>

አሳፋሪው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ( አበጋዝ ወንድሙ)

                                                                                                                

ከሰኔ 3-5 2010 የተካሄደው አስቸኳይ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ስብሰባውን ከጨረሰ በዃላ ያወጣው መግለጫ፣ምን ለማለት እንደፈለገ በግልጽ ማስቀመጥ የተሳነው ፣የተምታታና አሳፋሪ መግለጫ ሆኖ አግኝቸዋለሁ

የዚህ  አስቸኳይ ስብሰባው አስፈላጊነት እንደተነገረን ከሆነ  በቅርቡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኤርትራ ጋር የቆየውን ችግርና አንዳንድ መንግስት ይዞታ ስር ያሉ ድርጅቶችን በከፊል ለባለ ሀብት አክሲዮን በመሸጥ ላይ ያተኮረ መግለጫን አስመልክቶ ነበር።

ስብሰባው መጨረሻ የወጣው መግለጫ ሁለቱን ጉዳዮች አስመልክቶ መሰረታዊ ልዩነት እንደሌለው

አንደኛኤርትራን አስመልክቶ የተወሰደው ውሳኔም በመሰረቱ የኢትዮኤርትራ ጦርነት ከተጠናቀቀ በዃላ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በአጠቃላይ ለሁለቱ አገራት ወንድማማች ህዝቦች በተለይ ሲባል ስምምነቱን ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሕዝባችንና መላው አባላችንን በማወያየትና በማሳመን እንዲሁም ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ከጎኑ በማሰለፍ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።   ስለሆነም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ በመሰረቱ ከሰላም ፖሊሲያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ውሳኔ መተላለፉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ደምድሟል

ሁለተኛየኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁን የገጠመንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል ከመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል ቴሌ ፣ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች፣ሎጂስትክስና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ የግል ባለሃብቶችን ለማሳተፍ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ  ለማስተላለፍ የወሰነው ውሳኔ ከፕሮግራማችንና ፖሊሲዎቻችን ጋር የማይጋጭ ባለፉት ጉባኤዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎታል።በሚል ያትታል።

የተወሰኑቱ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው። እንኳን እንደ ኢህአዴግ ሃገርን የሚያስተዳድር ድርጅት ይቅርና ማንኛውም ስብስብ ስብሰባ ከመቀመጡ በፊት በስብሰባው ላይ የሚወያይባቸው  አጀንዳዎች ለአባላት እንደሚታደሉና፣ ተሰብሳቢዎቹም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ዝግጅት አድርገው እንደሚመጡ የሚጠበቅ ነው።

ኢህአዴግን አስመልክቶ ደግሞ፣ በስራ አስፈጻሚ ውስጥ የሚሳተፉ አባላት በውይይት አጀንዳዎች ላይ እናት ድርጅታቸው ውስጥ ተወያይተው  የየድርጅታቸውን አቋም ይዘው እንደሚመጡ ግልጽ ነው። በቅርቡ በተካሄደው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ላይ የተሳተፈውና ውሳኔውንም ያጸደቀው፣ ህወሃትን ወክሎ የተሳተፈው ቡድን ከዚህ የተለየ ነገር አድርጎም አንደሆነ አላሳወቅም ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ያወጣው መግለጫ ውሳኔዎቹንተገቢና ወቅታዊናቸውም ይላል።

ሂደቱ አንዲህ ሆኖ እያለ፣ አሁን ዋና ጥያቄ መሆን ያለበት፣ ለምንስ ነው ታዲያ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ  ስብሰባ የጠራው ? አሁንስ ደግሞ ምን ይሁን ብሎ ነው አስቸኳይ የኢህአዴግ ሥራ ስፈጻሚና ምክርቤት  ስብሰባ ካልተጠራ የሚል ጥያቄ የሚያቀርበው ነው።

