>

የሽግግር መንግስት አስፈላጊነት!??! (ዶ/ር ሰማሃኝ ጋሹ)

አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘዉ የለዉጥ ሂደት በተቃዋሚዉ ሃይል በኩል ሊወሰዱ ስለሚገባቸዉ እርምጃዎች የተለያዩ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ። በአንድ በኩል ዶ/ር አብይ እየወሰዳቸዉ የሚገኙት እርምጃዎች አበረታች  በመሆናቸዉ እሱን እየደገፍን የተሻለ ለዉጦች እንዲደረጉ ግፊት እናድርግ የሚል ነዉ። የእነዚህ ወገኖች  መከራከርያ በኢትዮጵያ ያሉት  የፖለቲካ ሃይሎች ያላቸዉ የፖለቲካ ፕሮግራም የተለያየ በመሆኑ የሽግግር መንግስት ይመስረት ቢባል አብረዉ መስራት አይችሉም የሚል ነዉ። በሌላ በኩል አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዋቂ የሰበአዊ መብት ታጋዮች የሽግግር ፥ የጥምር ወይም ባለ አደራ መንግስት መመስረት አለበት የሚል አቋማቸዉን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፥ መድረክና በቅርቡ የተመሰረተዉ የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ንቅናቄ ይገኙበታል።  ለዚህም ዋናው መከራከርያቸዉ ላለፉት 27 አመታት ስልጣን ላይ የቆየዉ መንግስት በራሱ መንገድ የሚያደርጋቸዉ የለዉጥ እርምጃዎች አስተማማኝና ዘላቂነት ሊኖራቸዉ ስለማይችል ዋና ዋና የፖለቲካ ሃይሎች የተሳተፉበት የለዉጥ ሂደት ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚያግዝና ለዉጡንም ዘላቂና አስተማማኝ ያደርገዋል በሚል ነዉ። እኔም የሽግግር መንግስት ማቋቋም ያስፈልጋል  ከሚሉት ወገን ስሆን መከራከርያየንም እንደሚከተለዉ አቀርባለሁ።
ኢትዮጵያ ላለፉት 45 አመታት አስቸጋሪ በሆነ የፖለቲካ ቀዉስ ዉስጥ አልፋለች። በተማሪዎች እንቅስቃሴ የተጀመረዉ ‘ የብሄር ጭቆና’ ትርክት በርካታ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲመሰረቱ ምክንያት ሆኑዋል። በተለይ ህወሃት የተከተለዉ የአማራዉን ብሄር እንደ ጨቋኝና ጠላት አድርጎ ያቀረበበት መንገድ አሁን ላለዉ የፌዴራል ስርአት ምስረታ እንደ ዋነኛ ግብአት አገልግሎአል። አማራዉ ጨቋኝ ሌሎች ተጨቋኝ ተደርገዉ የቀረቡበት መንገድ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ብሄሩ በጥርጣሬ እንዲታይና በሌሎች ክልሎች እንደ አገሩ በነፃነት እንዳይኖር የተደረገበትን ሁኔታን ፈጥሮአል። ህወሃት በ 1983 ዓም ባደረገዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደትም ሆነ ቀጥሎ በመጣዉ ህገ መንግስት የማርቀቅና ማፅደቅ  ሂደት ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ሃይሎች እንዳይካፈሉ የተከለከሉ ሲሆን ሁሉም ብሄሮች በተለያየ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲወከሉ አማራዉ ግን በሂደቱ እንዳይወከል ተደርጓል።
