>

የመፈናቀል ግፍ፥ የማፈናቀል ፖለቲካ (ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ)

ከየትም ቢሆን፥ በማንም ተደርጎ ቢሆን፥ የሰዎች ከቀዬአቸው አላግባብ መፈናቀል ሊኮነን የሚገባው ኢሰብዓዊ ተግባር ነው።  በየትኛውም አካባቢ።
ማንም (በዲሞክራሲያዊ አብላጫ ድምፅ አመራር ሂደትም ሆነ ያለ ዲሞክራሲ በሆነ እገዛዝ ውስጥ ያለ) አመራር በቁጥር አነስተኛ የሆኑ (minority) ቡድኖችን መሰረታዊ መብቶች የማክበር ሕጋዊና ሰብዓዊ ግዴታ አለበት። ይሄን ተላልፎ መገኘት በቀላሉ ሊታለፍ አይገባም።
ዛሬ ከየስፍራው የመፈናቀል ዜና ተበራክቷል። ዜናው አንዳንዴ ተጋንኖ ፥ አንዳንዴም ፍፁም ውሸት ላይ ተመርኩዞ፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ ድብቅ የማበጣበጥ ዓላማ ባላቸው መሰሪዎች ተጠንስሶ ወይም እውነቱ ተጠምዞዞ የቀረበ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን እውነተኛ የሆኑ የመፋናቀል ሁኔታዎች መኖራቸው ሃቅ ነው። የጊዜያችን፥ የዘመናችን መራራ ሃቅ!!!
እንዲህ ያለውን እውነተኛ የመፈናቀል ዜና ስንሰማ ማዘን ብቻ ሳይሆን ማውገዝና ፈፃሚዎቹን እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል። እንደየደረጃው ፖለቲካዊ፥ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ተግባሩ እንዳይደገም፥ ቡድኖቹም በድጋሚ ለተመሳሳይ ጥቃት እንዳይጋለጡ ማድረግ ያስፈልጋል።
አስፈላጊውን ከለላ ለመስጠት እንዲቻልና ቀጥተኛና (blunt) ቀጥተኛ ያልሆኑ (subtle)፥ ግልፅ (overt) እና ግልፅ ያልሆኑ (covert) ጥቃቶች እንዳይፈፀሙ በመዋቅራዊ አተያይ ሥርዓቱን በየጊዜው መፈተሽም አስፈላጊ ነው።
ነገር ግን…
ነገር ግን፥ ችግሩን ሁሉ አገሪቱ ውስጥ ባለው ሕብራዊነትን በመርህ ደረጃ በተቀበለው የፌደራል ሥርዓት ላይ ማላከክ፥ አንዳንዶች እንደሚሉት መፈናቀሉ የተከሰተው አንቀፅ 39 ሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ስላለ ነው ማለት የችግሩን መንስኤ በትክክል እለመዳሰስ (ወይም misdiagnos) ማድረግና ችግሩንም ሳያስፈልግ ማወሳሰብ ነው። ችግሩ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ብቻ የታየ ነው ማለትም በመረጣ ታሪክን የመርሳት (selective historical amnesia የሚባል) ተግባር ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ አላግባብ መፋናቀል፥ መነቀል፥ መገፋትና እስከ መጥፋት ለሚያደርስ ፍጅት መዳረግ  የቆየ ታሪካዊና መዋቅራዊ መሠረት ያለው ፖለቲካዊ ክስተት ነው።
የአገረ-መንግሥቱ አመሠራረት እራሱ በማፈናቀል፥ በመንጠቅና (በ dispossession) በመንቀል (በ eviction)፥ በመግፋትና (exclusion) በማጥፋት (በ extermination)፥ በመተካት (በ displacement) እና በመጨቆን (በ oppression) እንደነበር የአገሪቱ የመንግሥት ታሪክና ‘መመስረቻ ሰነድ’ ተብለው ሊወሰዱ የሚችሉ ሕገ-መንግሥታትና ሌሎች ሕግጋት በስፋት (እና በኩራት፥ሳያፍሩ፥ ሳይሸማቀቁ) ያስረዳሉ።
ስለዚህ፥
1. መፈናቀል ዛሬ እንዳልተጀመረ እንግባባ።
2. መፈናቀል ከ27 ዓመታት ወዲህ (ድንገት ሕገ-መንግሥት ከሚባል የወያኔ ሰማይ) የወረደብን ክስተት (ወይም በላ) እንዳልሆነም እንግባባ። የቆየና የደረጀ መዋቅራዊ መሰረት ያለውና ከዛ የሚመነጭ ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አካል (body politic) ሞልቶ የሚፈስ የግፍ ፅዋ እንደሆነም እንረዳ። Violence of exclusion meted out into the State’s very foundation is leaking from the body politic, and we are seeing only the symptoms.
