>

“ጠላት” እንዳይሰማ? አድዋ ተደብቃ እያለቀሰች ነው!! (ደረጄ ደስታ)

ትንናት በትግራይ አድዋ ከተማ ወጣቶችን “ለመቀስቀስ” አንድ ህዝባዊ ስብሰባ በከተማዪቱ ከንቲባ ሰብሳቢነት ሲካሄድ ነበር አሉ፡፡ በሰብሳቢው እና ህዝቡ በጥያቄና መልሱ ውይይት አልተግባቡም፡፡ አስተዳዳሪው ወቅታዊ ጉዳይና “ስለጠላቶች” ያንበለበሉትን መመሪያና ማብራሪያ ተሰብሳቢዎች ሳይቀበሉት ቀርተው ጥያቄያችንን መልሱልን እሚሉ ወገኖች እየተበከራቱ መጡ፡፡ ስብሰባው አልራመድ አለ። በዚህ ጊዜ የተቆጡት አስተዳዳሪ ፖሊስ አስጠርተው ተሰብሳቢውን በፖሊስና በቆመጥ ዱላ አስወቀጧቸው። አንድ ሃያ እሚሆኑ ተሰብሳቢዎችን መርጠው እስር ቤት ላኳቸው፡፡ ከተደበደቡት ዮሐንስ ገ/ኪዳን የተባለ ወጣት በብርቱ ቆስሎ ሆስፒታል ተላከ። ዛሬ ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ እስር ቤት በመሄድ ከጓደኞቹ እንዲቀላቀል ተወሰነ። ህዝቡ ሲጮኽ እንግዲያውስ የአምስት ሺ ብር ዋስ አስይዚና ውጣ ተባለ። አሁንም ህዝቡ ደግሞ እንዲህ አድርጋችሁ ደብድባችሁ ስታበቁ የምን ዋስትና ነው አምስት ሳንቲም አይከፈልም ትፈቱ እንደሁ ፍቱ ሲል አፋጠጠ። ጉዳዩ እየከረረ ሲመጣ ከክልል ፕሬዚዳንት ከደብረጽዮን ቢሮ የተላኩ አጣሪ ባለሥልጣናት ወደ ቦታው እየገሰገሱ ነው።  ይህ ሁሉ ሲሆን ስለ አንዳርጋቸው ዲፖርቴሽንና ከአገር መባረር በሚያወራበት አገር በሥርዓቱ ደጋፊ ካድሬዎች ትንፍሽ የተባለ ነገር የለም። አልፎ አልፎ በትግርኛ የወጡ ጽሆፎች ካልሆኑ በአማርኛ የወጣ አንድም ዘገባ አልታየም። ይህ በየጊዜውና በየቦታው እሚፈጸም ሲሆን ህወሃት ተጋልጦ የድርጅቱና የህዝቡ አንድነት እንዳይናጋ “ጠላትም ደስ እንዳይለው” ሲባል የተደበቀ ይመስላል። ገና እሚታሰርና እሚለቀቅ ሰው መኖሩን ተንብየው እሚዘግቡ ሰዎች ምን ያስደብቃቸዋል?
ለማንኛውም አድዋ ታስራ አዲስ አበባ ስትፈታ ፖለቲካው ማስገረሙ አይቀርም፡፡ ክልሎች የየራሳቸው እስረኞችን ሲያስፈቱ ትግራይ የራስዋን አጉራ ማቆየቷ እሱም አንሶ በላዩ በላዩ መጨመሯ ያስደንቃል፡፡ አብዮት ያለክልሏ ሄዳ የሰውን ልጅ ከምትበላው ይልቅ፣ የራሷን ልጅ መብላት ስትጀምር ለውጥ መቀስቀሷ አመጽ መጠንሰሷ አይቀርም፡፡ “አብዮት ልጆቿን ትበላለች” ይላል ብሂሉ!
የአረናው አብርሀ ደስታም በገጹ ሁኔታውን እንዲህ ገልጾታል…

የህወሓት የግርፍያ ቅጣት!

በምስሉ ምታዩት ወጣት ዮሃንስ ገብረኪዳን ይባላል። በትግራይ ክልል ዓድዋ ከተማ ነዋሪ ነው። የትግራይ ገዢዎች ህዝባዊ ስብሰባ ይጠራሉ። የዓድዋ ልጆችም ወደ ስብሰባ አዳራሽ ይገባሉ። በተሰብሳቢዎች እና በዓድዋ ከተማ ከንቲባ መካከል አለመግባባት ይፈጠራል። ወጣቶቹም ስብሰባው ረግጠው ይወጣሉ። ከተሰብሳቢዎች 20 የሚሆኑ ወጣቶች “ረብሸዋል” በሚል ምክንያት ታስረው ክፉኛ ተገርፈዋል። ይህ ስብሰባ፣ ረብሻና ግርፍያ የተፈፀመው ትናንት ግንቦት 21 (በግንቦት 20 ማግስት) መሆኑ ነው። በመሃል አገር የታሰሩት በሚፈቱበት ወቅት በትግራይ ክልል ግን ጥያቄ የሚጠይቁ ወጣቶች እንዲህ እየተገረፉ ነው። ልዩነቱ ግልፅ ነው።
Filed in: Amharic