>
5:13 pm - Saturday April 20, 1297

ግንቦትና ግንቦታውያን (ጌታቸው ሺፈራው)

ግንቦት በሞቃታማው በጋ እና በክረምቱ መካከል የሚገኝ የሙቀትና የወበቅ ወር ነው፡፡ ይህ ወር አየር ንብረቱ በቅጡ የማይታወቅ፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ የሚፈራረቅበት እንደመሆኑ ለሰዎች ጤና ተስማሚ አይደለም፡፡ ሙቀትና ቅዝቀዜው ድብልቅልቅ ባለበት በዚህ ወር አብዛኛው አርሶ አደር በበሽታ ይጠቃል፡፡ በዝናብ እጥረትና በረዥሙ በጋ ምክንያት ከብቶቻቸው ያልቃሉ፡፡ በአጠቃላይ ግንቦት ለአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የመከራና የስቃይ ወር ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ወሩን መልካም ነገር ይዞ እንዲመጣ አምላካቸውን ይማጸናሉ፡፡ ለአብነት ያህል ክርስቲያኖችና የሌሎች እምነት ተከታዮችም የግንቦት ልደታ ዕለት (አብዛኛዎቹ ከእምነት ይልቅ አምልኮ አዊ ያደርጉታል) ንፍሮ አንፍረው፣ ቡና አፍልተው የግንቦት ወር ጦስ በጭስና በንፍሮ ውሃ ለመሸኘት ይጥራሉ፡፡ ሆኖም ግን ለኢትዮጵያውያን ግንቦት የመከራ ዘመን፣ የደም ወር ከመሆን አላለፈም፡፡ ከዚህ ወር ጦሶች መካከል ለአሁኑ ዘመን መከራ ምንጭ የሆኑትን ግንቦታዊ ክስተቶች ብቻ እጠቅሳለሁ፡፡
27 አመታትን ወደኋላ ስንመለስ ኢትዮጵያ ለአሁኑ ፖለቲካዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊና ሌሎች አሉታዊ ገጽታዎች የዳረጋትን ውጥንቅጥ እናገኛለን፡፡ ግንቦት 8/1981 ዓ.ም፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮችና አመራሮቻቸው በጦርነት የተማረሩበት ወቅት ነበር፡፡ ከጀኔራሎቹም በላይ በእነ መንግስቱ ኃይለማርያም ይሁንታን ያገኘ ካድሬ ስለ ወታደራዊ ስትራቴጅ ለመተንተን የሚቃጣበትና ጀኔራሎቹን ያማረረበት ወቅት እንደነበር በርካቶች እማኝነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በገፈፋና በግድ ጦር ሜዳ ይቀላቀሉ የነበሩ ወታደሮች በቁርጠኝነት ይዋጋ የነበረውን ሰራዊት መንፈስ ቀይረውታል፡፡ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ያሳሰባቸው የጦሩ መሪዎች ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከስልጣን ካልተወገዱ ኢትዮጵያ የገባችበት ችግር ሊፈታ እንደማይችል አመኑ፡፡ ‹‹በጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም›› ላይ ይሞከራል ተብሎ የማይታሰበውን መፈንቅለ መንግስትም ወጠኑ፡፡ አዲስ አበባና አስመራም የመፈንቅለ መንግስት መሪዎቹ ማዕከል ሆኑ፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባው ማታ ላይ እንዲሁም አስመራው ደግሞ ከአንድ ቀን በኋላ ግንቦት 8/1981 ዓ.ም ከሸፈ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ሙከራውን ያደረጉት ጀኔራሎች ራሳቸውን ገደሉ፣ ተገደሉ፣ ታሰሩ፡፡ አስመራ ላይ ደግሞ ግንቦት 9/1981 ዓም  የ102ኛ አየር ወለድ ክ/ጦር በምስራቅና በሰሜን የገጠማትን ጦርነት ሲመሩ የኖሩትን ጀኔራሎች ዓይናቸ ውን ጎልጉሎ፤ በየጎዳናው እየጎተተ፣ አንገታቸውን ቆርጦ ብቻ ወታደር በመሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ጠላት በማረካቸው ላይ ሊያደርገው በማይታሰበው አረመኔያዊ ድርጊት አስመራን የደም አላባ አደረጋት፡፡