ይህ ህገ መንግስትም ሆነ እሱን መሰረት አድርገዉ የተቋቋሙት የፖለቲካ ተቋማትና ክልሎች  በህብረ ብሄራዊነትንና በግለሰብ መብት ላይ የሚያምነዉን ማህበረሰብና የአማራዉን  ህዝብ ጥቅም የጎዳ ነው። እነዚህ የህብረተስብ ክፍሎች ሳይወከሉ የፀደቀዉን ህገ መንግስት ብትወዱም ባትወዱም ተቀብላችሁ ቀጥሉ የሚል ለዴሞክራሲ እታገላለሁ የሚል የፖለቲካ ሃይል መኖሩ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ። አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች የሽግግር መንግስት ተመስርቶ መሰረታዊ የህገ መንግስት ለዉጥ እንዳይደረግ የሚፈገልጉት የብሄር የፖለቲካ ሃይሎች ብቻቸዉን የመሰረቱት ስርአት የብሄሬን መብት ከጠበኩት በላይ ያስከበረልኝ ስለሆነ እንዲነካብኝ አልፈልግም ከሚል የመነጨ ነዉ። እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች መረዳት ያለባቸዉ በጣም ከፍተኛ የህበረተስብ ክፍልን በማግለል የተመሰረተ ስርአት ዘለቅታዊ ሰላምና መረጋጋትን የማያመጣና ዉሎ አድሮ አገሪቱን ቀዉስ ዉስጥ የሚከት መሆኑን ነዉ። የአገሪቱን አጣብቂኝ የፖለቲካ ሁኔታ ለመቀየር አንዱና ወነኛዉ መንገድ በዚህ ስርአት ምስረታና ሂደት የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሂደቱ በማሳተፍ ነዉ። ስለዚህ ከላይ የተገለፁትን የህብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ መብቶች ለማስጠበቅ አሁን ያለዉን ህገ መንግስትን የማሻሻል ወይም የመለወጥ እርምጃ የግድ አስፈላጊ ነዉ። ይህንን አይነት መሰረታዊ ለዉጥ ለማካሄድ ደግሞ የግድ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችን ያሳተፈ ውይይትና ድርግር መደረጉ የግድ ስለሚል የሽግግር መንግስት ምስረታ አስፈላጊነትን ያጎላዋል።
እንደዚሁም የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን፥ የህገ መንግስት ጉባኤ አባላት የተመረጡበት መንገድና ህገ መንግስቱ የፀደቀበት መንገድ የተጭበረበረና ህዝብን ያላሳተፈ ነበር። የአንድን ህገ መንግስታዊ ስርአት ቅቡልነት የሚወስነዉ ዋነኛዉ መርህ ህዝብን ያሳተፈ መሆኑና የፀደቀበትም መንገድ ህጋው ሲሆን ነዉ። አሁን ያለዉ ህገ መንግስት ህዝቡን ያሳተፈ እንዳልነበር በመግለፅ የህገ መንግስቱ ጉባኤ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቃቸዉ አይዘነጋም። ይህንን በህገ ወጥ መልኩ የፀደቀ ህገ መንግስት ተቀብላችሁ ለሚቀጥለዉ ምርጫ ተዘጋጁ ማለት ቀልድ ነዉ። ስለዚህ ህገ መንግስቱን በማርቀቅና ማፅደቅ ሂደት ህዝቡ የሚሳተፍበትና በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ህገ መንግስት እንዲኖር ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያሳተፈ የሽግግር ሂደት መኖሩን ግድ ይላል።
 የቀዝቃዛዉ ጦርነት በማብቃቱ ምክንያት ህወሃት ለይስሙላ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የተቀበለ ቢሆንም  በመሰረታዊ ደረጃ ይህ  ህገ መንግስት የህወሃት የፖለቲካ ፕሮግራም ቅጂ ነዉ። በዚህም ምክንያት ህወሃት አገሪቱን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸዉ የተጠቀመበት ሲሆን በዚህም የተነሳ ለረጅም ዘመን ተሳስበዉና ተዋደዉ ይኖሩ የነበር የህብረተሰብ ክፍሎች የጎሪጥ እንዲተያዩ በማድረግ የብሄር ግጭት እንዲባባስና የገሪቱንም አንድነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል። በዚህም የተነሳ በፖለቲካ ሃይሎች መካከል የግለሰብና የብሄረሰብ መብት ማስከበርን፥ ኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሄረሰብ ማንነትን፥ የክልሎች አወቃቀርን ፥ የብሄረሰብ ማንነት በፖለቲካ ተስትፎ ዉስጥ ያለዉን ሚናን  አስመልክቶ ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሮአል። እነዚህን ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች ተነጋግሮ እልባት መስጠት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ለዚህም ነዉ የሽግግር መንግስት መመስረቱ  በአገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት ከፍተኛ እድል የሚሰጠዉ።
