>

ግጨው እና ጎቤ በረከት እና አዲሱ ለትግራይ የሰጧቸው ገዥ መሬቶች!?! (በቹቹ አለባቸዉ)

ወንድሜ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ግንቦት 6/ 2010 ዓ.ም “ብአዴን ሆይ ከእነ “እንቶኔ” የጡት ልጅነት መቼ ይሆን ነጻ የምትወጣው?” በሚል በፃፈዉ ፁሁፍ፤ ከግጨው ጋር በተያያዘ ሲያብራራ፡-
“እኔ እስከማውቀው ድረስ አቶ በረከት ስምዖን የግጨው ጉዳይ ይነሳ በነበረበት መድረክ ሁሉ ለኩርማን መሬት ብላችሁ በየስብሰባው ይህን ጉዳይ እያነሳችሁ ታላዝናላችሁ እያለ የሰሜን ጎንደር ካድሬዎችን ያሸማቅቅ የነበረ መሆኑን ነው (በዚህ ረገድ ቹቹ አለባቸው በሚገባ ሊያስረዳ ይችላል ብየ አምናለሁ)” ይላል፡፡
የግጨውና ጎቤ ነገር ተብሎ ተብሎ በእነ እንቶኔ ( በነረከት በሉት በነ አዲሱ፣እንዲሁም በኃለኞቹ እነ እነቶኔ) ሆን ተብሎ በተሰራ ደባ መድበስበሱና ባልተገባ መንገድ ለመቃጨት የተፈለገ መሆኑ ቢታወቅም፤ የዶ/ር ሲሳይን አባባል ለማረጋገጥ ያክል ብቻ ፤ እዉነታዉን ባጭር ለማቅብ ወደድኩ፡፡ ጉዳዩ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ረጅም ጽሁፍ ቢያሻም በሌላ ጊዜ በስፋት የማቀርበዉ ሆኖ፣ ለጊዜው ግን ባጭሩ መረጃ ለመስጠት ዋና ዋና ሀሳቦችን በተለይም የግጨውና የጎቤን ውዝግብ አጀማመር፤ እድገትና፤ ውዝግቡን ለመፍታት ስለተደረገው ጥረት፣ እንዲሁም በተዛባ መልኩ ነገሩ ስለተቋጨበት ሂደት፤ እውነቱን ለማወቅ ለምትፈልጉ ሁሉ እውነቱን በታመነ መረጃ ላይ ተመስርቼ እንደሚከተለዉ አቅርቤላችኃለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
መንደርደሪያ
ከአማራ ክልል ያላግባብ ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ሁመራ፤ ወልቃይት፤ ጠገዴና ጠለምት ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች በጎንደር ክፍለ ሀገር በዳባት አውራጃ ይተዳደሩ የነበሩ ቢሆኑም በሽግግሩ መንግስት ወቅት ያላግባብ ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉ ናቸው፡፡ እነዚህን አካባቢዎች( ከጠለምት በስተቀር) በስራ አጋጣሚ በደንብ አድርጌ አውቃቸዋለሁ፡፡ ለጊዜዉ በዚህ ጽሁፍ የጠገዴና የፀገዴን ውዝግብ በአጠቃላይና በተለይም ደግሞ ስለ ግጨውና ጎቤ ጎጦች ጉዳይን ብቻ አነሳለሁ፡፡
ጠገዴ ወረዳን ባጭሩ
አሁን የአማራ ጠገዴና የትግራይ ፀገዴ እየተባሉ የሚጠሩ ሁለት ወረዳዎች በ1984 ዓ.ም ሁለት ወረዳ ሆነዉ ሳይከፈሉ ጠገዴ ወረዳ በጐንደር ክፍለ ሃገር፤ በዳባት አውራጃ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን አዋሳኞቹም በሰሜን ወልቃይት ወረዳ (ካዛ ወንዝ)፤በደቡብ ታች አርማጭሆና ላይ አርማጭሆ፤ በምስራቅ ወገራ ወረዳ ፤በምእራብ ታች አርማጭሆ ወረዳዎች ነበሩ፡፡ ጠገዴ ወረዳ 28 ቀበሌዎች የነበሩትና በአንገረብና ካዛ ወንዞች መካከል የሚገኘውን ሰፊ፤ በረሀማና ለም መሬት የሚያካልል ነበር፡፡