 በመፈንቅለ መንግስት በአጠቃላይ ከ137 በላይ የጦሩ አመራሮች ታሰሩ፡፡ ከእነዚህ መካከልም 28 ጀኔራሎች፣ 20 በላይ ኮሎኔሎች፣ 20 በላይ ሻለቃዎች፣ 20 በላይ ሻምበሎች ይገኙበታል፡፡ ገንጣይ አስገንጣይ የሚባሉት ሳይቀሩ አንዳንዶቹ ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ቀኝ እጁን በግራ እጁ ቆረጠ!›› ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ የጦር መሃንዲሶቿን ገደለች፣ በላች›› ብለው ጽፈውታል፡፡ በዚህ ምክንያት 270 ሺህ ያህል ኤርትራ ውስጥ የነበረው ሰራዊት አመራር አልባ ሆነ፡፡
መፈንቅለ መንግስቱ በከሸፈ በሁለተኛው ቀን ግንቦት 10/1981 ዓም በርካታ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩና ከጦሩ ሲርቁ እንዲሁም ሰራዊቱም ሆነ አመራሩ ሞራሉ ሲላሽቅ ሻዕቢያና ህወሓት የኢትዮጵያን ሰራዊት ይዞት የነበረውን ሰፊ መሬት ማስለቀቅ ጀመሩ፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደ ውጭ ወራሪ ያለ ርህራሄ የተጨፈጨፈበት ጊዜ ነው፡፡ በትህነግ እና ሻዕቢያ የተማረከውን ሰራዊት ሳይቀር መሬት ላይ አስተኝተው በመድፍ ጨፍልቀውታል፡፡ ቁስለኛውን በጅምላ ሲፈልጉ ወደ ገደል፣ ሲፈልጉ ወደባህሩ አሊያም በጅምላ የጨፈጨፉበት ወቅትም ነው፡፡ ይህ ወር ኤርትራና ትግራይ በኢትዮጵያ ሰራዊት ደም የጨቀየበት ክፉ ቀን ነው፡፡
ይህ ግንቦት ያመጣው ጦስ የኢትዮጵያውያን እጣ ፈንታ በገንጣዮቹ እጅ እንዲወድቅ አደረገ፡፡ መንግስቱ ኃይለ ማርያም ለኢትዮጵያ አንድነት ‹‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው›› እስኪቀር እንደሚዋጉ ቃል ገብተው እንደነበር ይነገራል፡፡ በእርግጥ እርሳቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን ጦርነት ውስጥ ዘፍቀው መሸሸት እንደሌለባቸው በአደባባይ ነግረዋቸዋል፡፡
ለአብነት ያህል በመጨረሻው ሸንጎ አንድ የሀይማኖት መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱትን ሀገርና ህዝብ ጥለው መሄድ እንደሌለባቸው በግልጽ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፡፡ ‹‹….50 ሚሊዮን ህዝብ በጦርነት ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው፣ በእርስዎ ኃላፊነት 18 ዓመት ሙሉ መርተው ሳያደራድሩ፣ ሳያረጋጉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሳት ዳርገው፣ በአሁኑ ሰዓት ከመሞት በስተቀር፣ የቴዎድሮስን ጽዋ ከመጠጣት በስተቀር፣ ሌላ እድል የለዎትም፡፡ እንደሌሎች መሪዎች ኢሮፕ ይፈረጥ ጣሉ ብዬ እምነት የለኝም፡፡ እግዚያብሄር ምስክሬ ነው፡፡ ይህን ህዝብ አጋልጠው ይሄዳሉ አልልም፡፡ መንጌ፤ ከሷ ወንበር ላይ እንደቋንጣ ደርቀው እንደሚቀሩ አምንብዎ ታለሁ፡፡ ይህንን ባያደርጉ ግን ታሪክ ይፋረድዎታል፡፡››
