ የማይሽር ጠባሳ እየፈጠረ ያለ ጦርነት ነው። ስለሆነም ይህ ጉዳይ የኦነግ ስራ- ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ከተወያየባቸውና በዚህ ረገድ በህዝቦች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ኣደጋ ለመቀነስና ለማስቀረት በርትቶ ለመስራት ከወሰናቸው ኣበይት ጉዳዮች መካከል ኣንዱ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል እስትራቴጂና በኦሮሞ ህዝብና በኢትዮጵያ ኢምፓዬ መካከል ያለውን የፖለቲካ ችግር በንግግር(negotiation) መፍታትን በተመለከተ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትግሉን የሚመራበትን የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል እስትራቴጂ ለይቶ ሲቀይስ የኢትዮጵያ ኢምፓዬር ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ የተመሰረተበትንና ለዘመናት መንበረ-ስልጣኑን የተፈራረቁት መንግስታትም ተወራርሰው ሲያስቀጥሉት በነበረው ሁኔታ ተገድዶ ሌላ አማራጭ በማጣት ነው። የመጫና ቱለማ ማህበር መታገድና የማህበሩን ኣባላት የገጠመው መታሰርና መገደል ለዚህ ኣብይ ማስረጃ ነው። ያ ሁኔታ ዛሬም ኣልተቀየረም። ይህም ከሚኒሊክ ኣንስቶ ወደ መንበረስልጣን የመጡት ሁሉም ሃይሎች ያለጠመንጃ ኣፈሙዝ ሰላማዊ ቋንቋ የማያውቁ መሆናቸው ነው። የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ኢምፓዬር ህዝቦች ዛሬም በጠመንጃ ኣፈሙዝ ኣገዛዝ ስር ናቸው። ስለሆነም በጠመንጃ ኣፈሙዝ ስልጣን ይዞ ህዝቡን ነጻነት የነፈገን መንግስት ከላዩ ላይ በመንቀል ህዝቡ ነጻነቱን ተጎናጽፎ የሚበጀውን መንግስት መርጦ እንዲተዳደርበት ለማድረግ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከሚከተላቸው የኦሮሞ የነጻነት ትግል እስትራቴጂዎች መካከል ኣንዱ የሆነው የትጥቅ ትግል ዛሬም ሌላ ኣማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
ስለሆነም የግላቸውንና የቡድናቸውን ስልጣንና ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ያላቸውን የጦርና የፖሊስ ሃይል ሁሉ
ተጠቅመው ዓላማቸውን ከግቡ ለማድረስ ሰላማዊውን ህዝብ እያስጨረሱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን “የትጥቅ ትግል ጊዜው ያለፈበት ፋሽን ነው።” የሚሉት ኣካላት ንግግራቸው የኦሮሞ ህዝብን ዓላማ ከሚጻረረው ኣቋማቸው የመነጨ እንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የማያንጸባርቅና እውነታ የሌለው እንደሆነ ህዝባችን በሚገባ መገንዘብ ኣለበት።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያለውን የፖለቲካ ችግር  ንግግር(negotiation) ለመፍታት መሟላት የሚገባቸውን ነገሮች የሚገልጽ የበኩሉን ፖሊሲና ኣቋም ገልጾ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥሪውን ያደሰው ከቅርብ ጊዜያት በፊት (በሚያዚያ ወር 2018ዓም መግቢያ) ነበር። ይህንን ጥሪውንም በተለያዩ ኣለምኣቀፍ ሚዲያዎች ላይ ግልጽ ኣድርጓል። የኢትዮጵያ መንግስት ለዚህ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጥሪ እስከ ኣሁን ድረስ ኣግባብ ያለው ምላሽ ኣልሰጠም። ጥሪውን ወደጎን በመተው በተለያዩ መድረኮች ላይ በኣፍ የፖለቲካ ችግሮችን በንግግር ስለመፍታት ማውራት የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለማዋል ካልሆነ በስተቀር ለእውነተኛ ንግግር(negotiation) ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ኣይደለም። ህዝባችንም ይህንን ሴራ በሚገባ ነቅቶ በመገንዘብ በንግግር(negotiation) መፍትሄ ወደ ማስገኘት የሚያመራ ኣስተማማኝ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ እስከኣሁን ለተገኘው ድል መሰረት የሆነውና ለወደፊቱም ኣስተማማኝ ድል ማግኘት የሚያስችለውን የነጻነት ትግል እስትራቴጂ፡ የትጥቅ ትግሉን ማጠናከርና ጋሻና መከታው የሆነውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መንከባከብ ለነጻነቱ ቁልፍ መሆኑን በሚገባ መረዳት ኣለበት።

