>
5:13 pm - Monday April 19, 4877

‹ሽብርተኝነት›፣ በነጻነት አዋቂው አንዳርጋቸው ተበጣጠሰ! (ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ)

‹ሽብርተኝነት›፣ በነጻነት አዋቂው አንዳርጋቸው ተበጣጠሰ!

(ቦሌ፣ ኦሎምፒያ በደስታ ተናጠች!)

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ 

(ግዮን መጽሄት)

ስለታጋዩና ፖለቲከኛው አንዳርጋቸው ጽጌ ለመጻፍ ‹‹ከየት ልጀምር?፣ ከየቱስ ጀምሬ የቱ ጋር ልቋጭ? …›› በሚለው ሀሳብ ውስጤ መናጡ አልቀረም፡፡ ስለአንዳርጋቸው የትግል እንቅስቃሴ በዝርዝር የሚያጽፉ አንኳር ርዕሠ ጉዳዮች እጅግ ብዙ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ የአንዳጋቸው የፖለቲካ ጉዞ ብዙ መጽሃፎችንም ያጽፋል፡፡ እኔም በዚህቺ የፍጥነት ጽሑፍ ከአንዳርጋቸው ፍቺ ጋር በተያያዘ ከባለፈው ቅዳሜ (ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም) ጀምሮ እስከ ማክሰኞ (ግንቦት 21 ቀን 2010 ዓ.ም) ድረስ በግል ባየሁትና ባስተዋልኳቸው ነገሮች ላይ ማተኮርን መረጥኩ፡፡

ዕለተ-ቅዳሜ

አርብ (ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም) አመሻሽ ላይ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች እንደሚፈቱ መወሰኑ በአገዛዙ ሚዲያዎች ተሰማ፡፡ ሁላችንም ደስታ ተሰማን፤ ጻፍንም፡፡ ቅዳሜ ጠዋት ረፋድ ላይ ‹‹አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች ከ500 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ተፈቱ›› የሚል ይዘት ያለው ዜና በፋና ብሮድካስቲንግ ፖርፖሬሽን ድረ-ገጽ ላይ ተነበበ፡፡ ዜናውን ወዲያው ብዙ ሰው ከሀገር ውስጥ እስከውጪ ድረስ ተቀባበሉት፡፡ ፋና ብዙም ሳይቆይ የዜናውን ርዕሥ ‹‹…እንዲፈቱ ተወሰነ›› በሚል አስተካከለው፡፡ በቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ንቁ ተሳታፊ በነበረውና አሁንም በማኅበራዊ ሚዲያ በድፍረት ሀሳቡን በሚያራምደው ስንታየሁ ቸኮል የተመራው ግብረ ሀይል ወደቃሊቲ ገሰገሰ፡፡ ስንታየሁ ቃሊቲ አከባቢ ስላሉ መረጃዎች በፍጥነት ያደርሰን ነበር፡፡ እኔና እሱም በስልክ መረጃዎችን ስንለዋወጥ ነበር፡፡ ከሰዓት በኋላ፣ የአንዳርጋቸው ጽጌ ወላጅ አባት አቶ ጽጌ ሀ/ማርያም ወደቃሊቲ እስር ቤት አምርተው ወደውስጥ በመግባት ስለልጃቸው ፍቺ ጠየቁ፡፡ የቃሊቲ እስር ቤት ሃላፊዎችም ‹‹እኛው ራሳችን ቤት ድረስ እናመጣዋለን፤ እርስዎ ወደቤት ተመለሱ›› እንዳሏቸው ሰማን፡፡

የአቀባበል ዝግጅት

በእነአንዳርጋቸው ቤተሰብ መኖሪያ ቤት የአሁኑ ሰማያዊ እና የቀድሞ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ንቁ አባላትና አመራር እንዲሁም በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና መምህርትና ጸሃፊ መስከረም አበራ በፈቃደኝነት ያዋቀሩት አንዳርጋቸውን በክብር የሚቀበል ቡድን የደመቀ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንና አንዳርጋቸውን በማንኛውም ሰዓት ለመቀበል መዘጋጀቱን፤ የአንዳርጋቸው ምስል ያለበትንና ጀግንነቱን የሚገልጽ ካናቴራ በመልበስ ከወላጅ አባቱና ከአክስቱ ጋር ሆነው ፎቶግራፍ ተነስተውበማኅበራዊ ሚዲያ አሰራጩ፡፡ አንዳርጋቸው በዚያን ዕለት ባይፈታም ይኼ አንዳርጋቸውን የሚቀበል ወጣት እዚያው ቦሌ ኦሎምፒያ አከባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤት ማደራቸውን ገለጹ፡፡ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ያደርሱ ነበር፡፡