በዚያ የሀይማኖት መሪዎች ስለ እውነት ይናገሩ በነበረው ወቅት ከንግግራቸው ሁለት የግንቦት ጦሶችን በግልጽ እንረዳለን፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ፕሬዝደንት መንግስቱ የፈጠሩትን ቀውስ ‹‹….50 ሚሊዮን ህዝብ በጦርነት ባህር ማግደው፣ ቆስቁሰው፣ በእርስዎ ኃላፊነት 18 ዓመት ሙሉ መርተው ሳያደራድሩ፣ ሳያረጋጉ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለእሳት ዳርገው፣›› ሲሉ ስለ ቀውሱ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ይህን ህዝብ አጋልጠው ይሄዳሉ አልልም፡፡›› ሲሉ ህወሓትና ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል ጠላት እንደሆኑ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
ግንቦት 13/1983 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ  ‹‹ጓድ ሊቀመንበር››ን አሞካሽቶ የማይጠግበው ሚዲያ ‹‹ጦርነቱ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም፡፡ ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆም፣ ስምምነት እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃ/ማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጭ ሄደዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ም/ፕሬዘዳንት ሌፍትናንት ጀኔራል ተስፋዬ ወ/ኪዳን ተክተው ይሰራሉ፡፡›› ተባለ፡፡
‹‹ከመንግስቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!›› ይል የነበር ካድሬ ደግሞ ጆሮው ሊቀበለው የማይችለውን ነገር ሰማ፡፡ ለመንግስቱ ኃይለማርያም ቆሞ አመራሮቹን በጭካኔ ያረደው፣ በጭካኔ ዓይና ቸውን ያወጣውንና አስከሬናቸውን በአስመራ ጎዳና የጎተተው የ102ኛ ሰራዊት የመጨረሻው ተስፋውን ቆረጠ፡፡ ‹‹መንጌ!›› ሲል የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ እጣ ፈንታው ‹‹ገንጣይ አስገንጣይ›› ሲባሉና ኢትዮጵያን ሊገነጥሉ ሲታገሉ በኖሩት ሻዕቢያና ህወሓት ስር ሆነ፡፡ ሻዕቢያና ህወሓት በሚጠሏት ኢትዮጵያ ላይ የሚፈነጩበት መንገድ ወለል ብሎ ተከፈተ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጦሰኛ ግንቦት ወር አደጋ ውስጥ ገባች፡፡ ይባስ ብሎ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን የተኩት ተስፋዬ ወልደኪዳን መንግስቱ ጥሎ ከወጣበት ከሁለት ቀን በኋላ የኢትዮጵያ ጦር መሳሪያውን ለ‹‹ወንበዴ›› አስረክቦ ወደ ፈለገበት ቦታ እንዲሄድ አዋጅ አስነገሩ፡፡ ለአንድነት ሲዋጋ የኖረው ሰራዊትም መሳሪያውን እየጣለ ወደየትውልድ ቦታውና ወደ ከተማው ሲያቀና ለህወሓትና ሻዕቢያ እንዲሁም በደርግ ለተማረረው አርሶ አደር ጥይት ሰለባ ሆነ፡፡ እንደ ምንም ብሎ ህይወቱን ያተረፈው ደግሞ በዚህ ደሙን ባፈሰሰላት አገር ጎዳና ላይ ወደቀ፡፡
ሰራዊቱ ትጥቁን እንዲፈታ በጊዜያዊ ፕሬዝደንቱ መጠየቁን ተከትሎ ሻዕቢያ በወቅቱ ሁለተኛዋ የኢትዮጵያ ከተማ የነበረችውን አስመራን ተቆጣጠረ፡፡ አረመኔዎቹ የሻዕቢያ ታጋዮች ኢትዮጵያውያንን እንደ ወራሪ ጠላት መዓት አወረዱባቸው፡፡ ትህነግ/ ኢህአዴግ ከአራት ቀን በኋላ ግንቦት 20 አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ ደርግ መሸነፉን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ይህ ወር መልካም ነገር ይዞ ይመጣል ብለው ቢጠብቁም ያመጣው ግን ተቃራኒውን ሆነ፡