ጠገዴ ወረዳ ከታህሳስ 1984 ዓ.ም በፊት በሕወሃት ይመራ በነበረበት ወቅት እንደ ድርጅት ቶራት ን/ወረዳን ማዕከል በማድረግ በ3 ን/ወረዳዎች (ማለትም፤ንጉስ ከተማ፤ ቶራት-ቅራቅር፤ እና ደቅ አንባ) ይመራ ነበር፡፡ የእነዚህ ሦስት ን/ወረዳዎች አመራር በሙሉ ታህሳስ ወር 1984 ዓ.ም ወደ ቅራቅር ማዕከል እንዲገባ ታዘዘ፡፡ ከዚህ ጊዜ በኃላ ከታህሳስ – ሚያዝያ 1984 ዓ.ም 3ቱ ን/ወረዳዎች ማዕከሉን ቅራቅር አድርጎ በነበረው የሕወሃትና ብአዴን የጋራ አመራር መመራት ጀምረው ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የኢህዴን ሕልውና በጠገዴ መከሰት የጀመረው፡፡ በ1984 ዓ.ም ኢህዴንን ወክሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በጠገዴ ወረዳ መገኘት የቻለው ሐብቴ ገ/እየሱስ ይባላል፡፡ በ1985 ዓ.ም ደግሞ ላቀው ንጉሴ ኢህዴን/ብአዴንን ወክሎ የጠገዴ ወረዳ የድርጅት አመራር በመሆን የጠገዴን አመራር ተቀላቀለ፡፡
በወቅቱ የሕውሃት ድጋፍ ተራ ካድሬዎችን ከመመደብ ጀምሮ የኢህዴንን የአመራር ቦታዎች በመቆጣጠር ጭምር የሚገለፅ ስለነበር በርካታ የሕውሃት ካድሬዎች ከብአዴን ካድሬዎች ጋር ሆነው የአማራን ክልል የአመራር ቦታውን ጨብጠው መምራትና ማስተዳደር ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ በሰ/ጎንደር ዞን ፤ በዳባት አውራጃ ፤ በጠገዴ ወረዳ ለድጋፍ ተሰማርተው ከነበሩት የሕወሃት ካድሬዎች መካከል ነጋ በርሄ፤ ኃይሌ ገ/መድህን ፤ ኃይለ ስላሴ፤ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ የሕውሀት ካድሬዎች ከ1984 እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ ተጠሪነታቸውን ለሰ/ጐንደር ዞን የመንግስትና የድርጅት ጽ/ቤቶች ሁኖ ኢህዴን/ብአዴንን ወክለው ዳባት አውራጃንና ጠገዴ ወረዳን እስከ መምራት ደርሰው ነበር፡፡ጠገዴ ወረዳ ወደ ሁለት (የአማራ ጠገዴና የትግራይ ፀገዴ ወረዳዎች ሲከፈል) አመራሩም ወደ ሁለት ተከፈለ፡፡ በዚህም መሰረት ኃይሌና ኃ/ስላሴ ኢህዴንን ወክለው የአማራን ህዝብ እንዲያስተዳደሩ በኢህዴን ተሾሙ፡፡ መርዞና ሌሎች የህውሀት ካድሬዎች ደግሞ ማእከሉን ሰኞ ገበያ ወዳደረገው ፀገዴ ወደ ተባለው አዲስ ወረዳ ሄዱ፡፡
የጠገዴ ወረዳ ለሁለት የተከፈለበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው?
በ1984 ዓ.ም ጠገዴ ለሁለት ለምን ተከፈለ ለሚለው ጥያቄ በትግራይና በአማራ በኩል የተለያዩ መልሶች ይሰጣሉ፡፡ በትግራይ በኩል ( ኃይሌ ገ/መድን ) ቋንቋን መሰረት ተደርጎ ነው የተከፈለ ይላሉ፤ በአማራ በኩል ደግሞ፤ለመልካም አስተዳደር ተብሎ የተፈጸመ ድርጊት ነው ይላሉ፡፡ እውነቱ ግን የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር እንፍታ በሚል ሰበብ ነበር፡፡ እሄውም አንዱ ጠገዴ ወረዳ በጣም ስለሰፋ ህዝቡ እንደ ዳንሻ ካሉት እሩቅ ቦታዎች ድረስ እየመጣ ስለተቸገረ ቀረብ ባለ ቦታ አገልግሎቱን እንዲያገኝ በማሰብ ነበር፡፡ በወቅቱ የሁለቱም ወረዳዎች ተጠሪነት ለሰሜን ጎንደር ይሆናል ተብሎ ነበር የተነገረው፡፡ በነገራችን ላይ የጠገዴ ወረዳ ወደ ሁለት መከፈል ምክንያቱ የነበረው ህዝቡ በቋንቋ ስለሚለያይ ሳይሆን ወረዳው ስለሰፋና ለመልካም አስተዳደር ተብሎ እንደተከፈለ በ2008 ዓ.ም ባህርዳር ላይ በተከሄደው የብአዴን ኮንፈረንስ እሂን ሃሳብ እኔው ባራመድኩበት ወቅት፤ ከበደ ጫኔ በአንድ ወቅት ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመውን ኮሚቴ በመምራት ይሁን በመከታተል ሁኔታውን በደንብ ያውቀው ስለነበር፤ ለኮንፈረንሰኛዉ ጠገዴ ወረዳ ለሁነት የተከፈለበት ምክንያት በቋንቋ ሳይሆን ለመልካም አስተዳደር ተብሎ እንደነበር ሀቁን መስክሯል፡፡ እዚህ ላይ ከበደ ጫኔ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
