>

ከአንዳርጋቸው መፈታት ባሻገር ....(ዳንኤል ሺበሺ)

እኒህ የጀግና አባት በዚች ሰዓት ምን እያሰቡ ይሆን?… ልጃቸው አንዳርጋቸው ሲፈታ አቅፈው ለመሳም በደከመ ጉልበታቸው ቃሊቲ ተገኝተዋል። ያ መሆኑ ባይቀርም ባለቀ ሰዓትና በተወሰነ ጉዳይ ላይ ክፋታቸውን ማሣየት ልማድ የሆነባቸው ባገኙት አጋጣሚ በሽርፍራፊ ሰከንዶችም ቢሆን በማጉላላቱ ትንሽ ሀሤት ያደርጋሉ። የብዙዎች ሠዓትዋን መናፈቅ እዳለ ሆኖ መፈታቱ እርግጥ መሆኑ በቂ ነው።
አንዳርጋቸው እንደማንኛውም ግለሰብ የሞቀ እና የደመቀ ብሎም የተንደላቀቀ ህይወት መምራት በእጁ ነበር። እሱን አልፈለገም። ምክንያቱም የወጣበት ህዝብ በተበላሸ ፖለቲካ እና አመራር ሥቃዩን እየበላ እና በዴሞክራሲ ሥም ሲሸቀልበት እያየ ዝም ማለት ሥላልፈቀደ ነው። ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነበር። እንጠይቅ ከተባለ ሊጠየቅ የሚገባው ዴሞክራሢያዊ አሰራር ገቢር በማድረግ ፈንታ ፦”መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፤ ጫካውን ሞክሩት…” ሲል የነበረው አመራር ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰው በላ ነው። ሰው በላ እንዲሆን ያደረጉት ደግሞ ሥልጣንን ከሃብት ጋር ደምረው የያዙ አመራሮች እና ራዕይ አልባ መሪዎች ናቸው።
 የአንዳርጋቸው መፈታት ለእኔ ከፈንጠዝያ ባሻገር ብዙ ምልክት ይሰጣል። ነብሰ በላው ፖለቲካ ጥርሱን ጨርሶ ድዱ አልነክሥ ብሎት ወደ መቃብር እየወረደ ይሆን? ብየ ተሥፋ አደርጋለሁ። እንኩዋንም ጥርሱ አለቀ!!…በፖለቲካ ምክንያት አንድም ሰው የማይሞትባትና ጨለማ ክፍል የማይጣልባት ኢትዮጵያ እየተወለደች ይሆን?… እያልኩ ወደ ፈጣሪ አንጋጥጣለሁ።
አሁን እያየን ላለነው ለውጥ ህይወታቸውን የሰጡ፣ የታሰሩት እና የተሰደዱት… የዚህ አሥከፊ ታሪካችን የመጨረሻዎቹ ሰማእታት እንደሚሆኑ ተሥፋ አደርጋለሁ። ዋጋ የተከፈለበት የዴሞክራሢው ጉዳይም ዋና ጥያቄ ነው።
ለሃገሬ እና ህዝቦችዋ ፍቅር፣ ሠላም፣ መግባባትና መደማመጥ እመኛለሁ።
መግባባት ለዘላለም ይኑር!!!!
Filed in: Amharic