ግንቦት 20… ጥቁሩ ቀን
በግንቦት ወር የመጀመሪያ ቀናት ሻዕቢያና ትህነግ አሜሪካን ጨምሮ ከምዕራባውያን መንግስታት ጋር ሎንደን ውይይት አድርገው ነበር፡፡ ከዚህ ውይይት ዋና ጭብጥ መካከል አንዱ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል በሚል ከምዕራባዊያኑ በተለይም ከአሜሪካ የተነሳው ሀሳብ ነበር፡፡ ይሁንና መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደማያስፈልጋት ሽንጡን ገትሮ በመከራከር ምን አልባትም ‹‹ለማስተዳደር›› በሚፈልጋት አገር ሉዓላዊነትን አሳልፎ የሰጠ የመጀመሪያው “መሪ” የሚያደርገውን ከሃዲነት ፈጸመ፡፡ ግንቦት 21 ቀን ኤርትራ በሻዕቢያ ስር መተዳ ደር ጀመረች፡፡ ያ የተደከመበት፣ በርካታ የሰው ነፍስ የጠፋበት ሉዓላዊነት ግብጽ ጀምራው እነ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ሌሎች የአረብ አገራት ትኩስ ስንቅ እየቋጠሩላቸውና የደርግም ስህተት ተጨምሮበት በአገር አንድነት ላይ በተ ነሱት ‹‹ወንበዴዎች›› የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡ ሉዓላዊነቷ ተደፈረ፡፡
ትህነግና ሻዕቢያ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትም ጀምረው ተሻርከው እንጨት፣ ብረት፣ ቡና፣ ወርቅ፣ ብር፣ ሳይሉ ያገኙትን የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት መዘበሩ፡፡ ከደርግ ጋርም ሆነ ካለፉት ስርዓት ጋር ግን ኙነት አለው ያሉትን ህዝብ ላይ እስራት፣ ግድያና ሌሎች አሰቃቂ እርምጃዎችን ወሰዱ፡፡ እርግጥ ነው ይህ ተባብሮ ኢትዮጵያን የመመዝበር ተግባር በስምምነት አልዘለ ቀም፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ለማጋበስ በመ ነበራቸው አለመግባባት እርስ በእርስ መነካከስ ጀመሩ፡ ፡ በዚህ የሁለት ጅቦች ጠብ ምክንያትም ህወሓት የሚ ገዛት ኢትዮጵያ ግንቦት 4/1990 ዓ.ም በሻዕቢያ ተወረ ረች፡፡ በሁለቱ ግለሰቦች፣ ፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊና ድሮ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል በርሃ በነበሩበት ወቅት በተፈ ጠረ ቁርሾ 70 ሺ ያህል ህዝብ በዚህ ወርሃ ግንቦት በተፈ ጠረ ግጭት ሰበብ ውድ ህይወቱን አጣ፡፡ በዚህ ግጭት ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥርሳቸው ሳይቀር እየ ተነቀለ ከአስመራ ተባረሩ፡፡ ትህነግ/ኢህአዴግም ቢሆን ያ አብዛኛውን ተግባሩን ካስተማረው ሻዕቢያ በቀሰመው ተሞክሮ መሰረት ምላሹን ሰጠ፡፡
ትህነግ/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ እርዳታ ለመ ለመን እከተለዋለሁ ካለው የይስሙላ ዴሞክራሲ ስም አፋኝነቱን ያሰፈነ ድርጅት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ የራሱንና የሻዕቢያ ጥቅም አስቀድሟል፡፡ ኢትዮጵ ያውያንን በዘውግ ከፋፍሎ መግዛትን እንደዋነኛ ስልት ወስዶታል፡፡ የይስሙላህ ዴሞክራሲና ምርጫ አሰፈንኩ ቢልም ከመግዢያነት ያለፈ ግን አልነበረም፡፡ ለዚህም ህወሓት/ኢህአዴግ ስቃይ እያደረሰበት የሚገኘውን ህዝብ ጥላ ለመሆን በህገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋሙት ፓርቲዎችና