የግጨው ውዝግብ አጀማመር
ሕውሀት ትግሉን በ1968 ሲጀምር ስለትግራይ ህዝብና ስለ ትግራይ ደንበር በማኒፌስቶው የትግራይ ወሰን ፤በሰሜን መረብ ወንዝ፤በደቡብ አለውኃ፤ በምእራብ በኩል ደግሞ ወልቃይትና ፀለምትን ያጠቃላል ይላል :: በዚህ ወቅት ጠገዴ የሚባል ወረዳ በሕውሀት በኩል የታሰበ አልነበረም፡፡ ህውሃት ጠገዴ ወረዳና አካባቢውን መገንዘብ የጀመረው ከ1976 ዓ.ም በኃላ ወደ ጠገዴ ወረዳ ከገባ በኃላ ነው ፡፡ ሕውሀት ከወልቃይትና ጠለምት ባሻገር ጠገዴ ወረዳንና አርማጭሆን የበለጠ እያወቀ ሲሄድ በተለይም ጠገዴን ለሁለት ሰንጥቆ መዉሰድ እንዳለበት ወስኖ ተግባራዊ አደረገው ፡፡ ጠገዴ ወረዳን ወደ ሁለት የመክፈል እንቅስቃሴ በወቅቱ በአካባቢው ተዎላጆች አመራሮችና ሽማግሌዎች ቅሬታ ቢቀርብበትም ለሁለት የመከፈሉ ጉዳይ በአቶ ኃይሌ ገ/መድህን አማካኝነት ግንቦት 20/1984 ዓ.ም በአዋጅ ተበሰረ፡፡ በመጀመሪያው እሳቤ መሰረት በሁለቱም ወገኖች መካካድ ቢኖርም እኔ ጠገዴ አርማጭሆ ከገባሁ በኃላ የተሠጠኝ መረጃ፤ በወቅቱ ከነበሩት 28 ቀበሌዎች መካከል 11 ያህሉ ወደ ሐሙስ ገበያ ( ወደ ትግሬዩ ፀገዴ)፤17 ያህሉ ደግሞ ወደ ቅራቅር (አማራ ጠገዴ) እንደሚካለሉ ስምምነት የነበረ መሆኑን ነው፤ በርግጥ እሄን በትግራይ በኩል ያሉ ወገኖች አይቀበሉትም ቁጥሩን ይገለብጡታል፡፡
ይሁን እንጅ በተግባር ወረዳዎቹን ወደ ሁለት ማካለል ሲገባና የሰኔ 1984 ዓ.ም ምርጫን መቃረብ ተከትሎ ቅሬታዎች መከሰት ጀመሩ፡፡ ወደ አማራ ጠገዴ ወረዳ ይካለላሉ ተብለው ከነበሩት ቀበሌዎች መካከል የተወሰኑት ቀበሌዎች(ለምሳሌ ዳራ ፤ማይደሌ፤ጨጓር ኩዶ፤ሣርና እና ንአዲር ) በ1984 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል እንደሚመርጡ ይፋ ተደረገ፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች ጉዳዩን እንደሰሙ ምርጫው ከመድረሱ በፊት፤ጉዳዩ እንዲስተካከል በሚል ለሁለቱ ጠገዴ ወረዳዎች አቤት አሉ፡፡ መጀመሪያ ለአማራ ጠገዴ አቤት ቢሉም ጉዳያችሁ ሌላ ጊዜ ይታያል አሁን የምርጫው ጊዜ ስለደረሰ ለማስተካከል ጊዜ የለም፤ጉዳዩ በሂደት ይታያል፤ ለአሁኑ በትግራይ ፀገዴ ምረጡ ተብለው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደረገ፡፡
የምርጫ ቀን መድረሱን ተከትሎ ከላይ ለተጠቀሱት ሰባት ቀበሌዎች በወቅቱ የትግራይ የምርጫ ኮረጆ እንዲደርሳቸው ተደረገ፡፡ ነገር ግን ቀደም ብለው ቅሬታ እንዳላቸው ካሳወቁት ቀበሌዎች መካከል የሁለቱ ማለትም የሳርና እና ናአዲር ቀበሌዎች ህዝብ በድርጊቱ ተቆጥቶ እምቢ አንመርጥም ፤ እኛ የምንመርጠው በአማራ ምርጫ ካርድ ነው አለ፡፡ በወቅቱ ከትግራይ ፀገዴ ወረዳ ተልእኮውን ለማስፈጸም ተሰማርቶ የነበረው ተክላይ የተባለ የህወሃት ካድሬ ይቅርታ ጠይቆ መረጋገት በመፈጠሩ ህዝቡ በአማራ ምርጫ ኮረጆ እንዲመርጥ ተደረገ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በወቅቱ በአካባቢው ሁለት አይነት የምርጫ ኮረጆዎች ተሰራጭቶ ነበር ማለት ነው (ለአማራና ለትግራይ ምርጫ ክልል የሚያገለግል ማለት ነው)፡፡የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ በወቅቱ የንአዲር ቀበሌ ሊ/መንበር የነበረው አቶ አለምነህ ኪዴ የንአዲር ቀበሌን የምርጫ ኮረጆ አጅቦ ወደ ቅራቅር አመራ፡፡ አለምነህ ኪዴም በወቅቱ ለነበሩ የቅራቅር ወረዳ አመራሮች (ለነ አቶ ኃይሌ ) በኛ የምርጫ አካባቢዎች ሁለት አይነት ኮረጆዎች (ለትግራይና ለአማራ የሚያገለግሉ) ለምን ላካችሁ ብሎ ጠየቀ፡፡ ጉዳዩን ለማለዘብ ሲባል ችግሩን የፈጠረው ተክላይ የተባለው ጓድ ስለሆነ ማስጠንቀቂያ ይሰጠው ተብሎ ተወሰነ፡፡
