>

“ ህገ መንግስቱን ተቀበል” የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ወደ ድርድር አይገባም! (ፋሲል የኔዓለም)

አህመድ ሽዴ የተባለው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የእነ ኦቦ ሌንጮችን ጉዞ በተመለከተ የሰጠውን መግለጫ ሰማሁት። “ህገመንግስታዊ ስርዓቱን” የተቀበሉ ሃይሎች መግባት አለባቸው ይላል። ያው እነ መለስ ዜናዊ ሲሉት ከነበረው የተለዬ ነገር የለውም። ህገመንግስታዊ ስርዓቱ ሁሉንም በሚያሳትፍ መልኩ እንዲከለስ የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት እንደሌለው ከአህመድ ንግግር ለመረዳት ችያለሁ። በአጭሩ ወያኔ ለድርድር ያስቀመጠውን “ቅድመ ሁኔታ” አልለወጠም ማለት ነው። ቀደም ብሎም ህገመንግስቱን እንቀበላለን ያሉ አንዳንድ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ገብተዋል። ምን ውጤት እንዳገኙ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ህገመንግስቱ በኢህአዴግ አስተሳሰብ ተቀርጾ የኢህአዴግን ስልጣን ለማስጠበቅ የተዘጋጀ ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ አንዳንድ ክለሳዎች ካልተደረጉበት በስተቀር ሁሉንም ድርደርቶች በእኩል ሊያሳትፍ አይችልም። ፖለቲካው አሳታፊ እንዲሆን ከተፈለገ ህገመንግስቱና እሱን ተንተርሰው የወጡ ለአንድ ወገን ያደሉ ህጎች መፈተሽ አለባቸው። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አስቀድሞ ድርድር ማድረግ ያስፈልጋል። ህገመንግስቱን እስከ ግሳንግሱ ተቀብያለሁ ካልክ በሁዋላ የህገ መንግስት ማሻሻል ጥያቄ ላቅርብ ብትል አትችልም። ህገ መንግስቱን ያንተ አድርገህ የምትቀበለው ላንተም በሚስማማ መልኩ ሲቀረጽ ብቻ ነው። አሁን ባለው አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ የምናስበው ለውጥ አይመጣም። ዶ/ር አብይ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከጸሃይ በታች ባለ ነገር ሁሉ እንደራደራለን” ካላለ በስተቀር፣ ‘ህገመንግስቱን ተቀበሉ’ የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ድርድር የሚያሳብ ከሆነ ከመለስ መንገድ ፈቀቅ አለማለቱን ሊረዳው ይገባል ። ህገ መንግስት የሃይማኖት መጽሃፍ አይደለም፤ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የምንፈልግ ከሆነ ይህ ህግ ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ ሊፈተሽና ሊሻሻል ይገባዋል። ኢህአዴግ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ፖሊሲው የሚገፋ ከሆነ ተቃዋሚዎችም ለድርድር ሲጋበዙ ማስቀመጥ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታ፣ “ህገ መንግስቱን ማሻሻል” የሚል መሆን አለበት።
ድርድር የሃይል ሚዛንን ተንተርሶ የሚካሄድ በማቀበልና በመቀበል ላይ የተመሰረተ የችግር መፍቻ ዘዴ ነው። የሃይል ሚዛን ተመጣጣኝ ሲሆን ሀሉም አሸናፊ ሁሉም ተሸናፊ የሚሆንበት ድርድር ማካሄድ ይቻላል። አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶች ራሳቸውን ከኢህአዴግ ጋር አነጻጽረው ጉልበታቸውን ደካማ አድርገው ስለሚቆጥሩት ይመስለኛል፣ ብዙ ጊዜ ብዙ ሰጥተው ትንሽ ለመቀበል ሲጣደፉ አያለሁ። በራስ የመተማመን ችግር ካልሆነ በስተቀር የተቃዋሚዎች ሃይል ከኢህአዴግ ሃይል ቢበልጥ እንጅ አያንስም። ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር በእኩል እንዲደራደሩ የሚያደርጋቸው እኩል ወይም የበለጠ ሃይል እንዳላቸው የሚያምኑ አይመስለኝም። ቢያምኑም ባያምኑም ኢህአዴግ ያለባህሪው “ለውጥ አመጣለሁ” ብሎ ቃል እንዲገባ ያስገደደው፣ ተቃዋሚዎች በደንብ ሊረዱት ያልቻሉት ስውሩ ሃይል ነው። ስውሩ ሃይል ስውር ስለሆነ አይታይም፣ ስለማይታይም የሌለ ይመስላል። የለም ብለህ ስትለው አንድ ቀን ገንፍሎ ይወጣና መኖሩን ብቻ ሳይሆን፣ ሃይሉን የሚያቆመው ሌላ ሃይል እንደሌለ እንድትረዳ ያደርግሃል። ይህ ሃይል የት የሚገኘው? ህዝብ መሃል ነው። የህዝብ ሃይል ነው። በህዝብ ሃይል ከተለካ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግን በብዙ መጠን ይበልጡታል። የሃይል አጠቃቀሙን ያውቁበታል አያውቁበትም ሌላ ነገር ነው። ብቻ ማንኛውም እውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅት ህዝብ የሚባል ሃይል እንዳለው በማመን፣ ከኢህአዴግ ጋር በእኩል መደራደር እንደሚችል በቅድሚያ ራሱን ማሳመን አለበት፤ ራሱን ካሳመነ በሁዋላ ደጋፊውም የድርድሩን አላማ በደንብ እንዲረዳ በማድረግ ከአላማው ጎን እንዲሰለፍ ማድረግ አለበት። እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚመጣው 51 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ ተስማምቶ የሚገዛበት ህግ ሲረቀቅና በዚያ ህግ መሰረት ስንተዳደር ብቻ ነው። ህጉ ሲረቀቅ የመንግስት ተቋማትም በዚያው መልኩ እንደገና ስለሚዋቀሩ ብዙ ጥያቄዎች መፍትሄ ያገኛሉ። ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ እውነተኛ ለውጥ ሲያመጣ አይታየኝም። ከልቡ ለውጥ የሚፈልግ መንግስት ደግሞ በህጎች ላይ የሚደረግን ድርድር አይፈራም፤ አንድ ነገር ከጀርባው ካላስቀመጠ በስተቀር “ ህገ መንግስቱን ተቀበል” የሚል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ወደ ድርድር አይገባም።
አህመድ ሺዴ የተናገረው የራሱን ይሁን የአዲሱን መንግስት አቋም አላውቅም፤ ዶ/ር አብይ ግን አንድም ቦታ ላይ “ህገመንግስቱን” ከተቀበሉት ጋር ብቻ ድርድር እናደርጋለን ወይም የድርድሩ ቅድመ ሁኔታ ህገመንግስቱን መቀበል ነው ሲል አልሰማሁትም። አህመድ ሺዴ ከማን ወገን ነው? ከማን ወገን እንደሆነ እገምታለሁ።
Filed in: Amharic