ፖለቲከኞቻቸው የደረሰባቸውን መከራ ማንሳት በቂ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በየክልሉ ኦነግና ትህነግ/ኢህአዴግ ሲጨፈጭፉት የነበረውን ኢትዮጵያ ዊና የኢትዮጵያ አንድነት ለመታደግ የተነሳው መዐሕድ የመጀመሪያው ተጠቂ ነበር፡፡ የዚህ ፓርቲ መስራችና እውቁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ደግሞ የዚህ የግንቦት ዘራሽ አምባገነን ስርዓት ዋነኛ ተጠቂ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ እስር ቤት ሲማቅቁ ቆይተው ግንቦት 1/1991 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ የሚገርመው መንግስቱ ኃይለማርያም እና ውጫዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በከፈቱላ ቸው ቀዳዳ በግንቦት ነፋስ ወደ ስልጣን ብቅ ያሉትና የአሁኑ ስርዓት ‹‹መሃንዲስ›› መለስ ዜናዊም በዚሁ የደም ወር እውቁ ፕሮፌሰር ተሰቃይተው በሞቱበት ቀን የተወ ለዱ መሆናቸው ነው፡፡ ፕሮፈሰሩ ከሞቱ በኋላ የመዐሕድ አካል የነበሩም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በ1997 ተጠናክረው በአዲስ ምዕራፍ ለትግል የመጡበት ዘመን ነበር፡፡ በተለይ የግ ንቦት 1997 ምርጫ ኢትዮጵያውያን ካሉበት አምባገነ ናዊ አገዛዝ ነጻ እንዲሚያወጣ በኢትዮጵያውያኑ ብቻ ሳይሆን ህወሓት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናውና ለዓለምም እንደማይመጥንና እንደማይበጅ በተረዳው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ነጻ ለመውጣት በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ ጣቢያ የጎረፉ ትም በዚህ ቀን ነው፡፡ የሚያዝያው ሰልፍና ሌሎች መነ ቃቂያዎች ግንቦት 7 ኢትዮጵያውያንን ነጻ የምታወጣ ቀን አስመስሏታል፡፡ እነዚያ ንፍሮ ቀቅለው፣ ቡና አፍል ተው ግንቦት ክፉውን ይዞ እንዳይመጣ ተስፋ ሳይቆረጡ ሲልምኑ የኖሩት ኢትዮጵያውያን አሁን አዲስ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡  ተስፋው ከአንድ ቀን በላይ አልዘለለም እንጂ፡፡
ተቃዋሚ አጣን ሲሉ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ማታ ላይ ብቅ ብለው ይህን የግንቦት 7 ተስፋ አቧራ ነሰነሱበት፡፡ ማታ በኢቲቪ ብቅ ብለው አሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያንን ለቀየደው የጸረ ሽብር፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሚዲያ…..ሌሎች ቀያጅ አዋጆች መሰረት የሆነውን ጊዜያዊ አዋጅ አወጁ፡፡ በነጋታው ግንቦት 8/1997 ህዝብ ከቤት ውጭ ምንም አይነት ስብሰባም ሆነ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ተከለከለ፡፡ በዚሁ ቀን ‹‹አብዮታዊ›› ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ምንም ባላሳወቀበት ግንቦት 8 ከአዲስ አበባ ውጭ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ማሻነፉን በተቆጣጠረው ሚዲያ አሳወቀ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰላማዊ ትግልን የቀፈደዱ በርካታ እርምጃዎች በዚሁና በቀጣዩ ግንቦቶች ተወስደዋል፡፡ ግንቦት 2002 ዓ.