>

ቋንቋና ብሔራዊ ኩራት (ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ)

የጥንት አገሮችን እንመልከት። በጽሕፈት የሚገለጥ ቋንቋ አላቸው። ቅኝ ገዢዎች ሥር ቢወድቁም እንኳን፥ ቋንቋቸውን አለቀቁም። ኢትዮጵያም ክፍሏ ከጥንት አገሮች ጋር ስለሆነ፥ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ ቋንቋን በጽሕፈት ትገልጥ ነበረ። ብዙ ቋንቁዎች ባሉበት አገር አንድ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ የሚሆነው በቤተ መንግሥት የሚነገር ሲሆን  ነው። በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ  ውስጥ ግዕዝና አማርኛ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ ለብሔራዊ ቋንቋነት የተለያየ መንገድ ይዘው አገልግለዋል። ግዕዝ በጽሕፈት፥ አማርኛ በቃል ሁለቱም አገሪቱን ሲያገለግሉ ለረዥም ጊዜ ቆይተው፥ አንድ ዘመን ሲደርሱ፥ ግዕዝ ቤተ ክህነትን አማርኛ ቤተመንግሥትን በጽሕፈት እንዲያገለግሉ ታሪክ ወሰነላቸው።
አማርኛ ከነገድ ቋንቋ ወደ ብሔራዊ  ቋንቋ ሲያድግ የነገድ ቋንቋነቱን ሳይለቅ ነው። ለምሳሌ፥ ግዕዝ ብሔራዊም የነገድም ቋንቋ ነበር። ነገዱ ሲጠፋ (ማለት የአባላቱ አፍ መፍቻ ቋንቋ ግዕዝ የሆነ ነገድ፥ ነገደ አግዓዚ ሲጠፋ)፥  ግዕዝ የሀገር አቀፍ ቋንቋ ብቻ ሆነ። የነገድ ቋንቋነቱን አጣ። አማርኛ ግን አማራ የሚባል ነገድ ስላለና ነገዱ ቋንቋችን ነው ስለሚል፥ ሁለቱንም ማዕርጎች እንደያዘ ነው፤ ማለት፥ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የብሔረ ኢትዮጵያና የነገደ አምሐራ ቋንቋ ነው። የአጼ ዮሐንስና የመኳንንታቸው የሥራ ቋንቋ አማርኛ የነበረው በነገድ ቋንቋነቱ ሳይሆን በብሔረ ኢትዮጵያ ቋንቋነት ማዕርጉ ነው።
ነገደ አምሐራም ልክ ነገደ ግዕዝ፥ ነገደ ሐርላ እንደጠፉ ቢጠፋ፥ የነገድ ቋንቋነቱን ማዕርግ ያጣ ነበር። ይህ ባለመሆኑ፥ አንዳንድ የነገድ ቋንቋ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስለ አማርኛ ሲወሳ የሚታያቸው የነገድ ቋንቋነቱ ብቻ ሆነ። የአማሮች ቋንቋ ከኛ ቋንቋ በምን በልጦ ነው በነገድ ቋንቋነቱ ላይ የብሔራዊ ቋንቋነት ማዕርግ የተጨመረለት ማለት ጀመሩ።  ከነገዳቸው  ቋንቋ ጋር እያወዳደሩ ታሪክ የሰጠውን ማዕርግ መጋፋት ጀመሩ።   ምናልባት አማሮችም አማርኛ የብሔረ ኢትዮጵያ መሆኑን የሚደግፉት ታሪክ የሰጠው ማዕርግ ለማስከበር ሳይሆን፥ የነሱ ነገድ ቋንቋ  የብሔረ ኢትዮጵያ ቋንቋ ስለሆነላቸው ሊሆን ይችላል። “የኔ አባት ካንቺ አባት ይበልጣል” የልጆች ጫወታ።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሀገር ቋንቋ መናገር በሚያኮራ የሀገር ታሪክ መኵራት መሆኑን ለግብጽ ባለሥልጣናት በአማርኛ በመናገር አስመስክሯል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የጣሉ ኀይሎች አብረው የጣሉትን ክብር አነሣልን፤ አከበረን። አንዳንድ ሰዎች ሊደልለን ነው ይላሉ። የምንፈልገውን ካደረገልን ይደልለን። የመናገርና የመጻፍ መብታችንን እያስከበረ ይደልለን። የሚቀጥለውን ምርጫ ርቱዕ እያደረገ ይደልለን። የባሕር ኃይላችን እያጠነከረ ይደልለን። አሰብን በውድም በግድም እያስመለሰ ይደልለን። በዘር ማጽዳት ወንጄል መፈጸምን እያቆመ ይደልለን። ኢሕአዴጎች በዶክተር ዐቢይ ፊታውራሪነት ቀናውብ ብሔራዊ መንገድ እየያዙ ይደልሉን። ኢሕአዴጎችን የምጠላቸው በማነታቸው ሳይሆን በሚፈጽሙት ብሔራዊ ወንጀል ነው።
ዶክተር ዐቢይ የግብጽ ንግግሩን ሲጀምር፥ “አሰላሙ ዐለይኩም ወረሕመቱ አላሂ ወበረከቱ” ብሎ ነው። “ሰላም፥ የእግዚአብሔር ምሕረት፥ በረከቱም እናንተ ላይ ይረፍ” ማለቱ ነው። አንድ እንግዳ በአስተናጋጆቹ ቋንቋ ያን ያህል ሲናገር መስማማትን የሚያጠናክር ቁልምጫ ነው፤ ያስደስታል። የደቡብ አፍሪካ ዘፋኝ ማሪያ ማኬባ አዲስ አበባ የመጣች ጊዜ፥ ለዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪዎች፥ “አልማዝ ምን ዕዳ ነው” ብላ ስትዘፍንላቸው፥ የደስታ ድምፃቸው የአዳራሹን ግድግዳ ሊሰነጥቀው ደርሶ ነበር።
ዶክተር ዐቢይ ታሪኩን አልሰማ ይሆናል እንጂ፥ እስላሞች ንግግሩን እንደሚያደርጉት፥ “ቢስሚላሂ አራሕማን አራሒም” ብሎ ሊጀምር ይችል ነበር። ይኸን ሐረግ ለዐረቦች የሰጠናቸው እኛ ነን። ትርጕሙና መሠረቱ፥ የኛ መጻሕፍት፥ “በስመ እግዚአብሔር መሐሪ ወመስተሣህል” የሚሉት ነው። እኛ ታሪካችንን በምንተርክበት ጊዜ ከዚያም አልፈል ለዐረቦች መጻፍ ያስተማርናቸው እኛ መሆናችንን ልናስረዳ እንችላለን። ክቡር ቁራን  ውስጥ ብዙ የግዕዝ ቃላት እናሉ የሚያሳየውን የጥናት ውጤት መጥቀስ አንችላለን።
ግን ጠቅላይ ሚኒስቴራችንን አደራ የምንለው አንድ ጉዳይ አለን፤ እንደ ራዲዮ፥ ቲያትር፥ ወዘተ. ካሉ ዓለም ከተቀበላቸው የውጪ ቃላት አልፎ በአማርኛ ውስጥ የእንግሊዝ ቃል በመሰግሰግ አማርኛኝን እከክ የያዘው አካል ማስመሰሉን ያስቀርልን።
ሲጨንቀው የሚጠራው፥ ሲሰማው የሚያመሰግነው የኢትዮጵያ አምላክ ለኢትዮጵያና ለሱ የምንጸልየውን ጸሎታችንን ይስማልን፤ አሜን።
Filed in: Amharic