ሰንበት

በዕለተ እሁድም አንዳርጋቸው ሊፈታ ይችላል በሚል ከጠዋት እስከማታ ድረስ ብዙ ሰው በተስፋ ሲጠብቅ ዋለ፣ አመሸ፡፡ እነስንታየሁም ቃሊቲ በር ጋር በዚህ ቀን መሄዳቸው አልቀረም – የተለወጠ ነገር ባይኖርም፡፡ አንዳርጋቸው በሁለት ቀናት ውስጥ ከእስር ተፈትቶ እንግሊዝ ከቤተሰቡ ጋር እንደሚቀላቀል የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአንዳርጋቸው ባለቤት በስልክ ደውሎ መናገሩን ከስካይ ኒውስ መረጃ ለመረዳት ተቻለ፡፡ የአጭር ደቂቃ የቪዲዮ ቃለ ምልልስ፣ ከአንዳርጋቸው ባለቤትና ከልጆቹ ጋር ተደርጎ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰራጨ፡፡ ከዚህ መረጃ በኋላ ‹‹አንዳርጋቸው የእንግሊዝ ዜግነት ስላለው በቀጥታ ወደእንግሊዝ ነው የሚላከው›› የሚለው ሀሳብ ሚዛኑን ደፋ፡፡

ሰኞ፣ ግንቦት 20

ሰኞ በጠዋት በረከት ዓለሙ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር ተቀጣጥረን ወደቃሊቲ አመራን፡፡ ስንታየሁ ቸኮል አንዳርጋቸው ይፈታል ከተባለበት ቀን ጀምሮ ከጠዋት እስከማታ ድረስ ቃሊቲ በር ጋር ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በመሆን በንቃት ሲጠባበቅ ነበር፡፡ በዚህ ቀንም ስንታየሁና ሌሎች የትግል ጓዶቹ ቀድመው ተገኝተው ነበር፡፡ በዛ ያሉ ቪ-8 መኪኖች ወደቃሊቲ እስር ቤት ሲገቡ በማትየና ፎቶግራፎች ጭምር በማንሳትም በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ሲያጋረን ነበር፡፡ ከስንታየሁ ጋር በስልክ እየተነጋገረን እኛም ቃሊቲ ደረስን፡፡ ቃሊቲ እስር ቤት በር ፊት ለፊት በዛ ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ነበር፡፡ ከአንዳርጋቸው እህት ኑኑ ጽጌ ጋርም ከዓመታት በኋላ በአካል ተገናኘን፡፡ አባትየው ከዚህ ቀደም ‹‹መንግስት ለመገልበጥ አሲረዋል›› በሚል ክስ በእነብርጋድየር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብ ታስረውና ተከስሰው የዕድሜ ልክ ፍርደኛ የነበሩ ሲሆን፤ ከኑኑ ጋርም ፍርድ ቤት እንጋኝ ነበር፡፡ አባትየውም ከጥቂት ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ከእስር ተፈትተዋል፡፡

