>

እስካሁን (ደረጀ ደስታ)

እስካሁን

ደረጀ ደስታ

ከዚያ በፊት – ከደቂቃዎች በፊት ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ በየዓመቱ ሰኔ 16 /ጁን 23ን የፍቅር የይቅርታና የመደመር ቀን ሁኖ እንዲውል ታስባለች ሲል የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት አስታውቋል።

ከእስካሁኖቹ ዘገባዎች ያገኘኋቸው እነዚህን ነው-

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰልፉ ላይ መልእክት ካስተላለፉ ከደቂቃዎች በኋላም የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ለኢቲቪ በሰጡት መረጃ የተጎዱ ዜጎች 100 ያህል ይሆናሉ። ከነዚህ መካከል 15ቱ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በዘውዲቱ ሆስፒታል 23 – የካቲት 12 ሆስፒታል 56 ዜጎች አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ የተጠናና በሙያተኛ የታገዘ ነበር” ብለዋል። የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውንና ይህ ለለውጥ ሲባል የተከፈለ መስዋዕትነት ነው” በማለት ተናግረዋል።፡ ይህንን ባደረጉ ሰዎች ላይ ማዘናቸውንና የሞቱት ነፍሳቸው እንዲማር፣ የቆሰሉት እንዲታከሙ፣ ቤተሰቦች እንዲጽናኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ጽ/ቤታቸው ወደኋላ ባወጣው መግለጫ የሞተው ሰው አለመኖሩን ገልጿል። አንዳንድ ሰዎች ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ሳይሞቱ እንዳልቀሩም የጻፉ አሉ። ቢሆንም አላረጋገጥኩም።
የአስተባባሪ ኮሚቴው ጉዳት የደረሰባቸውን በተለያዩ ሆስፒታሎች እየሄደ በመጎብኘት ላይ እንደሚገኝ ከአዘጋጁ አንዱ የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ጽፈዋል።

በፍንዳታው ተጠርጥረው የተያዙት እነማን እንደሆኑ ባይገለጽም አበበ ቶላ ፈይሳ (አቤ ቶኪቻው) በድረ ገጹ የተጣራ ዜና በሚል ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙትን የሁለት ሴት እና ሁለት ወንድ ተጠርጣሪዎች ፎቶግራፍን አስፍሯል።

የኢህአዴግ ጽ/ቤት ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል-

የድርጅታችን ሊቀ መንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ በንግግራቸው ጥላቻና በቀልን ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን፤ ዘረኝነትንና ሙስናን ሳይሆን መደመርንና ሀገር ወዳድነትን ባከበሩበት የሚሊዮን ንፁህ ኢትዮጵያዊያን መድረክ ላይ የተፈፀመው ይህ የተሸናፊዎች የወንጀል ድርጊት በመስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ለአፍታም ሳንዘናጋ ጠብቀን እንድንዘልቅ፤ የጀመርነውን የፍቅር፣ የእርቅና የአንድነት ጉዞ አጠናክረን እንድንቀጥልበት የሚገፋን እንጂ ወደኋላ የሚጎትተን አይደለም።

ሰልፉ 24 ሺ በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎች እንደነበሩት ተገልጿል። የሰልፈኛውን ቁጥር ደግሞ እንግዲህ መገመት ነው። ከዚያ አንጻር ሊደርስ የታሰበው አደጋ ምን ያህል እንደነበር ማሰብ ይቻላል። የአደጋው ዝርዝር ሁኔታ ተጠናቆ አልተገለጸም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተበሳጩ ሰዎች ንዴታቸውን እየገለጹ ነው። አገር ከተወረወረው ቦምብ የተፈረች ቢመስልም ከዚያም የከፋው የቃል ቦምብ መወራወሩ ግን የተጀመረ ወይም ተባብሶ የቀጠለ ይመስላል። ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እየተደረጉ ባሉት የነቂስ ሰልፎች ግን ኢትዮጵያውያን ጨዋነታቸውንና ሰላማዊነታቸውን አሳይተዋል።

Filed in: Amharic