ከላይ እንዳነሳሁት ሣርና እና ንአዲር የተባሉት 2 ቀበሌዎች አሻፈረን ወደ አማራ እንጅ ወደ ትግራይ አንመርጥም ብለው በጽኑ በመቃዎማቸው፤ በወቅቱ በአማራ ክልል እንዲመርጡ ተደረገ፡፡ በዚህ ወቅት ንአዲር የምትባለው ቀበሌ ከነበሯት 6 ጎጦች መካከል ዛሬ ስማቸው በአለም ሳይቀር የታወቁት ግጨውና ጎቤ መገኛቸው ይችው ንአዲር ቀበሌ ናትል፡፡ በጠገዴና አርማጭሆ ጎጥ ማለት በደጋው አካባቢ አንድ ወረዳ ሊያክል የሚችል ነዉ፡፡ ስለሆነም የግጨውና ጎቤ ጉዳይ እንዴው እነ “እንቶኔ” ተራ ነገር አድርገው እንደሚያቀርቡት ሳይሆን፤ ከማንነት፣ ከስፋትም ይሁን ከልማት አኳያ ትርጉም ያላቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
በንአዲር ቀበሌ የ1987 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራን መጀመር ተከትሎ ውዝግቡ እንደገና ቀጠለ፡፡ በ1987 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የድሮው ጠገዴ እንደ አንድ ወረዳ ታይቶ የቆጣሪ ቡድኑም ከጎንደር ወደ ጠገዴ ወረዳ ለቆጠራ ተሰማራ፡፡ ኃይሌ እሂን ጉዳይ ሲያውቅ ይህን ጉዳይ መርዞ እንጅ እኔ አላውቅም በማለት ቆጠራውን ለማሰናከል ሞከረ፡፡ ጉዳዩንም አለሙ ጣማለው የተባለ አመራር ለትግረይ ፀገዴ ወረዳ አስተዳደሪ ለነበሩት ለመርዞ እንዲያሳውቅ ወደ ሐሙስ ገበያ ተላከ፡፡ አለሙ ጣምያለው በመርዞ ክፉኛ ተዘልፎ ተባሮ ተመለሰ፡፡ በዚህ ቆጠራ ወቅት በንአዲር ስር ይተዳደሩ የነበሩት መንደሮች (ግጨው፤ጎቤና ክሻ ወዘተ…) እንዲቆጥር ተሰማርቶ የነበረው አድማሱ የተባለ ባለሙያ ነበር፡፡ እሂን ጉዳይ ሲሰሙ የትግራይ ፀገዴ አመራሮች( እነመርዞ ) ጸጋየ የሚባል የዳንሻ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ፖሊስ ወደ ግጨው፤ጎቤና ክሻ አካባቢዎች በመላክ ቆጠራውን በማስቆም ባለሙያውን እንዲታሰር አደረገ፡፡ በዚህ ድርጊት የግጨውና ጎቤ ነዋሪ ህዝብ ክፉኛ ተቆጣ፡፡ የአካባቢው ህዝብ እኛ አማራ ስለሆን መቆጠር ያለብን በአማራ ክልል ነው ቢሉም ፖሊስ አዛዡ ስራውን አገደው፡፡ በድርጊቱ የተቆጣው ህዝብ ሙሌ ሙጨና ነጋ ምትኩ የተባሉ ተወካዮችን መርጦ ለአቤቱታ ቅራቅር ድረስ ላከ፡፡ ኃይሌም አቤቱታ አቅራቢዎቹን አስሮ ወደ ትግራይ ፀገዴ ወረዳ አስተዳደሪ ወደ መርዞ ላካቸው፡፡ መርዞም አነዚህን የህዝብ ተወካዮች 10 ቀን አስሮ ዳግም እንዲህ አይነት ስራ እንዳትሰሩ ብሎ እያንዳንዳቸው የ500 ብር ዋስትና በማስያዝ እንዲፈቱ አደረገ፡፡
