>

የአርበኞች ግንቦት 7 ልዩ መግለጫ

“የሰለጠነ ፓለቲካ” የምንመርጠው፣ የምናውቀውና የምንመኘው የትግል ስልት ነው!!!  የአርበኞች ግንቦት 7 ልዩ  መግለጫ

ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የሥራ ዘገባ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ በአንክሮ ተከታትለናል።
ዶ/ር አቢይ በዚሁ ማብራሪያቸው የኢህአዴግ መንግሥት የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የአሸባሪነት ተግባራትን የሚፈጽሙ እንደሆኑ በይፋ ከመናገራቸውም ባሻገር ፤ ፓርቲና መንግሥት ተቀላቅለው ነፃ ተቋማት እንዳይኖሩ መደረጉን እና የዳኝነት ሥርዓቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።  ንቅናቄዓችን ለዓመታት ሲናገር የነበረውን ሀቅ እሳቸው መናገራቸው፣ በአንድ በኩል እሳቸው በግላቸው ከእውነት ጎን ለመቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት ሲያመለክት -በሌላ በኩል ደግሞ እሳቸው የሚመሩት የለውጥ ቡድን ለሀገራዊ መግባባት እያሳየ ያለው ዝግጁነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል የሚል እምነት አሳድሮብናል። እነዚህ ቀድሞ ሲካዱ የነበሩ እውነታዎች በእርሳቸው አንደበት በምክር ቤቱ ስብሰባ መገለፃቸው፣ እስካሁን ሲፈፀሙ የነበሩ በደሎችን ለማስቀረት እና ጉድለቶችን ለማረም ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለን እናምናለን። ዶ/ር ዓቢይ እስካዛሬ በኢትዮጵያ የምክር ቤት ታሪክ ውስጥ ያልታየ ሀቀኝነት በማሳየታቸውም አድናቆቻችን ከፍተኛ ነው።
በሥራ ላይ ያለውንና  ቋንቋን መሠረት ያደረገውን የክልል አስተዳደራዊ መዋቅር በተመለከተ የተናገሩትም ትኩረት የሚስብ ነው። ቋንቋን መሠረት ያደረገ ማካለል በየቦታው ለሚነሱ የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎች አስተዋጽኦ ማበርከቱን፤ የሕዝብ መፈናቀልና መገፋት ማስከተሉን፤ ዘረኝነትን በማባባስ በሀገራችን ውስጥ በአስደንጋጭ ሁኔታ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እና ክፍለ አህጉራዊ እይታን ነስቶ ዜጎች ስለመንደራቸው ወሰን አብዝተው እንዲጨነቁ ማድረጉን የሚገልጸው የንግግራቸው ክፍልም- ለአብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ እና  የወደፊት መንገዳቸውን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር መሠረቱ ቋንቋ ነው ይባል እንጂ በተግባር የሚታየው ግን ዘር ነው። ይህ አደረጃጀት ለኢፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፤ አድልዎ ለተሞላበት አስተዳደርና ለሚሊዮች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ዶ/ር ዓቢይ ከቀናት በፊት ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል አወቃቀር ያስገኛቸውን ጥቅሞችና ጉዳቶችን መዝኖ አማራጭ የአደረጃጀት ንድፎችን የሚያዘጋጅ ኮሚሽን የሚዋቀር መሆኑን መግለፃቸውም- አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄን (አርበኞች ግንቦት 7) በእጅጉ አስደስቷል። በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን የበኩሉን ለማበርከት ዝግጁነቱን ይገልፃል።