ህወሃት ያካበተው ሃብትና ጡንቻ ቢኖረውም የአምላክ ታናሽ ወንድም አድርጎ የሚቆጥረው መሪው መለስ ከሞተ በዃላ፣ ግራ የተጋባውና ውሉን የሳተ ድርጅት ሆኖ ከርሟል። ወትሮም ሃገራዊ እይታውና ራአዩ የተንሸዋረረ የነበረው ድርጅት ወደባሰ አዘቅት እየተጓዘ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የዛሬ ስድስት ወር ግድም ሰላሳ ቀን ፈጅቶ የተካሄደው ጉባኤ ድርጅቱን ጭሩሱኑ ወደ አውራጃ ድርጅትነት ያወረደው ኩነት ተጠቃሽ ነው።

የህወሃትን መሪዎች  ልብ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በሀገራዊ ጉዳይ ስም የተሰበሰበው ማእከላዊ ኮሚቴ መግለጫ በኔ እይታ መታየት ያለበት፣ ኢህአዴግ ውስጥ ያለው አዲስ አሰላለፍ፣ ከዚህ ቀደም የነበረውን የበላይነት ስላቀጨጨቤት፣ በዚህም ከቀጠለ፣ የበላይነቱ ሙሉ ለሙሉ ተገፎ ከሌሎቹ አባል ድርጅቶች ጋር እኩል መሆኑና፣ ተጽአኖ መፍጠር የሚችለውም በሃሳብ የበላይነት እንጅ በጉልበት በመተማመን አለመሆኑን ከረፈድም ቢሆን ስለታየውና፣ይሄ ደግሞ የፈጠረበት የበታች የመሆን ስሜትና ስነልቡናዊ ጫና ፣ቢቻል ሁኔታውን ወደቀድሞ ለመቀልበስ እንዲያስችለው፣ አልያም አንዳናድ ችሮታዎችን ለማግኘትና ለመደራደር  ይመስላል።  

ከዚህ አንጻር የውሳኔ አካል ብሎ ያቀረበው መግለጫ ውስጥ የሚከተሉትን እናገኛለን

አንደኛ– ‘በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የኢህአዴግን ህገደንብ እና ተቋማዊ አሰራር ያልተከተሉ የአመራር ምደባዎች እንዲታረሙ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።

እኔ አስከሚገባኝ ድረስ በአዲሱ ጠቅላይ ምኒስቴር የተካሄዱት ምደባዎች የሀገሪቱ ህገመንግስት በሚደነግገውና ባጎናጸፈው ስልጣን የተካሄዱ ምደባዎች እንደሆነ ነው። ምናልባት የህወሓት ማአከላዊ ኮሚቴተቋማው አስራርየሚለው የጓሮ ዱለታና የኢህአዴግነፍስ አባቶችችሮታ አልተሰጠውም ከሆነ፣ ባቡር ከሄደ ትንሽ ቆየት ብሏልና እንድምንም አዲሱን ሁኔታ መላመድ የሚያዋጣው መንገድ ነውና፣ ፈጠን ብሎ ካልተሳፈሩ አዳጋች ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛለድርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሰጥ  የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኗል።

አቋም ተብሎ ከወጣው መግለጫ ለኔ ከሁሉ አሳፋሪ አንቀጽ ይሄኛው ነው። የህወሃት ነባር አባላት ተብለው እውቅና እንዲሰጥ የሚለው ምንነት ግልጽ ባይሆንም የተባሉት ግለሰቦች በተለይ ስብሰባው እንዲካሄድ ገፊ  ምክንያት በተባሉት ሁለት ጉዳዮች ማለትም ኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነትና ኤኮኖሚውን አስመልክቶ፣ ሚናቸው እጅግ አሳፋሪ ፣ጠንከር ሲልም በክህደትና በሌብነት ሊይስጠይቃቸው የሚችል መሆኑ ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው።

ስዩም መስፍን፣ ስብሐት ነጋ ፣(አጎብድዶ ከተመለሰ በዃላ) ደግሞ አባይ ጸሃዬ…. ወዘተ አብዛኛው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የአልጀርሱን ስምምነትተንበርካኪና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥበመሆኑ ልንቀበለው አይገባም ብለው ሲከራከሩ፣ ከመለስ ጋር አብረው በህገወጥ መንገድ በካድሬ ሆሆታ ከድርጅቱ ጭምር እንዳበረሯቸውና ፣ስምምነቱን እንደፈረሙ የምንዘነጋው አይደለም።

