>

በእስር ላይ ለሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ጋዜጠኞች ጠበቃ ኣመሃ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ (በዳዊት ሰሎሞን)

የስድስቱን ጦማርያንና የሁለቱን (የኤዶምና የተስፋለምን)ጉዳይ በመከታተል በፍርድ ቤት እየወከሏቸው የሚገኙት የህግ ባለሞያ አቶ አምሐ ሁልግዜም የህግ ደምበኞቻቸው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ግቢው ውስጥ ውጪ ለምንጠብቃቸው ጋዜጠኞች በዝጉ ችሎት ምን እንደተከናወነ ያለምንም መሰላቸት ያስረዳሉ፡፡በትናንትናው የፍርድ ቤት ውሎም ጠበቃው ከዋናው ግቢ ውጪ አሰፍስፈን ለጠበቅናቸው ጋዜጠኞች መረጃ አድርሰውናል፡፡ለተባባሪነታቸው፣ድካም ሳይነበብባቸው፣አንተ ወይም አንቺ ከየትኛው ሚዲያ ነህ/ሽ ሳይሉ ለሚዥጎደጉድላቸው ጥያቄ ምለሽ በመስጠታቸው ምስጋናዬ ይድረሳቸው፡፡
ጥያቄ —በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ፖሊስ አዲስ ያቀረበው ነገር ምንድን ነው
ጠበቃ አምሐ –አዲስ ያቀረበውን ነገር በዶክመንት መልክ አላቀረበም፡፡በቃል ያሉት የተወሰኑ ምስክሮችን መስማት መጀመራቸውን፣ለባንክ ቤቶች ለጻፍነው ደብዳቤ ከአንዳንዶቹ ምላሽ አግኝተናል፣የተወሰኑ ዶክመንቶችን አስተርጉመናል ነው ያሉት፡፡ነገር ግን ምን ያህል ምስክሮችን ለመስማት አቅደው ምን ያህሉን ማድመጥ እንደቻሉ አልተናገሩም፣ያስተረጎሟቸው ዶክመንቶች ጠረጠርንበት ለሚሉት ወንጀል ያለው አስረጂነት /ተቀራራቢነት ምን እንደሆነም አልገለጹም ፡፡
ጥያቄ– ፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ጊዜያት በፖሊስ ለሚጠየቀው የምርመራ ጊዜ እየፈቀደ ነገር ግን ቀጠሮ የተፈቀደበት ምርመራ ሳይከናወን ሲቀር ፖሊስ መጫን አይችልም
ጠበቃ አምሐ — የእኛም ትልቁ መከራከሪያ ይህው ነበር፡፡ፖሊስ ቀጠሮ የጠየቀበትን ምክንያት ሳይሰራ የተለያዮ ሰበቦችን እያቀረበ ደምበኞቼን እያጉላላ ነው ብለናል፡፡አሁን ግን ፍርድ ቤቱ ጠንከር ያለ ትዕዛዝ በመስጠት ይህው ትዕዛዝም መዝገቡ ላይ እንዲሰፍር አድርጓል፡፡አሁን የተሰጠው የሃያ ስምንት ቀን የምርመራ ጊዜም የመጨረሻው እንደሚሆን ፍርድ ቤቱ ገልጻል፡፡እኛም ይህ ትዕዛዝ መዝገብ ላይ መስፈሩን አረጋግጠናል፡፡
ጥያቄ– በየቀጠሮው ዳኞች እተቀያየሩ መቅረባቸው አሁን ተስፋ የሚያደርጉት ነገር ላይ ተጽእኖ አይፈጥርም
ጠበቃ አምሐ — አይፈጥርም በማለት መናገር አልችልም፡፡ለምሳሌ ከዚህ ቀደም አንድ ዳኛ ከመነሻው ክሳችሁን በሽብርተኝነት ያላደረጋችሁት በመሆኑ አሁን መለወጥ አትችሉም በማለት ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሊመራ እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡በሌላ ቀጠር ውሳኔው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ይህ ግን መዝገብ ላይ የሰፈረ በመሆኑ የዳኛው መለወጥ ለውጥ ይፈጥራል ብለን አንገምትም፡፡
ጥያቄ– አሁን ፖሊስ የሃያ ስምንት ቀን ጊዜ ቀጠሮ የተፈቀደለት በዚህ ግዜ ውስጥ ምን አደርጋለሁ ብሎ ነው?