የግጨውና የአካባቢው አርሶ አደሮች የመርዞን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ትተዉ አሁንም ለሚመለከታቸው ሁሉ አቤት ማለታቸውን ቀጠሉበት፡፡ በዚህም መሰረት በ1985/86 ዓ.ም በጠገዴ ወረዳ የ20 ብር ግብር መከፈል ሲጀምር የግጨውና ጎቤ አካባቢ ነዋሪዎች 820 የእርሻ ግብር ብር በብርሀኑ ኃይሌና አማረ ሻረው አማካኝነት ለቅራቅር ወረዳ አምጥተው አስገብተው እነደነበር ይታወቃል፡፡ሁኖም ይህ ድርጊታቸው ወደ አማራ ክልለ እንዲታቀፉ አረዳቸውም፡፡አሁንም ተስፋ ያልቆረጠው የግጨውና ጎቤ ህዝብ የጠገዴ አርማጭሆ ወረዳ በተመሰረተበት ወቅት እኛ አማራ ነን ስለሆነም ግብር ተቀበሉን ብለው መጥተው ነበር (አንግዲህ እዚህ ላይ አስተዳደሪው እኔ እንደነበርኩ ልብ በሉ)፡፡ እኔ አስተዳዳሪ በነበርኩበት ወቅትም ያቀረቡት አማራ ነን ፤ ግብር ተቀበሉን የሚለው አቤቱታቸው በድጋሚ እንደገና ተቀባይነት ሳይገኝ ቀረ፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ ጠገዴ ላይ የተሰራ ስራ ነበርና፡፡ ይሁን እንጅ ከዚህ በኃላም ተስፋ ባለመቁረጥ፤ሰልፍ አድርገው ሳንጃ ወረዳ ድረስ ለመምጣት ቢሞክሩም ሰሮቃ ከደረሱ በኃላ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ የግጨውና ጎቤ ህዝብ ህዝቦቹ ሰሚ በማጣቱ በሂደት ተስፋ እየቆረጠ፣ ከትውልድ አካባቢያቸው እየተፈናቀሉ በተለይም ወደ አብረሀጅራ፤ አብደራፊ፤ ሰሮቃ፤ ክሻ ወደ ተባሉ አካባቢዎች ተሰደዱ ፤ በሂደትም ግጨውና አካባቢው ተንኮል ባዘለ ሰፈራ ስም በትግርኛ ተናጋሪዎች ተዋጠ፡፡
እዉነታዉን ለማስጠበቅ የተደረገ ጥረትና የተቋጨበት አሳዛኝ ሁኔታ
ግጨውንና ጎቤን መነሻ አድርጎ ለ25 አመት የዘለቀውን የአማራ ጠገዴና የትግራይ ፀገዴ ወረዳዎች ውዝግብ ለመፍታት ያልተደረገ ጥረትና ሙከራ አልነበረም፡፡ ይህም ከሰላማዊ ድርድር እስከ ግጭት ያመራ ነበር፡፡ ችግሩን ለመፍታት በህዝቡ፣ በአመራሩና በሽማግሌዎች ጭምር ቡዙ ያልተሳኩ ሙከራዎች ተካሂደው ነበር፤ ሙከራዎችን በአጭሩ እንመልከታቸዉ፡-
ሀ. በህዝቡና አመራሩ የነበረ ጥረት
የግጨው አካባቢ ህዝብ በተለይም ከ1987 ዓ.ም በኃላ ወደ ትግራይ አስተዳደር መካላቸውን በመቃወም ጉዳዩ እነዲስተካከል በተደጋጋሚ ቅሬታቸውንና አቤቱታቸውን ለሚመለከተው ሁሉ አቅርበዋል፡፡ ውዝግቡ በሰላም እንዲቋጭ የግጨውና ጎቤ አማራዎች ብቻ ሳይሆኑ መላው የጠገዴ ወረዳ ህዝብ ለረዥም አመታት አብሯቸው ጩሆ ነበር፡፡ ችግሩ በወቅቱ ባለመፈታቱ የግጨውና የአካባቢው አ/አደሮች በነ መርዞ የሚደርስባቸውን ጫናና እንግልት መቋቋም ባለመቻላቸው ከኖሩበት ቀየ እየተፈናቀሉ፤ ወደ ክሻ፤ እርጎየና ሰሮቃ አካባቢዎች ሲሸሹ በለለቁት ቦታ ከመሀል ትግራይ ህዝብ በማምጣት እንዲሰፍርበት ተደረገ፡፡ በዚህም መሰረት አካባቢው የትግረኛ ተናጋሪ ቁጥር የበዛበት ፤የአማረኛ ተናጋሪው ቁጥር እየቀነሰና የሄደበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡
የአመራሩን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ፣ በተለይም የወረዳና የቀበሌ ማለቴ ነው፤ እንዲሁም የሰ/ጎንደር ዞን አመራር ከነበሩት መካከል ጌታቸው ጀንበር፤ግዛት አብዩ ወደ ኃላ ደግሞ አገኘሁ ተሸገር ችግሩን ለመፍታ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን ወሳኙ ሌሎች የሆኑበት ሁኔታ ስለተፈጠረ፤ ችግሩን አዳምጦ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ጥያቄውን የሚያነሱ ሁሌም እንደ እባብ እራሰ እራሳቸውን ይቀጠቀጡ ነበር፤ ስራህን መስራት ሲያቅትህ ግጨውን ሰበብ ታደርጋለህ፤ እኛ የታገልነው ለህዝብ እንጅ ለመሬት አይደለም፤ግጨው የትምክህት ምሽግ እየሆነች ነው ወዘተ….እየተባለ ሆን ተብሎ ችግሩ እንዳይፈታ ተደረገ፡፡ ስለሆነም የአመራሩም ጥረት እንዲሁ እንደህዝቡ ባዶ ጩከት ሁኖ ቀረ፡፡ በአንድ መድረክ ላይ አንድ አሁን በስልጣን ላይ ያለ፤ ነገሩን ከስር መሰረቱ ሚያውቅ አመራር ፤የተለመደውን የግጨው ጉዳይ አነሳና በመካከሉ ላይ ” እንዴው ለመሆኑ የግጨው ጉዳይ ሲነሳ እንቅልፍ የሚይዛችሁ ለምንድን ነው ?” ሲል ጥያቄ ማቅረቡን እናስተውሳለን፡፡