ሌላዉ የሽግግር መንግስት ማቋቋም አስፈላጊ የሚሆነዉ ስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት የሚያደርገዉ ለውጥ በአመዛኙ ጥገናዊ ለዉጥ በመሆኑ ነዉ። እስካሁን  በዶ/ር አብይ የሚመራዉ ቡድን ያደረጋቸዉ ለዉጦች ላለፉት 3 አመታት ከነበርንበት ቀዉስ እንድናገግም የረዳና አንፃራዊ መረጋጋትን ያመጣ ነዉ።  በጠ/ሚኒስትሩ የሚወስዱት እርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም ጥልቀት ያለዉ ለዉጥ ያመጣሉ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ዶ/ር አብይ አስቀድመው የለዉጥ ፍኖተ ካርታቸዉን ያላሳወቁ በመሆኑ አገዛዙ ስር ነቀል ለሆነ ለዉጥ መዘጋጀቱን የሚሳይ ማስረጃ የለም። አገዛዙ ስር ነቀል ለዉጥ አመጣለሁ ቢል ስልጣን ላይ የመቆየት እድሉን ስለሚያመነምነዉ ስር ነቀል ለዉጥን በራሱ ተነሳሽነት ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ስር ነቀል ለዉጥ ህገ መንግስቱን የማሻሻል፥ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት  ግንባታ እንቅፋት የሆኑትን እንደ አብዮያዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግስት የሚባሉትን የአገዛዙን ዋና ዋና ርዮታለማዊ መሰረቶች የመለወጥን፥ ላለፉት 27 አምታት የተፈፀሙትን ወንጀሎችና ዝርፊያዎች  በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ማድረግን የመሳሰሉትን ስለሚያጠቃልል አገዛዙ ስር ነቀል ለዉጥን በራሱ ፈቃድ ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም። ለዚህም ነዉ እውነተኛና መሰረታዊ ለዉጦችን ለማካሄድ የሽግግር መንግስት መመስረቱ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚኖረዉ።
ሌላዉ የሽግግር መንግስት መኖርን አስፈላጊ የሚያደርገዉ የሽግግር ፍትህ ( transitional justice) ለማካሄድ የተሻለ እድል መፍጠሩ ነዉ። አንድ በግጭትና ጭቆና ዉስጥ ያላፈች አገር በአለፈዉ  ስርአት የተፈፀሙ ወንጀሎችን በማጣራት ተጠያቂዎችን ለፍርድ በማቅረብ ወይም በምህረትና ይቅርታ ያለፈዉን ታሪክ በመዝጋትና ያ ሁኔታ እንዳይደገም ቃል በመግባት አዲስ ጅማሮን ማድረግ ይኖርባታል። ይህንን መሰረታዊ ሂደት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማካሄድ የግድ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች በሂደቱ ሊሳተፉ ይገባል። ለዚህም የሽግግር መንግስት ምስረታ በጣም ጠቃሚ ነዉ። በአጠቃላይ ከላይ በዝረዘርኳቸዉ ዋና ዋና ምክንያቶች ስርአቱ መሰረታዊ ለዉጦችን ያደርጋል ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ ሂደቱ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች የተሳተፉበት እንዲሆን የሽግግር መንግስት ምስረታ እንዲደረግ ግፊቱ መቀጠሉ አስፈላጊ ይሆናል።
Filed in: Amharic