>

ቡዳን "ቡዳ" ስትላት "እንዴት አወቅክ ቡዳ!" ትለሃለች!!!  (ደረጄ ደስታ)

“ስድብሽና ስድቤ እኩል ነው ትርፉ ሰው መስማቱ ነው”– ይባላል። ዛሬ በኢትዮጵያ እየሆነ ላለው ሁሉ ሰዎቹን ተጠያቂ እያደረግን ነው። እነሱ ትናንት ነገረ ዓለሙን ሁሉ አሸባሪ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ የአገር ክህደት፣ እያሉ ያገኙትን ሁሉ ሲከሱ እንደኖሩት ዛሬ የአፋቸው የግብራቸውን እያገኙ ይመስላል። ክፉ ነገር ሁሉ እነሱ እየሆኑ ነው። ሰው ሲገዳደል እነሱ ሁከት እነሱ ምቀኝነት እነሱ ተቃውሞ እነሱ እየሆነ ነው። ለነገሩ እነሱም ለዚህ የተመቹ ሆነዋል። ሰው ባወቀው እንዲሰለፍ ቤት ያፈራውንም እንዲሰጥ እነሱም ቀና ነገር አልወጣ ብሏቸዋል። “እነሱ!” መባላቸው እኛ እኛ እኛ ማለትን ከሌሎቹ ልቀው በማብዛታቸው እንጂ ሌላው ያልሆነውን ጎሰኝነት በማሳየታቸው አይደለም። ግን አገር ጎሰኝነት በሽታ ነው፣ አንድነትና ፍቅር መድሃኒት ነው ብሎ ሲሰለፍ እነሱ ሰልፉን ለማደናቀፍ እንደታሪካቸው ቀድመው መገኘታቸው ነው። ቡዳን “ቡዳ ስትላት እንዴት አወቅክ ቡዳ ትለሃለች” እንደሚባለው ሸጠው የጨረሱትን ፣ ክደው የወጉትን አገር መልሰው ሊከሱበት አፋቸውን ሲከፍቱ መስማት ያማል። እሚሸጥ ነገር የለም እንጂ  ነገራቸው ሁሉ መኪናውን የሸጠ መለዋወጫው (ስፔር ፓርት) ለምን ይሸጣል? ብሎ ዘራፍ እንደሚለው ሰው ይመስላል። ለዚያም ሀሳብ አቅርበውና ገፋፍተው ያስወሰኑትን ውሳኔ አሻሻጡን እንጂ ሽያጩን አልተቃወምንም በሚል የድርቅና መግለጫቸው ሲንተባተቡ መስማት ያስጠላል። “እሚነዛብን ጥላቻ በአሸኳይ ሊቆም ይገባል” እሚል ማስጠነቀቂያ ሲሰጡ፣ እነሱ ፍቅር ሲዘሩ፣ አበባ ሲበትኑ፣ ሰው ሲያፋቅሩ የኖሩ ያስመስሉታል። አገር ሸጠው ባገኙበት ገንዘብ ለህዝባቸው ጠላት ሲገዙበት ኖሩ እንጂ ሌላ ምን አደረጉለት? እስኪ ሄደው ተረባርበው የተኙበትና ያፈኑትን ህዝባቸውን ይልቀቁትና እሚለውን እንስማ!
እውነት የትግራይ ህዝብ ወዷቸው ከሆነ፣ እውነት የትግራይ ህዝብ ያለነሱ መሪ ማፍራት አቅቶት ከሆነ፣ እውነት የትግራይ ህዝብ “የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን ድንቅ መሪዎቼን ያድንቅልኝ፤ በስሜ አስረው ሲገርፉትና ሲጠብሱት በኖረው ኢትዮጵያዊ ስም ሸልማችሁ እንዲያውም ከቻላችሁ ወደሥልጣንና ሌብነታቸው መልሳችሁ አንግሡልኝ..” ብሎ ከሆነ ልቀቁትና እንስማው። ለነገሩ እንኳን ሮጣችሁ ጓዛችሁን ጠቅልላችሁ የሠፈራችሁበት የትግራይ ህዝብ ቀርቶ ዛሬ ወላይታም ሆነ ወልቂጤ መኖር የለባችሁም። የበተናችሁት መርዝ እናንተን ወክሎ ሥራውን እየሠራ ነው። ሌላው በተጋደለ እናንተን ተጠያቂ የማድረጉ ምክንያት ኖራችሁም ሄዳችሁም የበተናችሁት የዘረኝነት መርዝ ሥራውን መስራቱን ስለሚቀጥል ነው። እንግሊዞች ቀብረውት የሄዱት መርዝ ዘመን እንደማያነጻው፣ የናንተም ገና የትና የት መርዞን ይቆያል። በጣም እሚገርመው ነገር “ኢትዮጵያ ያለኛ ትበታተናለች” እሚለው ዛቻችሁ ነው። እሱንኮ አምነናል። ኖራችሁም ያው ሆኖብን እንጂ ስትሄዱ የአጥፍቶ ጠፊነት ጀግንነታችሁን ዘንግተነው አይደለም።
ይልቁንም ይቅር ተባብለን እኛም እናንተም ድነን አገራችንን አገራችሁ ካደረጋችሁ አገራችሁንም አገራችን እናድርጋትና አብረን እንኑር። ከሥልጣን ጋር ወደ ውስጥ መገንጠል ያላማረባችሁ ያለሥልጣን እንዴት ይሆንላችኋል? ከኤርትራ መዋሃድ እያማራችሁ ወደ ኤርትራ ኩርማን መሬት ሄደብን ብላችሁ ምን ያሳብዳችኋል? የአገር ኩባንያዎችን መሸጡንም ድንበር ገምሶ መስጠቱንም ብሔር ለብሔር ከፍሎ ክልል ከልሎ መሸንሸኑንም እናንተ ናችሁ ያመጣችሁት? ስለዚህ መልሳችሁ እናንተኑ በደገፍናችሁ ባቀናነው ስድብ መልሳችሁ አትስደቡን! ሁሉ የተፈጸመው በናንተ እኛ ምን አድርገን እንሰደብ!
Filed in: Amharic