ለ. ታፍኖ የቀረው የግጨውና ጎቤ ጎጦች ህዝብ የጥናት ውጤት
ጉዳይን እልባት ለመስጠት ይቻል ዘንድ ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እስከ 1984 ዓ.ም በከባቢው ሰፍሮ የነበረው አብዛኛው ህዝብ ማን እንደነበር እንዲጠና ተደረገ ፡፡ የቀረበዉ የጥናት ሪፖር እንዳረጋገጠው እስከ 1984 ዓም የግጨውና ጎቤ ነዋሪ አብዛኛው ነዋሪ አማራ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር ፡፡ የጥናቱ ግኝት እዉነታዉን በግልጽ ቢያሳይም የትግራይ አመራሮች ውጤቱን አንቀበለውም ስላሉ ብቻ የጥናቱ ውጠየት ተግባራዊ ሳይደረግ ታፍኖ ቀረ፡፡ በጥናቱ የተሳተፉና ሪፖርቱን አዘጋጅተዉ ያቀረቡ የብአዴን አመራሮች ዛሬም ስልጣን ላይ ሀቁን ሊያረጋግጡት ይችላሉ፡፡
ሐ. የከሸፈው የሽምግልና ጥረት
እስከ 1984 ዓ.ም በግጨውና ጎቤ ከባቢ አብዛኛው ነዋሪ ማን እንደነበር አጥንቶ መፍትሄ ለመስጠት ታስቦ የተሰራውን ስራ መክሸፍ ተከትሎ ሌላ አዲስ ሙከራ ተጀመረ፡፡ ችግሩን በሽማግሌዎች መፍታት፡፡በዚህም መሰረት ባልስጣናትና የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉባቸው በርካታ መድረኮች በተለያዩ ቦታዎች ከተካሄዱ በኃላ፤ ከሁለቱ ወገኖች ጉዳዩን የሚያስፈጽሙ 3 የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ሽማግሌዎቹም ከካቲት 04/2007 እስከ የካቲት 18/2008 ዓ.ም ድረስ 36 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡እነዚህ ሽማግሌዎች በአገር ባህል መሰረት መስቀል አስወጥተው እያስማሉ በሁለቱ ወገኖች የቀረቡትን ምስክሮች ቃል ሰምተዋል፤ በዚህ ምስክሮችን የመስማት ሂደት በግራ ቀኙ 44 ፤ 44 በድምሩ 88 ምስክሮች ምስክርነታቸውን መስጠታቸውንና ሂደቱም 130 የሰነድ መረጃዎች ልውውጥ ተደርጎ እንደነበር መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡
የምስክር መስማቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ፤ የምስክሮች ውጤት ትንተና ተካሄደ፤ውጤቱ አሁንም ወደ አማራ ማዘንበሉ ግልጽ ሆነ፤ ሁኖም አሁንም እንደተለመደዉ በትግራይ በኩል ያሉት ሽማግሌዎች በውጤቱ ላይ አንፈርምም ስላሉ የጥናቱን ውጤት በጋራ ለሁለቱ ክልሎች አማራሮች ሳይቀርብ ቀረ፡፡ ይሁን እንጅ የትግራይ ተወካዮች አንፈርምም ቢሉም፤ በአማራ በኩል የተወከሉት ሽማግሌዎች፣ ውጤቱን በሠነድ መልክ በዝርዝር አዘጋጅተው ለብአዴን አመራር እንዳቀረቡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ(የካቲት/2008 ዓ.ም)፡፡ እንግዲህ ጉዳዩን ስንመለከተው፣ በድርጅት ደረጃ ጉዳዩ ተያዘ ፤ውጤቱን የትግራይ አመራር አፈረሰ፤ በህዝበ ውሳኔ ተባለ ውጤቱን የትግራይ አመራር አፈረሰ፤ በሽምግልና ተሞከረ፤ይህም ሙከራ በትግራይ አመራር ፈረሰ፡፡ በቃ እንዲህ ነበር ነገሩ ሁሉ፡፡