በቃሊቲ ሰው ቀስ በቀስ እየጨመረ መጣ፡፡ እኛም ቆመን ሁነቱን እየተከታተልን በመጠበቅ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መወያየትና መከራከር ቀጠልን፡፡ ጸሃይዋም ከርራለች፡፡ ጸሃይ ላይ መቆሙ ድካም ሲያመጣ፣ ቡና ለመጠጣትና ለማረፍ ብለን ክራውን ሆቴል ገባንና ጨዋታችንን ቀጠልን፡፡ በግምት ከ45 ደቂቃ በኋላ፣ ቃሊቲ የገቡት መኪኖች ወጡ ተባለ፡፡ እኔና በረከት በበረከት ቪትስ መኪናም መኪኖቹን ለመከተል ጥረት አደረግን፡፡ በመኪኖቹ ውስጥ አንዳርጋቸው ይኑርበት አይኑርበት ግን የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡ መኪኖቹም መጠነኛ ርቅት ስለነበራቸው ከተወሰነ ርቀት በኋላ ተሰወሩብን፡፡ ‹‹እቤት ሊወስዱት ይችላሉና ወደቤት መሄዱ ይሻለናል›› በማለት ከበረከት ጋር በቦሌ መስመር ነጎድን፡፡ በቦሌ ሚሊኒየም አደባባይ አከባቢ ወጣቶች በሞተር ብስክሌትና በመኪና ከኋላ መጥተው በጥሩንባ አከባቢውን አነቃነቁት፡፡ ደስ የሚል ትዕይንት ነበር፡፡ እስከኦሎምፒያ አደባባይ ድረስ መኪኖችና ሞተር ብስክሌቶች በጥሩንባ፣ ወጣቶች ደግሞ በድፍረት ዝማሬና የአንዳርጋቸውን ስም በጀግንነት በማንሳት እየጨፈሩ በአይኔ አየሁ፡፡ በረከትም የመኪናውን ጥሩንባ እያሰማ ወደቤት አከባቢ ደረስን፡፡ አከባቢው እጅግ በበዛ ሰው ተከብቧል፡፡ ሰው የአንዳርጋቸውን መፈታት በደስታ፣ በተስፋና በትዕግስት እየተጠባበቀ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ግን አሁንም አልመጣም፡፡ ‹‹የት ወሰዱት?››፣ ‹‹ኤምባሲ ወስደውት ነው፡፡ ከዚያ እዚህ ያመጡታል››፣ ‹‹ቤተመንግስት ነው››፣ ‹‹እንግሊዞች የጤና ምርመራ እንዲደረግለት ሆስፒታል ወስደውታል››፣ ‹‹ከቃሊቲ አልወጣም››፣ ‹‹ወደእንግሊዝ ማታ እንዲበር የጉዞ ፕሮሰስ እያደረጉለት ይገኛል››፣ ‹‹እዚህ ሳያመጡት ቀጥታ ማታ ወደእንግሊዝ ይልኩታል››፣ ‹‹ከዐብይ አህመድ (ዶ/ር ጋር ተገናኝቷል›› ….ወዘተ የሚሉ መላምቶች በተለያዩ ሰዎች አንደበት ሲገለጽ ዋለ፡፡ ‹‹አሁን ሊመጣ ነው ተዘጋጁ›› የሚልም መልዕክት ወደአመሻሽ አከባቢ መጣና በርካታ ሰዎች በተለያዩ አነቀቂ ሃገራዊ እና የአንዳርጋቸው ጽጌ የግንቦት ሰባት የትግል መዝሙር [‹‹ላንቺ ነው ሀገሬ›› የሚለው]) በመኖሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በደስታ ይጨፍሩ ጀመር፡፡ ግቢው በደስታ ቀለጠ፡፡ ዘናቡ መዝነብ ቢጀምርም በዝናብ ውስጥ ወጣቶች በደስታ ከመጨፈር አላገዳቸውም፡፡ ዝናቡ ሲበዛ ብዙ ሰው መጠለያ ወደመፈለግ መጣ፡፡ ሆኖም ሳይጠለሉ ዝናቡ እስኪያባ ድረስ በመዝፈንና በመጨፈር የቀጠሉ ብርቱ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ነበሩ፡፡

