>

ሕዝብ ለዴሞክራሲ ያሳየውን ፍቅር በጥላቻና በሽብር መግታት አይቻልም!!! (አርበኞች ግንቦት 7)

ሕዝብ ለዴሞክራሲ ያሳየውን ፍቅር በጥላቻና በሽብር መግታት አይቻልም!!!

ከአርበኞች ግንቦት 7

ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ መስቀል አደባባይ ወጥቶ በዶ/ር ዐቢይ አህመድ መሪነት ለተጀመረውን የለውጥ ሂደት ያለውን ድጋፍ በከፍተኛ ሥነሥርዓት እና ጨዋነት ገልጿል። ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አቻችለው የፈቀዷቸውን ሰንደቆችና አርማዎችን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል፤ የተለያዩ ዜማዎችን አዚመዋል። ዛሬ ኢትዮጵያዊያንን አገራዊ አንድነት፤ የነፃነት ፍላጎት እና የለውጥ ተስፋ አስተባብሯቸዋል። የዶ/ር አቢይ የለውጥና የመቻቻል መርህ ገዢ ሀሳብ ሆኖ ቀርቧል።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ፍጹም ሰላምተኛ ሕዝብ በተሰበሰበበት፤ ለውጥ፣ ፍቅርና መቻቻል በተሰበኩበት መድረክ ላይ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሟል። በዚህም ምክንያት በሰው ሕይወትና አካላት ላይ ጉዳት ደርሷል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህንን የሽብር ጥቃት በጽኑ ያወግዛል። ድርጊቱ ተጣርቶ የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል።
ንቅናቄዓችን አርበኞች ግንቦት 7 እንዲህ አይነቱ እኩይ ድርጊት እንዲፈጸም ሃሳብ የሚያመነጩ፣ የሞራልና የቁስ ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙትን አካላት በሙሉ፣ ይህ የጥላቻና የጠብ መንገድ ከማንም በላይ በመጨረሻ የሚጎዳው እራሳቸውን እንደሆነ “የጫረው እሳት ሲፈጀው ታዬ” በሚለው የአባቶቻችን አባባል እያስገነዘበ፣ አደብ እንዲገዙ ያሳስባል።
አርበኞች ግንቦት 7 ለሞቱት ወገኖቻችን ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፤ እነዚህ ወገኖች ለለውጥ፣ ለፍቅርና መቻቻል የከፈሉት ዋጋ ሲዘከር ይኖራል። ንቅናቄዓችን በዚህ አደጋ ለቆሰሉት ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በደረሰው አደጋ ሳይደናገጥ፤ ስሜቱም ሳይረበሽ የለውጡን ሂደት እንዲያፋጥን አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል። ለሰላምና ለዴሞክራሲ ሁላችን ዘብ እንቁም።
አንድነት ኃይል ነው !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
Filed in: Amharic