መ. ሲያልቅ አያምር
የሁለቱ ጠገዴ ወረዳዎች ውዝግብ ሳይፈታ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ተነስቶ ነገሮች በባሰ ሁኔታ ተበላሹ፡፡ ጉዳዩ ያሳሰበው የኢህአዴግ ም/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የወልቃይትን የማንነት ጥያቄ በማንሳት ጉዳዩ ህገ መንግስቱን ተከትሎ እንዲታይ፤ የሁለቱ ጠገዴ ወረዳዎች የደንበር ውዝግብም የሁለቱ ክልሎች መንግስታት በአስቸኳይ እንዲፈቱ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ይህን ውሳኔ ተከትሎም አመራሩንና ህዝብን የማወያየት ስራ ተጀመረ፡፡ ህዝባዊ አመጹ እንደበረደ በትግራይና አማራ ክልሎች ነገሮች ተበላሽተው ነበርና እሂንን ለማሻሻልና ውዝግቡን ለመፍታት የሚያስችል ህዝባዊ ኮንፈረነስ መቀሌ ላይ ተካሄደ፤ የመቀሌው ኮንፈረንስም ቀጣዩ ኮንፈረንስ ጎንደር ላይ እንዲካሄድ ወሰነ፡፡ ሁኖም ለጎንደሩ ኮንፈረንስ ችግሩን ፈትታችሁ እንድትመጡ ብሎ ለሁለቱ ክልሎች አመራር ኃላፊነት ሰጠ፡፡
በትግራዩ ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱና በአማራው ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የክልሎቹ አመራር የጎንደሩ ኮንፈረንስ ከመድረሱ በፊት ጠገዴ ወረዳ ላይ የተወሰኑና ህዝብ ያልመረጣቸውን ሰዎች በመሰብሰብ ስምምነት ደርሰናል ብለው ስምምነታቸውን በፊርማቸው አስቀመጡ፡፡ በስምምነቱ መሰረትም ከ25 አመት በላይ በጉልበት የተወሰዱትንና ያን ያክል የተደከመባቸውን፤ አንዴ በህዝበ ውሳኔ፤አንዴ በኮሚቴ፤ ሌላ ጊዜ በአገር ሽማግሌ እየታየ የአማራ መሬት መሆናቸው የተረጋገጡትን ግጨውና ጎቤን ለትግራይ ብለናል ብለው ነገሩን፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ የውዝግብ ማዕከል ያልነበረውን ስላንዲን የተባለውን በረሀ ለአማራ ይሁን ብለናል አሉን፡፡ ስላንዲን እኮ ድሮም ሰሮቃ ወንዝ ማዶ በንአዲር ቀበሌ ውስጥ ሚገኝ አንዱ የግጨውና ጎቤ ጎጦች አካል ነው፡፡ ብቻ እንዲህ እውነትና ፍትህ በተዛባ ሁኔታ ውዝግቡ ተቋጨ ተብሎ ታወጀ፡፡ እኔ በግሌ የውሳኔውን መስመርና የጠገዴ ህዝብ እሄን ውሳኔ ከልቡ ስለመቀበሉ እጅግ ሲበዛ እጠራጠራለሁ፤ ምክንያቱም ህዝቡ የሚያውቀው እውነትና የተዛባ ፍትህ ስላለለ ነው፡፡ ለአካባቢው ባለኝ ቅርበት የተነሳ እንዳገኘሁት መረጃም የጠገዴና አርማጭሆ ህዝብ በዚህ ውሳኔ ደስተኛ አይደለም፡፡ እውነተኛው የህዝብ ስሜት፣ አቶ ገዱ እውነቱን እያወቀ፤ እጁን ተጠምዞ ፈረመ የሚል ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አለ፤ ገዱም ሆነ አሁን ያለው አመራር ምንም ሊያደረግ አይችልም፤ ገዱም ሆነ አሁን ያለዉ አመራር እነ “እነንቶኔ” ባበላሹት ነገር ገብቶ በእሳት እየተጠበሰ ያለ የክልል አመራር መሆኑን ከኔ በላይ የሚመሰክር ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ አሁን ያለው የክልል አመራር እጅግ የተበላሸ ሁኔታ ተረክቦ ነው የነግጨውን ጉዳይ በሰለም ለመቋጨት እሰራ የመጣው፡፡በእኔ እምነት ለግጨውና ጎቤ ያለ አግባብ ወደ ትግራይ መከለል ዋነኛ ተወቃሾቹ በረከትና አዲሱ ናቸው፤ እሂን ደግሞ ፊትለፊት በኮንፈረንሱ ነግሪያቸዋለሁ፤ አልተቀበሉኝም እንጅ፡፡
የድንበር/ ወሰን ውዝግቡን ለመፍታት ለምን እረዥም ጊዜ ጠየቀ?
