>

የፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት ወልደዬስ 90ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ  (ልኡል አምደጽዮን ሰርጸ ድንግል)

ስመ ጥሩ ሐኪምና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት ወልደዬስ ዐልታዬ የተወለዱት ከዛሬ 90 ዓመታት በፊት (ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም) ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት ወልደዬስ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም ከአባታቸው ከአቶ ወልደዬስ ዐልታዬ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ፡፡ አባታቸው በፀሐፊነትና በአስተዳደር፣ እናታቸው ደግሞ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የአቶ ወልደዬስ ዐልታዬ እና የወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ትዳር በፍቺ በመቋጨቱ ምክንያት ህፃኑ ዓስራት ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ ሄዱ፡፡
ሩዶልፎ ግራዚያኒ እነ ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ለቃጡበት የግድያ ሙከራ አጸፋውን ሲመልስ ከተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ አቶ ወልደዬስ ዐልታዬ ነበሩ፡፡ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው የአቶ ወልደዬስ ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው ከሕጻን ልጃቸዉ በሞት ተለዩ፡፡
ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊው ዓስራት ከአያቱ ከወይዘሮ ባንቺወሰን ይፍሩ-ለሱሲሉ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ አጎቱ አቶ ዘውዴ ወረደወርቅም እዚያው ድሬዳዋ ይኖሩ ነበርና ታዳጊውን የቄስ ትምህርት እንዲማር አስገቡት፡፡
ታዳጊው ዓስራት የቄስ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት “በቀለም አቀባበሉ ጎበዝ ነበር” ይላሉ አስተማሪው አለቃ ለማ፡፡ አለቃ ለማ ምስክርነታቸውን ሲሰጡም ‹‹አስራት በልጅነቱ በጣም ጎበዝ በመሆኑ ዓመት ሳይሞላው ወንጌሉን ከቁጥሩ አንበልብሎ፤ ከፍካሬ እስከ ነቢያት ድረስ ደግሞ ድቁና ተቀበለ›› ይላሉ፡፡
ከቄስ ትምህርቱ ጎን ለጎን ድሬዳዋ ይገኝ ከነበረው ፈረንሳይ ሚሲዮን ት/ቤት ገብቶ ቀለም መቁጠር ጀምሮም ነበር፡፡ የእናቱ አባት ቀኛዝማች ጽጌ ወረደወርቅ ታዋቂ አርበኛ ነበሩ፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ አስሮ ከፈታቸው በኋላ (ወደ ጣሊያን ተወስደው ታስረው ነበር) ታዳጊውን ዐሥራትን ወደአዲስ አበባ አስመጥተው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ ከት/ቤቱ ተማሪዎች ሁሉ አንደኛ በመውጣት ተሸላሚ ሆነ፡፡
በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል ላቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡትን ወደ ውጭ ሐገር ልኮ ማስተማር ተጀምሮ ነበርና ዓስራትም በዚሁ የትምህርት ዕድል ምክንያት ግብጽ ወደሚገኘው የእንግሊዞች ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተላከ፡፡
በቪክቶሪያ ኮሌጅም ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ባስመዘገበው የላቀ ውጤት በስኮላርሽፕ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ስኮትላንድ ኤደንብራ ዩኒቨርስቲ አቀና፡፡ በወቅቱም ህግ እንዲያጠና ከትምህርት ሚኒስቴር ቢነገረውም አሻፈረኝ ብሎ የህክምና ኮሌጁን ተቀላቀለ፡፡ ትምህርቱን እንደጨረሰም ፈጥኖ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ …
[ከዚህ በኋላ ‹‹አንተ›› ማለቱን ትተን ‹‹አንቱ›› ማለት እንጀምራለን]
በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት እውቁ አርበኛ ደጃዝማች ፀሐይ እንቁሥላሴ ዶ/ር ዓስራትን አስጠርተው የጤና ሚንስትርነቱን ቦታ እንዲይዝ ይጠይቋቸዋል፡፡ ዶክተር ዓስራት ግን ‹‹አይሆንም!›› ሲሉ ተቃወሙ፡፡ በዚህም የተነሳ የልዕልት ጸሐይ ኃ/ሥላሴ ሆስፒታልን ተቀላቀሉ፡፡ በሆስፒታሉም ለአምስት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ታላቋ ብሪታኒያ አቀኑ፡፡
ኤደንብራ ዩንቨርሲቲ ገብተውም የቀዶ ጥገና ህክምናን አጠኑ፡፡ ዶ/ር ዓስራት በቀዶ ጥገና ህክምና ዘርፍም አስራት የመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ሐኪም ሆኑ፡፡
