>

የኦሎምፒክ ጌጣችን ጤናዋ ታውኮ ጸበል ቦታ መቀረጿ  ያስከተለው ውዥምብር

የኦሎምፒክ ጌጣችን አትሌት ጌጤ ዋሚ ጤናዋ መታወኩ ትልቅ ርእሰ ጉዳይ ሆኗል። “የማህበራዊ ሚድያው ማህበራዊ ቀውስ እያመጣ ነው፤ ሊያጠፋን ነው ማስቆም አለብን…” ባዩን አትሌት ሀይሌን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎችን ምልከታ አካተናል፡-

በፈውስ ቦታ የቪዲዮ ካሜራ መቅረጽ ለምን አስፈለግ???

ሚልዮን በላቸው
የተለመደው አእምሯዊ ስራው ከቁጥጥር ውጪ የሆነን ሰውስ መቅረጽስ ተገቢ ነው ወይ? ከተቀረጸስ በኋላ በዚህ መልኩ ከራሷ ከጌጤና በስፍራው ከነበሩ ሰዎች ውጪ ለአለም ለማሳዬት መፈለጉ ምክንያቱ ምንድነው? ማስታወቂያ ነው ወይስ ምንድነው?
ጌጤ ራሷን በማታቅበት ሁኔታ እንድትቀረጽ ፈቅዳለች ወይ? (በሚስጥር መጠበቅ ያለባቸው የግለሰብ ጉዳዮች ከግለሰቡ ፈቃድ /Consent/ ውጪ የህክምናን መረጃ ለሌላ ወገን አሳልፎ መስጠት እዚህ በምንኖርበት አገር እንደ ወንጀል ተቆጥሮ እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስርና ከ50 ሺህ ዶላር በላይ ቅጣት ይኖረዋል፣ እንደ ጉዳዩ ቅጣቱ ሊቀንስም ሊጨምርም ይችላል )?
 በፈውስ ስርዓቱ ላይ የሚገጥማትን ሁኔታ ቀርጾ ማስተላለፉ በሒወቷ፣ በልጇ፣ በቤተሰቧ ላይ ተጽእኖ ስላለማሳደሩስ ቀርጸው ያስተላለፉት ሰዎች እርግጠኛ ሆነዋል ወይ የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው??? ከዚህ በኋላ በእርሷም ሆነ በቤተሰቦቿ ላይ የሚደርስ የሞራል ጉዳት ቢኖርስ ሃላፊነቱን ማን ይወስዳል?
የጌጤ ቅርብ ሰዎች እንደሚነግሩን ይሄ ጉዳይ ከተፈጸመ ትንሽ መቆዬቱን፣ ስለነበረው ነገር ምንም እንደማታስታውስ ጌጤ መናገሯን ነው የሚገልጹት።
እንደ ኢትዮጵያዊነት የሚነሳው ሌላው የሞራል ጥየቄ የሚሆነው ፈውስ በቪዲዮ መቀረጹ፣ ከተቀረጸም ፈውስን ለማግኘት መጥቶ የተቀረጸው ሰው ፈቃድ አለመጠዬቁ ነው?
ማህበራዊ ህይወታችን እጅግ የተሳሳረ በመሆኑ ተጽእኖውም የዛኑ ያህል ጠበቅ ሊል ስለሚችል እንዲህ አይነቱ ድርጊት ጥንቃቄ፣ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን የሚጠይቅ መሆን ይኖርበታል…

 “ሰው ተዋርዶ ሰይጣን ክብር ያገኘበት ዘመን”