በዚህ ዶፍ ዝናብ ውስጥ እየተደበደቡ ባንዲራ ይዘው አንድ አርበኛ ወደግቢው ዘለቁ፡፡ የሚጨፍሩ ወጣቶች አይተዋቸው ደስ በሚል ሁኔታ ወደእኚህ አዛውንት ሄዱና አቀፏቸው፡፡ አብረዋቸውም ጨፈሩ፡፡ እኚህ ሰው፣ ቁጭ ሲሉ አጠገባቸው ሄጄ አነጋገርኳቸው፡፡ ቀኝ አዝማች አለባቸው ሃይሌ ይባላሉ፡፡ በጎጃም ከ/ሀገር በጎንቻ እነሴ ወረዳ ልዩ ስሙ እነገት በሚባል ቦታ ተወልደው በአርበኝነት ብዙ ሀገራዊ ተግባራትን ለሀገራቸው ያበረከቱ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ በእጃቸው የያዙትንም ዶክመንቶች እያወጡ አሳዩኝ፡፡ አዛውንቱ የአንዳርጋቸው ጽጌን ፍቺ ዜና ሰምተው የመጡ ናቸው፡፡ የአያትታቸው፣ የአባታቸውንና የራሳቸውን የአርበኝነት ሜዳሊያ አድርገዋል፡፡ አንዱን ሜዳሊያ በእጄ ይዤ ሳየው ‹‹ድል የትግል ውጤት ነው›› ይላል፡፡ እውነት ነው፣ ድል የትግል ውጤት ነው፡፡ የአንዳርጋቸው ፍቺም የሁላችንም የሀገር ልጆች የትግል ውጤት ነው፤ የህዝብ ትግል! በግሌ፣ አንዳርጋቸው ከየመን ተይዞ (ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም የዛሬው የአገዛዝ ሥርዓት ተላልፎ መሰጠቱ በግልጽ በታመነ ቀን፣ በአንዳርጋቸው መታሰር እጅግ ማዘኔን በማኅበራዊ ሚዲያ ጽፌ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ‹‹አንዳርጋቸው ጽጌ የነጻነት ታጋይ እንጂ አሸባሪ አይደለም!›› በማለት በግልጽና በድፍረት ጽፌያለሁ፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉና የደፈሩ ሌሎች በርካቶችም ስለአንዳርጋቸው ጽጌ የሚምኑበትን ሀሳብ በድፍረት ጽፈዋል፡፡ እንዲፈታም በጽኑ ወትውተዋል፡፡

እኚህ አርበኛ እንዴት ሊመጡ እንደቻሉ ጠየኳቸው፡፡ ‹‹ጠንካራ ወገኔ ይፈታል ሲባል ደስ ብሎኝ መጣሁ!›› ብለውኛል፡፡ …በእነአንዳርጋቸው መኖሪያ ቤት እስከምሽት ድረስ ጭፈራው ደርቶ ነበር፡፡ ይሄም በአባይ ሚዲያ በቀጥታ ሲተላለፍ የነበረ ሁነት ነው፡፡ እኔም የጭፈራ ጽዋ ደርሶኝ ትንሽ ጨፍሬያለሁ፡፡ ‹‹ጭምት ናቸው፣ አይጨፍሩም›› ብዬ ያሰብኳቸው ሰዎች ጭምር ጭፈራቸውን በደስታ ሲያደሩ ተመልክቼም ከልቤ እየሳኩ በግርምት ተመልክቻለሁ፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ ….አንዱ የአንዳርጋቸው አቀባበል! በዚህ በግንቦት ሃያ ቀን ግንቦት 7 አሸነፈ የምትለዋ አገላላጽም አይረሴ ናት፡፡

