>
5:13 pm - Saturday April 20, 1748

ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ወደ አዘቅት እየወሰዳት ነው!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

በፓርቲና በመንግስት መካከል ለወጉም እንኩዋ ድንበሩ የጠፋባት ሃገር ኢትዮጵያ ናት። ዛሬ ኢህአዴግ መንግስትን ወክሎ የሚንስትሮች ም/ቤትም ሆነ ፓርላማው ሳያስፈልገው የመንንግስትን ፖሊሰ ‘ለውጥ’ ያለውን አሳውቆናል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ዛሬ ለአስር ዓመት የኢትዮጵያን ጥሪት አሙዋጠው እሱም አልበቃ ሲል በእርዳታና በብድር ሃገራችንን እስከ አንገቱዋ አስምጠው ለስልጣንና ለዘረፋ ሲሉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ GTP 1 እና GTP2 ብለው የወጠኑት ሜጋ ፕሮጀክት በፖሊሲ ክሽፈት በመውደቁ ሳያፍሩ ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወር ወስነናል አሉ። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙና ሃገሪቱዋን አላላውሳት በማለቱ ቴሌና መብራት ሃይል መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዶ እድሜ ማራዘሚያና ትንፋሽ መግዣ ቢሆን ተብሎ ለግል ባለሃብቶች ክፍት እንዲሆን ተብሉዋል።በተጨማሪም የፈረንጆችን ልብ ለማራራትና ዶላር ለመለመን ይመስላል በየዓመቱ የፓርላማ መክፈቻ ማድመቂያ የሆነውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት የነበረውን ፖሊሲ ብዙም ሳይለወጥ የአልጀርሱን ስምምነት በመርህ ደረጃ ተቀብለናል ይባል የነበረውን የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ እናደርጋለን በሚል ተተክቶ በድጋሜ እናረጋግጣለን በሚል አዲስ ማደናገሪያ ይዘው ብቅ ብለዋል።
ለእኔ ይህ ሁሉ መደናበርና ግራ መጋባት የሚያሳየኝ የኢህአዴግ መስመር ሙሉ በሙሉ መክሸፉንና የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዴግ አቅም በላይ መሆኑን ነው። ኢትዮጵያን ካለችበት አዘቅት ለማውጣት አዲስ የችግር አረዳድና የመፍትሔ አቅጣጫ ያስፈልጋታል።የፈረንጅን ልብ ለማማለል የሚደረግ ምልክትን የማከም ዘዴ ችግርን ከማከማቸት ያለፈ ፋይዳ የለውም።
Filed in: Amharic