  (ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት)
“የቤተ ክርስቲያናችን የገድላትና የተአምራት መጻሕፍት ሲጻፉ፣ የሰዎቹን ክብር በሚጠብቅ መንገድ ካልሆነ በቀር ችግር ደርሶባቸው ተአምር የተደረገላቸውን ሰዎች የተጸውዖ ስም አይገለጡም፣ ወይም የክርስትና ስማቸው ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ሰዎቹን በስማቸው መጥራት ቢያስፈልግ እንኳን ለዝርዝር ማንነታቸው በማይመች ስም ይገለጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረግበት ዋናው ምክንያት የሰውን ልጅ ሰብአዊ ክብር(Human dignity) ለመጠበቅ ነው፡፡ እነርሱ ቢያልፉም እንኳን ልጅና ልጅ ልጅ ይኖራልና፡፡
እኅታችን ጌጤ ዋሚ ‹ሩጫን በሚከለክሉ በአጋንንት› ተያዘች ተብሎ የተለቀቀባትን ቪዲዮ ስመለከት በእምነት ስም የሚነግዱ ሰዎች የደረሱበትን ሞራላዊ ኪሣራ አየሁት፡፡ ከመጀመሪያው ሰይጣንን እየቀዱ ለገበያ ማዋል በየትኛውም የቅዱሳን ሕይወት ውስጥ የማናየው ነው፡፡ መቼም ሰይጣን እንደዚህ ዘመን በክብር መድረክ ያገኘበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህም አልፎ ልጅ፣ ቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ዓለም አቀፋዊ ተክለ ሰብእና ያላትን አትሌት በዚያ ዓይነት ክብርን በሚነካ ሁኔታ እያሰቃዩ በቪዲዮ ማሳየት ፈጽሞ የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰውነትን ማዋረድ እግዚአብሔርን ማዋረድ ነውና፡፡ አስፈላጊ ነው ካለች እርሷ ራሷ ትንገረን እንጂ ይህንን የመሰለ ቪዲዮ እንኳን ሌላው እርሷም ልታሳየን የተገባ አይደለም፡፡
ሃይማኖት ታረደ ደሙን ውሻ ላሰው
ከንግዲህ ልብ ልብ አልተገናኘም ሰው

እንደተባለው ሆኖብን ነው እንጂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወትስ በሰውነት ክብር ላይ የሚቀልድ አልነበረም፡፡ የአንድን ሰው ‹ፈዋሽነት› ለማሳየት የሌላን ሰው ዝና፣ ክብርና ሰብአዊ መብት መከስከስ በምንም መልኩ ጸጋ እግዚአብሔርን አያመለክትም፡፡ የወንድማቸውን ክብር ለመጠበቅ ያልፈጸሙትን ፈጸምን ብለው መከራ የተቀበሉት የነ አባ መቃርስ፣ የነ እንባ መሪና፣ የነ ሙሴ ጸሊም፣ ቤተ ክርስቲያን፤ ለራሳቸው ክብር ሲሉ የወገኖቻቸውን ክብር በሚደፈጥጡ ‹አጥማቂዎች› ሲቀለድባት ማየት ያማል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም የጳጳሳትን ዝውውር ከሚመለከት ይልቅ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሕግና ሥርዓት እንዲኖራቸው ቢያደርግ መልካም ነበር፡፡ ማን ያጥምቅ? የተጠማቂዎች ሰብአዊ ክብር፣ የተጠማቂዎችን መረጃ የመጠቀም መብት፣ በአደባባይ ራቁትን መቆምና ራቁትን ፎቶ የመነሣት ጉዳይ፣ የምስክርነት አሰጣጥ ሥነ ምግባር፣ የሴቶችና የሕጻናት መብቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና የአእምሮ ሕሙማን መብቶች፣ ወዘተ ሕግና ደንብ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ገና ከዚህ የከፋም እናያለን፡፡”

