>

በባድመና የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ዙሪያ (አፈንዲ ሙተቂ)

የኢትዮጵያ ኤርትራ የድንበር ግጭት የተከሰተበት ፍጥነት በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ጭሮ እንደነበረ ይታወሳል። ጥቂት የማይባለው የህብረተሰብ ክፍልም “የድንበር ግጭቱ ለማስመሰል የቀረበ ነው፣ የግጭቱ መንስኤ ሻዕቢያ ከኢትዮጵያ ሲያገኘው በነበረው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ በሩ መዘጋቱ ነው” የሚል እምነት አዳብሮ እንደነበረ ይታወቃል።
ኢኮኖሚውን አስታክከው የተወሰዱት እርምጃዎች ግጭቱን ወደ ሙሉ ጦርነት ቀይረውት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የድንበር ውዝግቡ ከግንቦት 6/1990 በፊትም እንኳ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ሲካሄድ እንደቆየ ከጦርነቱ በፊትና ጦርነቱ ከፈነዳ በኋላ ከህዝብ ዘንድ የደረሱት መረጃዎች ያመለክታሉ። እዚህ ላይ በደንብ የማስታውሳቸውን ሁለት አብነቶች ልጥቀስ።
1. እኤአ በነሐሴ 1996 የሁለቱ ሀገራት የጸጥታ ሀይሎች በድንበር ላይ ተታኩሰው ሰዎች ሞተው ነበር። ይህንኑ ግጭትና በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተመለከተ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ እና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በእጅ የተጻፉ ደብዳቤዎችን ተለዋውጠዋል። እነዚህ ደብዳቤዎች ኦፊሴላዊ ሳይሆኑ ጓደኛ ለጓደኛ የሚጽፈው ዓይነት ነበሩ። ደብዳቤዎቹ ይፋ የሆኑት ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በሁለት ወሩ ይመስለኛል።
ደብዳቤዎቹን ይፋ ያደረገው አካል በግልጽ አይታወቅም። ነገር ግን በኢኮኖሚያዊ አሻጥር ሲከሰስ የነበረው ሻዕቢያ የድንበር ግጭቱ የቆየ መሆኑን ለማስመስከር በኢንተርኔት እንደለቀቃቸው ይታመናል።
በነገራችን ላይ ደብዳቤዎቹ በጊዜው ይወጡ በነበሩ በርካታ የሀገራችን ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ታትመው ነበር (ደብዳቤዎቹ የታተሙበት አንድ የኢትኦጵ መጽሔት ኮፒ አዲስ አበባ በምትኖረው እህቴ ቤት በተውኳቸው እቃዎቹ ውስጥ አለኝ)።
2. በየካቲት/መጋቢት/ ወር የታተመ አንድ የሪፖርተር ጋዜጣ ይዞአቸው ከወጣው ዜናዎች ውስጥ አንዱ ስለድንበር መካለሉ ጉዳይ የሚያወሳ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ይህም ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ከሁለት/ሶስት/ ወራት በፊት ነው።
—-
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ደግሞ ሻዕቢያ ብቻ ሳይሆን የሻዕቢያ ቀንደኛ ባላንጣ የሆነው ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ (ጀብሃ) እና ሌሎች ኤርትራዊያን ተቃዋሚ ድርጅቶችም ባድመ የኤርትራ እንደሆነች ይናገሩ ነበር። በባድመ ህዝብ የተወከሉ አንድ የፓርላማ አባል በኢቲቪ ቀርበው በሰጡት መግለጫ ባድመ በትጥቅ ትግሉ የመጀመሪያ ዓመታት በጀብሃ ይዞታ ስር እንደነበረች መናገራቸውን እናስታውሳለን። ይሁንና ሰውዬው “ጀብሃ ያለ አግባብ ነው የያዛት” ማለታቸውም ትዝ ይለናል። ጀብሃ ደግሞ በወታደራዊ አቋሙ መክኖ እንኳ “ባድመ የኤርትራ ናት” ሲል ነበር። ጀብሃ እንዲህ የሚለው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ ነው።
እነዚህም ሁናቴዎች ውዝግቡ ከግጭቱ በፊት ይታወቅ የነበረ መሆኑን ነበር የመሰከሩልን።
—-
የሁለቱ ሃይሎች መዋጋት አግራሞትን ቢፈጥርም ጦርነቱ በድንገት የተከሰተ አልነበረም። በ1990 የመጀመሪያ ወራት እንኳ ወደ ግጭት የሚወስዱ አዝማሚያዎች እንደነበሩ ህዝቡ ተረድቶ ነበር። በድንበር ጠብ ሳቢያ የተከሰተውን ውጥረት ያባባሱት በ1990 የተወሰዱት ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች ነበሩ። በዚሁ ዓመት መጀመሪያ ላይ በዘመነ ደርግ የወጣው የኢትዮጵያ ብር መለወጡ እና ኤርትራም “ናቅፋ” የተሰኘ ገንዘቧን ማሳተሟ ይታወሳል። በህወሓትና በሻዕቢያ መሪዎች መካከል ውስጥ ለውስጥ ሲካሄድ በነበረው ቁርቋሶ ሳቢያም ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ መጠቀሟን አቁማ ፊቷን ወደ ጅቡቲ ወደብ መልሳለች። ሌሎች በርካታ ምልክቶችም ታይተዋል።