ጠበቃ አምሐ — ፍርድ ቤቱ ተባባሪዎቻቸውን ለመያዝና የትርጉም ስራ ለመስራት ለሚለው ተጨማሪ ጊዜ እንደማይሰጠው አስታውቋል፡፡በተጨማሪው ጊዜ አለኝ የሚለውን ማስረጃ ሰብስቦ እንዲጨርስና ምስክሮቹን እንዲያደምጥ ተነግሮታል፡፡በእርግጥ ፖሊስ ያልያዝኳቸው ተባባሪዎች አሉ ክፍለ ሃገር ስለሄዱብኝ ላገኛቸው አልቻልኩም ብሏል፡፡በነገርህ ላይ ፖሊስ በቀጣዮ ጊዜ ሲቀርብ ፍርድ ቤቱን ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ጥያቄ– ምናልባት ፖሊስ የጸረ ሽብር አዋጁን በማስታከክ ይሆን ቀጠሮ እየደጋገመ የሚጠይቀው
ጠበቃ አምሐ — አዎን አዋጁ ለአራት ወራት ፖሊስ ቀጠሮ በመጤቅ የምርመራ ስራውን እንዲሰራ ይፈቅድለታል፡፡ይህ ተባለው ግን ለምርመራ ነው፡፡ምንም ሳይሰሩ ምርመራዬን ስላልጨረስኩ እንዲል ግን አይፈቅድለትም፡፡ፍርድ ቤቱም ይህንኑ በመረዳቱ ይመስለኛል ከአሁን በኋላ አልፈቅድም ያለው፡፡
ጥያቄ — ደምበኞችዎ ዛሬ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በማዕከላዊ ከዚህ ቀደም ተናግረውት ከነበረ ውጪ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደደረሰባቸው ተናግረው ይሆን
ጠበቃ አምሐ –ጋዜጠኛ አስማማው ሁለት ነገሮችን ዛሬ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ነበር፡፡የጀርባ ህመም እንዳለበት በመግለጽ መርማሪው ወንበር እንዲያቀርብለት ነግሮት የነበረ ቢሆንም ይህ አልተደረገልኝም ብሏል፡፡የእህቱ የባንክ ደብተር በፖሊስ በመወሰዱም ቤተሰቡ ችግር ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ለማዕከላዊ ሰዎች ነግሯቸው ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል፡፡የአስማማው መርማሪ በበኩሉ ህመምተኛ መሆኑን እንደነገረው ነገር ግን ወንበር ስጠኝ አላለኝም በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የአስማማውን እሀት የባንክ ደብተር ከምርመራው ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኖራል በማለት ከጠረጠረ ሊያቆየው እንደሚችል የጠቀሰ ሲሆን ህመምተኛ በመሆኑ ግን ጤንነቱ እንዳይጎዳ ፖሊስ አገሪቱ በምትችለው መጠን ሊያስተናግደው እንደሚገባና ይህንኑ ማግኘትም ህገ መንግስታዊ መብቱ መሆኑን በማውሳት የጠየቀው እንዲፈጸምለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡መርማሪውም የተባለውን እንደሚያደርግ ለፍርድ ቤቱ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
ጥያቄ –ጉዳዮን እንደሚከታተል ጠበቃና ግለሰብ በሂደቱ ላይ ያለዎት ተስፋ ምንድን ነው
ጠበቃ አምሐ — ብሩህ ነገር ይታየኛል ማለት ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ምክንያቱም እንደሚገባን እየተደመጥን አይደለም፡፡ፖሊስ የጠየቀውን እያገኘ ነው፡፡ ይህ ነገር ተስፈኛ እንዳንሆን ያደርገናል፡፡

Filed in: Amharic