>

ዶ/ር አቢይ እውን ይህን ሰራዊት ያውቁታል? አይመስለኝም!??! (መካሻ በምህረት)

 
ዶ/ር አቢይ አህመድ የወያኔን ሠራዊት ሰብስበው ትምህርት ሲሰጡ ሰማሁ።ዶ/ር አቢይን እንደአስተማሪ ስመለከት እንደአስተማሪ አንድ ነገር ወደ አእምሮየ መጣ።አስተማሪ ሆኘ ስገባ የምገባብት ክፍል ተማሪዎች የትምህርት ደረጃቸው ምን እንደሆን በቅድሚያ አውቃለሁ።የማስተምረውን ትምህርት ለየትኛው የክፍል ደረጃ እንደሆን በሂሳብ ውስጥ አስገብቸ አዘጋጃለሁ።ሌላው ደግሞ የማስተምራቸው ተማሪዎች ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋና የትምህርት ደረጃቸውን በሚመጥን  የቋንቋ ደረጃ መጠን ይሆናል ብየ አምናለሁና ስሌቴ ይህን አገናዝቦ ይሆናል።
ታዲያ ዶ/ር አቢይ አህመድ ለወያኔ ጄኔራሎች ያዘጋጁትን ትምህርት እስከ ቪዲዮው መጨረሻ ተመለከትኩና የሚከተሉትን ጥያቂዎች እንድጠይቅ አስገደደኝ።ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር የኖረና አሁንም የሚቆጣጠር የወያኔ ሠራዊት እውነት ሠራዊቱ የሚሊተሪ ሳይንስ የማያውቅና እንዲሁ በመላ ምት የሚሰራ ነው እያሉን ነው?ይህ የወያኔ ሠራዊት ሲዋቀር በትግርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ስለሆነ የስብሰባው ቋንቋ ትግርኛ ብቻ እንደሆነ አልተገነዘቡ እንዴ?ለምን አማርኛና እንግሊዝኛ የተቀላቀለበት ቋንቋ ማስተማሪያው እንዲሆን ተፈለገ?በእውነት የወያኔው ሠራዊት የትምህርት ደረጃው የሃያ አንደኛው ዘመን ቴክኖሎጂና ቋንቋ ተክኖበታል ብለው ሊነግሩን ፈልገው ይሆን?የሊቃውንት ቁንጮ የሆኑት አፈሩ ይክበዳቸውና አቶ መለሰ ዜናዊ ነባር የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት አፍርሰው አሁን በሳሞራ ዩንስ የሚመራውን የወያኔ ሠራዊት ሲያዋቅሩ እርስዎ የሚሉትን የሚሊተሪ ሳይንስ በግንዛቤ ሳያስገቡ ነው ብለው ነው አሁን የሚገነባው የመከላከያ ሠራዊት የሚገነባው በምን መልክ እንደሆነ የገለጹልንና ለወያኔ ሠራዊት ያስተማሩት?
 በዚህ አዳራሽ ያሉትን ጄኔራሎች ሁኔት ስመለከት ከፊል ምስል የሚመስሉ፤ከፊል የሚጽፉ ፤ከፊል የሚያንቀላፉ፤ከፊል ከሃይላንድ ጋር ግብ ግብ የገጠሙ ሲሆኑ አንዳንዶቹ እርስዎ እያስተማሩ መቕሌ ደርሰው የውንብድና ሥራቸውን ያሚይውጠነጥኑ፤ከፊሎቹ ደግሞ ከሱማሌ አብዲ ኢሌ ጋር የኮንትሮባን ንግድ እንደሚያካሂዱ የሚያስቡ፤ከፊሎቹ ዶላር ከኢትዮጵያ እንዴት አድርገው እንደሚያሾልኩ መንገድ የሚቀይሱ ይመስላሉ።
ዶ/ር አቢይ አህመድን የምጠይቀው እውነት የኢትዮጵያን የጦር ሠራዊት ያውቁታል?እርግጥ እርስዎ በዚህ መንግሥት ውስጥ ያደጉና የጦር መኮንን ስለሆኑ አያውቁም ለማለት አልደፍርም።ግን እኔ እንኳን ወታደር ሳልሆን፤ከሩቅ ሆኘ ስመለከት አሁን እርስዎ ሰብስበው የሚያስተምሯቸው የወያኔ ጄኔራሎች ትምህርቱን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን ወታደር የሆኑበት መንገድም የእርስዎን ትምህርት የሚረዳና የሚቀበል አእምሮ የለውም።ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከፊት ለፊት ተቀምጦ ስመለከተው ሃውልት ሆኖ ነው ያገኘሁት።ጄኔራል ሁን ተብሎ የሆነ እንጂ ጄኔራል ለመሆን የሚያስችለው ጭንቅላት ስላለው አይደለም።አለቃው የሆነው ጄኔራል ሳሞራ ዩንስ ከእንግሊዝ አገር በሚያገኘው የተልእኮ ትምህርት በመምህሩ ሲጠየቅ መለሰ የተባለውንና የዶ/ር አቢይ አህመድን የሚሊተሪ እስትራቴጂና ታሪክ ሳገናዝብ የሰማይና የምድር ርቀት ያህል ልዩነት እንዳላቸው አስተዋልኩ።ለምን ቢሉኝ መልሴ እንዲህ ይቀርባል።ጄኔራል ሳሞራ ዩንስ መምህሯ አንተ በላከው መልስ ላይ የሰፈረው መልስ ምልካም ነውና ለምን አንተ አትመልስም ብላ ስትጠይቀው እኔ አልሠራሁትምና ለጥያቄሽ መልስ ለመስጠት አልችልም አለ ተብሎ ተነግሮናል።እውነቱን ነው ሂድ ሲባል የሄደን፤ተቀመጥ ሲባል የተቀመጠን፤ጄኔራል ነህ ሲባል የጄኔራል ልብስ የለበሰን ሰው ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ ተማር ማለት ማስጨነቅ ነው።በዚህ መልክ የመጣ ጄኔራል እርሱ ጄኔራል የሚያደርጋቸውን ሁሉ ምን ዓይነት ጭንቅላት እንዳላቸው መገመት አያዳግትም።ይህ ሆኖ እውነታው ዶ/ር አቢይ አህመድ ይህን ዓይነት ትምህርት፤ በዚህ ዓይነት የኖረን የወያኔን ሠራዊት ምን እንዲሆን ፈልገው ነው?እውነት ይማራል ብለው ነው?እውነት ይለወጣል ብለው ለሚገነባው ሠራዊት እያዘጋጁት ነው?