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ትብብርን በተመለከተ

ለኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ዓላማ በኣፋጣኝ ከግቡ መድረስ ያለንን የሰው ሃይል፣ እውቀትና ሃብት የህዝባችንን
የጋራ ጥቅም ማስጠበቅ በሚያስችል ሁኔታ ኣንድ ላይ በማምጣት የህዝባችን ትግል ይበልጥ ሃይል እንዲኖረው
ማስቻል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቋሚ ፖሊሲ ነው። ስለሆነም የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም በማስከበሩ ላይ ኣብረን ሰርተን የህዝባችንን የነጻነት ዕለት ለማቅረብ ከምንችል ሁሉም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተባብረን መስራት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በኣሁኑ ጊዜ ኣስፈላጊ መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያምናል። ይህንን እውን ለማድረግም ጠንክሮ ይሰራል።
ካሁን ቀደም ስምምነት ፈጥረን ኣብረን ስንንቀሳቀስ የነበርን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ስምምነታችንን በማፍረስ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተንቀሳቀሱበት ያለው ሁኔታ የህዝባችንን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ የማይረዳ መሆኑ ከግንዛቤ ገብቶ ይህ የስህተት ኣካሄድ እንዲታረም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ድርጅቶች ቆም ብለው እራሳቸውን እንዲያዩና ህዝባችንም ድርሻውን እንዲወጣ የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው ያሳስባል።

የህዝቦች ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ (PAFD) በተመለከተ

የህዝቦች ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ(PAFD) ከተመሰረተ ኣንስቶ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች የፖለቲካ መፍትሄ ለማበጀት ሰፊ ስራ ሰርቷል። እውነተኛ የፖለቲካ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ሰፊ ሃሳብ መሪ ኣቅጣጫ(Road Map) ጠቁሞ የዚህን መፍትሄና ራዕዩንም የካቲት 2018ዓም በለንደን ኣካሂዶ በስኬት ባጠናቀቀው ስብሰባ ላይ ይፋ ኣደረገ። የለንደን ስብሰባ ኣያሌ ድርጅቶችን ያቀፈ ሰፊ ተሳትፎ የታየበት፣ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶችና የኣውሮፓ ምክር ቤት ኣባላት የተሳተፉበት ነበር። ይህ መሪ ኣቅጣጫ (Road Map) ይበልጥ ሰፍቶ በርካታ ድርጅቶችን በማወያየትና በማሳተፍ ወደ ሁሉን-ኣቀፍ ስርዓትና የሽግግር መንግስት(All Inclusive Transitional Arrangement) እንዲያመራን እየተሰራበት ይገኛል። ይህን የመጨረሻና እውነተኛ፣ እንዲሁም ሁሉን ኣሳታፊ መፍትሄ በማጎልበት ኣሁን ላለው የፖለቲካና የደህንነት ችግር በማያዳግም ሁኔታ መፍትሄ ለማስገኘት ሁሉም እንዲተባበር የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያስተላልፋል። ኦነግ ትብብሩ እያደረገ ላለው ጥረትና ለስኬታማነቱ በሙሉ ሃይሉ የበኩሉን ይወጣል።
ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ኢምፓዬር የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የፖለቲካ ሃይሎችና ሁሉንም የሚመለከታቸው ኣካላት ያሳተፈ የሽግግር ጊዜ ሁኔታ (All Inclusive Process) መፈጠር ወቅታዊ ጥያቄ መሆኑን ኦነግ ያምናል። ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ሃሳባቸውን
በሙሉ ነጻነት ለህዝቡ ኣቅርበው ሁሉም ህዝቦች ያለኣንዳች ግፊት በመጻዒ ዕድላቸው ላይ መወሰን ሲችሉ ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩሉ ሁሉን-ኣሳታፊ የሽግግር ሂደት እንዲሳካ የሕዝቦች ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ/PAFD ኣባላት ከሆኑ የትግል ኣጋሮቹ ጋር በመሆን ይሰራል። ሌሎች
መሰል መሪ ኣቅጣጫ(road map) ያላቸው ቡድኖች መኖራቸውንም ኦነግ ይገነዘባል። እንደነዚህ ያሉ ቡድኖችና ለዲሞክራሲና ለነጻነት በመስራት ላይ የሚገኙ ሁሉም ሃይሎች ይህንን ሂደት ለማሳካት እንዲሰሩና በዚያው ውስጥ ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ለሁሉም ድርጅቶችና ሃይሎች ጥሪውን ያስተላልፋል። እንዲሁም መላው ኣለምኣቀፍ ማህበረሰብና መንግስታት ይህንን እንዲደግፉ ጥሪያችንን ኣጥብቀን እናስተላልፍላቸዋለን።