3. ፌደራሊዝሙ በአግባቡና በቀናነት ሲታይ ይሄን መዋቅራዊ ግፍ ለመሻር፥ አግላይ፥ ጨቋኝና አፋኙን የአገረ-መንግሥት መሠረት ለማስተካከል፥ እናም አገሪቱንና መንግሥቷን በተደላደለ መሠረት ላይ (እንደገና) ለመመስረት የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ይመስላል።
ነገር ግን በሕወኃት-ኢሕአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ እና የአነስተኛ ቡድን የበላይነትን የማስፈን ፍላጎት (TPLF’S hegemonic aspiration) ምክንያት ይሄ ዓላማ ተትቶ አገሪቱ ሌላ የአፓርታይድ አገዛዝ መሞከሪያ ሜዳ ሆና ከርማለች። (ዛሬም የሕወኃት የግጭት ሸቃጮች ከዛው ውስጥ የጠብና የብጥብጥ ካሽ ለመመንዘር ሲፈልጉ ይታያል።)
ያም ሆኖ የመፈናቀሉ ምክንያት ፌደራሊዝሙ ወይም ፌደራሊዝሙ የተቀመረበት ሕገ-መንግሥት እንዳልሆነ ልንግባባ ይገባል። እስቲ እስካሁን ማነው በሕገ-መንግሥታዊ ሂደት፥ በፌደራሊዝም መተግበር ምክንያት የተፈናቀለው?
4. አንቀፅ 39 ስለ ብሔሮች የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ይናገራል። ፖለቲካዊ (ንዑስ ቁ. 1), ባህላዊ (ንዑስ ቁ.2)፥ እና አስተዳደራዊ (ንዑስ ቁ 3) የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች እውቅና ያላቸው መሆኑን ይደነግጋል።
ይሄ በምንም ዓይነት አተረጓጎም መፈናቀልን ሊያመጣም ሆነ ሊያበረታታ አይችልም።
እንደው ለክርክር ያህል መፈናቀልን ያስከትል ይሆናል ቢባል እንኳን እስካሁን የትኛውም ቡድን ይሄን መብት ተጠቅሞ እንደማያውቅ ሁላችንም እንግባባለን። ታድያ ማንም ያልተጠቀመው መብት እንዴት አድርጎ ነው ሕዝብን ያፈናቀለው?
እናም…
ማፈናቀል ኢሰብዓዊና ህገወጥ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መፈናቀል (ድሮም ነበረ) ዛሬም አለ። መፈናቀልን ማቆም፥ መዋቅራዊ መሠረቱንም መናድ–ያውም በአስቸኳይ–ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ ተጠያቂነት ያለው ዴሞክራሲያዊ የበላይነት ያለው ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ሆኖ፥ አነስተኛ ቁጥር ያለው ቡድን ባለሙሉ መብት ዜጋ የሚሆንበትን (a democratic order of majority rule and minority rights) ሥርዓት መፍጠር እና መገንባት ያስፈልጋል። የችግሩ መንስዔ ይሄ አለመኖሩ  ነውና።
መንስዔውን (አውቀውም ሆነ ሳያውቁ) መሳት (እና ማሳሳት)፥ ማለትም misdiagnos ማድረግ፥ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም።
ይሄንን አሳዛኝ አጋጣሚ በመጠቀም የደረጀ ጥላቻቸውን (በተለይም የኦሮሞ ጥላቻቸውን) ለማራመድና ፀረ-ሕብራዊነት ዘመቻቸውን ለማካሄድ መሞከር (የሚሞክሩ አሉ!!) ለማንም አይረባም።
ይልቅ ተፈናቃዮቹን እንርዳ። ይልቅ አፈናቃዮቹን ተጠያቂ አናድርግ። ይልቅስ የመፈናቀልን መዋቅራዊ መሠረት እንቀይር።ይሄ ነው አገርንና ሕዝብን የመቤዠት መንገድ።
Filed in: Amharic