ማክሰኞ – የፈቺ ቀን

ሰኞም ከእስር ተፈትቶ መውጣት ያልቻለው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ እሱን ጨምሮ ሌሎች ከ500 በላይ እስረኞች እንደሚፈቱ በገዥው ሃይል በኩል በጠዋቱ መረጃ ወጥቶ በትዊተር ላይ መገለጹን ከጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ አነበብኩ፡፡ ተስፋ ያልቆረጠው ሕዝብም በዚህ ቀን የአንዳርጋቸውን መፈታት በመጠባበቅ ከጠዋት እስከማታ ድረስ በመኖሪያ በቤቱ ከተመ፡፡ እህቱ ወ/ሮ ኑኑም ‹‹አንዳርጋቸው ዛሬ ተፈትቶ እቤቱ ይመጣል፤ እርግጠኛ ነኝ›› የሚል ምላሽ ሰጥታን ነበር፡፡ በቤቱ ውስጥ ድንኳን ተደኩኖ ሰዎች በሥነ-ሥርዓት ተቀምጠው ምሳም በሉ፡፡ ቀትር አልፎ የከሰዓቱ ጊዜ መንጎድ ሲጀምርም ብዙ ሰው ግራ የመጋባት ስሜት ተፈጥሮበት ነበር፤ እኔን ጭምር፡፡ ግቢሱ ይጨፍራል፡፡ ገሚሱ ግቢውን በቄጠማ ያሳምራል፣ ገሚሱ አበባ መንገድ ላይ ይበትናል፡፡ ገሚሱ ይቀመጣል፣ ገሚሱ ይንቆራጠጣል፡፡ ገሚሱ ከሞባይል ስልኩ ጋር ተፋጥጦ ስልኩን ይነካካል፡፡ ገሚሱ ቡና ለመጠጣት ላይ ታች ይላል፡፡ በተስፋ ውስጥ ያለ ድካምና መጠነኛ መሰለቸትም ትንሽ በማይባሉ ሰዎች ዘንድ በጉልህ ይታይ ነበር፡፡ ይኼም ገዥውን ሃይል ካለማመን የመነጨ ነው፡፡ ከቀኑ 10፡15 ሰዓት በኋላ እህቱ ከቤት በመውጣት መንታ መንገድ ላይ ቆማለች፡፡ በንቁ አስተያየት የአንዳርጋቸውን መምጣት እየተጠባበቀች መሆኑ ፊቷ ላይ ይነበብባታል፡፡ ሌሎች ሰዎችም ወደመንገዱ መጥተው መቆማቸው ቀጠለ፡፡ ብርሃኑ ተ/ያሬድም መንገድ ላይ ለተሰበሰቡ ሰዎች ‹‹አንዳርጋቸው ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ይመጣል›› ብሎ ተናገረ፡፡ ትንሽም ጭፈራ መንገዱ ላይ ተደረገ፡፡ እኔም ሰዓቴን ሳየው 10፡45 ሆኗል፡፡ ‹‹ማምጣት ካለባቸው እንዴት እስከአሁን ይቆያል?›› በማለት አጠገቤ ለነበሩት የዞን 9 ጦማሪያን አቤል ዋባላ እና አጥናፍ ብርሃኔ ነገርኳቸው፡፡

ፈጇቸው!

ወዲውም አንዲት አንቡላንስ በፍጥነት ወደተሰበሰበው ሰው ድረስ መጥታ አለፈች፡፡ መኪናዋን የጠረጠሩ ሰዎች ግን አንቡላንሷን ጠጋ ብለው ተመለከቱ፡፡ አንዳርጋቸውን አዩት መሰለኝ፣ ‹‹አንዲ …አንዲ …ጀግናው መጣ …ጀግናው መጣ …›› በማለት በሩጫ ተከተሉት፡፡ በተለይ አንቡላንሷ ወደእነአንዳርጋቸው ቤተሰብ መኖሪያ ቤት ስትጣጠፍ፣ ህዝቡ እየጮኸ መሮጡን ቀጠለ፡፡ እኔም በአቅራቢው ነበርኩና ሮጥኩ፡፡ እውነት ነበር፣ አንቡላንሷ በር ላይ ቆማለች፡፡ መኪናው በህዝቡ ተወረረ፡፡ ተኩስ የሚመስል ድምጽ ይሰማም ጀመር፡፡ ርችት መሆኑ ገባኝ፡፡ ርችቱ እንደጉድ ተንጣጣ፡፡ [ራሄል ረጋሣ የምትባል አንድ ጓደኛዬም ወደስፍራው እየመጣች ነበርና ከርቀት የርችቱ ድምጽ የተኩስ ድምጽ መስሏት ‹በቃ ፈጇቸው!› ብላ በድንጋጤ መብረክረኳን ምሽት ላይ በስልክ ነግራኝ በሳቅ ሞቻለሁ፡፡] አከባቢው በጩኸትና በጭፈራ፣ በትርምስምስ ተደበላላቀ፡፡ ማንም ሰው ማንንም አይሰማም፡፡ ሁሉም ስሜቱን ነበር የሚከተለው፡፡ መኪናዋ ሙሉ በሙሉ በሚጨፍሩ፣ አንዳርጋቸውን በሚያወድሱ፣ በሚጮሁና በበደስታ በሚያለቅሱ ሰዎች እንደታይታኒክ መርከብ ሰጠመች፡፡