ከራሱ ሐሳብ የተጣላው ኃይሌ

መላቱ አለነ
አትሌት ኃይሌ በጌጤ ዋሚ መታመም ዙሪያ ጋዜጠኛ አበበ ጊደይ ሸገር ላይ ላቀረበለት ጥያቄዎች አስተያየት ሰጥቷል። ኃይሌ በመልሱ ያነሳቸውን ነጥቦች አንድባ’ንድ እንመልከት
1.”ሶሻል ሚዲያ ሊያጠፋን ነው – scoial media is social crisis”
ይህን ያለው የጌጤን  ቪዲዮ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ ስለተመለከተው ነው። ይሁን እንጂ ቪዲዮው የተቀረጸው በአባ ግርማ የቪዲዮ/የሚዲያ ክፍል ለመሆኑ ከዚህ በፊት የሳቸውን ስራዎችን የተመለከተ በቀላሉ ይገነዘባል።መውቀስ ካለበት እሳቸውን ብቻ መሆን አለበት። (አበበ ጊደይ እዚህ ጋር የቪዲዮውን ዋና ምንጭ ለኃይሌ ቢነግረው ጥሩ ነበር) አባ ግርማ በበኩላቸው ቪዲዮው እንዲታይ የሚፈልጉት “የፈውስ” ስራቸው እውነተኛነትን ለማሳየት፣ለማረጋገጥ ብለው ይሆናል::
ታዲያ ሰውስ ለምን ያባዛዋል?  ሰዎች  በYouTube ያገኙትን ቪዲዮ ወደ ፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚያመጡት በተለያዩ ምክንያቶች ሊሆን ይችላል። በአባ ግርማ “ፈውስ” የሚያምኑ ከሆነ የእምነታቸውን ዋጋ፣ ታምረ አምላክን ለማሳየት። ሌሎች ደግሞ በጌጤ ወቅታዊ ሁኔታ ተገርመው፣ ተደናግጠው…
ኃይሌ ግን ከዚህ ቀደም በኢትዮጲያ የተነሳውን ሕዝባዊ ቁጣ ከሶሻል ሚዲያ ጋር አገናኝቶ የማውገዙን ትክክለኛነት ለማጠናከር በፍጥነት ወደዚያ ገበቶ ሌላ ስህተት ፈጸመ። ማህበራዊ ድረ ገጽ የብዙ ሰዎችን ሰዎች ሐሳብ በአንድ ቋት የምታገኝበት ሰፈር ነው። እንደ ከዚህ በፊቱ ያንተንና የአከባቢህን፣ የመሰሎችህን ብቻ እንደምትሰማው የገሀዱ ዓለም የአካል ግኑኝነት-ንግግር ሳይሆን የሺህዎችን ሐሳብ በአንድ ጊዜ የምትወደውንም የማትወደውንም ይዞ የሚያጎርፍ ነው። በዚህ መድረከ ላይ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገባቸውን ነገሮች አስተዳድሪዎቹ ፌስቡክም ሆነ ሌሎች በዝርዝር አስቀምጠዋል። ይህን ተላልፎ የሚገኝ ካለ ሪፖርት ማድረግ ነው። የአባ ግርማ ቪዲዮ ግን ለዚያ የሚበቃ አይመስልኝም። ምክንያቱም የውሸት ነገር አልተሰራጨም (ፈውሱ ሳይሆን ቪዲዮ ቀረፃው:: ስለፈውሱ ኀይማኖተኞች ይወያዩ)። በርግጥ ኃይሌ በድፍረት “ተቀነባብሮ ነው” ሲል ይደመጣል።
የለ ሁኔታውን በኛ ባህል እንዳኘው ካልን ደግሞ ጌጤ የሄደችው ሕዝብ በሚሰበሰብበት የፈውስ አገልግሎት አደባባይ ነው። ቪዲዮውን በማየት ብቻ የሕዝብ ብዛቱን መገመት ይቻላል። ጌጤ ስትሄድ ደግሞ ይህንን አምናበት ነው። ቪዲዮው ሲቀረጽ ትመለከታለች ወይም ይዘዋት የሄዱ ሰዎችም ያውቃሉ፣ያያሉ። አባ ግርማ ከዚህ በፊት ሐሰተኛ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ቢታሰሩም በነፃ ተለቀዋል። ተከታዮቻቸውም ሺህዎች ናቸው።በatheist እይታ ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ የኢ-አማኒ አማኞችና የኀይማኖት ተከታዮች ክርክር እንጂ ከጌጤ ጋር አይገናኝም።
2. “አጋንንት የለም፣ የት ነው ያለው ጥንቆላ፣መተት የለም ስፖርት ላይ የለም ውሸት ነው፣ወሬ የወለደው ነው”