እነዚህን ምልክቶች ያጤኑት የግል ጋዜጦች በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት መፈንዳቱ እንደማይቀር ተንብየዋል። ታዲያ የኢህአዴግ መሪዎች የሀገሪቱን የመከላከያ ሃይል በማደራጀት ሳቢያ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ወደ ማጥላላቱ ነበር የገቡት። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለእፎይታ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ “በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ግጭት የለም፣ ግጭቱ ያለው በትምክህተኞች ጭንቅላት ውስጥ ነው” ማለታቸውን እናስታውሳለን።
—-
በዚህ ረገድ የኢህአዴግ መሪዎች ብዙ ነገር ዋሽተውናል። አንደኛ የድንበር ውዝግቡ የቆየ መሆኑን እያወቁ በአንድ ጀንበር የተከሰተ አስመስለዋል። ሁለተኛ በሻዕቢያ ላይ ያላቸውን ቁጭትና የቆየ ቁርሾ በድንበር ግጭቱ በማስታከክ ለመወጣት ሞክረዋል። ሶስተኛ የድንበር ውዝግቡንና ከሻዕቢያ ጋር የነበራቸውን የኢኮኖሚ ንትርክ አንድ ላይ በመቀላቀል ህዝቡን ለጦርነት አነሳስተውበታል። አራተኛ ባድመ ስለምትባለው ወረዳ የተጋነኑ ወሬዎችን ኢንፎርማል በሆነ መንገድ በመልቀቅ የጦሩንና የህዝቡን ስነ ልቦና ለመሰለብ ሞክረዋል (ለምሳሌ: “ባድመ ወርቅ አላት፣ ነዳጅ አላት፣ የተትረፈረፈ የድንች ምርት ታመርታለች ወዘተ)። አምስተኛ ከአአድና ከአሜሪካ መንግስት የመጣውን “Technical arrangements” አንቀበልም በማለት ነጋሪት እየጎሰሙ ጉዳዩን በጦርነት ብቻ ለመጨረስ ወስነዋል። ስድስተኛ በጦርነቱ አማራጭ ተጉዘው በባድመ እና በዛላንበሳ ድል ካደረጉ በኋላ እንደገና ተመልሰው በጠረጴዛ ዙሪያ ተደራድረዋል። መሬቶቹ የኛ ናቸው ብለው ካመኑ እነርሱን ካስመለሱ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ብቻ ነበር መፈረም የነበረባቸው። በደምና በመስዋትነት የተመለሰ መሬት ለድርድር አይቀርብም።
—-
የኢህአዴግ መሪዎች የፈጸሙት ወንጀል ከዚህም በላይ ነው። ለምሳሌ በግንቦት ወር 1992 የኢትዮጵያ ጦር በምዕራብ ኤርትራ የሚገኙትን ባሬንቱንና ተሰነይን ከፍተኛ መስዋእትነት በጠየቀ ውጊያ ተቆጣጥሮ ነበር። የአሜሪካና የአውሮጳ ጩኸት ሲበረታ ከተሞቹን ለቆ ወጣ። ሻዕቢያ “የኢትዮጵያን ጦር ያባረርኩት እኔ ነኝ” የሚል ፕሮፓጋንዳ ሲያፋፍም ግን ጦሩ እንደገና በትልቅ መስዋእትነት ወደ ኤርትራ ገብቶ ከተሞቹን ያዘ። “ለምን ይህንን አደረግክ” ሲባል መሪዎቻችን “ሻዕቢያ ከከተሞቹ አባርሮን እንዳልወጣን ለማሳየት ነው” የሚል የህፃን መልስ ሰጡ። በጦርነቱ የሚማገደውን የደሃ ልጅ እንደ ጭራሮ ነበር የቆጠሩት።
—–
ወዳጆቼ! 
የባድመ ጉዳይ የተበላ እቁብ ሆኗል። ባድመን እና ሌሎች ግዛቶችን ያስረከቡት የአልጀርሱን ስምምነት የፈረመው መለስ ዜናዊ እና የህወሓት ጓዶቹ ናቸው።
ይህንን አጭር ጽሑፍ ስጽፍ ሻዕቢያ በጦርነቱ ዘመን ሲያሳይ የነበረውን ድንቁርና፣ በሀይደር ት/ቤት በሚማሩ ህፃናት ላይ ያካሄደውን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ፣ “ከባድመ ከወጣን ጸሐይ ጠለቀች” በማለት የተኩራራበትን ትዕቢት ወዘተ አልዘነጋሁትም። ነገር ግን ያቀረበው ማስረጃ ይግባኝ በሌለው ፍርድ ቤት አሸናፊ መሆኑ ተመስክሮለታልና ከእንግዲህ ብንዘረጥጠው ምን ልናመጣ እንችላለን?
የጦርነቱ ታሪክ ሲጻፍ ሁሉንም መዘርዘር ይቻላል። አሁን ለደረስንበት ችግር የሚወቀሱት ግን ለዘመናት የሀገራችንን ፖለቲካ ሲያሾሩ የነበሩት ህወሓቶች ናቸው። በተለይም ህወሓቶች የባድመን ጉዳይ ሲያሽከረክሩ የነበሩት ለብቻቸው እንደሆነ እነ ተወልደ ወ/ማሪያምና ስዬ አብረሃ ነግረውናል። ስለዚህ ኃላፊነቱ የመለስ ዜናዊ እና የነርሱ ነው።
Filed in: Amharic