ጥሪ:

ለሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ህዝባችን በሃገር ቤትና በውጪም በከፍተኛ ንቃትና ያለመታከት ከነጻነት ትግሉ ጎን ቆሞ እስከዛሬ ድረስ እያበረከተ ያለው ድርሻ የሚደነቅ ነው። ከባድ መስዋዕትነት በከፈልንበት መራር ትግል ዛሬ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ወደ ነጻነታችን ተቃርበናል። ይሁን እንጂ ህዝባችን በውድ መስዋዕትነት እያገኘ ያለውን ድልና ውጤት ቀምቶ ኣቅጣጫውን በማስሳት ለራሳቸው የፖለቲካ ዓላማ ለማዋል የሚፍጨረጨሩት እየተበራከቱ መምጣታቸው መዘንጋት የለበትም። ስለሆነም ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ለትግላችን የምናደረውን ድጋፍና ተሳትፎ በእጥፍ ድረብ እንድንጨምርና በከፍተኛ ንቃት እንድንራመድ የሚጠይቀን ነው። በሃገር ውስጥና በውጪም ያለው ህዝባችን እየተካሄደ ያለውን ይህንን ሁኔታ በሚገባ ተገዝንቦ የልጆቹን የመስዋዕትነት ፍሬ ከፖለቲካ ነጋዴዎች ጠብቆ ትግሉን በኣፋጣኝ ከግቡ ለማድረስ ድርሻውን በብቃት እንዲወጣ የኦነግ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያድሳል።
ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላትና ደጋፊዎች ህዝባችን ነጻነቱን ለመጎናጸፍ ለዓመታት እያካሄደ ዛሬን በደረሰው ፍትሃዊ ትግል ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላት ድርሻ ከፍተኛ ነው። ዛሬ የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል እየተጎናጸፈ ላለው ድል ሁሉ መሰረት የሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኣባላት ለዓላማቸው ያላቸው ትዕግስት፣ ቆራጥነትና ጽናት እንዲሁም ታማኝነትና የኦሮሞ ብሄርተኞች ድጋፍ ነው ።
ዛሬ ትግላችን ከደረሰበት ደረጃ ፍልሚያውን በመቀጠል ከግባችን ለመድረስ ዛሬም የኦነግ ኣባላትና ደጋፊዎች ድርሻ የላቀ ነው። የቀረን መንገድ ኣጭር ነው። ይበልጥ ማሳጠሩ ደግሞ የኛን ቆራጥነት፣ ንቃትና እራስን መስጠት ይጠይቃል። የድርጅታችን ኣባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ይህንን በመረዳት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡ የስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ለጀግናው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የኦሮሞ ህዝብ አለኝታና መከታ የሆንከው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከሃይል፣ ከሃብትና ከእውቀትም በላይ መተኪያ የሌላትን ህይወትህን ለህዝብህ ነጻነት በመስጠት ለኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ስታበረክት የነበረውና በማበርከት ላይ የምትገኘው ድርሻ በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ዝንተዓለም ከፍተኛውን ስፍራ ይዞ ይኖራል። ኣንተ ጋሻና መከታው እንደሆንከው ሁሉ የኦሮሞ ህዝብም በኣሁኑ ወቅት ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ጥላና ከለላህ ከመሆኑም በተጨማሪ ባለው ኣቅም ሁሉ ከጎንህ ለመቆም መወሰኑን
በተግባር እያሳየ ነው። እስከኣሁን በከፈልከው መስዋዕትነት ኣያሌ ኣኩሪ ታሪክና ድሎችን ኣስመዝግበሃል። የህዝብህን ነጻነት በማረጋገጥ ከዚህ የላቀ ታሪክና ድል ለማስመዝገብ እራስህን ኣዘጋጅተህ በከፍተኛ ቆራጥነትና ንቃት እንድትንቀሳቀስ የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ለቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ቄሮ ቢሊሱማ ኦሮሞ ወዳጅና ጠላትን ባስደመመ ቆራጥነትና ሚስጢራዊ ጥበብ እራስህን ኣደራጅተህ በመንቀሳቀስ የሰራሀው ኣኩሪ ታሪክ የኦሮሞን ህዝብ ታላቅ ክብር ያጎናጸፈ ነው። ንቅናቄህና መስዋዕትነትህ በኣለም ላይ ተሰሚነትና ድጋፍ ከማግኘቱም በተጨማሪ የኦሮሞን ህዝብ የነጻነት ትግል ወደ ኣዲስ ምዕራፍ ኣሸጋግሯል። ይሁን እንጂ በኣሁኑ ወቅት ትላንት መኖርህን ሲክዱ፣ መጥፋትህን ሲመኙና ኣደረጃጀትህንና ንቅናቄህን ለማጥፋት ባላቸው ሃይል ሁሉ ዘምተውብህ እስራትና ዘግናኝ ግድያ ሲፈጽሙብህ የነበሩትና ዛሬም እንዲህ ካለው ድርጊት ያልታቀቡት ሃይሎች እራሳቸውን በመስዋዕትነትህ የተገኘው ድል ባለቤት ለማድረግ ሲያጣጥሩ እያየህ ነው። ስለሆነም ይህን መሰሉን ሴራ ነቅተህ በማክሸፍ እስከኣሁን ለከፈልከው መስዋዕትነት ፍሬ ለማስገኘት በላቀ ንቃት እንድትንቀሳቀስ የስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴው መልእክቱን ያስተላልፍልሃል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስርዓትን በማገልገል ላይ ለሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች

በኑሮ ኣስገዳጅነትና በተለያዩ ሁኔታዎች ተገፋፍታችሁ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም በተለያዩ የመንግስቱ የስራ መዋቅሮች ውስጥ የኢህኣዴግ መንግስትን በማገልገል ላይ የምትገኙ ብሄርተኛ የኦሮሞ ልጆች የህዝባችሁ የነጻነት ትግል በኣሁኑ ወቅት ከናንተ የሚፈልገውን ግዴታ በማወቅ በያላችሁበት ቦታ ሁሉ በግልም ይሁን በመደራጀት ባመቻችሁ ሁኔታ ሁሉ የህዝባችሁን ነጻነት እውን ለማድረግ በሚረዳ ነገር ላይ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ሆናችሁ እንድትንቀሳቀሱ የኦነግ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ መልዕክቱን ኣጥብቆ ያስተላልፍላችኋል።

በኢትዮጵያ ኢምፓዬር ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ብሔሮችና ብሄረሰቦች

የኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ዓላማ ከግቡ መድረስ የኦሮሞን ነጻነት ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የኢትዮጵያ ኢምፓዬር ህዝቦች ነጻነትና መብት መከበር እንዲሁም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ዋስትና ሊሆን እንደሚችል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጽኑዕ እምነት ነዉ። የኢሕኣዴግ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሸርበው ሴራ የኢሕኣዴግን እድሜ ለማራዘምና እስራት፣ ግድያና የሃብት ዝርፊያን ጨምሮ በተለያየ መልኩ በህዝቦች ላይ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከማስቀጠል በስተቀር የትኛውንም ህዝብ የማይፈይድ መሆኑን በሁሉም ከግንዛቤ መግባት ኣለበት። ስለሆነም በኢትዮጵያ ኢምፓዬር ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህንን ተገንዝበው የኦሮሞ ህዝብና ሌሎችም ተጨቋኝ ህዝቦች ነጻነታቸውን ለመጎናጸፍ የሚያካሄዱትን ፍትሃዊ ትግል በሚችሉት ሁሉ እንዲደግፉ የኦነግ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያቀርባል።