ኃይሌ “ስፖርት በልፋት፣በስራ የሚገኝ ነው” ማለቱ ትክክል ቢሆንም። ጥንቆላና መተት ለመኖሩ የግድ ያለበት ቦታ መሄድ አያስፈልግም።ኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም አለ። “ጌጤ ያለችው በውስጧ የምታስበውን ነው። እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ስትሄድ የምትናገረው በወስጥህ ያለውን በመድገም ነው” ይላል። እዚህ ጋር ኃይሌ psychiatrist ሆነ:: ድናም ይሁን አለዳነች ጌጤ ራሷ መልስ ይኖራታል።
የፈውስን ጉዳይ ለፈጣሪ የሚተወው ኃይሌ “የሰይጣን ስራ ይባላል። አንዳንድ ጊዜ የሰይጣንና  አጋንንት ስራ ለኔ አይገባኝም። እዚያ ላይ የማየው ማን ነው ሰይጣኑ ፣ ማነ ነው አጋንንቱ… የፈጣሪ ስራ ነው።   ለገንዘብ፣ለፕሮፓጋንዳ፣ የራስን ተፈላጊነት ለማጉላት… ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገው ስራ የፈጣሪ ስራ አይደለም። ይኼ የፈጣሪ ስራ ሳይሆን የአጋንንት ስራ ነው” ብሎ ይደመድማል።
አባ ግርማ ገንዘብ ይቀበላሉ እንዴ? ከተቀበሉ ፣ ልክ ለጠበል ገንዘብ እንደሚጠይቁ ቤተክርስትያኖች መወገዝ አለባቸው። ፈጣሪ የሰጠውን መንፈሳዊ ኃይል ስለምን ይሸጣል?
3.”ጌጤ psychiatrist የአዕምሮ ሕመም ሕክምና ባለሞያ ማየት ይገባታል”
ጀገናው አተሌት ትክክል ነው። ሰዎች በእምነታቸው በመንፈሳዊ ፈውስ እንደሚድኑ ሁሉ ሳይናሳዊ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። ዋናው መዳኑ ነው።
ኃይሌ ” ጓደኛዬ ናት” ብሎ እየተናገረ ጌጤ አባ ግርማ ጋ እስክትሄድ፣ ጉዳዩ በቪዲዮ እስኪቀረጽና ለማህበራዊ ሚዲያ እስኪቀርብ ድረሰ ይህ የኃይሌ መፍትሔ የት ሄዶ ነበር?
4.”ጌጤ ኃይለኛ ናት” 
ሲጀምር “ማህበራዊ ሚዲያ ሊያጠፋን ነው” ብሎ በሕዝብ አደባባይ የተቀረፀው የጌጤ ጉዳይ በማህበራዊ  ሚዲያ መሰራጨቱን የኮነነው ኃይሌ የተናገረውን በደቂቃዎች ውስጥ ዘንግቶ የጌጤን ምስጢር ራሱ መዘርዘር ተያያዘ።
“ኃይለኝነቷ እየጎዳት መጠቷል። በተለያየ ምክንያት በቤተሰብም ለማስታረቅ (ከባሏ ጋር)  የሞከርናቸው ነገሮች አሉ:: በሷ ኃይለኝነት ሊሳኩልን አልቻለም:: ትላንት በፊልም ውስጥ ያየሁት ያንን ኃይለኝነቷን ነው።” ይላል ኃይሌ። ለምን ይህን ምስጢር ወይም በግል የሚያውቀውን ጉዳይዋን ለአደባባይ ያበቃዋል? ይህንንም ከማህበራዊ ሚዲያ “ጥፋት” እንመድበው?
ሌላው እውነት ደግሞ ኃይሌ የጌጤን ችግሮች ያውቃል ማለት ነው። ስለዚህ እንደዚያ ከሆነ  ለማስታረቅ ከመሞከር ባለፈ መፍትሔ ብሎ ያቀረበውን psychiatrist በተጨባጭ ሞክሯል ወይ?
ኃይሌ ለጌጤ ችግር መፍትሔ ሊሰጥ ወይም የመፍትሔ ሐሳብ ሊያቀርብ ቀርቶ ከራሱ ሐሳብ ጋር መስማማት አቅቶት ተስተውሏል::
“ማህበራዊ ሚዲያ ሊያጠፋን ነው” ብሎ የተንገበገበውን ያህል ሕዝብና ሀገር በጥይት የሚያጠፋውን መንግስት አንድም ቀን አውግዞ አያውቅም። “ሶሻል ሚዲያ ማህበራዊ ቀውስ አመጣ” የሚለው ኃይሌ ሀገራዊ ቀውስ ያንሰራፋውን ህወሓት-ኢህአዴግ አንድም ቀን ወቅሶ አያውቅም። እንዲህም ሆኖ የሀገር ሽማግሌ የሚል ማዕረግ ከተሸከመ 13 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ብሔራዊ ጀግናችን እንደመሆኑ ከአንደበቱ የሚወጡ ቃላቶችና የሕይወት ጉዞዎቹ ሁሉ  ጥቅም ወይም ጉዳት እንደሚኖራቸው ተረድቶ አስተውሎ ቢራመድ መልካም ነው።
Filed in: Amharic