>

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ወቅቱ የሚጠይቀው ውሳኔ ቢሆንም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አስከትሏል!!! (ዶ/ር አብይ አህመድ) 

የተከበራችሁ የሃገራችን ህዝቦች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሀገር እና ህዝብ ያሉበትን ነባራዊ እውነታ እና በቀጣይም እንደ ሀገር ሊገጥም ይችላል ተብሎ የሚገመት አደጋን ለመከላከል በመደበኛው ህግ እና አሰራር የማይቻል ሆኖ ሲገኝ የሚመርጥ አስገዳጅ አማራጭ ነው።
ሃገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት አመታት ባጋጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲታወጅ ተደርጓል።
ይህንን ተከትሎም በመንግስት ዘንድ በተከናወነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እና በተከታታይ በተወሰዱ እርምጃዎች ህዝቡ መንግስት ባለው ችግሮችን የመፍታት ፍላጎት እና አቅም ላይ ተስፋን ሰንቋል፤ በዚህም ምክንያት ህዝቡ የሰላሙ ዘብ በመሆን ላለፉት ሁለት ወራት በሀገራችን አንጻራዊ የሰላም ንፋስ መንፈስ ጀምሯል።
ዛሬ ያሉበትን እና ነገም የሚደርሱበትን ተፈጥሯዊ የህይወት ኡደት- ሰላማዊ የመሆኑን እንዴትነት ባለማመን ውስጥ መኖር በሰርክ ህይወታችንና በእድገት ስኬታችን ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ እጅግ ብዙ ነው።
ሀገራችን ገብታበት በነበረው ውስብስብ ቀውስ ሳቢያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በማወጅ ነገሮች መስመር እንዳይስቱ እና መልሶ ለማረቅም እንዳያዳግቱ ውጤታማ ስራ መስራት ችሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜያዊ መፍትሄ እንጂ መደበኛና ዘላቂ ሰላምን የሚያመጣ ባለመሆኑ መንግስትም ይህንኑ በመረዳት የሀገራችን እና የህዝቦቿ ሰላም ከውጫዊ አዋጅ እና ክልከላ ሳይሆን ከዜጎች ፍላጎትና የሰላም ወታደርነት የሚፍለቅ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በተደረጉት እንቅስቃሴዎችም በመላው ሀገራችን አንጻራዊ ሰላምን ማሰፈን ተችሏል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለነበርንበት ችግር ወቅቱ የሚጠይቀው አማራጭ ውሳኔ ሆኖ ቢያሻግረንም ለማደግ መለወጥ እንደሚታትር ታላቅ ህዝብ ደግሞ ያስከተላቸውና የሚያስከትላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መኖራቸው አይካድም።
በመሆኑም የረጅም ዘመን ታሪክ አኩሪ እና በዘመን የተፈተነ የአብሮነት ልክ የማይደራደርበት የሞራል ጥግ ራሱን እና ሌሎችንም ጭምር የሚጠብቅበት ባህላዊ የሰላም መቀነቻ ድግ እና ትላንቱን ዘክሮ፣ ዛሬውን መርምሮ እና ነገውንም ተንብዮ ሀገር አድባሩን በሰላም የሚሞላ ህዝብ ላላት ድንቅ ሀገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ከቆየችው በላይ ትቆይ ዘንድ አይገባትም።
እንደ ኢትዮጵያ ላለች የዲፕሎማቲክ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መናገሻ ለሆነች ሀገር የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቆይታን ለማብቃት የሚደረግ ጥረት እና የጋራ ርብርብ አንድምታው ብዙ ነው።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለማንሳት እና ህዝቡንም ወደ መደበኛው የአስተዳደር፣ የህግ እና የፍትህ መስመር ስለመመለስ ሲያስብ አዋጁን ለማወጅ ካስገደዱት ተግዳሮቶች አንጻር ያለውን ችግር በተመለከተ የመፍትሄውን ቁልፍ በማግኘት በኩል ሙሉ እምነቱ ያለው በህዝቡ እና በህዝቡ ላይ ብቻ ነው።