ከዚህም በላይ ስዩም መስፍን በአልጀርስ ድርድር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ፣ የሀገር ውጭ ጉዳይ ምኒስቴር ተብሎ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ፣ ውሳኔውን አስመልክቶ ከአንድ የመንደር ወሮበላ የማይጠበቅ ተራና አጭበርባሪ  ቅጥፈት የተሞላው መግለጫ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያቀረበና ህዝብን ለማወናበድ የሞከረ ከአጠቃላይ ደካማነቱ በላይ በዚህ ስራው ብቻ ከስልጣኑ መነሳት የነበረበት ጉድ ነው።

አባይ ጸሃዬ ደግሞ ከትምክህተኛ፣ አድርባይና ከሃዲ አቋሙ በላይ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን የበላይ ሹም ሆኖ ሀገራችንን በቢልዮን ብሮች ለሚቆጠር ኪሳራ የዳረገ፣ ሲሆን ፍርድ መቆም የሚገባው ግለሰብ አንጂ ልዩ እውቅና የሚገባው አይደለም።  

አቦይ ስብሃትም ቢሆኑ የኤፈርት ዋና ሆነው ምን አደረጉ የሚለው ምናልባትም ወደ ፊት ግልጽ የሚሆን ይሆናል እንጂ ካገኙት በላይ እውቅና የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ መቀጠልም ይቻላል፣ግን አስፈላጊ ስላይደለ እዚሁ አቆማለሁ ።

አሳ ጎርጓሪ ነገር እንዳይሆን ለሰላምና ለይቅር ባይነት ሲባል ነገሮችን እንዲሁ መተው አዋጭ መንገድ ነውና የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ሊገነዘበው ይገባል።

 ሶስተኛ ደግሞ ትንሽ ህዝቡን ለመሸንገያበኢትዮኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብና ሚሊሻ ላለፉት 20 አመታት ከኑሮአቸውና ከስራቸው ተፈናቅለው……… ለከፈሉት የማይታመን መስዋአትነት……..ድርጅታችን ኢህአዴግ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን በቂ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚገባ ወስኗል።

የሻአቢያን ትንኮሳና ወረራ አስመልክቶ በተካሄደው ጦርነት የአካባቢው ህዝብ ብቻ ሳይሆን 10ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከኑሮ መፈናቀል ብቻ ሳይሆን ምትክ የሌለው ውድ ህይወታቸውን ገብረዋል።

በወቅቱ መለስ የሚያሽከረክረው ህወሃት ግን ደማቸውን መና ያስቀረና የሀገራችንን መሰረታዊ ጥቅም የማያስከብር ስምምነት በመፈረሙ፣ በድንበር አካባቢ ያለው ህዝብ ላለፉት 20 አመታትበለጠ ስቃይ መዳረጉ የማይካድ ነው።

እኔ እስከሚገባኝ ያሁኑ ውሳኔ ለአመታት የዘለቀውን ኪሳራ ማቆሚያ አበጅተን ህዝቡንና አካባቢውን ከጦርነት ቀጠናነት አውጥተን  ሰላማዊ ኑሮውን የሚቀጥልበት መንገድ እንፈልግ የሚል ነው።  ማናቸውም የመንግስት ውሳኔ ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ  የህዝብ ይሁንታ ያስፈልገዋልና፣ ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ በፊት ግን ሰፊ ጥናትና ምክክር እንደሚያስፈልጋቸው እኔም የማምንበት ነው።

ከዚህ ውጭ ግን ለመበጥበጥ ካልሆነ  አስቸኳይ ስብሰባ የሚያስጠራ አንዳችም አሳማኝ ምክንያት ስለሌለ የህወሃት አመራር ሀገር ከሚያምስ ተግባር ቢቆጠብ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ

  

 

Filed in: Amharic