ለሁሉም የኣለም መንግስታትና ማህበረሰብ

በኢትዮጵያ ስልጣን ሲፈራረቁ የነበሩት መንግስታት ሁሉ ጸረ- ዲሞክራሲ የሆነን የጭቆናና የዝርፊያ ስርዓት በጠመንጃ ኣፈሙዝ በህዝቦች ላይ በመዘርጋት እንዳሻቸው ህዝቡን እያሰሩ፣ እየገደሉ፣ ሀብቱን እየዘረፉና ከመሬቱ ኣፈናቅለው ለድህነትና ለስደት በመዳረግ ሲጨቁኑት ኖረዋል።
የኢህኣዴግ ፓርቲ በ1991ዓም ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ኣንስቶ በዲሞክራሲ ስም ምሎ፣ የሃሰት የፌዴራሊዝም ኣወቃቀር በመዘርጋት ከዓለም መንግስታትና ማህበረሰብ ድጋፍ እያገኘ ዛሬን ደርሷል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እውተኛውን የኢህኣዴግ ማንነት ለህዝቦች፣ ለመንግስታትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ኣካላት ሁሉ ከማስገንዘብ የተቆጠበበት ጊዜ የለም።
ዛሬ ህዝቦች (በተለይም የኦሮሞ ህዝብ) ውድ መስዋዕትነት በመክፈል ባካሄዱት ትግል የኢህኣዴግ እውነተኛ ማንነት በሁሉም ዘንድ ተጋልጧል። ኢህኣዴግ ላለፉት 27 ዓመታት በህዝቦች ላይ ሲፈጽም የነበረው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የተለያዩ ወንጀሎች የሽብርተኝነት ተግባር መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የተለያዩ ኣካላት ሲገልጹት ከነበረው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. ኣብይ ኣህመድ በኢህኣዴግ “ፓርላማ” ፊት ቆሞ በአንደበታቸው መመስከር ጀምሯል። ኢህኣዴግ በጠመንጃ ኣፈሙዝ በህዝቡ ላይ የዘረጋው የሽብርተኝነት ስርዓትና መዋቅር ዛሬም በቦታው ኣለ። የኣለም መንግስታትና ማህበረሰብ ላለፉት 27 ዓመታት መንግስታዊ ሽብርተኝነትን(State Terrorism) ሲያካሄድ የነበረውና እሱ የዘረጋው ስርዓትና መዋቅር ኣሁንም በቦታው ባለው ስርዓት ሊመጣ የሚችል ለውጥ እንደሌለ መገንዘብ ኣለባቸው።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኣለም መንግስታትና ማህበረሰብ ኢህኣዴግ በኣፉ የሚለፍፈውን “ለውጥ” ኣምነው ስርዓቱን ከመደገፍ ተቆጥበው መብቶቻቸውን ለማስከበር ፍትሃዊ ትግል በማካሄድ ላይ ካሉ ህዝቦች ጎን እንዲቆሙና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የትግል አጋሮቹ ከሆኑት ከህዝቦች ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ (PAFD) ኣባል ድርጅቶች ጋር በመሆን እየሰራበት ያለውን ሁሉንኣቀፍ ሽግግር እንዲሳካ ድርሻቸውን እንዲወጡ የኦነግ ስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን ያድሳል።
በዚህ ኣጋጣሚ ከቅርብ ጊዜ በፊት የኣሜሪካ ኮንግረስ ያሳለፈውን እንደ ኤች ኣር-128 (HR-128) የመሳሰሉ ውሳኔዎችንና የኣውሮፓ ህብረት በተለያዩ ጊዜያት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እያደነቅን የዲሞክራሲ ስርዓትንና የህዝቦችን ነጻነት እውን ለማድረግ የሚረዱ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኦነግ ስራ ኣስፈጻሚ ኮሚቴ ይጠይቃል።

ዘመኑ የጭቆና ፍጻሜ ዘመን ነው !
ድል ለኦሮሞ ህዝብ !
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስራ-ኣስፈጻሚ ኮሚቴ
ሰኔ 20, 2018ዓም

Filed in: Amharic