>
5:13 pm - Wednesday April 20, 1087

ሕዝብ የት ነው? (ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም)

የሰሞኑ ወሬ የኢትዮጵያን አገዛዝ አመራር አደናጋሪ አድርጎታል፤ አንደኛ ከእስር ሊፈቱ የማይገባቸው ሰዎች ተፈቱ፤ ሁለተኛ ሹመት የማይገባቸው ሰዎች ተሸሙ፤ ሁለቱም አብዛኛውን ሰው ያበሳጫሉ፤ ከዚያም አልፎ የለውጡን ተስፋ ያደበዝዛል፤ በሁለቱም ላይ አብዛኛው ሕዝብ ላይ ያደረበት ስሜት አያስደንቅም፡፡
ነገር ግን አዋቂዎችና ምሁራን፣ ጉዳዩን በብዙ መልኩ እያገላበጡ የማየት ችሎታ ያላቸው ሰዎች ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች የማይፈቱ ሰዎች በመፈታታቸውና የማይሾሙ ሰዎች በመሾማቸው ሊደነቁ አይገባም፤ እነዚህ ሰዎች በእውቀታቸውና በልምዳቸው ከጉዳዩ በስተጀርባ ያሉትን ተፎካካሪ ኃይሎች የሚያውቋቸውና የትግሉንም ልክ ከሞላ›ጎደል መረዳት የሚችሉ ናቸው፤ ስለዚህም የተጠቀሱትን ሁለት ጉዳዮች በተመለከተ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከባድ ጫና የፖሊቲካ ተንታኞች ነን የሚሉት ሁሉ ሊስቱት አይገባም፤ ለውጥ በመካሄድ ላይ ነው፤ አላለቀም፤ ማለትም የደረጁና ሃያ ሰባት ዓመታት ሙሉ ሀብት ያካበቱ ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ፤ የዓቢይና የለማ ወገኖች ገና ዳዴ እያሉ ነው፤ በተጨማሪም ነባሮቹ የደኅንነትና የጦር ኃይሎች አሏቸው ይባላል፤ አዲሶቹ ያላቸው በሕዝብ ላይ ያላቸው እምነት ብቻ ነው፡፡
ሕዝብ እንደልማዱ አድፍጧል፤ አሸናፊው ሲታወቅ እልል ለማለትና ለማጨብጨብ ተዘጋጅቶ ይጠብቃል፡፡
Filed in: Amharic