ወደግቢው ገብቼ በአንዱ ነጻ ቦታ ላይ ቆሜ ትዕይንቱን በቅድሚያ በፎቶግራፍ፣ ቀጥሎ ደግሞ በፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት በመቅረጽ ማስተላለፉን ተያያዝኩት፡፡ ዶፍ ስናብም ይዘንብ ጀመር፡፡ ዝናቡ የአንዳርጋቸውን አድናቂዎች አልበገረም፡፡ የሚጨፍረውም ይጨፍራል፡፡ በሰው መተረማመስ የወደቁና የተጎዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጭፈራው ደርቷል፣ ዝናቡም ይወርዳል፡፡ አንቡላንሷ ወደግቢው ልትገባ ጥረት አደረገች፡፡ ግን እንዴት ተችሎ? በስንት ትግል ግን አንዳርጋቸውን ከመኪናው አውርደው፣ አቅፈውና ተሸክመው በድንኳኑ ውስጥ ወጣቶች ይዘውት መጡ፡፡ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አየሁት፡፡ አቀባበሉን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስልኬ ቀጥታ እያስተላላፍኩ ቢሆንም አንዳርጋቸውን ለመመልከት ጥረት አደረኩ፡፡ አንዲ፣ ወጣቶች ላይ ተኝቷል፡፡ ግራ ተጋብቷል፤ ፊቱ ላይ ግን የደስታ ስሜቱ በጉልህ ይታያል፡፡ ጉልበተኛ ወጣቶች በስንት ትግል የሰውን ግርግር አልፎ ወደቤት አስገቡት፡፡ ጥቂት ሰዎችም ከእርሱ ጋር ገብተው በሩ ተዘጋ፡፡ ዝናቡ ይዘንባል፡፡ መቆም አልቻለም፡፡ ብዙ ሰው የሚጠለልበት አልነበረውም፡፡ እኔም እንደምንም አንዲት ጠባብ ክፍል በር ላይ መቆም ቻልኩ፡፡ እዛም ላይ ሆኜ ሁነቱን ለመቅረጽ በትንሹ ረድቶኛል፡፡ ግቢው ትምምስምር ብሏል፡፡

የአንዳርጋቸው ንግግር

ከቆይታ በኋላ፣ ‹‹አንዳርጋቸው ሶስት ደቂቃ ያህል መናገር ስለሚፈልግ ሥነ-ሥርዓት እንያዝ›› የሚል መልዕክት ከአስተባባሪዎች ተሰማ፡፡ በቦታው ግን ሥነ-ስርዓትን ለማስፈን እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች ትግልና መገፋፋት በኋላ አንዳርጋቸው ለሚጠበቀው ብዙ ሰው ሊናገር ወጣ፡፡ አሁንም ትርምሱ ቀጠለ፡፡ አንዲት እናት ጎን እንደምንም አስቀመጡት፡፡ እዚህ ጋር አንዳርጋቸው በሁነቱ እጅግ ተገርሞ እጁን በአፉ ያዘ፡፡ አንድ ወንበር ላይ እንዲቆም ተደርጎም ጥቂት ንግግሮችን አደረገ – ደስታም እንባም መገረምም ተደበላልቆበት፡፡ ትንሽ ከተናገረ በኋላ፣ እድምተኛው ያጨበጭባል፣ አድናቆቱንም ይገልጻል፡፡ ‹‹አንዴ ዝም ብሉ!›› ይባልና በድጋሚ ይናገራል፣ ተመሳሳይ ነገር ይከሰታል፡፡ አንዳርጋቸው፣ በንግግሩ እንዲህ አይነት አቀባበል እንዳልጠበቀ፣ በዚህ በጣም መገረሙንና በጣምም ሁሉንም ማመስገኑን ገለጸ፡ ፡…ከንግግሩ በኋላም በድጋሚ ወደቤቱ ገባ፡፡ ተመሳሳይ ትርምስ ተከተለ፡፡ ‹‹ላንቺ ነው ሃገሬ›› የሚለው እሱ የደረሰው የትግሉ መዝሙርም ተከፈተ፡፡ ድጋሚ ተቋረጠ፡፡ ….የፕሮግራም መናበብ ችግር በጉልህ ታይቷል፤ ያው ደስታ የፈጠረው እና የዝናቡ ክብደት መሆኑ ባይዘነጋም፡፡

አንዳርጋቸው በጃኖ!

ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም በድጋሚ ጃኖ ለብሶ ንግግር ሊያደርግ አንዳርጋቸው ከቤት ወጣ፡፡ በስንት ትግል ሰውን አልፎ ፎቅ ላይ መጥቶ ቆመ፡፡ እዛም ላይ ሆኖ አድናቂዎቹን ወደታች ሰላም ይል ጀመር፤ በዚህ ጊዜ ፊቱ በደስታ ተሞቷል፡፡ ….‹‹ላንቺ ነው ሃገሬ›› የሚትለዋ መዝሙርን እንዴት ሊደርሳት እንደቻለ እንባ እየጠናነቀው ትርክቱን ገለጸ፡፡ ከንግግሩም በኋላ ለአራት ዓመታት ተመላልሰው በጠየቁት በወ/ሮ ታደለች ታዬ በኩል 18 ግራም የወርቅ ሃብል ተበረከተለት፡፡ ጭፈራው፣ ፌሽታው ደራ፡፡ በመጨረሻም አንዳርጋቸው ‹‹እኔም ቤተሰብን ላግኝ፣ አባቴንም አላገኘሁትም፡፡ እናንተም ደክሟችኋል እረፉ፡፡ ለተወሰኑ ቀናት እዚህ ስላለሁ ተረጋግተን እንገናኛለን፡፡›› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አስተላለፈና ህዝቡን በደስታ ተሰናበተ፡፡ አንዳርጋቸውን ለመቀበል የመጣው ሰው ቁጥሩ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡

ከፎቁም ወርዶ ሰዎችን እየጨበጠ በደስታ ሰላምታ መስጠቱን ቀጠለ፡፡ ከቢቢሲ ጋርም ጥቂት ቃለ-ምልልስ አደረገና ድጋሚ ወደቤት ገባ፡፡ በቤት ውስጥም ከአባቱ ጎን ተቀምጦ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የማስታወሻ ፎቶግራፍ ደስ ብሎት ይነሳ ጀመር፡፡ አንዳርጋቸውን ሰው ጋብ ካለም በኋላ ሰውን ሰላም በማለት፣ የማስታወሻ ፎቶግራፍ በመነሳትና ስልክ በማነጋገር ሲስቅ እና ሲጫወት እስከምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ አይቸዋለሁ፡፡ እኔም በኩል ኢሳት ውስጥ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች ጋርም በስልክ አገናኝቼው መኝታ ክፍል ውስጥ ገብቶ እየሳቀ ጭምር ሲያነጋር ነበር፡፡ ….የፍቺው ቀን ሁነት ምሽቱ ይሄንን ይመስል ነበር፡፡

ከአንዳርጋቸው ፍቺ የተረዳሁት ነገር፣ ሰፊው ህዝብ እውነተኛ ነጻነትን፣ ዴሞክራሲን ፣ ፍትህን፣ እኩልነትን፣ …እጅጉን በተግባር መሻቱን ነው፡፡ ለዚህ እውን መሆኑ አንዱ አሸባሪ ተብለው ተፈረጁ ድርጅቶች (ግንቦት 7፣ ኦነግና ኦብነግ) ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ስማቸው በተግባር መነሳት አለበት፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊ ዜጎችንና ሀገሪቷን ዋጋ ያስከፈለውና እያስከፈለ የሚገኘው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁም ይሻር፡፡ ወይም ብዙሃንኑ ዜጋ በሚያጠቃ ሳይሆን በሚጠቅም፤ የአገዛዙን ዕድሜ በሚያራዝማ ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች ጥበቃ ሊሆን በሚችል መልኩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚስማሙበት ደረጃ መሻሻል ይኖርበታል፡፡ ጠላት-ተኮር የፍረጃ ፖለቲካም ያክትም፡፡ በጸረ-ሽብርተኝት አዋጁ ዋጋ መክፈል ይብቃን! ህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ባለቤት ይሁን!

[ይኼ ጽሁፍ፣ ትናንት ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም በልዩ ዕትም አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ብቻ አትኩሮ ለንባብ በበቃው ግዮን መጽሄት ላይ የተስተናገደ ነው።]

#ኢትዮጵያ!

Filed in: Amharic