መንግስት እና ህዝብ አዋጁን በማንሳት የሀገራችንን ሰላም እና የዜጎችን ደህና ወጥቶ ደህና የመግባት መብት፣ ምኞት እና ጸሎት እውን ለማድረግ በሚታትሩበት ወቅት ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመግፋት እና ዞረን ተዟዙረን የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር ለማድረግ የሚጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሊኖሩ የመቻላቸውን ነገር ለአፍታም ቢሆን ቸል ልንል አይገባም።
መንግስትም ስጋቱን እንደ ስጋት የሚጋራው ቢሆንም እንደ ታላቅ ሀገር እና እንደ ኩሩ ህዝብ ከአስጊው ስጋት ይልቅ ከኩሩው ህዝብ እምነት ጋር በመደመር ነገን ብሩህ ለማድረግ መስራት የመንግስት ምርጫ ሆኗል።
ህዝባችን በገዛ ፈቃዱ መዳፉ ውስጥ ያኖረውን ሰላም ከሌላ መዳፍ ውስጥ አኑሮ ያለፈቃዱ የሚሰጋ- ያገሩን ሰላም የሚያናጋ ሳይሆን የሰላሙ ዘብ ራሱ መሆኑን በማመን ሀገር- ቀኤውን ከቀውስ የሚጠብቅ እንደሚሆን መንግስት በጽኑ ያምናል፤ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የህዝባችን ጥያቄ ሆነው የቆዩ የተለያዩ ጉዳዮች ሁነኛ ምላሽ ያገኙ ዘንድ ያለመታከት ይሰራል።
ከችግሮቹ ስፋት እና ጥልቀት አንጻር ህዝብ በሚፈልገው ልክ እና መጠን ለሁሉም ጥያቄዎች አሁናዊ ምላሽ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም መንግስት የመጨረሻውን የፍጥነት እና የትጋት ልክ ተጠቅሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር ነገሮች ሁሉ መልካም እንዲሆኑ ከህዝቡ ጋር ይረባረባል።
ምንም እንኳን ዛሬ ለነገ መሰረት የመሆኗ ነገር ባያጠያይቅም ዛሬ ሰላም መሆን ማለት ግን ነገም ሰላም ትሆናለች የሚል ዋስትናን አይሰጠንም፤ ነገ ሰላም የምትሆነው በሁላችንም ጥረት እና ዛሬ ላይ ለነገ በምንጥለው የፍቅር መሰረት ብቻ ነው።
በመሆኑም መንግስት ህዝብን እና ህዝብን ብቻ አምኖ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ህዝባችንም በሀገሩ ምድር ሁሉ ላይ የሁልጊዜም የሚሆነውን እና ከየሰው አእምሮ የሚመነጨውን ተፈጥሯዊ የሰላም አዋጁን በህብረት እንደሚያውጅ እምነቴ የጸና ነው።
ይህ ሲሆን ብቻ በእርግጠኝነት ነገ ከዛሬ የተሻለች ትሆናለች፤ ሀገራችን እና ህዝባችን ዘላቂ ሰላም እና የማያቋርጥ ለውጥ መገለጫቸው እንዲሆን ካስፈለገ መተኪያ የሌለው የሁሉም ነገር መሰረት እና ካስማ ሰላም እና ሰላም ብቻ ነው።
በዚህ ሀሳብ መነሻነትም ባለፉት ወራት በሀገራችን ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነሳ መሆኑን እያሳወኩ በቀጣይም የሀገራችን ህዝቦች፣ የፌዴራል እና የክልል የጸጥታ ሀይሎች፣ በየደረጃው የምንገኝ የፌዴራል እና የክልል የስራ ሀላፊዎች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባሎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና የሚድያ ሰዎች፣ የሀገራችን የቅርብ ወዳጆች እና አጋሮች፣ የሀገራችን ምሁራን እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል በማለት የዚህች ሀገር ደግ ቀን እንዲነጋ በተለያዩ መንገዶች የበኩላችሁን እያደረጋችሁ ያላችሁ በውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ከምንም በላይ ለዚህች ሀገር ብልጽግና እና ለህዝቦቿም ሰላም ቅድሚያ ሰጥተን በጋራ እንድንረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ምንጭ:- OBN
Filed in: Amharic