ዶ/ር አቢይ አህመድ ህወሓትንና የትግራይ ሕዝብን ለያይቶ ስለመመልከት የተናገሩትም- ንቅናቄዓችን ከልብ የሚያምንበትና በጽናት ሲያራምደው የቆየው እምነት ነው። ህወሓት በርካታ አኩይ ተግባራትን የፈጸመ፤ የአገዛዙን የደህንነትና የፀጥታ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሚቃወሙትን ሁሉ እስር ቤት በማጎር በፈጸመው ሰቆቃ- በርካታ ዜጎችን ለኣካልና ለስነልቦና ጉዳት የዳረገ፤  ሺዎችን የገደለና ሚሊዮኖችን ለስደት የዳረገ፤  የመንግሥት ሥልጣንን ለሀብት ዘረፋ መጠቀምን ብቸኛ አማራጭ ያደረገ ፍጹም አምባገነንና ዘራፊ ድርጅት ነው። በዚህም ሁሉ ምክንያት ነው ህወሓትን የምንታገለው። ይህ ድርጅት በነፃ ምርጫ ሳይመረጥ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ነኝ ማለቱ ሳያንስ ራሱን ከትግራይ ሕዝብ ጋር እኩል አድርጎ የሚያቀርብ ትዕቢተኛ ድርጅት ነው። በዚህም ተግባሩ የትግራይን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ አራርቆታል። ይህ መቆም አለበት። ለዚህም ነው ሕዝብንና ድርጅትን የመለየት አስፈላጊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁን እጅግ በጣም ጥሩ ነገር ነው ብለን ያመንነው።  ይህ መልዕክት ለትግራይ ብቻ  ሳይሆን በፍትሃዊና ነፃ ምርጫ ተመርጠው ሳያሸንፉ የሕዝብ ተጠሪ ነኝ የሚሉ ድርጅቶችን ሁሉ የሚመለከት ነው ብለን እናምናለን። ህወሓትን በተመለከተ ጥቂት ተጨማሪ ነገር ማውሳት የምንፈልገው-ህወሓትን የምንታገለው ከትግራይ ሕዝብ ጎን ቆመን መሆኑን ነው። ይህ ብቻ ሳይሖን በራሱ በህወሓት ውስጥም የለውጥ ኃይሎች መኖራቸውን  ጠንቅቀን እናውቃለን። የኢትዮጵያን ሰቆቃ በመቀነስ ረገድ የእነዚህ  ህወሓት ውስጥ ያሉ የለውጥ አራማጆች ሚና ከፍተኛ ነው ብለንም እናምናለን። ስለሆነም፣ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተባብረን ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።
አርበኞች ግንቦት 7፣  ኦነግና አብነግ ከአመጽ ትግል ተቆጥበው ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲሸጋገሩ ጠቅላይ ሚኒስት ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በፓርላማው ንግግራቸው ጥሪ አድርገዋል። በመገዳደል ሥልጣን መያዝም ሆነ በስልጣን ላይ መቆየት ጊዜው ያለፈበት “ኋላ ቀር ፓለቲካ” መሆኑን ገልፀዋል።  ይህ አገላለፃቸው የአርበኞች ግንቦት 7 የቆየ እምነት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የመሣሪያ ትግል ዋነኛ የትግል ስትራቴጅው አድርጎ፤ በዚህ መንገድ የፓለቲካ ስልጣን የመያዝ ዓላማ ኖሮት አያውቅም። ሆኖም ግን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ገጥሞን የነበረው ባላንጣ የኋላ ቀር ፓለቲካ ቀንደኛ አራማጅ የነበረ በመሆኑ ፣ዜጎች አገዛዙ ከሚያደርስባቸው ሽብር ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ድርጅታቸውን፣ ማኅበረሰባቸውንና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲከላከሉ ሲያበረታታ ቆይቷል። ራስን ከጉልበተኛ አጥቂ መከላከል፣ ፍትሀዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮዓዊ መብት ነው፤ አጥቂ ከሌለ ግን  ይህ አያስፈልግም።
ዶ/ር አቢይ አህመድና የለውጥ ቡድናቸው ተስፋ እየሰጡ ባሉበት መንገድ ኢትዮጵያን መርተው ዜጎችን የሚያሸብር አገዛዝ እንዳይኖር የሚያደርጉ ከሆነ፤ የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲካሄድ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን በተግባር መውሰዳቸውን ከቀጠሉ፤ የህወሓት አገዛዝ ለነፃነትና ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ኃይሎች ላይ በፓርላማ አስጸድቆ ያሳወጀውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ካነሱ፤ ለዲሞክራሲ መስፈን እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ህጎች ከተሻሩ እና ነፃ ተቋማት እንዲመሠረቱ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ አርበኞች ግንቦት 7 ራስን በመከላከል ተግባር ላይ ሕይወት፣ ጊዜና ንብረት የሚያጠፋበት ምንም ምክንያት የለውም።  ምክንያቱም የሰለጠነ ፓለቲካ የምንፈልገውና ለሀገራችን የምንመኘው የትግል ስልት ነው።