ይህ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ጄኔራል ሳሞራ ዩንስ በጡረታ ሲገለሉ በምትካቸው ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ፤የጄኔራል ሳሞራ ዩንስ ግልባጭ፤ የወያኔ የጦር ኃይል ዋና አዛዥ ሆነው ተሹመዋል።የሚሊተሪው ሳይንስ የሚፈልገው ጭንቅላት ሌላ የተሾመው ጭንቅላት ሳይንሱን የማይሸከም ሆኖ እናገኘዋለን።እዚህ ላይ ያለኝ ፍርሃት ጄኔራል ሳሞራ ዩንስ ወጥተው ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ያንኑ የሃያ ሰባት ዓመት የወያኔ የወታደር ሥርዓት የማይቀጥል ለመሆኑ የሚያመላክቱ ነገሮች ባለማየቴ ነው።ግደለው ፤ቅበረው፤ስረቀው፤ዋሸው፤አሳደው፤ዘርን እየለየህ አውድም፤አበጣብጥ እየተባለ የሰለጠነ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን አለቃው በሕይወት እያለ በራሱ ተማምኖ የእርስዎን ትምህርት በሥራ ላይ ያውላል የሚል እምነት የለኝም።ጄኔራል ሳሞራ ዩንስ እንኳን በሕይወት ባይኖር ብዙ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑሶች በወያኔ ሠራዊት አሉና ጄኔራል ሰዓረ መኮንን የሰው ጥላ ሁሉ የሚያስፈራው ሰው ይሆናል።
ዶ/ር አቢይ አህመድ በትምህርትዎ ውስጥ አንድን የአሜሪካ ጄኔራል በምሳሌ አቅርበው ሳይ አስደነቀኝ።የአሜሪካ ጄኔራል ለወያኔ ሠራዊት ምሳሌ መሆኑ ተገቢና የሚመጥን ሆኖ አላገኘሁትም።ለምን ቢሉኝ በአሜሪካ ጄኔራልና በወያኔ ጄኔራል መካከል ያለው ልዩነት በጠፈር ምርምር ሊቅ በሆነ ሰውና በፊደል ቆጣሪ ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ያህል የሚያሳይ ሆኖ አይቸዋለሁና።ከዚህ ጋር በማያያዝ ይህ የአሜሪካ ጄኔራል ያቀረበውን የምርምር ውጤት አስመልክተው ሲናገሩ የበለጠ አስገረመኝ።ፊደል ቆጣሪ የምርምር መጽሐፍ እንደአሜሪካው ጄኔራል የወያኔ ጄኔራሎች የምርምር ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ሲጠቁሙ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አስባለኝ።ይግረምህ ብለው ደግሞ ሁላችሁም ይህን የአሜሪካ ጄኔራል መጽሐፍ አንብቡት ብለው ተናገሩ።መናገሩ አይከፋም ግን የሚናገሩትን ሰው ማወቅም መልካም ነው።ከእኛ ጭንቅላት በላይ ላሳር ነው ሲል የኖረና አዲሱን የወያኔ ትውልድ ያስተማረ እንደ እርስዎ ካለ አሳብ ሲቀርብ ይቀበላል ለማለት ይከብደኛል።እርስዎ አሁን እደረሱበት ደረጃ እንዳይደርሱ ያለማቋረጥ የዋሸ ሠራዊት ነው።አሁንም ሌት ቀን እየሠራ ነው።ስላልቻለና ካለው ኃይል የበረታ ኃይል ስለመጣበት እንጂ እርስዎን በደስታ የሚቀበል ሠራዊት አይደለም።የሱማሌው የአብዲ ኢሌ ወታደሮች ድርጊት ብዙ ያስተምረናል።ወያኔ የሚመራው የመከላከያ ሠራዊት ሊገታው አልሞከረም።ዶ/ር አቢይ አህመድ የሱማሌ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳላልሆነ አልቀበለውም አለ።በአውሮፕላን ጣቢያ የተለጠፈውን የኢህ አዴግ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፎቶ አወረደ።የመለሰ ዜናዊ ፎቶ ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር?አንድ ትግሬ ሲነካ መላው የወያኔ ሠራዊት ይንቀሳቀሳል እርምጃም ይወስዳል።ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከሱማሌ ክልል ሲፈናቀሉ የወያኔ ሠራዊት ምን አደረገ?በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አማሮች ሲፈናቀሉ የአገርን ሰላም የሚያስጠብቀው የወያኔ ሠራዊት ምን ሠራ?አምባሳደር ስዩም መስፍን መቕሌ ላይ ሲያጓራው የነበረ ለቅሶ ምን ያመለክተናል?እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ።
Filed in: Amharic