ም ምርጫ ደግሞ አፋኝነቱን ያጠናከረው ኢህአዴግ አስፈራርቶም፣ አጭበርብሮም 99.6 በመቶ አሸንፎ ‹‹አውራ ነኝ›› ያለበትን ኢትዮጵያውያንን በገዥነት እንደሚቀጥል ያቀደበት ወቅት ሆነ፡፡ ባለፉት 5 አመታት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲካውን ያነቃቃሉ ብሎ የፈራቸውን ብሎገሮች አስሮ፣ ህዝቡን 1ለ5 ጠርንፎ፣ እና አጭበርብሮ የዘንድሮውን ምርጫ 100 በ100 እንዳሸነፈ እየተነገረ ነው፡፡ በእርግጥ በተለይ ከ1997 በኋላ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ኢህአዴግ የሚወዳደሩት ሳይሆን የሚታገሉት እንደሆነ በማመናቸው ምርጫውን 90፣99.6፣ 100 አሸነፍኩ ቢል የሚገርማቸው አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ግን ግንቦት ለኢትዮጵያውያን የመከራ ወር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
በአጠቃላይ ግንቦት 20 ህወሓት/ኢህአዴግ ሳይገባው፣ ለኢትዮጵያውያን ሳያስብና ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ኢት ዮጵያን የተቆጣጠረበት፣ በኢትዮጵያውያን  ‹‹ህገ አራዊት›› መተግበር የጀመረበት፣ ዓለም አንድ በሆነችበት ወቅት መገንጠልን በወርቃማ መብትነት ያጸደቀበት፣ ኢትዮጵያውያን አገራ ቸው ውስጥ እንዳይዘዋወሩ የማንነት ግንብ የገነባበት ጥቁር ቀን ነው፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያዊ አላማ ያፈነገጠ መሆኑ፣ ኢትዮጵያው ያንን በስስ ማንነት መከፋፈሉ፣ ለራሱ ቡድናዊ ጥቅም መሯሯጡ ትህነግ/ ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትን ቀን ለኢትዮጵያውያን ጨለማ፣ አዲስ የጭቆና ዘመን ነው፡፡ ይህን ቀን ምናልባትም የጀርመኑ ሂትለር ለቤልጀም ሳይሆን ለራሱ የስልጣንና ልሂቃን ጥቅም፣ በበላይነት ተወጥሮ ቤልጀምን ከወረረበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግንቦት 1940 ተመሳሳይ ወቅት (ግንቦት 20) ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ እንዲያውም ናዚዎቹ የጀርመንን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ቤልጀምን ሰጥ ለጥ አድርገው ለመግዛት ግልጽ አላማ ይዘው ነው የገቡት፡፡ ትህነግ ግን እስካሁንም ድረስ፣ ለባለፉት 23 አመታት የሚጠላትን አገር የገንጣይ ስምና አላማውን እንዳነገበ እየገዛት ይገኛል፡፡ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያን ንፍሮ አንፍረው፣ ቡና አፍልተው ‹መከረኛውን› አምላካ ቸውን መለመናቸው ቀጥለዋል፡፡ ግንቦት የሰጠው ‹‹አብ ዮታዊ›› ፓርቲ ግን በከፍፍለህ ግዛ፣ በስራትና ግርፋት፣ በኑሮ ውድነት፣ በመሰረታዊ አገልግሎት እጥረት፣ በሙስና ኢትዮጵያን የመከራ ምድር አድርጓታል፡፡ ግንቦት ደግሞ በአየር ንብረት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ውም ውጥንቅጡ የወጣ ክፉ ወር ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህም ነው ግንቦት አሁንም የትህነግ/ኢህአዴግ እንጂ የኢት ዮጵያውያን ወር አይደለም ለማለት የሚያስደፍረው፡፡
Filed in: Amharic