>

የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያ ገበሬዎችን ሰብል አወደመ (ጌታቸው ሺፈራው)

የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያ ገበሬዎችን ሰብል አወደመ

ጌታቸው ሺፈራው
የሰሜን ሱዳን ወታደር የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ሰብል ማውደሙን ነዋሪዎች ገልፀዋል። ትናንት ሰኔ17/2010 ዓም  ዲሽቃና መትረየስ ጨምሮ  ከባድ መሳርያዎችን ታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የገባው የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ገበሬዎች ጋር ተኩስ መግጠሙ ተገልፆአል። የሱዳን ጦር በመተማ ወረዳ አቲሚቲ የተባለ ቦታ የገበሬዎችን ሰሊጥ ማሳ በትራክተር በማረስ ያወደመ ሲሆን ለአብነት ያህልም መከተ እና ማርቆስ የተባለ ገበሬዎች ማሳ መውደሙ ታውቋል።
የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ከተሰጠ በኋላ ድንበሩን መጠበቅ ያቆመው የኢትዮጵያ  መከላከያ ሰራዊት ዛሬ ሰኔ 18/2010 ዓም ከቦታው በመድረስ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን ወደኋላ እንዲመለሱ አድርጓል ተብሏል።
በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለት በቋራ ወረዳ በሱዳን ጦርና በገበሬው መካከል ተኩስ እንደነበር ተገልፆአል።  መሬታቸው ለሱዳን የተሰጠባቸው ገበሬዎች መሬቱን በኪራይ ሲያርሱ የቆዩ ሲሆን ከ2008 ዓም ጀምሮ  “በራሳችን መሬት ኪራይ አንከፍልም” በማለታቸው ከሱዳን ጦር ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፀምባቸው ቆይቷል። በአንፃሩ የኢትዮጵያ ጦር ድንበሩን በመጠበቅም ሆነ ገበሬዎችን ከሱዳን ጦር ጥቃት በመከላከል ተግባር ላይ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።
Filed in: Amharic