የኛ እምነት ግን ከዚህም ያልፋል።
ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት መገንባት የበርካታ ዜጎችና ቡድኖች ትብብርን የሚጠይቅ፤ በአንዴ ተገንብቶ  የማይጠናቀቅ፤ ጊዜና ሌሎች በርካታ ግብዓቶችን የሚጠይቅ የማኅበራዊ ልማት ውጤት መሆኑን እንገነዘባለን። ዜጎችን የማያሸብር መንግሥት በዶ/ር ዓቢይ ወይም በቡድናቸው ጥረት ብቻ የሚመጣ እንዳልሆነም እናውቃለን። የዚህ ትግል ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም በዚህ ረገድ ዶ/ር ዓቢይና የለውጥ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም በሚያደርጉት ትግል አብረናቸው መሆናችንን ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን።
ዶ/ር አቢይ በመግለጫቸው ይህንን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች እየፈጸሙ ያለውን አሻጥር ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባና ቅልበሳውንም ለመከላከል የማኅበረሰቡን ሰፊ ድጋፍና ተሳትፎ እንደሚፈልግ መናገራቸው፤ እኛም እንደ ድርጅት ስናስጠነቅቅ የነበረውና እንዲህ ዓይነት ቅልበሳን ለመከላከል በኢህአዴግ ውስጥ ካሉ የለውጥ ኃይሎች ጋር ሙሉ ትብብር እንደምናደርግ ከዚህ በፊት ያሳወቅነውን አሁንም በግልጽ ደግመን እናሳውቃለን።
ይህ የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታና ከዚህ ሂደት የሚወጣው የፖለቲካ ሥርዓት ሰፋ ያለ ማኅበራዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ሰፋ ያሉ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበረሰብ ኃይሎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ ውይይት በቶሎ የመደረጉን አስፈላጊነት አሁንም በድጋሚ በአንክሮ ማሳሰብ እንፈልጋለን። በእንዲህ ዓይነት ውይይትም ድርጅታችንም ሆነ ከድርጅታችን ጋር ተባብረው የሚሠሩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች የሚጠበቅብንን ሙሉና ቀና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።
አርበኞች ግንቦት 7 ራሱ፣ በታሪካችን ውስጥ እስካሁን ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ እውነተኛ ፉክክር የታየበት የምርጫ 97 ውጤት ነው። የአርበኞች ግንቦት 7 አመራርና አባላት በምርጫ 97ቱ የሰለጠነ ፓለቲካ  ተሳትፎ ያደረጉ ዜጎች መሆናቸውን ኢትዮጵያዊያን ያውቃሉ። የንቅናቄዓችን ተልዕኮም በግንቦት 7 ቀን 1997 ለአጭር ጊዜ አጣጥመን በጉልበት የተነጠቅነው የሰለጠነ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ህጋዊ የፓለቲካ ስልጣን ሽግግርና በዚህም ሂደት የሀገሪቱን አንድነትና የሕዝቡን አብሮነት ያስጠበቀ፤ የሁሉንም የሀገራችንን ዜጎች እኩልነት ያስረገጠ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ነው።
ስለሆነም ዜጎች ላይ የሚደርስ ግልጽ ጥቃት እስከሌለ ድረስ ራስን በመከላከል ላይ ሕይወት፣ ጊዜ፣ ጉልበትና እውቀትን ማባከን ምርጫችን አለመሆኑ እንገልፃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !
ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ ም
Filed in: Amharic