የሁለቱ ጠገዴ ወረዳዎች የወሰን ውዝግብ ሳይፈታ እረዥም ጊዜ መውሰዱ ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው፡፡ ምክንያቶቹም በዋነኛነት ከሕወሃት እና ብአዴን ከፍተኛ አመራር ጋር የተያያዙ መሆናቸው የታወቀ ነው ፡፡ከሕወሃት አንጻር የድንበሩን ውዝግብ የሚያይበት እይታ ከመሬት ስስት ፍላጎቱ በመነሳት ነው፡፡ በተለይም በኪሮስ ቢተውና ፀጋይ በርሄ ይመራ የነበረው የትግራይ አመራር፣ ጠገዴ ወረዳ በ1984 ዓ.ም ሲከፈል ደጋማው እንጅ በረሀማው አካባቢባቢ አልተካለለም፣ የትግራይ ድንበሩ ማርዘነብ የተባለውን ሰፊና ለም መሬት ባጠቃለለ መልኩ አንገረብ ወንዝ ምላሽ ነው ወዘተ…የሚል አመለካት ስለነበራቸው ችግሩን በቀላሉ እንዳይፈታ አደረገው፡፡
በወቅቱ የነበረዉ የብአዴን አመራ ርደግሞ፣ ከህወሃት ጋር እሰጣ አገባ መግባትን ካለመፈለግ የተነሳ ይሁን ሌላ መነሻ ይኑረው፤ የደንበሩን ውዝግብ ቀለል አድርጎ በማየትና ሌላውም እንደዛ እንዲመለከተው በመፈለግ ፣ ግጨውና ጎቤን ለህወሃት በመልቀቅ ጭምር ጉዳዩ እንዲቋጭ የመፈለግ አመለካከትና ተግባሩን አሳይቷል፡፡ በተለይም እዚህ ላይ በሚገባ መወቀስ ካለባቸው አዲሱ ለገሰና በረከት ስምዖን ናቸው፤ እውነቱን እያወቁ ግጨውና ጎቤን አሳልፎ በመስጠት የነሱን ያክል ልባችንን ያደማው የለም፡፡ በርግጥ ደመቀ መኮንንም እዚህ ላይ ነጻ አይደለም፡፡ ደመቀ መኮንን አዲሱ ለገሰንና በረከት ስምዖንን ተጋፍጦ ታምር ይፈጥር ነበር ባልልም ችግሩ ሲፈተር ጀምሮ አብሮ የነበረና ለመፍትሄውም አንድም ቀን ሲሰራ ስላላስተዋልኩት አሁን ካለው የብአዴን አመራር በተለየ ደመቀ መኮንንን የችግሩ አካል አድርጌ እመለከተዋለሁ፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ከሀውሀትና ከብአዴን ከፍተኛ አመራር በተጻራሪው የቆመ የአካባቢው ህዝብና የታችኛው አመራር (አንዳንድ የዞን አመራሮችን ጨምሮ) ፍትሀዊ ጥያቄ አለ፡፡ እኒህ ሦስት ወገኖች በተለያየ ቁመና ላይ መገኘታቸው ነገሮቹ በጊዜና በወቅቱ እንዳይፈቱ አድርጓል፡፡ ህዝቡና የታችኛው አመራር ፍትህ ፍለጋ፤ ህውሀት መሬት ፍለጋ፤ ብአዴን ደግሞ በኋላ ቁርጡን ቢያሳይም ዥዋዥዌ አቋም፤ ይሄ ነበር ድራማዉ ፡፡
እንግዲህ የግጨውን ጉዳይ ግንቦት 20 በሚከበርበት ዋዜማ ላይ ሁነን ማንሳቴ፤ በአጋጣሚ እንጅ ታስቦበት አለመሆኑ ይታወቅልኝ፤ በርግጥ ነገሩ ግጥምጥሞሽ አለው፤ እሄውም ለግጨው ውዝግብ መከሰት መነሻ የሆነው ግንቦት 20/1984 ዓ.ም ጠገዴ ወረዳን ለሁለት የመክፈል ውሳኔን መሆኑን ስናይ ነገሩ እውነትም መገጣጠሙን እንገነዘባለን፡፡
ከቡዙ በጥቂቱ ላነሳ የወደድኩት እሄን ነው፤ እኔ የሳትኩት/ያዛባሁት ካለ ደግሞ አሁንም በሂደቱ በዋናነት ተሳታፊ የነበራችሁ ሰዎች ስላላችሁ ማስተካከል ይቻላል፡፡
Filed in: Amharic