ዶክተር ዓስራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆስፒታል እውን አደረጉ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋምም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት ዶክተር አስራት ነበሩ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም ዶ/ር ዓስራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የሕክምና ት/ቤቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን (Dean) ሆኑ፡፡ በደርግ ወቅትም በካድሬዎች ይደረግባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሐገራቸውን ሳይለቁ ህዝባቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዶ/ር ዓስራት በወቅቱ በተደጋጋሚ ወደ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፤ የሄዱባቸውንም ዘመቻዎች በብቃትና በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በ1968 እና በ1969 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል፣ አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቐለ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዶ-ጥገና ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዶ/ር ዓስራት በህክምናው ዘርፍም ‹‹አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል›› እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴም የግል ሐኪም ነበሩ፡፡ ፕ/ር ዶ/ር ዓስራት በ1985 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩ ከ40 በላይ አንጋፋ ምሁራን መካከል አንዱ ነበሩ፡፡
የደርግ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ ፕ/ር ዶ/ር ዓስራት ወደፖለቲካ ያዘነበሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በሽግግር መንግሥት ምስረታው ወቅት ተወካይ ያልነበረውና በየአካባቢው አሳዛኝ ግፍና በደል ማስተናገድ የጀመረው የዐምሐራ ሕዝብ ተወካይ እንዲኖረው በማሰብ ሁኔታው ካሳሰባቸው ሌሎች ምሁራን ጋር በመተባበር ታኅሳሥ 2 ቀን 1984 ዓ.ም ‹‹የመላው ዐምሐራ ህዝብ ድርጅት (መ.ዐ.ህ.ድ)››ን መሰረቱ፡፡
ከዚህ በኋላ የነበረው የፕሮፌሰር ዶክተር ዓስራት ወልደዬስ ሕይወት መታሰርና መፈታት ብቻ ሆነ፡፡ የሚከሰሱበት የወንጀል ዓይነት፣ እስር ቤትና ፍርድ ቤት የሚመላለሱበት ጊዜ መብዛቱ እጅግ ያስገርም እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ፕሮፌሰር አስራት ከ150 ጊዜያት በላይ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል ይባላል፡፡
በእስር ላይ ሳሉ ያጋጠማቸው የጤና መጓደልም አዳከማቸው፡፡ ለብዙ ሰው መድኃኒት የሆኑት ጀግና ሰው መድኃኒት ተከለከሉ፡፡
የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም ታህሳስ 18 ቀን 1991 ዓ.ም ወደ ውጭ ሐገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ፡፡ ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላም ወደ አሜሪካ ተጓዙ፡፡
ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ግዛት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ‹‹ባልታወቀ ምክንያት›› ህመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ፡፡
በመጨረኃም ሞትን ድል ሲያደርጉ የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ አርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ፡፡ በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የዓለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተውት ነበር፡፡
(ምንጭ ፡ ልዩ ልዩ)
90ኛው የፕ/ር ዶ/ር ዓስራት ወልዴስ የልደት መታሰቢያ የሚዘከረው እርሳቸው የተሰውለትን ትልቅ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከሕልፈታቸው በኋላ የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲ (“የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/ዐብን – National Movement of Amhara/NAMA”)  በተመሰረተበት ማግሥት ነው፡፡
Filed in: Amharic