>

ግብጽም የአባይ ፖሊሲዋን ቀየረች? (ደረጄ ደስታ)

የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ምኒስትር  ዶ/ር አብይ አህመድና የግብጹን ፕሪዚዳንት አል ሲ ሲን ማለፊያ ንግግር ተከትሎ የግብጽ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ባወጣው መግለጫ “የሁለቱን ሃገራት የመልማት ፍላጎት ባከበረና ያንዳቸውንም ጥቅም ባልተጻረረ መልኩ በአዲስ መንፈስ በጋራ ለመስራት መስማማታቸው” ተዘግቧል።
ግድቡ በአባይ ወንዝ ላይ ስለሚያስከትለው ለውጥ እሚያጠና የሳይንቲስቶች ቡድን ለማቋቋምና የሁለቱም ከፍተኛ የልዑካን ቡድኖች በካይሮ ተገናኝተው እሚነጋገሩበት ሌላ ስብሰባ ለጁላይ 3/2018 ቀጠሮ ተይዟል።
ስብሰባውና ጥናቱ እማያባራ መስሏል። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሳይቋረጥና ሳይቋጭ ቀጥሏል። የዚህ ምክንያቱ የግብጽ ስጋትና ጥርጣሬ መሆኑ ይገመታል። ሁለቱም ወገኖች የመሰብሰቢያ ቦታና አገር እንዲሁም ኮሚቴና አጀንዳ እየቀያየሩ ሲያጠኑና ሲያስጠኑ ዘመን ተቆጥሯል። ይህ ጊዜ መግዛት በግብጽ የተያዘ ስትራቴጂ መስሎ ቆይቷል። ኢትዮጵያም በትዕግስት እልህ ሳትገባ እልህ የማስጨረስ ስትራቴጂን እየተከተለች ግድቧን ለማጠናቀቅ የምትፈልግ መስላለች።
ይህም ሆኖ ግን ከቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች አዲሱ የግብጽ ፕሬዚዳንት ሁለቱም አገሮች ይበልጥ ተጠቃሚ እሚሆኑበትን መንገድ ለማፈላለግ “አንጻራዊ” በሆነ መልኩ የተሻሉ መስለዋል። አንዳንድ ግብጻውያውንም ሁኔታው ጨርሶ አይሞከርም ከሚለው ክርክራቸው ወጥተው እንግዲያውስ ግብጽ ግድቡን ራሷ ተቆጣጥራ ማስተዳደር ይገባታል የሚል ምክርና ፕሮፖዛል እያቀበሉ ነው። በዛሬው እለት በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይትና ስምምነት ግብጽ በአባይ ጉዳይ ላይ ያላትን ፖሊሲ የመቀየር ምልክት ያሳያችበት ነው እያሉ ለመናገር የበቁ የግብጽ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎችም እየተሰሙ ነው። የግብጽ ማዕከላዊ የስትራቴጅክ ጥናትና ምርምር ኃላፊ የሆኑት ሜጀር ጀኔራል Hani Ghoneim ከእነዚህ አንዱ ናቸው።
Hani “ግብጽ በአባይ ግድብ አስተዳደር ውስጥ እጇን ብታስገባ የወንዙን ኃይል ለመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን ሲኖራት አስተዳደሩም ላይ ተሳታፊ በመሆንዋ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገባች ማለት አይደለም። በሌላም በኩል ኢትዮጵያ ግድቡን ለመጨረስ ገንዘብ ስለሚያስፈልጋት ግብጽም ደግሞ በአሰተዳደሩ ተሳታፊ ከሆነች ወጭውንም በመጋራት ኢንቨስት ልታደርግ ስለምትችል ሁሉም ተጠቃሚ እሚሆንበት ጉዳይ ያለ ይመስለኛል በማለት አስተያየታቸውን ለግብጽ መገናኛ ብዙሃን ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ላይ ያላት አቋም ምን እንደሆነ አልተገለጸም። ዛሬም በመሪዋ የተገለጸው አቋም ግን ኢትዮጵያ ምንም ሆነ ምን የግብጽን ፍላጎት የመጉዳት ዓላማ እንደሌላትና የራሷንም ጥቅምና መብት ማስከበር ግን የምትሻ መሆኑን ብቻ ነው። ሁለቱን አገሮች አስተማምኖ ሊያስታርቅ እሚችል ስምምነት ግን ምን ሊሆን ይችላል?
ባለሙያዎችና ስለጉዳዩ እውቀት ያላችሁ ምን ትላላችሁ?
Filed in: Amharic